Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበአንድ ሕፃን ላይ በተፈጸመ የሕክምና ስህተት ሳቢያ ከ3.2 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ...

በአንድ ሕፃን ላይ በተፈጸመ የሕክምና ስህተት ሳቢያ ከ3.2 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ ተፈረደ

ቀን:

ዮሐንስ ዘውዱ ዓይናለም የተባለ የአራት ዓመት ሕፃን ለቀዶ ሕክምና ጥር 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በየካቲት ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ገብቶ በተፈጠረ የሰመመን መድኃኒት አሰጣጥ ስህተት (ቸልተኝነት) ምክንያት፣ የአካል መጉደል እንዲደርስበት ማድረጋቸው የተረጋገጠባቸው ሆስፒታሉና የሕክምና ባለሙያው ከ3.2 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ እንዲከፍሉ ተፈረደባቸው፡፡

የሕፃን ዮሐንስ ዘውዱ ወላጆች አቶ ዘውዱ ዓይናለምና ወ/ሮ ጥሩወርቅ ገብረ መስቀል፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ፍትሐ ብሔር ችሎት ያቀረቡት የክስ አቤቱታ እንደሚያስረዳው፣ ልጃቸው የተወለደው ሐምሌ 11 ቀን 2004 ዓ.ም. ነው፡፡ ሕፃኑ ሲወለድ የሽንት መሽኛው ቀዳዳ በተፈጥሮ ሊገኝ የሚገባው ቦታ ላይ አልነበረም፡፡

በመሆኑም ከታኅሳስ 22 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ሕክምና ሲከታተል ቆይቶ፣ የሽንት መሽኛ ቀዳዳውን በትክክለኛ ቦታ ለመመለስ የቀዶ ሕክምና ለማድረግ ጥር 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀዶ ሕክምና ክፍል መግባቱን የክስ አቤቱታው ያስረዳል፡፡

- Advertisement -

የሕፃን ዮሐንስ ቀዶ ሕክምና በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን በቅድሚያ የሰመመን መድኃኒት የ76 ዕድሜ ባለፀጋ የሆኑት የሕክምና ባለሙያ አቶ ዘውዱ ዳምጤ ከወጉት በኋላ፣ የመተንፈሻ ቱቦ በአየር ቧንቧ የመተንፈሻ አካሉ ውስጥ ለማስገባት ጥረት ሲደረግ በተፈጠረ የሕክምና ስህተት፣ የሕፃኑ አንጎል በቂ ኦክስጂን ማግኘት ባለመቻሉ ቀዶ ሕክምናው ሳይደረግ መቋረጡን ለፍርድ ቤቱ የቀረበው የክስ አቤቱታ ይገልጻል፡፡

በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የገጠመው ችግር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለማሳካት በሪፈራል የተላለፈው ሕፃን ዮሐንስ፣ ለ27 ቀናት በፅኑ ሕሙማን ክፍል እንዲቆይ ተደርጎ ከወጣ በኋላ፣ በሆስፒታሉ ሕፃናት ክፍል ለ14 ቀናት ቆይቶ እንዲወጣ መደረጉም በክሱ ተጠቅሷል፡፡

የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ፈቃድ የሌላቸውንና መስማት የማይችሉ የሕክምና ባለሙያ እንዲሠሩ ከማድረጉም በተጨማሪ፣ መቆጣጠሪያ የሌለው ኦክስጂን ለሕፃኑ እንዲሰጥ ማድረጉንም የሕፃኑ ወላጆች በክስ አቤቱታቸው አመልክተዋል፡፡

የመስማት ችግር ያለባቸው የ76 ዓመት የሕክምና ባለሙያ ያለረዳት ማደንዘዢያ በመስጠታቸው፣ ልጃቸው የኦክስጂን እጥረት ሲገጥመው በወቅቱ አፋጣኝ ዕርምጃ ባለመውሰዳቸው የከፋ ጉዳት ላይ ሊደርስ መቻሉንም ወላጆቹ ገልጸዋል፡፡

ሆስፒታሉን ባለሙያው በፈጸሙት የሕክምና ግድፈት (ቸልተኝነት) በልጃቸው ላይ ከባድ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት እንደደረሰባቸውም ወላጆቹ አክለዋል፡፡

ሕፃኑ በተፈጠረበት የሕክምና ግድፈት ሁለት ዓይኖቹ እንደማያዩና ጆሮው መስማት እንደተሳነው፣ እጆቹና እግሮቹ ፓራላይዝድ በመሆናቸው መቆምና መቀመጥ እንደማይችል፣ የነርቭና የሚጥል ሕመም እንደያዘውና ሽንቱንም ሆነ ዓይነ ምድሩን መቆጣጠር እንደማይችል ወላጆቹ በዝርዝር በክስ አቤቱታቸው ላይ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ወላጆቹ በልጃቸው ላይ በደረሰው ከባድ ጉዳት ለሕክምናና ተያያዥ ችግሮች ከአቅማቸው በላይ መሆናቸውን አስረድተው፣ ፍርድ ቤቱ ተገቢ ካሳ ማለትም 5.6 ሚሊዮን ብር እንዲያስከፍላቸው ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡

ሆስፒታሉ የክስ ማስረጃ ደርሶት በሰጠው መልስ ሕፃኑ ለቀዶ ሕክምና መግባቱን አረጋግጦ፣ የደረሰበት ችግር የመተንፈሻው ቱቦ ወደ ውስጥ አለመግባት የሕፃኑ የተፈጥሮ ችግር እንጂ የባለሙያ ስህተት አለመሆኑን አስረድቷል፡፡ የሕክምና ባለሙያውም ከ60 ዓመታት በላይ ያለምንም ስህተት ሲሠሩ የኖሩ ባለሙያ መሆናቸውንና ከተለያዩ ተቋማት የሙያ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ያገኙ መሆኑን አስረድቷል፡፡ ነገር ግን የምስክር ወረቀቶቻቸውን፣ የምግብ፣ ጤና ክብካቤና አስተዳደር ቁጥጥር ባለሥልጣን የሰረዘባቸው ቢሆንም ቀደም ብሎ የተሰጣቸው የሙያ ፈቃድ ግን እንደነበራቸው አክሏል፡፡

የሕክምና ባለሙያውም በሰጡት ምላሽ ሕፃኑ በተፈጥሮ የሽንት መሽኛ አካሉ ቀዳዳ ሊገኝ በሚገባው ቦታ አለመኖሩ፣ ሕፃኑ በትክክል የሰው አካል ቅርፅ ይዞ ያልተወለደና ከፍተኛ ችግር ያለበት መሆኑን መረዳት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

ሆስፒታሉ ባለሙያው ከ60 ዓመታት በላይ ልምድ እንዳላቸው ገልጾ ለፍርድ ቤቱ ምላሽ የሰጠ ቢሆንም፣ ባለሙያው ግን ከ40 ዓመታት በላይ የአገልግሎት ዘመን እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡ ከአገር ውስጥና ከአገር ውጭ አብረዋቸው የሠሩ ባለሙያዎች የምስክርና የምሥጋና ወረቀቶች የሰጡዋቸው ምሥጉን ሠራተኛ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ የመስማትና ማዳመጥ ችሎታም እንዳላቸውና ስላለመስማታቸው ማስረጃም እንዳልቀረበባቸው ገልጸዋል፡፡  

ተከሳሾቹ ዘርዘር ያለ ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ የምስክሮች ቃል መስማቱንም ገልጿል፡፡

በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ የመተንፈሻ አካል ውስጥ የመተንፈሻ ቱቦ የማስገባት ችግር የተከሰተው በሕፃኑ የተፈጥሮ ችግር ነው? ወይስ የሕክምና አሰጣጥ ስህተት? በሕክምና ስህተት ነው ከተባለ ንፁህ አየር ማጣት የሚጥል በሽታን ያስከትላል? ወይስ አያስከትልም? ተከሳሾቹ ኃላፊነት አለባቸው? ወይስ የለባቸውም? አለባቸው ከተባለ ምን ያህል የጉዳት ካሳ ሊከፈል ይችላል የሚሉ ጭብጦችን ይዞ መመርመሩን በውሳኔው መዝገብ ላይ አስፍሯል፡፡

በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ሁሉንም የክርክርና የማስረጃዎችን ከተገቢው ሕግ ጋር በማገናዘብ ከመረመረ በኋላ፣ በሕፃኑ ላይ የተከሰቱ በሽታዎችና ችግሮች በተፈጥሮ የመጡ ሳይሆኑ፣ በሆስፒታሉና በሕክምና ባለሙያው ስህተት መሆኑን በማረጋገጥ፣ ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡ ሁለቱ ተከሳሾች 3,002,452 ብር ካሳ እንዲከፍሉ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ድርጊቱ የወንጀል ኃላፊነትንም ስለሚያስከትል በወንጀል ተከሰው ጉዳዩ በሒደት ላይ መሆኑም ታውቋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...