Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹የኛ›› ፕሮጀክት ዕርዳታው የተቋረጠበት በፕሮግራሙ ችግር ሳይሆን በእንግሊዝ የውስጥ ፖለቲካ ነው አለ

‹‹የኛ›› ፕሮጀክት ዕርዳታው የተቋረጠበት በፕሮግራሙ ችግር ሳይሆን በእንግሊዝ የውስጥ ፖለቲካ ነው አለ

ቀን:

‹‹የኛ በተሻለና በላቀ ደረጃ ይቀጥላል›› ወይዘሮ ሰሎሜ ታደሰ

የኛ ፕሮጀክት ከእንግሊዝ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት ዲፊድ (DFID) ያገኝ የነበረው ድጋፍ የተቋረጠው በፕሮግራሙ ችግር ሳይሆን፣ እንግሊዝ ከአውሮፓ ኅብረት በመውጣቷ ምክንያት እየተንፀባረቀ ባለው የቀኝ ዘመም ፖለቲካ ተፅዕኖ ሳቢያ መሆኑን፣ የየኛ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰሎሜ ታደሰ ማክሰኞ ጥር 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቁ፡፡

አሁን ባለው የእንግሊዝ ፖለቲካ እንደ የኛ ያሉ ማብቃትንና ማስቻልን ዓላማ ያደረጉ ፕሮጀክቶች ላይ ሳይሆን፣ እንደ አስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ያሉ የነፍስ አድን ድጋፎች ላይ ማተኮር ይመረጣል ብለዋል፡፡ ‹‹ከመነሻውም የኛ አስቻይ መሆኑን ተናግረናል፡፡ የኛ ተደብድባ ዓይኗ የጠፋ ሴት የምትገባበት መጠለያ እንዲኖር ሳይሆን፣ ዓይኔ አይጠፋም የምትል ሴት መፍጠር ነው፤›› በማለት ወ/ሮ ሰሎሜ አስረድተዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም በወቅታዊው የፖለቲካ ተፅዕኖ የኛ ቀዳሚ ዒላማ እንደሆነ ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ አስረድተዋል፡፡

ዕርዳታ መስጠት የመቀነስና የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታዎች ላይ ትኩረት እንዲደረግ የሚያደርገው የቀኝ ዘመም ፖለቲካ በአውሮፓም በአሜሪካም እየተንፀባረቀ ቢሆንም፣ የኛ ያነገበውን ዓይነት ዓላማ ከሚደግፉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር አጋርነቱን እንደሚያጠናክር የገለጹት ወ/ሮ ሰሎሜ፣ የኛ በተሻለና በላቀ ደረጃ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡ በቀጣይ አብሯቸው ሊሠራ የሚችል ዓለም አቀፍ ተቋም መኖሩን የጠቆሙት ወይዘሮ ሰሎሜ፣ የተቋሙን ስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፡፡ እስካሁን ከተቋሙ ባገኘው ድጋፍ ለቀጣዮቹ ስድስት ወራትና ከዚያም በላይ እንደሚዘል ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ትልቁ ነገር በውጭ ዕርዳታ መንቀሳቀስ ሳይሆን በራስ አቅም መሥራት በመሆኑ፣ የአገር ውስጥ ፈንድ ማግኘትንም እንደ ሌላ አማራጭ እንደሚመለከቱት ጠቁመዋል፡፡ የተቋማት ማኅበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ነገር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትንሹም ቢሆን እየታየ መሆን በዚህ ረገድ ተስፋ እንደሆነም እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

የእንግሊዝ ዓለም አቀፍ እርዳታ ድርጅት (ዲፊድ) ለየኛ የሚሰጠውን ድጋፍ ማቋረጡ፣ በቀጣይ ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ለመመሥረት የሚፈልገው አጋርነት ላይ ተፅዕኖ ይኖረው እንደሆነ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የተነሳላቸው ወ/ሮ ሰሎሜ፣ ውሳኔው በዚህ ረገድ ተፅዕኖ ይኖረዋል ብለው እንደሚምኑ አስረድተዋል፡፡

የየኛ የሬዲዮ ፕሮግራሞች ላለፉት ሦስት ዓመታት ተኩል አየር ላይ ውለዋል፡፡ ዲፊድም በእነዚህ ጊዜያት በሠራቸው ዓመታዊ ግምገማዎች የኛ በእያንዳንዱ “A”  ማግኘቱን ወ/ሮ ሰሎሜ ገልጸዋል፡፡

የዲፊድ አጋር ገርል ኢፌክት (Girl Effect) ሲሆን፣ የኛ ደግሞ አንዱ የገርል ኢፌክት ፕሮግራም ነው፡፡ የዲፊድ የአሁኑ ውሳኔም ሙሉ በሙሉ የገርል ኢፌክትን በጀት ማቋረጥ ነው፡፡ ሪፖረተር ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ይህ ውሳኔ ድንገተኛ በመሆኑ ሊደረግ ይገባ እንደነበረው አጥኚ ቡድን መጥቶ ሁኔታውን ገምግሞ የተወሰነ አይደለም፡፡ ይህም የፕሮግራሞቹን ሽግግር አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል፡፡

ዲፊድ ከዚህ ቀደም ለኢትዮጵያ ይሰጥ ከነበረው ዕርዳታ ከፍተኛውን መቀነሱም ይታወሳል፡፡

የኛ በመባል የሚታወቀው ፕሮጀክት በገሃዱ ዓለም ውስጥ ታዳጊ ሴቶች የሚያጋጥማቸውን ችግሮች ማለትም ያለዕድሜ ጋብቻ፣ ጥቃትና የትምህርት ክልከላ በድራማና በሙዚቃ አማካይነት በሴቶች ልጆች ላይ የሚንፀባረቀው አመለካከት እንዲቀየርና ሴቶች ልጆችም ስለራሳቸው የነበራቸውን አስተሳሰብ ለመለወጥ የሚሠራ ነው፡፡ በዚህም ሚሊዮኖች ዘንድ በመድረስ በአዎንታዊ ጎኑ መነጋገሪያ መሆን የቻለ ፕሮጀክት ነው፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...