– ኮርፖሬሽኑ ዘንድሮ ከውጭ ስኳር አላስገባም ብሏል
ለረዥም ዓመታት የተጓተቱና ከተያዘላቸው በጀት በላይ የበሉ ስኳር ፕሮጀክቶችን ለመታደግ፣ መንግሥት በሽርክና መሥራት ለሚፈልጉ ኩባንያዎች ባቀረበው ግብዣ በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፍላጎታቸውን አሳዩ፡፡
ከአፍሪካ፣ ከአውሮፓና ከሩቅ ምሥራቅ አገሮች የመጡ በርካታ ኩባንያዎች ከመንግሥት ጋር በሽርክና ኢንቨስት ለማድረግ ጥያቄ እያቀረቡ፣ የመግባቢያ ሰነድ እየተፈራረሙና ዝርዝር ጥናቶችንም ማካሄድ መጀመራቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የኩባንያዎቹን ጥያቄ ለማስተናገድ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የኢንቨስትመንት ጥናትና ልማት ዘርፍ ኮሚቴ አዋቅሮ እየሠራ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡ ይኼ ኮሚቴ የኩባንያዎቹን ምክረ ሐሳብ ከመረመረ በኋላ በኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አብተው ለሚመራው የስኳር ኮርፖሬሽኑ ሥራ አመራር ቦርድ አቅርቦ እንደሚያስወስን ታውቋል፡፡ ቦርዱ ካፀደቀውና የኩባንያዎቹ ጥያቄ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በየነ ገብረ መስቀል ቀርቦ ይሁንታ ካገኘ ወደ ሥራ ይገባል ተብሏል፡፡
በውስብስብ ችግሮች ውስጥ የተዘፈቀው የኢትዮጵያ ስኳር ልማት ካለበት ችግር ውስጥ ለማውጣት፣ በአገር ውስጥና በውጭ ኢንቨስተሮች ላይ ትኩረት ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ፍላጎት ያላቸው የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ወደ ዘርፉ እንዲገቡና በስኳር ልማት እንዲሳተፉ ጋብዟል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በነባር ስኳር ፋብሪካዎችና በተጀመሩ አሥር የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶች በተለይ በስኳር ልማት፣ በኢታኖል ልማት፣ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ በመሬት ልማት፣ በቤቶች ግንባታ መስኮች ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ ኩባንያዎች ግብዣ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በተለይ በኢታኖል ልማት ራሳቸውን ችለው ለሚያለሙ ኩባንያዎች በሩን ክፍት ማድረጉንም ጨምሮ ገልጿል፡፡ ፍላጎት ያላቸው ኩባንያዎች በቂ ካፒታል፣ የዕውቀት ሽግግር ማድረግ የሚችሉ፣ የገበያ ትስስር ያላቸው መሆንም እንዳለባቸው ኮርፖሬሽኑ ባወጣው የፍላጎት መግለጫ ላይ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በነባሮቹ መተሐራ፣ ፊንጫና ወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካዎች የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች አካሂዷል፡፡ ተንዳሆን ጨምሮ 11 አዳዲስ ስኳር ፕሮጀክቶችም በመካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ አዳዲስ ስኳር ፕሮጀክቶች በኮንትራት አስተዳደርና በፋይናንስ ዕጦት ውስጥ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ እነዚህን ፕሮጀክቶች ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ኮርፖሬሽኑ የአሠራር ለውጥ አድርጓል፡፡ ‹‹የአሠራር ለውጡ ኩባንያዎቹ ከመንግሥት ጋር በጋራ ሠርተው የትርፍ ተካፋይ እንዲሆኑ በማድረግ በዘርፉ ለውጥ ማምጣት፤›› ነው ሲሉ አቶ ጋሻው ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን በተለይ ወደ ምርት ያልገቡት ስኳር ፋብሪካዎች ከአገር ውስጥና ከውጭ ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ የተበደሩ ቢሆንም፣ ፕሮጀክቶች በሥራ አፈጻጸም ችግር ከመዘግየታቸው ባለፈ የብድር መክፈያ ጊዜያቸው የቀረበ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡
ከአገር ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ከውጭ ደግሞ የህንድና የቻይና ባንኮች ለፕሮጀክቶቹ ብድር ካቀረቡት መካከል ይገኙበታል፡፡ በሼባ ቦንድ ተጨማሪ ገንዘብ ማግኘቱም ይታወሳል፡፡
ተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ በ1997 ዓ.ም. ሲጀመር 64 ሺሕ ሔክታር መሬት ለማልማት 26 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ስኳር እንደሚያመርት፣ ይኼ ፕሮጀክትም በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞ ነበር፡፡
የተንዳሆ ብድር የተገኘው ከህንድ እንደመሆኑ ግንባታውም ኦቨርሲስ ኢንፍራስትራክቸር አልያንስ ለተሰኘ የህንድ ኩባንያ ተሰጥቶ ነበር፡፡
ነገር ግን ተንዳሆ ከተያዘለት ጊዜ እጅግ ዘግይቶ ከ12 ዓመታት በኋላ ቢጠናቀቅም፣ ማምረት ግን አልጀመረም፡፡ ይህ ፕሮጀክት ግድቡ ብቻ በ1.8 ቢሊዮን ብር ይጠናቀቃል ተብሎ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን 5.6 ቢሊዮን ብር እንደወጣበት ተገልጿል፡፡
ሌሎችም ፕሮጀክቶች ይጠናቀቃሉ ተብሎ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ መጠናቀቅ ካለመቻላቸውም በላይ፣ ከተያዘላቸው በጀት በላይ እየወጣባቸው መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡
ኮርፖሬሽኑ እነዚህን ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ የግድ የውጭና የአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ተሳትፎ እንደሚፈልግ ተገልጿል፡፡
ከአገር ውስጥ ኩባንያዎች ውስጥ አሁን ባለው ሒደት አሚባራ ግብርና ልማት ኩባንያ ተሳታፊ ሆኗል፡፡ አሚባራ በስድስት ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ ሸንኮራ አገዳ አልምቶ ለከሰም ስኳር ፋብሪካ ማቅረብ መጀመሩን አቶ ጋሻው ገልጸዋል፡፡
ስኳር ኮርፖሬሽን በተያዘው በጀት ዓመት ከውጭ ስኳር ሳያስገባ ለመጀመሪያ ጊዜ በአገር ውስጥ ለመሸፈን ማቀዱን አቶ ጋሻው ተናግረዋል፡፡ ከነባሮቹ በተጨማሪ አርጆ ደዴሳ፣ በብረታ ብረትና ኢንጅነሪግ ኮርፖሬሽን የሚገነባው ኩራዝ ቁጥር አንድና በቻይናው ኮምፕላንት የሚገነባው ኩራዝ ቁጥር ሁለት ስኳር ፋብሪካዎች ወደ ምርት ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡
ከእነዚህ አዳዲስ ፋብሪካዎችና ከነባሮቹ በአጠቃላይ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ይመረታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ይህም ለአገር ውስጥ ፍጆታ በቂ በመሆኑ የአገር ውስጥ ፍላጎት በአገር ውስጥ ምርት ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሚሸፈን አቶ ጋሻው ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ባለፈው በጀት ዓመት የተገዛው 1.5 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ወደ አገር በመግባት ላይ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ጋሻው፣ ይህ ስኳር መጠባበቂያ ይሆናልም ብለዋል፡፡