Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ከፍተኛ አመራሩ ተጠያቂ ያልሆነው ማስረጃ ስለሌለ ነው›› ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም...

‹‹ከፍተኛ አመራሩ ተጠያቂ ያልሆነው ማስረጃ ስለሌለ ነው›› ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

ቀን:

ሰኞ ጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በጽሕፈት ቤታቸው ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ከረጅም ጊዜ በኋላ በተሰጠው በዚህ መግለጫ ጋዜጠኞች አንገብጋቢና በቅድሚያ ምላሽ ያስፈልጋቸዋል ያሉዋቸውን ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በከፍተኛ አመራሩ ላይ ዕርምጃ ያልተወሰደበት ምክንያት፣ የትግራይና የአማራ ክልሎች አመራሮች ጥፋተኛ ከተባሉ በኋላ ለምን ዕርምጃ እንዳልተወሰደባቸው፣ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅምን በዝርዝር የሚደነግገው ሕግ ለምን እንዳልወጣ፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ይደረጋል የተባለው ድርድር የት እንደደረሰና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል ዋነኛ ፖለቲካዊ አንድምታ ያላቸው ከነምላሻቸው በዮሐንስ አንበርብር እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ጥያቄ፡- አመራሩ ሥልጣንን ለግል ጥቅም የማዋል ዝንባሌ እንዳለው በፓርቲ ደረጃ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በተወሰደው ዕርምጃም አንዳንድ የካቢኔ አባላት ተነስተዋል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ መልሰው ተሹመዋል፡፡ ለምን ተነስተው ለምን መልሰው ተሾሙ?

ጠ/ሚ ኃይለ ማርያም፡- ኢሕአዴግ ብዙ መስዋዕትነት ከፍሎ በኢትዮጵያ የሰላም፣ የዴሞክራሲና የፍትሐዊ አስተዳደር ሥርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ የሠራ ድርጅት ነው፡፡ በየጊዜው ራሱን በራሱ እያረመ የዘለቀ ድርጅት ነው፡፡ የሚመራውም መንግሥት እንደዚሁ ራስን በራስ የማረም መርህ ተከትሎ የመጣ መንግሥት ነው፡፡ ስለዚህ በቅርቡ ያካሄደውም ተሃድሶ በዚህ መርህ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ለማንኛውም ድርጅትም ሆነ መንግሥት የአመራር ሥርዓቱ ወሳኝ ነው፡፡ በሒደት የካፒታሊዝም ሥርዓት ለመገንባት ጥረት እየተደረገ እንደመሆኑ ሁሉ፣ ሥርዓቱን የሚያጋጥመው አደጋዎች ምንድናቸው የሚሉትን በውል ለይተናል፡፡ ከእነዚህ አደጋዎች አንዱ በአመራር ላይ ያለ አካል ቀስ በቀስ የራሱን ኑሮ ለማሻሻል የግል ብልፅግናውን የመፈለግ፣ ከዚያም አልፎ የቆመለትን ዓላማ እየሸረሸረ የመሄድ ይህም በመጀመሪያ በአመለካከት ደረጃ በሒደት ደግሞ በተግባር የሚገለጽ ችግር እንደሚያጋጥም ነው፡፡

ኢሕአዴግ በተሃድሶ እንቅስቃሴዎቹ የፓርቲውን መሠረታዊ መርህ የሚሸረሽሩ ነገሮችን ማስተካከል ይገባል በሚል ሲሠራ ነው የቆየነው፡፡ በአሁኑ የተሃድሶ እንቅስቃሴም ያጋጠሙንን ፈተናዎችና ተግዳሮቶች ለይተናል፡፡ ከእነዚህም መካከል ዋናውና በውልም ለይተን የያዝነው የመንግሥትን ሥልጣን የምናይበትን መንገድ ነው፡፡ ይህንን በምንፈትሽበት ጊዜ በሌብነትና በሙስና የሚገለጽ የመጨረሻው ደረጃ ብልሹነት አለ፡፡ ከዚህም ባሻገር የያዘውን ሥልጣን ለሕዝብ አገልግሎት መጠቀም ሲገባ ኑሮውን፣ ቤተሰቡን፣ ሕይወቱን በመምራት ዙሪያና ምቹ ኑሮ ለመኖር የመሞከር ነገር ተስተውሏል፡፡ ባይሰርቅ እንኳ ስርቆት ድረስ የመሄድ አመለካከት ተለይቷል፡፡ ከዚህ በመነሳት እጅግ አብዛኛውን አመራር እያጠቃ ያለው ለሥራ ከመትጋትና መስዋዕትነት ከመክፈል ይልቅ መዝናናትን የመምረጥ፣ ባለጉዳይን ያለማስተናገድ፣ ቢሮ ያለመገኘት ወይም ዝግ መሆን፣ ከሥራ ሰዓት ውጪ ያለመሥራት፣ እንደ ማንኛውም ሲቪል ሠራተኛ 11፡30 ሰዓት ሲሆን ከቢሮ ወጥቶ መሄድ፣ የተለያዩ ጉዞዎችን የማብዛትና የመሳሰሉት ውጤታማ የማያደርጉ ዝንባሌዎች ይታያሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሥልጣንን ለኅብረተሰብ ጥቅም ብሎ ለወሰነ ፓርቲ የማይገባ ሥነ ምግባር ነው፡፡

ስለዚህ በቅርቡ ባደረግነው የአመራር ለውጥና ሽግሽግ ውስጥ እንዲካተቱ የተደረጉት ከታች እስከ ላይ በዚህ ችግር ውስጥ ያልገቡትን ነው፡፡ አመራሮች የሕዝብ አገልግሎት ውስጥ ሊሳተፉ ይገባል በሚል መርህ ነው፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ከአቅም ማነስ ማለትም ከዕውቀት ወይም ከክህሎት ማነስ ጋር ተያይዞ ነው የተቀነሰው፡፡ ስለዚህ አመራሮቹ ሲነሱ ከእነዚህ በአንዱ ተገምግመው ነው ማለት ነው፡፡ ዝቅ ብሎ የተመደበ ከሆነ በቀደመው ቦታ ላይ አቅም አልነበረውም ተብሎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በተመሳሳይ ወደ ላይ የተመደበ ወይም ወደ ሌላ አካባቢ የተሸጋገረም ከሆነ በተመሳሳይ የተሻለ አቅም አለው ተብሎ መታየት አለበት፡፡ አንድ ግልጽ ሊሆን የሚገባው ነገር በስርቆት፣ በሌብነት፣ በሙስና ተሳትፎ ማስረጃ የተገኘበት በምንም መልኩ ተጠያቂ ሳይሆን ሊቀር አይችልም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ጥርጣሬዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ወደ ሕግ ተጠያቂነት ለመውሰድ በቂ ማስረጃ ሊኖር ይገባል፡፡ ጥርጣሬዎች በሚኖሩበት ጊዜ ሊወሰዱ የሚችሉ ዕርምጃዎች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው አስተዳደራዊ በሆነ መንገድ ከሥልጣኑ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡ ከሥልጣኑ ከወጣ በኋላ በቂ ማስረጃ ካለ ወደ ሕግ ቀርቦ ይጠየቃል፡፡ በቂ ማስረጃ ሳይኖር ወደ ሕግ አቅርቦ ማሸነፍ ስለማይቻል ትርጉም የለውም ማለት ነው፡፡ ሙስና በጣም ውስብስብ የሆነ ወንጀል ነው፡፡ የተቻለውን ያህል ባገኘነው በቂ ማስረጃ አመራሮችን ተጠያቂ እያደረግን መጥተናል፡፡ ነገር ግን በዚህ ያበቃል ማለት አይደለም፡፡

ሙስና ውስብስብነቱ ታውቆ አሁን ከሥልጣን የወረዱ፣ እንዲሁም በሥልጣን ላይ ያሉና በሙስና የተሳተፉትን በየጊዜው በጥናት ላይ በመመሥረት የማፅዳት ሥራ መከናወን አለበት፡፡ ሁለተኛው በተሃድሶ ንቅናቄው ውስጥ እንደ ሥርዓት ሊቀመጥ ይገባል ብለን ያቀድነው ኅብረተሰቡ በፀረ ሙስና ትግል ውስጥ በስፋትና በጥልቀት የሚሳተፍበትን ሁኔታ ማመቻቸት ማስረጃዎችን ለማግኘት ወሳኝ መሆኑን ነው፡፡ በብዙ አገሮች እንደተለመደው የሙስናን ውስብስብ ባህሪ ታሳቢ አድርገን ኅብረተሰቡ ማስረጃ በማቅረብ የሚሳተፍበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለብን፡፡ ከዚህ አኳያ መንግሥት የወሰነው የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል አቋቁሞ ኅብረተሰቡ ለዚህ ማዕከል በየጊዜው ማስረጃዎችንና መረጃዎችን የሚሰጥበት ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ ሌላው የመንግሥት ባለሥልጣናት ሀብትና ንብረት ይፋ የሚሆንበትን ሁኔታ በማመቻቸት፣ ይፋ ከሆነው በተጨማሪ ‘እከሌ የተባለ ባለሥልጣን ንብረት አለው’፣ ‘በራሱ ብቻ ሳይሆን በዘመዶቹ ወይም በወዳጆቹ የተያዘ ሀብት አለው’ በማለት እንዲጠቁሙ ለማድረግ ታቅዷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የዴሞክራሲ ተቋማትን ማለትም በቅርቡ በተጠናከረ መንገድ ያቋቋምነው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አለ፣ የፀረ ሙስናና ሥነ ምግባር ኮሚሽንም አለ፣ በተጨማሪም በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ በተለየ መንገድ በአሜሪካ እንዳለው ኤፍቢአይ ዓይነት የምርመራ ቢሮ አቋቁመናል፡፡ ኅብረተሰቡ ዘመናዊ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂዎችን የሚጠቀምበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባ በመወሰን እየሠራን ነው፡፡

      ዋናው ጉዳይ ግን አመለካከትን መቀየር ነው፡፡ ሙስናን የሚጠየፍ አመራርና ማኅበረሰብ መገንባት ነው መፍትሔው፡፡ በተሃድሶ ጊዜ ዋነኛው ድል ሆኖ ያገኘነው ማንኛውም ዓይነት የሙስና ዝንባሌ ሐሜት እንኳን ቢሆን ወደ መድረክ ወጥቶ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ በአገራችን ሙስና የማይፈቀድ ተግባር መሆኑ ላይ ግንዛቤ ይወሰዳል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰው ራሱን የሚገዛበትና የሚጠበቅበት ሁኔታን ያመቻቻል፡፡ ስለዚህ የንፅህና ጉዳይ የሚለካው በተግባራዊ እንቅስቃሴና ኅብረተሰቡ የሚያቀርባቸውን መረጃዎች መሠረት አድርጎ በሚከናወን ትግል ነው፡፡

ጥያቄ፡- [ችግር እንዳለበት የተገመገመው ከፍተኛ አመራር ያልተጠየቀበትን ምክንያት አስመልክቶ የሰጡት ማብራሪያን ያልተዋጣላቸው ጋዜጠኞች ጠቅላይ ሚኒስትሩን በድጋሚ ጠይቀዋል፡፡] ኅብረተሰቡ እያለ የሚገኘው መንግሥት የራሱን አጥፊዎች ሲቀጣ በሁለት ለይቶ የላይኛውና የታችኛው አመራር በሚል ነው፡፡ የላይኛው ከፍተኛ አመራር በሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነት አይጠየቅም፡፡ መካከለኛና የታችኛው አመራር ነው እየተጠየቀ ያለው፡፡ ከፍተኛው አመራር ለምን አይጠየቅም? በኪራይ ሰብሳቢነት አልተሳተፈም ቢባል እንኳን እነዚህን ችግሮች ተመልክቶ የማስቆም ኃላፊነት አልነበረበትም ወይ? ከዚህ ቀደም የወልቃይት ፀገዴ ጉዳይን በተመለከተ ሲመልሱ ዋነኞቹ የችግሩ ፈጣሪዎች የሁለቱ ክልሎች አመራሮች እንደሆኑና እጃቸውን ማስገባታቸውን ገልጸው ነበር፡፡ እነዚህ የሁለቱ ክልል አመራሮች መቼ ተጠየቁ? ከዚሁ የወሰን ጥያቄ ጋር ተያይዞ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ጠፍቶና ንብረት ወድሞ ሳለ ዋነኛ የችግሩ ባለቤት የተባሉት የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ለምንድነው በሕግ ተጠያቂ የማይሆኑት?

ጠ/ሚ ኃይለ ማርያም፡- የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር በዋናነት የአመለካከት ችግር ነው፡፡ የዚህ የአመለካከት ችግር የከፍተኛ አመራሩ ነው፡፡ እንዲያውም ብሶ የሚታየው በከፍተኛ አመራሩ ላይ ነው፡፡ ከፍተኛ አመራሩም በግምገማው ወቅት ይህ ስህተት ነው ብሎ አምኖ ተቀብሏል፡፡ ትክክለኛ ኢሕአዴግአዊ አመለካከቶችን እንዲጨብጡ ተደርጓል፡፡ ትልቁ ድልም ይኼ ነው፡፡ በዚህ ላይ ተመሥርቶም ሕዝቡ የሚፈልገውን መልካም አስተዳደርና ልማት ለማምጣት ቆርጠን መሥራት አለብን የሚል ድምዳሜም ላይ ደርሰናል፡፡ ባገኘነው ማስረጃ ልክ ተጠያቂ መሆን የሚገባቸው ተጠያቂ ሆነዋል፡፡ አሁን ከጥያቄዎቻችሁ እንደገባኝ አንድ ትልቅ ባለሥልጣን እንኳን ቢታሰር በቃ ማሰር ጀምረዋል የሚለውን ማየት የሚፈለግ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ዝም ተብሎ ተነስቶ ሰው አይታሰርም፡፡ ሰው ለማሰር ማስረጃ ያስፈልጋል፡፡ እኔ ደግሞ መልሼ የምጠይቀው የትኛውን ባለሥልጣን ነው ማስረጃ ኖሮን ያላሰርነው? ይነገረን እያልኩ ነው ያለሁት፡፡ የሚዲያ ባለሙያዎችም ይኼ ማስረጃ እያለኝ አላሰራችሁም የምትሉ ከሆነ ይነገረን፡፡ ፈትኑን፡፡ ይኼ ማስረጃ አለ ነገር ግን በዚህ ላይ ተመሥርታችሁ ዕርምጃ አልወሰዳችሁም ይባልና በዚህ ማስረጃ ላይ ተመሥርተን ዕርምጃ ያልወሰድን ከሆነ ሊነገረን ይገባል፡፡ በዚህ መንገድ ካልተገነዘብነው ብዙ ጊዜ ተራራ የሚያክል ነገር ይወራና ማስረጃ ሲባል አይጥ የማይሸፍን ነገር ይሆናል፡፡ ስለዚህ በወሬ ዕርምጃ አይወሰድም፡፡ ለዚህ ነው ይህንን ውስብስብ ሙስና የማጋለጥ ጉዳይ ኅብረተሰቡን ማሳተፍ ያስፈልጋል ያልኩት፡፡ ስርቆት በግልጽ አይፈጸምም፡፡ ውስብስብ አድርጎ ነው የሚሰረቀው፡፡ ይህ ሊጋለጥ የሚችለው ኅብረተሰባዊ ንቅናቄ ሲኖር ነው፡፡ ባወቅነውና ባለን መረጃ ልክ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው የመጣነው፡፡ አሁንም ግን ዝግ ነው ማለት አይደለም፡፡ ማስረጃ ከተገኘ የትም ደረጃ ላይ ያለ አመራር ይሁን መተው የለብንም፡፡ በዚሁ ደረጃ በቁርጠኝነት መሥራት ይገባናል የሚለውን እንደ መተማመኛ ብንይዝ የተሻለ ይሆናል፡፡

ጥያቄ፡- ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላት ሕገ መንግሥታዊ ልዩ ጥቅም እስከ ኅዳር ውሳኔ ያገኛል ተብሎ የነበረ ቢሆንም እስካሁን የተወሰነ ነገር የለም፡፡ እንዲሁም በወልቃይት ፀገዴ ከወሰን ለውጥ ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሚመለከታቸው የአማራና የትግራይ ብሔራዊ ክልሎች ችግሩን ይፈቱታል ተብሎ ነበር፡፡ ሁለቱ ክልሎች ምን እየሠሩ ነው?

ጠ/ሚ ኃይለ ማርያም፡- ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ ያላት ልዩ ጥቅም በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠ ጉዳይ ነው፡፡ ልዩ ጥቅሙን በተመለከተ ሕግ እናወጣለን፡፡ ክቡር ፕሬዚዳንቱ የሁለቱን ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ በመክፈቻ ንግግራቸው ሲከፍቱ በዚህ ዓመት ሕግ ይወጣለታል ነው እንጂ ያሉት ወር አልጠቀሱም፡፡ ይህ ሕግ የሚወጣው በሩጫ አይደለም፡፡ የሕጉ የመጀመሪያ ረቂቅ ተቀርጿል፡፡ ረቂቁን ከተለያዩ የኅብረተሰብ አካላትና ባለድርሻዎች ጋር ሳይመከርበት ወደ ሥራ እንዲገባ የሚደረግ ከሆነ የራሱን ጣጣ ይዞ ይመጣል፡፡ ስለዚህ የተቀረፀው ረቂቅ ሕግ በአመራር ደረጃ ከታየ በኋላ ባለድርሻዎች እንዲወያዩበት ተደርጎ በመጨረሻም የሕግ አወጣጥ ሒደትን ተከትሎ መፅደቅ አለበት እንጂ በሩጫ የሚሆን ነገር አይደለም፡፡ ይህ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳይ ስለሆነ ማንም ሊከራከረው የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ ስለዚህ ተግባራዊ የሚሆን ነው፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ከወሰንና ከማንነት ጋር ተያይዞ የተነሱ ጉዳዮችን በተመለከተ በተለይ የማንነት ጉዳይ ከወሰን ጋር የሚያገናኘው ነገር የለውም፡፡ የማንነት ጉዳይ ሕገ መንግሥታዊ ነው፡፡ ማንኛውም የማንነት ጥያቄ አለኝ የሚል አካል ራሱ ነው መጠየቅ ያለበት፡፡ ወክዬህ እጠይቅልሃለሁ የሚል አካል ሊኖረው አይገባም፡፡ ራሱ ሕዝቡ ነው መጠየቅ ያለበት፡፡ ሕዝቡ ደግሞ እንዴት መጠየቅ እንዳለበት የተቀመጡ መሥፈርቶች አሉ፡፡ ስለዚህ በየትኛውም አካባቢ የማንነት ጥያቄ አለኝ የሚል አካል ካለ በዚያው አካባቢ ላለው መስተዳድር አካል ጥያቄውን ያቀርባል፡፡ በዚያ መሥፈርት ይካሄዳል ብለን አስቀምጠናል፡፡ ይህንን የሚገድብ ምንም ነገር የለም፡፡ ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው፡፡ ይህንን መብት ለማስፈጸም ትክክለኛ የሕዝብ ጥያቄ መሆኑን ማረጋገጥ የግድ ነው፡፡ ከዚህ አልፎ የወሰን ጉዳዮችን በተመለከተ ሁለት ቦታዎች ላይ በፍጥነት መሥራት ያለብን አለ፡፡

አንደኛው በትግራይ ወልቃይት ፀገዴና በአማራ ወልቃይት ጠገዴ አካባቢ ያለ የወሰን ጉዳይ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ይህ የወሰን ጥያቄ ያልተፈታው ውስብስብ ስለሆነ አይደለም፡፡ ያልተፈታው በአመራሮቻችን ውስጥ ባለ የአመለካከት ችግር የተፈጠረ ነው በሚል በተሃድሷችን ውስጥ በዝርዝር አይተናል፡፡ አሁን በቅርቡ ባደረግነው ግምገማ መሠረት ይህ የአመለካከት መዛነፍ ተስተካክሎ ከላይ እስከ ታች እስከ ቀበሌ ድረስ ይህንን የወሰን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለን ገምግመናል፡፡ ስለዚህ የወሰኑን ጉዳይ መወሰን ብዙም ከባድ አይደለም፡፡ በዚያ አካባቢ ያሉ ሕዝቦች ከማናችንም በላይ የሚተዋወቁ ናቸው፡፡ ወሰንህን ራስህ ወስን ብለን ብንተወውና ሌላ ከውጭ የሚገፋ ኃይል ባይኖር በራሳቸው መወሰን ይችላሉ፡፡ ውስብስብ ያደረገው የእኛ አመራር እጅ በረጅሙ ስለሚገባበት ነው፡፡

ሁለተኛው የወሰን ችግር ያለው በሱማሌና በኦሮሚያ በተለይም በምዕራብና በምሥራቅ ሐረርጌና ከዚህ ጋር አጎራባች የሆኑ የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ዞኖችና ቀበሌዎች ነው፡፡ ከዚህ በፊት ሕዝበ ውሳኔ ተካሂዶ የነበረ ሲሆን፣ ይህንን ሕዝበ ውሳኔ ተግባራዊ በማድረግ ዙሪያ በሁለቱም አካባቢዎች መዋቅሮች ያለ ችግር ያወሳሰበው ጉዳይ ነው፡፡ ይህም የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሕይወት እንዲጠፋ ያደረገ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ከመሠረቱ ለመፍታት የሚያስችል አመለካከት ተፈጥሯል፡፡ ሁለቱን ክልሎች ለመርዳት የፌዴራል ጉዳዮችና አርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴር እያስተባበራቸው ጉዳዩን እንደሚፈቱት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ጥያቄ፡- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአገሪቱ የተከሰተውን ግጭት መቀልበስ መቻሉን ተከትሎ ከተያዘለት የስድስት ወራት ጊዜ ቀደም ብሎ ሊነሳ ይችላል ወይ? ገዥው ፓርቲም ሆነ መንግሥት የሁሉንም ኅብረተሰብ ክፍል ድምፅ የሚሰማበት የፖለቲካ ሥርዓት ለማስፈን ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ፈቃደኛ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡ ይህ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል?

ጠ/ሚ ኃይለ ማርያም፡- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳትን በተመለከተ ሊታይ የሚገባው አንደኛውና የመጀመሪያው ጉዳይ ያገኘነው ሰላምና መረጋጋት መሠረታዊ መሆኑን ማረጋገጥ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ የሕዝቡን አስተያየት ማግኘት ይገባናል፡፡ ሕዝቡ አስተማማኝ ሰላም አግኝቻለሁ ስለዚህ አዋጁ ቢነሳ ችግር የለብንም የሚል አስተያየት ከሰጠ፣ አዋጁ በመሠረታዊነት ዘላቂ ሰላምን እንደሚያመጣ ስናረጋግጥ የምናነሳው ይሆናል፡፡ ከሕዝቡ ጋር ተወያይተንና መተማመን ፈጥረን በዚህ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ነው የሚሆነው፡፡ እስካሁን ባለው አፈጻጸም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተጠበቀውን ግብ አሳክቷል፡፡ ይህ ስኬት ዘላቂ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ስናረጋግጥ በማንኛውም ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሊነሳ ይችላል፡፡ ይህ ካልተረጋገጠ ደግሞ ሊራዘም የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ የሚያጣድፈን ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም በኢኮኖሚያችን ላይ ያመጣው ተፅዕኖ የለም፡፡ በዲፕሎማሲያችን ላይም ያመጣው ተፅዕኖ የለም፡፡

ከተቃዋሚዎች ጋር የሚደረግ ግንኙነትና እንደዚሁም ደግሞ ድርድርና ውይይትን በተመለከተ መንግሥትና ገዢው ፓርቲ የወሰኑት ነው፡፡ ዴሞክራሲን የማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው የማድረግ ጉዳይ ተወስኗል፡፡ ከዚህ ውስጥ አንደኛው ከተቃዋሚዎች ጋር የመገናኘት ጉዳይ ነው፡፡ በመንግሥት በኩል የዴሞክራሲ ግንባታን የሚከታተል ማዕከል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ውስጥ ተቋቁሟል፡፡ ይህ ማዕከል ዕቅዱን አውጥቷል፡፡ አንደኛው የዕቅዱ አካል ከተቃዋሚዎች ጋር የመደራደርና የመነጋገር ጉዳይ ነው፡፡ የሚያነሷቸው ጉዳዮች ምን እንደሆኑ አናውቅም፡፡ ነገር ግን መድረኮችን የምናዘጋጅ ይሆናል፡፡ ከዚህ አኳያ ኢሕአዴግን የሚወክል ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡ በድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር [አቶ ደመቀ መኮንን] የሚመራና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ያሉበት ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡ ይህ ኮሚቴም የራሱን ዕቅድ አዘጋጅቶ በሒደት ከተቃዋሚዎች ጋር መነጋገርን ይጀምራል፡፡

እንግዲህ ድርድሩ ሳይጀመር በፊት ድርድሩ ምን ሊሆን ይችላል ብሎ መወሰን አይቻልም፡፡ ስለዚህ ውይይቱ በቅርቡ ይጀመራል ብለን እናምናለን፡፡ ነገር ግን በእኛ ዕይታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የራሳቸውን አማራጭ ፖሊሲ ለሕዝብ በማቅረብ ሚናቸውን እንዲወጡ በመርህ ደረጃ እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን በእኛ አገር ይህ ነው የእኔ አማራጭ ፖሊሲ ብሎ የሚያቀርብ አልታደልንም፡፡ የኢሕአዴግን አፈጻጸምና የኢሕአዴግን ፖሊሲ መተቸት፣ ማብጠልጠል እንጂ አማራጭህ ምንድነው ተብሎ ቢጠየቅ የሚቀርብ ምላሽ እስካሁን አላየንም፡፡ የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሞክሩ አሉ፡፡ እነዚህ መበረታታት ይገባቸዋል፡፡ የድርድር አጀንዳዎችን አብረን ከተቃዋሚዎች ጋር የምንወስን ይሆናል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...