Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የጅምላ ፍረጃው ማብቂያው መቼ ይሆን?

እነሆ መንገድ። ከጎተራ ወደ ስታዲየም ልንጓዝ ነው። አያ ትርምስ የውጥንቅጥ አባት፣ ጎዳናውን ዛሬም አለቅ እንዳለ ነው። ያም ያስኬዳል። ይኼም ያስኬዳል። ተጓዥ እግሩ ሳይዝል ሐሳቡ ተምታቶ መሀል መንገድ ቆሟል። እርግጥ ሰው መሄዱን ይሄዳል። ጀንበር እንቅልፏን ለጥጣ አድራ ማልዳ ስታፋሽክ ያው ኑሮአችን በመባዘን ሜዳ ተሽቀዳደሙ ይለናል። እንዲያው በአጭሩ ሁኔታችን ሁሉ የታካች ውጣ ውረድ ይመስላል። “ተወኝ እስኪ አንተ። ይህቺም በአቅሟ መኪና ተብላ ነው የምትነዘንዘኝ? ይከፈልሃል አትጨቅጭቀኝ፤” ቀጠን ረዘም ያለች ደርባባ ከወያላው ጋር ገጥማለች። “ይቺም መኪና ተብላ ነው ያልሽው? ሂጂና ሱዳን ሰጋር በቅሎ ገዝተሽ ነይ፤” ሸበቶው ወያላችን እንደ ድርያ ወገቡ ላይ ሰፍቶ የሚንሳፈፍ በሲባጎ የታሰረ ቦላሌውን ወደ ላይ እየጎተተ ይመልስላታል። “ድንቄም ታሪክ አዋቂ! ባቡር ሲመጣ ነው ሰጋር በቅሎ የምትጠቁመኝ? ጠቁመህ ሞተሃል። ካልክስ አሸባሪ ጠቁም። ምኑ ነው እናንተ!” እሳት እንደያዘው የኤሌክትሪክ ገመድ ተንጣጣች ነገሩን የምር አድርጋው፡፡ የተተናኳሹ ሳያንስ የተተነኮሰው እየባሰ ፍዳ አየን ዘንድሮ!

“እስኪ አሁን በተከበርኩበት አገር ‘ለማች ለማች’ እያሉ ዓይን ዓይኗን እያዩዋት መሀል አዲስ አበባ መንግሥት ለቼቭሮሌና ‘ለመርሰዲስ’ አሽከርካሪዎች መንገድ ሠርቶ የወለቀ ልቡን ሳይጠግን፣ ከሱዳን በቅሎ አምጪ ይለኛል? ምናለበት እዚህ አንኮበር ቢለኝ? እዚህ ሰላሌ ፍቼ? ስንት ከጋሪው ያቄመ ጎዳና ተዳዳሪ ፈረስ እያለ?” ብላ ነገሩን ስታቀልጠው፣ “ኧረ ረጋ በይ! እንኳን ሊቢያ አላለሽ…” ይላታል አጠገቧ ከሾፌሩ መቀመጫ ጀርባ የተሰየመ ጎልማሳ። በአጥፍቶ ጠፊ ‘ኮሜንት’ የተካነ ‘ፌስቡከር’ ዓይኑን ስማርት ፎኑ ላይ ዓይኑን እያንከራተተ፣ “እውነቴን ነው! በቅሎ ማለቱም አንድ ነገር ነው። ከዘንድሮ የትራንስፖርት አበሳ እንኳን በቅሎ ዔሊም አትናቅም። ከዚያ በተረፈው ‘ሰው ባለው ነው’ እያሉ ሐሜተኛን ዝም ማስባል መቻል አንዱን የሚሊኒየም የልማት ግብ እንደማሳካት የሚቆጠር ነው፤” ይላል። ከኩመካው ጀርባ የማን እጅ አለበት ተብለን እንዳንታጎር የፈራ ተሳፋሪ ይርበተበታል። ቆይ ግን በ‘ሆረር ፊልም’ መሳቅ የጀመርነው ‘ቴረር ፊልም’ በገሃድ ስለምንሠራ ይሆን እንዴ? ነገሩን ነው!

ጉዟችን ሊጀመር ነው። ሾፌራችን የታክሲዋን ሞተር እያስጓራ ልባችንን አንጠልጥሎታል። “እንዴት ነው ነገሩ? ‘ሒሊኮፕተር’ ላይ ነው እንዴ የተሳፈርነው? ወደፊት ለመሄድ ይኼ ሁሉ ነዳጅ ማባከን እስኪ አሁን ሙስና አይደለም ይባላል?”  ሦስተኛ ወንበር ከአጠገቤ የተቀመጠ ይለፈልፋል። “ምን ይታወቃል ዘንድሮ የሚወስድህንም ሆነ የምትሄድበትን እኮ መለየት ይከብዳል፤” ስትል መጨረሻ ወንበር የተቀመጠች በስላቅ ታብራራለች። ‘ቀቀቀቀ’ ይላል ማርሹ አልገባ ብሎ። “ወይኔ! ‘ፈርስት ክላስ’ በተሳፈርኩ ኖሮ፤” ማኅበራዊ ድረ ገጽ ውስጥ ገሀድ ማኅበራዊ ትዕይንቱን ሰልችቶ ከተመሰጠው ወጣት አጠገብ የተሰየመች ወጣት ትቆጫለች። “እዚህ ሕዝባዊ ‘ክላስ’ የጎደለ ነገር አለ?” ፌዘኛው ጎረቤቴ ይጠይቃታል። “አትሰማም እንዴ ሸንኮራ ሲቆረጥ። እዚህ አገር ከፊት ካልተቀመጥክ አልያም ካልተወለድክ መረቁ የተመጠጠለት ደረቁ ነው እኮ የሚታደልህ። እሱንም ቅን ሾፌር ካጋጠመህ፤” ትለዋለች። ወቸ ጉድ?

“ኧረ ሰላማዊ ሠልፍ ጠርተው ያዋከቡን ይበቃል። ደግሞ በተቀመጥንበት ልታሳፍሱን ነው?” ሻሽ ካሰረች ቀዘባ አጠገብ መጨረሻ ወንበር ላይ የተሰየመች ወይዘሮ ትናገራለች። ይኼን ጊዜ ሾፌሩ በሩን ከፍቶ ይወርዳል። ወይዘሮዋ፣ “የፈራሁት ሊደርስ ነው መሰል?” ስትል በራሷ የፈጠረችውን አጉል ፍርኃት አንዳንድ ተሳፋሪዎች ላይ ታጋባለች። የሾፌሩን መውረድ ተከትሎ ወያላውም ወርዶ ወደ ሾፌሩ አመራ። “ምን ይማከሩብናል አይዘውሩትም? ሃሎ አትሄዱም?” ከወያላው ጋር የተነቋቆረችው ደርባባ ትጮሃለች። “እስኪ ቢያልፍብንም ጊዜ እንስጣቸው የመኪናውን ችግር እያጣሩ ይሆናል፤” ሲል ካጠገቤ ሊያረጋጋት ይጥራል። “አደራ ሰው መሆናችንም አብሮ ይጣራ፤” ብሎ ደግሞ ‘የመኪናው ችግር ይጣራ’ የተባለውን ብሶት ማስተንፈሻ የሚያደርገው ጎልማሳው ነው። ‘የባሰው ብቻ ነው የሚሳፈረው?’ እስክንል ድረስ የማንሰማው የለም! ወይ ጊዜ?

    ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ ሁለት ደንዳና ጎልማሶች ተበሳጭተው የሚያበሳጭ ወሬ ያወራሉ። “ከእንግዲህ ምን ቀረን? ከቁርጥ እኩል ቲማቲም መቁረጥ እኮ ነው የቀረን! በቃ እኮ!” ይላል አንደኛው። “ኧረ ተወኝ! አንደኛውን ዓይን አወጣ አሁንስ፤” ይላል የወዲያኛው። ከእነሱ ጀርባ አብሮኝ የተቀመጠ ወጣት “ፓ የፆታ እኩልነት እያየህልኝ ነው? እኛን ስለአስቤዛ እያስጨነቁ እነሱ የምግብ ፍጆታቸውን አሉ የተባሉ ‘ካፍቴሪያዎች’ እና ‘ሬስቶራንቶች’ አደረጉት፤” እያለ ሁሉን አጠቃሎ የዘመኑን ሴቶች ያማልኛል። የጅምላ ፍረጃ ማብቂያው የትና መቼ ይሆን? ጎልማሶቹ ምሬታቸውንና ብሶታቸውን መቆጣጠር ያቃታቸው ይመስላል። “ቆይ ታዲያ መጨረሻችን ምን ሊሆን ነው በዚህ ዓይነት?” ሲል አንደኛው ጎልማሳ፣ “ማየት ነዋ! ዝም ብሎ ጠብቆ ማየት፤” ካለ በኋላ የወዲያኛው፣ “ብትጮህም መቼ መልስ ያጣሉ? ‘የታሸገ ውኃ ገዝቶ የሚጠጣ ሕዝብ 25 ብር ምኑ ነው?’ ሊሉህ ይችላሉ። አይጥ በበላ ዳዋ እኮ ነው መልሳቸው ሁሉ፤” እያለ መንግሥትን ይወርፋል። ‘ሆድ ለባሰው …’ አሉ?

የዚህ ዓይነት የሐሜት አደባባይ ታክሲ ብቻ ነው፡፡ ሦስተኛ ወንበር ላይ ከአንዲት ቀዘባ ልጅ ጋር አብሮ የተቀመጠ ተሳፋሪ፣ “ቲማቲምን በሚመለከት ብቻ ለምን ሰላማዊ ሠልፍ አንወጣም?” ሲል እንደ አሪፍ የሳይንስ ግኝት በሐሳቡ እያታበየ ይጠይቃል። “ነገር ደህና አደርክ?” ሲል እሰማዋለሁ በሹክሹክታ አጠገቤ የተቀመጠው ወጣት። “እ? እንዴት ይመስላችኋል?” እያለ በጥያቄ ላይ ጥያቄውን ሲያከታትል ተሳፋሪዎች በሙሉ “ምን ነካው ይኼ? አሁን ግብፅን ያየ በሠልፍ ይጫወታል?” እያለ ይገላምጠዋል።  ቆየት አለና ደግሞ አንዱ፣  “ሾፌር ቴፑ አይሠራም? ሙዚቃ ክፈትና ገላግለን ከዚህ ሰው፤” ሾፌሩ ፈጠን ብሎ፣ “አብሽር ምን ልጋብዛችሁ ደስ ያላችሁን፤” ብሎ ምርጫውን ለተሳፋሪዎች ቢሰጥ የተመካከሩረ ይመስል ሁሉም በአንድነት ‘ቲማቲም በጤና!’ ብለውት ተሳሳቁ። ምን ያድርግ ስለግሽበት አውርቶ ሳይጨርስ ስላልፋፋው ዴሞክራሲያችን ሲነሳበት?!

ወያላው እያዋከበ ሒሳብ መቀበል ጀምሯል። የሾፌሩን ትግልና የታክሲዋን አሮጌነት ከግምት ውስጥ አስገብታ አካሄዳችን ያልጣማት ወይዘሮ፣ “ኧረ እናንተ ሰዎች ዛሬ ተገልብጠን ጉድ እንዳንሆን?” ትላለች። “ከአቅም በላይ የተጫኑትንና የተጫኑንን ይጭነቃቸው እንጂ ብንገለበጥ ባህር አይበላን። በምላስ የተላሰ የመሰለ አስፓልት ላይ ነው ፈልሰስ የምንለው። በበኩሌ አብዛኞቻችን ከምንተበኛት ፍራሽ ይኼ አስፓልት የተሻለ ሳይመቸን አይቀርም፤” ይላል ጎልማሳው። “በበኩሌአሟሟቴ ነው የሚያስጨንቀኝ። እንዳልሆን ሆኜ ማለፌ ሳያንስ ቢቻል አገር ባይቻል ሰፈር በእንባ እንዳይራጭልኝ በመኪና አደጋ መሞት አልፈልግም፤” ስትል ባለሻሿ፣ “ሞት መቼም ልማዱን አይተው። ግን ከተለመደ ሞት ያልተለመደው በልጦ በረሃና ባህር ለበላው እንደምናዝነው በመኪና አደጋ በየቀኑ የሚያልቀውን ነፍስ ያቃለልነው መስሎ ይታየኛል። ቆይ ግን የሐዘናችን ምንጩ ሞት ነው አሟሟት ነው? እኔ እኮ መለየት ከበደኝ፤” ስትል ቆንጂት ትጠይቃለች። “እሱ ሳይሆን ቁም ነገሩ ቋሚ ቆሞ ሲሄድ ሁሉን የምር አድርጎ በልቶ ለማይጨርሰው ሀብት እህት ወንድሙን አስለቅሶ፣ ሕዝብና መንግሥት አናክሶ ሳያስበው ማለፉ ነው። በረባ ባልረባው ክልትው እያልን (ያውም በዚህ ጊዜ) ሞት በጥጋብ ተሸሽጎ በሚናጠቀን ክፉ ቀን ልብ መግዛት ያቃተን ሚስጥሩ አይገባኝም፤” አለች ወይዘሮዋ። እንዲህ ነው እንጂ!

“ደላላችን በዝቶ ነዋ። ምን እናድርግ? ከመሠረታዊ እስከ የቅንጦት ምኞታችን ያለገንዘብ ምንም ናችሁ የሚሉን ደላሎችን መቋቋም ከበደን። ይኼው ነው! ታዲያ በዚህ መሀል ሰው መሆን ትርጉሙ ቢጠፋብን ይገርማል? ፍትሕ ስንል ያለስም፣ ያለዝና፣ ያለሥልጣን የለም! ካሉን፣ ሚስት ካለጥሪት ዝንብህን እሽ አትልም! ከሆነ ጨዋታው ‘እሺ ለአንድ ራሴ ጠግቤ ልደር’ ስንል እንኳን እህል አፒታይት ቆላፊው ጫት ሳይቀር ዋጋው አሻቅቦ የ‘ኢንቨስተር ዲዘርት’ ሲሆን ካየን ግራ እንደተጋባን ሞት ቢቀድመን ይገርማል? አሟሟታችን ቢከፋ ይደንቃል?” ብላ ደርባቢት አነበነበች። “ወይኔ ዘንድሮ ምርጫ ኖሮ በዕጩነት ቀርቤ ‘ጫት በነፃ አድላለሁ’ ብል ኖሮ ያዋጣኝ ነበር ማለት ነው፤” የሚለኝ ከጎኔ የተቀመጠው ነው። አንዳንዱ ሰው ምን እንደሚያወራም አላስተውል አለ እኮ እናንተ! ይኼ ያልታረመን ሐሳብ ‘ፖስት’ እና ‘ሼር’ የማድረግ አባዜ ገና ብዙ ፈር እንዳያስተን ያስፈራል!

ወደ መዳረሻችን ነን። ግን ጥቂት ይቀረናል። መንገዳችን ሙሽሮች ጭኖ በአበባና ፊኛ ባሸበረቀ ሽንጠ ረዥም ሊሞዚን መኪና ተዘግቷል። ተቀላጥፎ መጠምዘዝ ስላልቻለ መንገዱን ዘጋግቶታል። ተሳፋሪው መኪናውን እያየና ሠርገኞቹን ለማየት እየተንጠራራ ወግ ጀመረ። “የዘንድሮ ሰው ብልጥ ነው ሲባል ይገርመኛል። አሁን በዚህ ኑሮ በሊሞዚን ቅልጥ አድርጎ ደግሶ መጋባት እንዴት ያለው የብልጥነት ምልክት ይሆን?” ይላል አንዱ። “እኛ በራሳችን ኪስ እያየነው ነዋ። ምን ታውቃለህ የዘንድሮን ሰው ማንነትና ምንነት?” ይባላል ከኋላ። “ኧረ እሱስ እውነት ነው፤” አለ መልሶ። “እኔ የምፈራው የእኛ አገር ዕድገት እንደ ህንድና ብራዚል ሆኖ እንዳያርፍነው፤” ትላለች ከወደፊት የተቀመጠች ወጣት። በሀብታምና በደሃው መካከል የሚፈጠረው የሰማይና የምድር ዓይነት ልዩነት ስታስበው እያንገፈገፋት። “የት ይቀራል? ‘የጠሉት ይደርሳል የፈሩት ይደርሳል’ አይደል የሚባለው? በዚያ ላይ ሙስናው፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦቱ፣ የቢሮክራሲው ብዛትና መንዛዛት ኧረ ስንቱ ገና ይከተለን ይሆን?” ይላሉ አዛውንቱ ከጋቢና። ሊሞዚኑ መንገዱን ለቆ ጉዟችን ሊጠናቀቅ ይጣደፋል። “ታዲያ ያን ጊዜ ምን ልንል ነው?” ብሎ ሲጠይቅ ጎልማሳው አዛውንቱ ዞር አሉና “ምን እንድንል ትጠብቃለህ? ‘የጠላነው ወርሷል የፈራነው ደርሷል’ ነዋ!” አሉት። ወያላው “መጨረሻ” ሲለን ነገር ሁሉ በዚህ ከቀጠለ አዛውንቱ እንዳሉት የጠላነው እንዳይወርሰን የፈራነው እንዳይደርስ ስንፈራ ስንቸር ከታክሲያችን ወረድን። ‹‹ሁሌም በጅምላ ሥሪት አስተሳሰብ እየተመራን በጅምላ የምንፈራረጅበት ጊዜ ማብቂያው ይናፍቀኛል…›› እያለ የሚያነበንብ ሰው ድምፅ ሰምቼ ቀና ስል እሱ በፍጥነት ጉዞውን ቀጥሏል፡፡ መልካም ጉዞ!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት