በኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የፋይናንስ የሥራ ሒደት ዳይሬክተርና የደንበኞች ግንኙነት አስተዳደር የሥራ ሒደት ዳይሬክተር፣ ባንኩን ከ276.6 ሚሊዮን ብር በላይ በማስመዝበር ተጠርጥረው ታሰሩ፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የባንኩ ኃላፊዎች አቶ ሳሙኤል ግርማ ደሴና አቶ በለጠ ዋቅቤካ ሂርጳ ናቸው፡፡ የተጠረጠሩበትን ወንጀል ፈጽመዋል የተባለው በባንኩ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ላይ መሆኑን፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት አስረድቷል፡፡
ሁለቱም ተጠርጣሪዎች በቅርንጫፉ ኃላፊ ሆነው በሚሠሩበት ወቅት በቅርንጫፉ ‹አካውንት ሪሲቨብል›፣ ‹ኤክስፖርት ሴትልመንት አካውንት› የሚባል ሒሳብ ከባንኩ ዕውቅና ውጪ በመክፈትና ከሌሎች ግለሰቦች ጋር በመመሳጠር፣ 276,675,572 ብር ባንኩ እንዲመዘበር ማድረጋቸውን ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል፡፡
በመሆኑም ከጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ሥር አውሎ እየመረመራቸው እንደሚገኝ ፖሊስ በማስረዳት፣ የወንጀል አፈጻጸሙ ውስብስብና አስቸጋሪ መሆኑን በመግለጽ ለተጨማሪ ምርመራ 14 ቀናት እንዲፈቀድለት ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡