[የክቡር ሚኒስትሩ ልጅ ላፕቶፑ ፊት ለፊት ሆኖ ይስቃል]
- ምንድነው የሚያስቅህ?
- በጣም ደስ የሚል ነገር ነው፡፡
- እኮ ምንድነው?
- በጣም ተደስቻለሁ ዳዲ፡፡
- ይኼ ፌስቡካችሁ ተለቀቀ እንዴ?
- እሱ ይኼን ያህል ያስደስታል ብለህ ታስባለህ?
- እና ቫይበር ተለቆ ነው?
- ኧረ እሱ አይደለም ዳዲ፡፡
- እና ምን ሆነህ ነው?
- ኢሜይል ተልኮልኝ፡፡
- የምን ኢሜይል ነው እንደዚህ የሚያስቅህ?
- ስኮላርሽፕ አገኘሁ ዳዲ፡፡
- እውነት?
- ይኸው ተመልከተው ዳዲ፡፡
- እስቲ አምጣው፡፡
- በጣም የሚያስደስት ዜና ነው፡፡
- ሙሉውን አንብበኸዋል ግን?
- አዎን ዳዲ ምነው?
- ግማሽ ስኮላርሽፕ ነው እኮ?
- ቢሆንስ ዳዲ?
- ግማሹ ከየት ይመጣል ብዬ ነው?
- እንዴ ዳዲ?
- ምነው?
- በፊት ቢሆን እንደዛ እጨነቅ ነበር፡፡
- አሁንስ?
- አሁንማ ምንም አያሳስብም፡፡
- እኮ ለምን?
- ሚኒስትር ሆነሃላ፡፡
- አንተ ልጅ?
- አሁን እኮ አስተሳሰቤ ተቀይሯል፡፡
- ማለት?
- የሚኒስትር ልጆች ምን ጥቅም እንዳላቸው ጠንቅቄ ነው የማውቀው፡፡
- እኔ ጠፋሁ?
- ዳዲ ግማሹ እኮ ወደ 20 ሺሕ ዶላር ብቻ ነው፡፡
- እና ከየት ይመጣል?
- ሕፃን ልጅ አደረግከኝ እንዴ ዳዲ?
- ምን እያልክ ነው?
- ለቢሯችሁ ስንትና ስንት ስኮላርሽፕ ይመጣ አይደል እንዴ?
- እሱማ ይመጣል፡፡
- እና የሚሄደው ሰው ግን ሠራተኛችሁ ሳይሆን ገንዘብ ያለው ሰው አይደል እንዴ?
- ምን?
- ዳዲ ዋናው እኔ ስኮላሩን ላግኘው እንጂ አንተ እንደምንም ትልከኛለህ፡፡
- ከየት አምጥቼ ነው የምልክህ?
- የሚኒስትር ልጅ ነኝ አልኩህ እንግዲህ፡፡
- ከሌላው ኢትዮጵያዊ ልጅ በምን ትለያለህ ታዲያ?
- በሁሉም ነገር፡፡
- የኪራይ ሰብሳቢ አስተሳሰብ ተጠናውቶሃል ልበል?
- ዳዲ አሜሪካ እኮ ነው፡፡
- ቢሆንስ?
- ወተትና ማር የምታፈልቀዋ ምድር፡፡
- ስማ እንዳትሸወድ ይኼ ተራ አፈ ታሪክ ነው፡፡
- አንተ በተደጋጋሚ ሄደሃል አይደል እንዴ?
- ያየሁትን እኮ ነው እየነገርኩህ ያለሁት፡፡
- ለማንኛውም እኔም ሄጄ እስከማያት ድረስ ወተትና ማር እንደምታፈልቅ ነው ማመን የምፈልገው፡፡
- እዛ በመሄድህ ለውጥ አመጣለሁ ብለህ ታስባለህ?
- በሚገባ ዳዲ፡፡
- በምን?
- በሽቀላ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከአንድ ባለሀብት ጋር በውድ ሬስቶራንት ውስጥ ምሳ እየበሉ ነው]
- እንዴት ነዎት ክቡር ሚኒስትር?
- አንተ ምን ዓይነት ሬስቶራንት ነው እባክህ?
- ወደዱት ክቡር ሚኒስትር?
- በጣም የሚገርም ሬስቶራንት ነው፡፡
- ውስጡ ያሉትን ሰዎች ተመልክተዋል?
- ብዙ የማውቀው ሰው አየሁ፡፡
- የማይመጣ ሰው የለም ስልዎት፡፡
- ውድ ምግብ ቤት መሆኑንም ሰምቻለሁ፡፡
- ያን ያህል እንኳን ውድ አይደለም፡፡
- ለአንድ ምግብ ከሺሕ ብር በላይ ነው የሚከፈለው አሉ፡፡
- ታዲያ ምን አላት ክቡር ሚኒስትር?
- ምን አልከኝ?
- ብዙ አይደለም እኮ፡፡
- በወር እኮ ከዚህ በታች የሚከፈለው አለ፡፡
- ምን ያደርጉታል ታዲያ?
- እና ይኼ ሁሉ ሰው ሠርቶ ነው ሰርቆ የሚከፍለው?
- ሠርቶም ሰርቆም የሚከፍል አለ፡፡
- አንተ ከየትኛው ወገን ነህ?
- ኧረ እኔ ሠርቼ አዳሪ ነኝ፡፡
- እውነት?
- ዛሬ ራሱ ለሥራ ነው የቀጠርኩዎት?
- ታዲያ ለሥራ ቢሮ አይሻልም?
- ከቢሮ ይልቅ እዚህ ብዙ ይሠራል፡፡
- እ….
- ይኼ ሁሉ ሰው እኮ ስለሥራ ነው የሚያወራው፡፡
- እሺ ምንድነው ሥራው?
- ባለሀብቶች አሉ፡፡
- የምን ባለሀብት?
- የውጭ ባለሀብቶች ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እሺ፡፡
- እርስዎን መተዋወቅ ይፈልጋሉ፡፡
- ለምን?
- አይ ክቡር ሚኒስትር ለምን ብሎ ጥያቄ አለ እንዴ?
- አልገባኝም?
- እንድንጠቃቀም ነዋ፡፡
- ስማ ሰውዬ!
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- እኔ እንዲህ ዓይነት ነገር አልፈልግም፡፡
- ምን እያሉ ነው?
- አታነካኩኝ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ደግሞ ባለፈው ስጦታ ተልኮልዎት አልነበር እንዴ?
- እኔ ማን እንደላከው መቼ አወቅኩ?
- ክቡር ሚኒስትር መግደርደሩ ቢቆይዎት ጥሩ ነው፡፡
- እ….
- አሁን የሚፈልጉት ነገር የለም?
- ምን አልከኝ?
- ከቅድም ጀምሮ ሳይዎት ራሱ አንድ የሚያስጨንቅዎት ነገር ያለ ይመስላል፡፡
- ያስታውቅብኛል እንዴ?
- እኮ ምንድን ነው የሚፈልጉት?
- እሱ የግል ጉዳይ ነው፡፡
- ንገሩኝ ቤተሰብ አይደለንም እንዴ?
- ልጄ ስኮላርሽፕ አግኝቶ ነበር፡፡
- እንኳን ደስ አለዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ግን ግማሽ ስኮላርሽፕ ነው ያገኘው፡፡
- ስንት ነው ግማሹ?
- 20 ሺሕ ዶላር፡፡
- በቃ እኔ 50 ሺሕ ዶላር ዛሬ በስሙ አስገባለታለሁ፡፡
- ምን?
- ከነመዝናኛው ጭምር ነው አያስቡ፡፡
- እውነትህን ነው?
- አያስቡ ስልዎት፡፡
- ምን ይባላል?
- አመሰግናለሁ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቢሮ ሲገቡ አማካሪያቸውን አገኙት]
- እንዴት ነበር ምሳ ክቡር ሚኒስትር?
- የሚገርም ቦታ ነው፡፡
- አዩት ያን ሬስቶራንት አይደል?
- ሒሳቡን ሳይ ልቤ ልትቆም ነበር፡፡
- ለምን ክቡር ሚኒስትር?
- ለግምጃ ቤት ኃላፊው የምንከፍለውን ደመወዝ እኮ ነው ከፍለን የወጣነው፡፡
- ውይ መጠጥ አልቀማመሳችሁም ማለት ነው፡፡
- አዎ ውኃ ነው የጠጣነው፡፡
- ወይን ብትጨምሩባት የእኔና የእርስዎን ደመወዝ ይሆን ነበር፡፡
- ሰው ግን ከየት ነው የሚያመጣው?
- የግል ዘርፉ ሄዷል እኮ፡፡
- እሱን ነው እኔም የተረዳሁት፡፡
- እና ምን አለዎት?
- አንድ የውጭ ኢንቨስተር ይመጣል ነው የሚለው፡፡
- እውነት ክቡር ሚኒስትር?
- አዎን ምነው?
- አንድ ነገር ልምከርዎት?
- ምን?
- ይኼ አጋጣሚ ሕይወትዎን ሊቀይረው ይችላል፡፡
- እንዴት?
- በቃ የቀድሞው ሚኒስትር ሕይወታቸው እንደዚህ ነው የተቀየረው፡፡
- እና ምን ላድርግ?
- አንድ የተለመደች ነገር ይጠይቁት፡፡
- ምን?
- ኮሚሽን!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር ወደ ቤት እየሄዱ ነው]
- ኧረ አልቻልኩትም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምኑን?
- የሰሞኑን ብርድ፡፡
- አየሩ ተቀይሯል፡፡
- እኔማ የመንግሥት እጅ ያለበት መስሎኝ ነበር፡፡
- እንዴት?
- ያው ሚኒስትሮቹ ሲቀያየሩ በዛውም አየሩንም ከቀያየሩት ብዬ ነዋ፡፡
- ዝም ብለህ አትዘባርቅ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ግን ከእንትኑ ጋር አይያያዝም?
- ከምኑ ጋር?
- ከጥልቅ ተሃድሶ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ሲገቡ ሚስታቸውን አገኟቸው]
- ና የእኔ አንበሳ፡፡
- ምን ተገኘ ደግሞ?
- አንተ እኮ ጋማ የለህም እንጂ የእውነት አንበሳ ነህ፡፡
- ምንድን ነው የምትጠጪው?
- ብሉ ሌብል ነዋ ባሌ፡፡
- እ….
- ዛሬ ያልጠጣሁ መቼ ልጠጣ?
- ማን አምጥቶ?
- ከዚህም በላይ መጥቷል፡፡
- ምን ተገኘ ዛሬ?
- የልጃችን ስኮላርሽፕ ብትል፡፡
- ግማሽ እኮ ነው ስኮላርሽፑ?
- 50 ሺሕ ዶላሩ ገባለት አይደል እንዴ?
- ምን?
- ምን እሱ ብቻ?
- ሌላ ደግሞ ምን መጣ?
- ከዚህች እልህ አስጨራሽ መኪናም ልሰናበት ነው፡፡
- እ…
- ላኩልን እኮ፡፡
- ምኑን?
- ቁልፉን፡፡
- የምኑን?
- የቪ8ቱን!