Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የገልፍ አገሮችን ተቀማጭ እንዲያማትር መንግሥትን ያስገደደው የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢኮኖሚ ዘርፉን በተመለለከተ በተለይ አገሪቱ የገጠማትን የውጭ ምንዛሪ ዕጥረትን የተመለከተው ጥያቄ ብዙ ሲያነጋግር ቆይቷል፡፡ ለበርታ ተከታታይ ዓመታት በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት መታየቱ ሲነገር ቢቆይም፣ መንግሥት ሲያጣጥለው ቆይቷል፡፡ ጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቻው መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከብዙ ማቅማማት በኋላ ግን የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት መኖሩን ያመኑት በገርማሜው ነበር፡፡ በተደጋጋሚ የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት የለም፣ ችግር አልገጠመንም ሲሉ መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡

ለምንዛሪ ዕጥረቱ ችግሮች ተብለው የሚጠቀሱ በርካታ ነጥቦች ሲኖሩ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአገሪቱ የወጪ ንግድ ገቢ በከፍተኛ መጠን እያሽቆለቆለ መምጣቱ አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ከወጪ ንግዱ የተገኘው ገቢ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር ያነሰ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ለዚህ ደካማ አፈጻጸም ድርቁ አስተዋጽኦ እንደነበረው ሲነገር ቢቆይም፣ መንግሥት እምብዛም እንዳልጎዳው ሲከራከር ቆይቷል፡፡ ዘንድሮ በተከሰተው የፖለቲካ ቀውስና በዓለም ገበያ ከሚታየው የሸቀጦች ዋጋ መቀዛቀዝ አኳያ፣ የወጪ ንግዱ ዘንድሮም መዋዠቅ ውስጥ እንደሚገባ ይገመታል፡፡

ለገቢው ማሽቆልቆል ምክንያት እየተደረጉ ከሚገኙ አንኳር ችግሮች መካከል የመገበያያ ገንዘብ የሆነው የብር የመግዛት አቅም ከኢኮኖሚው አቅም ጋር ያልተናበበና ከአቅም በላይ ዋጋ እንዲኖረው መደረጉ አንዱ ነው፡፡ ስለዚህም የምንዛሪ ለውጥ በማድረግ፣ የብር የመግዛት አቅም እንዲቀንስ ማድረግ ይገባል የሚለው ጥያቄ ይጎላል፡፡

ስለዚህ ጉዳይ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት በእኛ የዕድገት ደረጃ ላይ የነበሩ አገሮች ሁሉ ያጋጥማቸው የነበረ ችግር ነው፡፡ ዛሬ በኢኮኖሚያቸው ውስጥ ትርፍ መጠባበቂያ (ሰርፕለስ) ያላቸው እነ ኮሪያ፣ እነ ጃፓን ሁሉ በእኛ ደረጃ በነበሩበት ወቅት የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ክፉኛ ተፈታትኗቸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ የሴቶቻቸውን ፀጉር ሳይቀር ቆርጠው ኤክስፖርት እስከማድረግ ተገደው ነበር፡፡  ችግሩ ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም፡፡ በዚያ መነጽር ካላየነውና ለኢትዮጵያ ብቻ የመጣ ጣጣ ካደረግነው ትክክል አይመጣም፤›› ብለዋል፡፡

ይሁንና የኤክስፖርት ዘርፉ ከዓምናው አኳያ ተመሳሳይ አፈጻጸም እንዳለው ገልጸዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ግኝት በፖለቲካ ቀውስ ምክንያት ሳይሆን በመዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሁኔታና በሚዋዥቀው የግብርና ዘርፍ ምክንያት ችግር እንደሚታይበት ተናግረዋል፡፡ ከግብርና ይልቅ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለውጭ ገበያ የማቅረብ ዓላማ በመያዝ መንግሥት እየሠራ እንደሚገኝ፣ ለዚህም መንግሥታቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የመሳሰሉ ግንባታዎችን በማካሄድ ዘርፉን እየደገፈ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ የግብርና ምርቶች እየጨመሩ እንደሚገኙና በ20 በመቶ ጭማሪ መታየቱን ይልቁንም ግን ዓለም አቀፍ ገበያው በመዋዠቁ ምክንያት የወጪ ንግድ ገቢ መቀነሱን ጠቅሰዋል፡፡

ላለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት የአገሪቱ የግብርና ሸቀጦች የወጪ ንግድ መጠን መጨመሩን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይሁንና ግን የዓለም ገበያ ከፍና ዝቅ ማለቱ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ገቢ እየጎዳው እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ‹‹አንዳንዴ ያልታሰበ ገቢ ታገኛለህ፡፡ አንዳንዴ ሳታስበው መቀመቅ ትወርዳለህ፡፡ ስለዚህ እዚህ ቁማር ላይ ማተኮሩ ብዙ እንደማያዋጣ ነገር ግን በልዩነቱ ምክንያት የሚመጣውን ጫና ለመቀነስ መፍትሔው ወደ ውጭ የሚላከውን መጠን መጨመር ነው፡፡ በእኛ ቁጥጥር ሥር ያለው ይሄው ስለሆነ መፍትሔውም ይሄው ነው፤›› ብለዋል፡፡ እስከ 80 ከመቶ የሚሆነውን የአገሪቱን የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ የተቆጣጠረው ይኸው የግብርና ዘርፍ በየጊዜው የሚላከው መጠን እየጨመረ ቢሆንም፣ የዓለም ገበያ ባሳየው መቀነስ ምክንያት የተፈጠረው ማሽቆልቆል ግን ‹‹ማሽቆልቆል ተብሎ አይወሰድም›› በማለት ተከራክረዋል፡፡

‹‹መነጻጸር ያለበት መጠኑ ነው፡፡ ዕድገትን የሚያሳየውም ይኸው በመሆኑ ነው ዋጋው ግን እንደገበያው ሁኔታ የሚወሰን ነው፤›› ያሉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ ከግብርና ይልቅ በማኑፋክቸሪንግ ሸቀጦች መስፋፋት መትፍሔ መሆኑም ያብራራሉ፡፡ 12 የኢንዱስትሪ ፓርኮች እየተገነቡ እንደሚገኙ፣ ከእነዚህ መካከል አንድ ቢሊዮን ዶላር የኤክስፖርት ገቢ የሚጠበቅበት የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ምሳሌ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

ሌላኛው ስትራቴጂ ከኢትዮጵያ ግንኙነት ያላቸው ወዳጅ አገሮች በተለይም የባህረ ሰላጤው አገሮች ተቀማጭ ሒሳባቸውን በውጭ ምንዛሪ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲያስቀምጡ ማድረግ ሲሆን፣ ዓምና ይሄ እንደተሞከረና ዘንድሮ ተጠናቅሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡ የወጪ ንግዱ አፈጻጸምም ሆነ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ችግር በመኖሩ ምክንያት ባንኮች በወረፋ የማዳረስ አሠራራቸው ተገቢ እንደሆነ ሞግተዋል፡፡ ‹‹ዕጥረት ካለ ወረፋ ጠብቀህ መውሰድ የማይቀር ነው፡፡ ዕጥረት ካለ ወረፋ ይኖራል፡፡ ከዚህ በፊት የግል ባንኮች ለንግድ ዘርፉ ብቻ ይሰጡ የነበረውን አሠራር ቅድሚያ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሰጡ የብሔራዊ ባንክ መመርያ በማውጣቱ የፖሊሲ አቅጣጫ ነው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ማሽቆልቆሉ ብቻም ሳይሆን የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ ይደረግ የሚለው ጥያቄም እውነታ እንዳለው አምነዋል፡፡ የተመን ማሻሻያ በማድረግ ወጪን ማዳን እንደሚቻልና የተወሰነ ገቢ ለማግኘትም እንደሚያስችል ጥሪ እየቀረበ ቢሆንም፣ ይህንን ጥሪ ግን አደጋ የሚያስከትል ሲሉ ገልጸውታል፡፡

‹‹የውጭ ምንዛሪ ተመን እንዲቀንስ የሚጠይቁ ባለሙያዎች የሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት አለው፡፡ ነገር ግን የምንዛሪ ተመን ለውጥ ሲደረግ የሚመጣ አደጋ አለ፡፡ እንደ ታዳጊ አገር በርካታ ኢንቨስትመንቶችን እያካሒድን ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ተመን እንዲቀንስ ሲደረግ [ከውጭ የሚገባው ዕቃ] በአገር ውስጥ የሚሸጥበት ዋጋ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ይህ ከሆነ ከውጭ የሚገባው ዕቃ በከፍተኛ መጠን እንዲገታ ስለሚያደርግ አገራዊው ባለሀብት በከፍተኛ ደረጃ እንዲመታ ያደርጋል፤›› በማለት የማሻሻያ ጥያቄውን ከሁለት ሰይጣኖች አንዱን ለመምረጥ እንደሚያስገድድ በምሳሌ በማስገደፍ የውጭ ምንዛሪ ለውጥ ከማድረግ ከሚገኘው ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን በመሆኑ፣ የምንዛሪ ለውጥ ማድረጉ ለጊዜው የመንግሥት ምርጫ እንደማይሆን አስታውቀዋል፡፡

እነ ባህሬን፣ ኩዌት፣ ኦማን፣ ኳታር፣ ሳዑዲ ዓረቢያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የባህረ ሰላጤው አውራ አገሮች ከኢትዮጵያ ጋር የንግድና የኢንቨስትመንት ሸሪክ የመሆን ፍላጎት እንዳላቸው ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ከእነዚህ አገሮች ጋር ቀና የኢኮኖሚ ትስስር ለመመሥረት ደፋ ቀና ሲል ቆይቷል፡፡ ከአንዳንዶቹ አገሮች ጋር በፖለቲካዊ ቅራኔ ውስጥ ቢገባም ወደ ባህረ ሰላጤው አገሮች ከሚላከው ሸቀጥ ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ማግኘት ጀምሯል፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት የነበረው የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ከ180 ሚሊዮን ዶላር ጥቂት ፈቅ ያለ ነበር፡፡

እነዚህ አገሮች የምግብ ሸቀጦችን ለማሟላት እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ላይ ዓይናቸውን መጣላቸው ዕሙን ነው፡፡ የምግብ ሸቀጥ ብቻም ሳይሆን የመጠጥ ውኃ አቅርቦት ለማግኘት የሚያስችላቸውን ስምምንት እስከማድረግ መድረሳቸው የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው፡፡ ከእነዚህ አገሮች መካከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወዳጆቻችን ካሏቸው ጋር ባለው የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ባሻገር አገሮቹ ገንዘባቸውን በኢትዮጵያ እንዲያስቀምጡ ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ አገሮቹ ለኢንቨስትመንት የሚመች ከባቢ ሁኔታዎች ፍጠሩ ማለታቸውና የኢስላሚክ ባንክ አግልግሎት ፍቀዱልን የሚለው ጥያቄያቸው የሚያገኘው ምላሽ ቀርፋፋ መሆኑ እየታየ ነው፡፡

መንግሥት ከወጪ ንግድ ባሻገር የገልፍ አገሮችን፣ የውጭ ሐዋላንና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ገቢዎች እያማተረ ይገኛል፡፡ በየዓመቱ በ30 ከመቶ ጭማሪ እያሳየ እንደሚገኝ የተጠቀሰለት የውጭ የሐዋላ ገቢ ትልቅ ሚና እንዳለው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ጥቂት በጥቂቱ ማሻሻያ የሚደረግበት የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ እንደሚኖር ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች