Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየተሃድሶው ስኬት በቁጥቁጥ ውጤቶቹ መለካት የለበትም

የተሃድሶው ስኬት በቁጥቁጥ ውጤቶቹ መለካት የለበትም

ቀን:

በከበደ ካሳ

ኢሕአዴግ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በተለይም ካለፈው ዓመት ጀምሮ እየተነሱ ላሉ የሕዝብ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች መንስዔ የሆኑትን ለይቶ ለመፍታት እንዲቻል ጥልቅ ተሃድሶ በማድረግ ላይ ይገኛል። የተሃድሶ ሒደቱ ከተጀመረ አምስት ወር ሆኖታል። ተሃድሶው ምን ውጤት አስገኘ? የሚለው ጥያቄ ወደ ኋላ የምመለስበት ሆኖ በቅድሚያ ግን በተሃድሶው ሒደት ላይ የሚታዩ የተዛቡ አስተሳሰቦችንና ትችቶችን፣ ከእነዚህም በመነሳት የሚደረሱ የተሳሳቱ ድምዳሜዎችን መተቸት እፈልጋለሁ።

በእኔ እምነት በጥልቅ ተሃድሶው ላይ የሚታዩ ሦስት ዋና ዋና የተዛቡ አስተሳሰቦች አሉ። አንደኛው የተሃድሶውን የስኬት መጠን በተባረረና ፖለቲካዊ ወይም ሕጋዊ ዕርምጃ በተወሰደበት አመራር መጠን መመዘን ሲሆን፣ ሁለተኛው ከዚህ ተሃድሶ የመስመር ለውጥ (ideological shift) ወይም የመስመር ማጥራት (ideological purification) መጠበቅ ነው። ሌላው የተሳሳተ አስተሳሰብ ተሃድሶውን የቀናት ወይም የጥቂት ወራት ሥራ አድርጎ መውሰድ ነው። እነዚህ የተሳሳቱ አስተሳሰቦች የሚንፀባረቁት ደግሞ ከድርጅቱ ውጪ ባሉት ብቻ ሳይሆን፣ በተሃድሶው ሒደት ውስጥ በማለፍ ላይ በሚገኙ የድርጅቱ አባላትም ጭምር ነው።

- Advertisement -

ስኬቱን ዕርምጃ በተወሰደበት አመራር መጠን መመዘን

የአንድ ፕሮጀክት የስኬታማነት መጠን የሚወሰነው መርሐ ግብሩ ከመጀመሩ በፊት ከተቀመጡለት ዓላማዎችና ግቦች አንፃር ነው። ኢሕአዴግ እያካሄደ ያለውን ዳግም በጥልቀት የመታደስ ሒደት ከመጀመሩ በፊት ተሃድሶው በአጭርና በረጅም ጊዜ ያስገኛቸዋል ያላቸውን ውጤቶች አስቀምጧል። የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴና የኢሕአዴግ ምክር ቤት ባለፈው ዓመት መጨረሻ ባካሄዱት ስብሰባ፣ በዚህ ዳግም በጥልቀት የመታደስ ሒደት ድርጅቱን ቀጣዩን የትግል ምዕራፍ ሊመራ ከሚያስችለው የአስተሳሰብ ጥራትና ከፍታ ላይ ማድረስ፣ እንዲሁም በሒደት እየተሸረሸሩ የመጡ የድርጅቱን አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ባህሪ ወደ ቀደመው መመለስ የሚሉ ዓላማዎችን አስቀምጠዋል።

ምክር ቤቱና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ለተሃድሶው ከቀረጿቸው ግቦች መካከል ደረጃውና መጠኑ ምንም ይሁን ምን የድርጅትና የመንግሥት ሥልጣንን ያላግባብ ለግል ኑሮ መሠረት ለማድረግ የሚታየውን ዝንባሌ ለማረምና ለመግታት የሚያስችሉ ዕርምጃዎችን መውሰድና ከራሳቸው ጀምሮ የሚታዩ የጥገኝነት አስተሳሰቦችና የዚህ መገለጫ የሆኑትን ጠባብነትና ትምክህተኝነትን በጥብቅ ታግሎ ማስተካከል ይገኙበታል፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን በማስረፅና ለትውልድ ባህል አድርጎ በማቆየት ረገድ የላቀ ሚና ያላቸውን እንደ የሕዝብ ምክር ቤቶችን፣ ብዙኃን ማኅበራትን፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና የመገናኛ ብዙኃን ዓይነት የዴሞክራሲ ተቋማትን ከመደገፍና ከማብቃት አኳያ ድርጅቱ ያጋጠሙትን ውስንነቶች ምንም ዓይነት መንጠባጠቦች ሳይኖሩ በሙሉዕነት የመፍታት ግቦችንም አስቀምጠዋል።

ይህ አስቀድሞ የተቀመጠ ግብና ዓላማ ከታየ የተሃድሶው ውጤት ባባረረው ወይም ፖለቲካዊና ሕጋዊ ዕርምጃ ባስወሰደበት አመራር መጠን ሊለካ አይችልም፣ አይገባምም። ምክንያቱም ድርጅቱን ከላይ እስከ ታች ላጋጠመው የአመለካከት ዝንፈት ዋናው መፍትሔ ሰዎችን ማባረር ወይም ማሰር ወይም መቅጣት አይሆንም። መፍትሔው በድርጅትና በመንግሥት ሥልጣን አጠቃቀም ዙሪያ የተከሰተውን ጉድለትና የዚህ መገለጫ የሆኑ አስተሳሰቦችን ታግሎ ማስተካከል ነው። ይህ ማለት አመራሩም ሆነ አባሉ የወደቀበትን ቦታ ሳይሆን የተዳለጠበትን ቦታ ለይቶ ችግሩን ከመሠረቱ መንቀል ማለት ነው። አመራሩ ከመውደቁ በፊት ያዳለጠው ደግሞ የድርጅትና የመንግሥት ሥልጣንን የሕዝብን ኑሮ ለማሻሻልና አገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ከማዋል ይልቅ፣ የግል ኑሮ መሠረት አድርጎ መመልከት የጀመረ ጊዜ ነው። ስለዚህ እንደ ሌሎች ጊዜያት በሥራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ተመሥርቶ ‹‹ሠርተሃል››፣ ‹‹አልሠራህም›› የሚል ሰዎችን የማንሳትና የማሸጋሸግ ጉዳይ ሳይሆን፣ መሠረታዊ የሆነ የአስተሳሰብ ትግል የተደረገበትና ድርጅቱ ውስጣዊ የአስተሳሰብ ጥራቱን ያስጠበቀበት ሒደት መሆኑን ማረጋገጥ ነው የሚያስፈልገው፡፡

ይህ መሠረታዊ ሐሳብ እንደተጠበቀ ሆኖ ለዳግም ተሃድሶው ከተቀመጡት ግቦች አንዱ ለቀጣይ የተግባር ጉዞ አስተማሪ ይሆን ዘንድ ውጤት በማያስመዘግቡ፣ ወንጀል በፈጸሙና በከፋ የሥነ ምግባር ችግር ውስጥ በገቡ አመራሮች ላይ ተገቢ የሆነ ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ዕርምጃዎችን በማያዳግም ሁኔታ መውሰድ የሚል ይገኝበታል። የአመለካከት ብልሽታቸው በተጨባጭ ደረቅ ወንጀል ላይ እንዲሳተፉ ላደረጋቸው አመራሮች፣ ከፖለቲካዊና ከአስተዳደራዊ ዕርምጃዎች (ማስጠንቀቂያ፣ ከኃላፊነት ዝቅ ማድረግ፣ ከማዕከላዊ ኮሚቴ ወይም አባልነት ማገድ፣ ወዘተ…) በተጨማሪ ሕጋዊ ተጠያቂነት መከተል አለበት፣ እየተከተለም ነው።

በቅርቡ የፌዴራል ፖሊስ በሰጠው መግለጫ በጋምቤላ ክልል በመንግሥት ውስጥ ያሉ የአሠራር ክፍተቶችን ተጠቅመው በመመሳጠር የሕዝብና የመንግሥት የጋራ ሀብት የሆነውን መሬት በመዝረፍ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ግለሰቦች ተጋልጠዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ድርጅቶችም እንዲሁ ቁጥራቸው ቀላል በማይባል አመራሮች ላይ በተለያየ ደረጃ ዕርምጃ ወስደዋል። ለአብነት ብአዴን የሚመራው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት 748 ያክል አመራሮችን ከኃላፊነት አንስቷል። ድርጅቱ የሙስና ወንጀል በፖለቲካና ግለሰባዊ ግምገማ ብቻ ሊደረስበት አይችልምና ሥልጣንን ያላግባብ በመጠቀም የግል ሀብት ያፈሩ አካላትን ወደ ሕግ ማቅረብ የሚያስችል መስቀለኛ ማጣራት እንዲካሄድ ውሳኔ አስተላልፏል። ይህ ውሳኔ በተጠረጠሩ ባለሥልጣናት ቤተሰቦች ላይ ተጨማሪ ማጣራት እስከማካሄድ የሚደርስ ነው። ስለሆነም የጥልቅ ተሃድሶው መድረክ በዋነኛነት እንቅፋት የሆኑ አመለካከቶችን በመቀየርና ወደቀደመ ሕዝባዊና አብዮታዊ ባህሪ መመለስ ላይ ተመርኩዞ፣ ከዚህ በመለስ ደግሞ አስፈላጊውን ፖለቲካዊ፣ ሕጋዊና አስተዳደራዊ ዕርምጃዎችን በመውሰድ እየተጓዘ እንደሚገኝ ማየት ይቻላል።

ተሃድሶውን የተጠናቀቀ አድርጎ መውሰድ

ኢሕአዴግ ተሃድሶ አደረግሁ ቢልም መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎችን እስካሁን አልፈታም ተብሎ ትችቶች ሲሰነዘሩ ይደመጣል። ባለፈው ዓመት ከተነሱ ጥያቄዎች ውስጥ የድንበርና የወሰን ጉዳዮችን፣ የማንነት ጥያቄን፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን፣ የሥራ አጥነት ችግርን፣ ወዘተ… በምሳሌነት በማንሳት ሒደቱን ፍሬ አልባ ለማስመሰል የሚጥሩ አሉ። አንዳንዶቹ ከዚህ ተነስተው ለውጥ አይመጣም ወደሚል ድምዳሜ መድረስ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎችም በዚሁ ቅኝት እንዲሄዱ የሚገፉ ጽሑፎችን አውጥተዋል። ቀድሞም እንዳደረጉት የሕዝቡን ተገቢና ፍትሐዊ ጥያቄዎች ለፖለቲካ አጀንዳቸው ማድመቂያነት ለመጠቀም የሚቀሰቅሱትን ሳይሆን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ በግንዛቤ ማነስ የተነሳ የተፈጠሩ ብዥታዎችን ማጥራት ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ።

ተሃድሶውን የተጠናቀቀ አድርጎ የመውሰድ የተሳሳተ አመለካከት የሚመነጨው ተሃድሶውን ሒደት (process) ሳይሆን ኩነት (case) አድርጎ ከማሰብ ነው። እንደሚታወቀው ባለፉት አምስት የተሃድሶ ወራት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴንና ምክር ቤቱን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች፣ በየደረጃው ያሉ መካከለኛና ጀማሪ አመራሮችና የሚበዛው የድርጅቱ አባል በተሃድሶው የግምገማ መድረክ ውስጥ አልፈዋል። ነገር ግን ይህ ተሃድሶ በገዢው ፓርቲ ውስጥ የተጀመረ ይሁን እንጂ፣ አገራዊ እንቅስቃሴ ሆኖ እንዲወጣ አስቀድሞ ግብ የተቀመጠለት ነው። ይህ ማለት መሪው ድርጅት ብቻ ሳይሆን በፓርቲው የሚመራው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት፣ ከዚያም መላው ፈጻሚ ሕዝብ በተሃድሶው ውስጥ ያልፋል ማለት ነው። የአሁኑን ተሃድሶ ከመጀመሪያው ተሃድሶ ከሚለዩት ጉዳዮች አንዱም ይኼው ንቅናቄውን በስፋትና በጥልቀት ለማስኬድ የተያዘለት ዓላማ ነው። በሌላ ጸሐፊ አገላለጽ፣ ‹‹አሁን ኢሕአዴግና መንግሥት ብቻ አይደሉም እየታደሱ ያሉት። ሕዝቡና ዜጎችም እየታደሱ ነው። ዴሞክራሲያችን፣ ልማታችን፣ አብሮነታችን፣ መቻቻላችን፣ ዴሞክራሲያዊ አንድነታችንወዘተ የመሳሰሉት በተሃድሶው ሒደት ውስጥ ያልፋሉ፡፡››

በዚህ መሠረት ሰሞኑን በመንግሥት ሠራተኞች የተጀመረው የተሃድሶ መድረክ ወደ አጠቃላይ የሕዝብ ውይይት ይሸጋገራል። ወጣቶችና ሲቪክ ማኅበራትም የዚሁ አካል ናቸው። ኢሕአዴግ በምርጫ ቦርድ ዕውቅና አግኝተው እየተንቀሳቀሱ ካሉ ሁሉም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች (የሥነ ምግባር አዋጁን ከፈረሙትም ካልፈረሙትም) ጋር የምርጫ ሕጉን ጨምሮ በሌሎች የፖለቲካ አጀንዳዎች ላይ የሚያደርገው ውይይትም፣ በዚሁ የድርጅቱ የመታደስ ሒደት ውስጥ የሚታይ ነው። እነዚህ መድረኮች የራሳቸውን ጊዜ የሚጠይቁ ናቸው።

በሌላ በኩል እነዚህ ሁሉ የተሃድሶ መድረኮች ምንም እንኳን አጀንዳቸው በተግባር ያለፍንባቸው አፈጻጸሞች ቢሆኑም አፍኣዊ ውይይት ከመሆን አይድኑም። በተጨባጭም ሕዝቡን ለቅሬታ የዳረጉ ችግሮችን መፍታት የሚቻለው መድረኮቹ ላይ በቀረቡ አስተያየቶችና ውሳኔዎች ሳይሆን፣ እነዚህን አስተያየቶችና ውሳኔዎች ጨብጦ መሬት በማስነካት ነው። በመድረኮቹ ውይይት የተደረገባቸው ጉዳዮች በአዲስ መንፈስና ቁርጠኝነት የሚመሩ አመራሮችንና ፈጻሚ ሕዝብን ይፈልጋሉ። እናም በተግባር የተፈጸሙ ጥያቄዎች የታደሰ ተግባራዊ ምላሽ ይሻሉ ማለት ነው። ለአብነት የወጣቶች ችግር የሚቀረፈው መድረኮቹ ላይ በተቀመጡት አቅጣጫዎች ብቻ ሳይሆን፣ ይህን ይዞ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወጣቶችን የሥራ ዕድል ባለቤት ማድረግ ሲቻል ነው። ተሃድሶው ግቡን የሚመታውም ያኔ ነው። እነዚህን አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ለመፈጸም ደግሞ ገና እየተካሄዱ ባሉት የተሃድሶ የግምገማ መድረኮች ስምምነት ላይ ደርሶ መውጣት የማስፈለጉ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ የአፈጻጸም ጊዜም ይጠይቃል። የተሃድሶውን ስኬታማነት ለመለካት የተጠቀሱት መርሐ ግብሮች የሚወስዱትን ጊዜ ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል።

ያም ሆኖ የጥልቅ ተሃድሶው ፋይዳ እንዲሁ በአጭር ጊዜ ወይም የተነሱ የሕዝብ ቅሬታዎችንና ችግሮችን በመመለስ ላይ የታጠረ ተደርጎ መወሰድ አይገባውም። እንደሚታወቀው ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ የተካሄደው የመጀመሪያው የኢሕአዴግ ተሃድሶ በዛው ዓመት ካስገኛቸው ወቅታዊ (Immediate) ውጤቶች ባሻገር አገራችን አሁን የምትመራበት ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር ነጥሮ የወጣበት፣ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ምርጫ ላይ ግልጽነት የተፈጠረበትና ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የፈለቁበት ነው። በዚህ ተሃድሶ ፍሬዎች በመመራት ላለፉት 15 ዓመታት በርካታ ድሎች ተመዝግበዋል። ኢሕአዴግ አሁን እያደረገ ባለው ጥልቅ ተሃድሶው እየገመገመ ያለውም ይኼንኑ የ15 ዓመታት የተሃድሶ ጉዞ ነው። በተመሳሳይ የአሁኑ ተሃድሶም በተቀመጡለት ግቦችና በጥልቀቱ ካልሆነ በስተቀር በመሠረታዊ እሳቤዎቹና አካሄዶቹ ከቀደመው የተለየ አይደለምና አሁን እየታዩ ያሉ ችግሮችን መፍታት ብቻ ሳይሆን ላልተወሰኑ ዓመታት አገሪቱን ወደሌላ የድል ምዕራፎች የማሸጋገር ዘለቄታዊ ፋይዳ እንዲኖረው ይጠበቃል።

ጥልቅ ተሃድሶው እስካሁን ያሉትን ተቋማት መልሶ ማደራጀትና ማጠናከርን ያካትታል፡፡ በተለይ የሕዝብ ምክር ቤቶችና ሌሎቹ የዴሞክራሲ ተቋማትም ተልዕኳቸውን በብቃት እንዲወጡ ማድረግ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ የአገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን ባለቤት የሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈጻሚውን አካል የመቆጣጠር ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ማብቃት ይጠበቅበታል፡፡ ተሃድሶው አገራችንን በጥቂት ዓመታት ውስጥ መካከለኛ ገቢ (lower middle income) ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍና በረጂም ጊዜ ደግሞ የኢትዮጵያን ህዳሴ ለማረጋገጥ የሚያስችል ሩቅ አዳሪ ግብ የሰነቀ ነው። የድርጅቱን አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ባህሪ ማጎልበትና የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲን ማስፋትም ከዚህ ተሃድሶ የሚጠበቁ ዘለቄታዊ ውጤቶች ናቸው፡፡ ስለሆነም ዳግም በጥልቀት የመታደስ ሒደቱ የስኬት ደረጃ መለካት ያለበት እነዚህን ዘላቂ ፋይዳዎቹን ጭምር ታሳቢ በማድረግ እንጂ፣ እግረ መንገዱን እየፈታቸው በሄዱ የቁጥቁጥ ውጤቶቹ ብቻ አይደለም።

የመስመር ለውጥ መጠበቅ

ሌላው የተሳሳተ የተሃድሶው መመዘኛ ሆኖ እየተወሰደ ያለው ጉዳይ ከዚህ ተሃድሶ የመስመር ወይም የፖለቲካዊ አስተሳሰብ ለውጥ ወይም የመስመር ማጥራትን መጠበቅ ነው። ኢሕአዴግ መልኩን ብቻ ሳይሆን ስሙንና ቅርፁንም ቀይሮ እንዲወጣ የሚጠብቁ ሰዎች አሉ። ልማታዊና ዴሞክራሲያዊው መስመር በኒዮ ሊበራሊዝም ወይም በሌላ ፍልስፍና፣ የአራት ብሔራዊ ድርጅቶች ግንባርነቱ ወደ ጥምረት ወይም ውህደት፣ ኢሕአዴግ ‹‹በመቃብሬ ላይ…›› የሚልላቸው አጀንዳዎች በሰጥቶ መቀበል ድርድር፣ በሕዝብ ነፃ ምርጫ የተገኘ ሥልጣን ወደ ሥልጣን ማጋራት፣ ወዘተ… እንዲቀየር የሚፈልጉ አሉ። በአጠቃላይ ከሁለተኛው ተሃድሶ የቀድሞውን ተሃድሶ ዓይነት ፍሬዎች የመጠበቅና ከዚህም በመነሳት የተሃድሶውን ስኬት የመለካት አዝማሚያዎች በስፋት ይታያሉ።

በመሠረቱ እነዚህ የለውጥ አጀንዳዎች ቀድሞውንም ለዳግም ተሃድሶው ግብ ወይም ዓላማ ተደርገው አልተያዙም። ይህ የሆነው ግን መስመሩና ከእሱ የተቀዱት ፖሊሲና ስትራቴጂዎቹ ዘለዓለማዊ ስለሆኑ አይደሉም። አገራዊና ዓለማዊ ሁኔታዎች መለወጣቸውን ግድ ሲሉ ይለወጣሉ። የልማታዊ መንግሥት ፍልስፍናን ለመከተል ግድ ያሉን እንደ ገበያ ጉድለት (market failure) እና የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካል ኢኮኖሚ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎች ሲቀየሩ የምንከተለው ፍልስፍናም ይቀየራል። ኢሕአዴግ ወደ ውህደት የሚሸጋገርበት ወይም የማኅበራዊ መሠረቱን የለውጥ ሁኔታ ተከትሎ አብዮታዊነቱ ሳይቀር ሊከስም የሚችልበት ዕድልም ዝግ አይደለም። ይህ የለውጥ አጀንዳ ከዚህኛው ተሃድሶ የማይጠበቀው ወደ ዳግም ተሃድሶው የተገባበት ምክንያት ይህ ስላልሆነ ነው።

የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ የሆነው በሥልጣን መባለግ ከመስመሩ የጥራት ችግር የመነጨ ሳይሆን፣ ኢሕአዴግና በእሱ የሚመራው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ራሳቸውን ከኪራይ ሰብሳቢነት አዝማሚያዎች የመጠበቅና ነፃ የማድረግ ግዴታቸውን መወጣት ላይ ባሳዩት ቸልተኝነት የተነሳ፣ ኪራይ ሰብሳቢነት ከልክ በላይ እንዲገዝፍና ሥርዓቱን የሚፈታተን አደጋ እንዲሆን በር በመክፈታቸው ነው፡፡ ስለሆነም መፍትሔው ይኼንኑ በአፈጻጸም ሒደት ያጋጠመ ጉድለት ማረም ይሆናል እንጂ፣ በተግባር ተፈትሸው ውጤታማነታቸው የተረጋገጡትን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ፕሮግራሞች መቀየር አይደለም።

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ ባደረገው ግምገማ እንደገና በጥልቀት የመታደስ የንቅናቄ መድረኮቹ በተቀመጠላቸው አቅጣጫ መሠረት እየቀጠሉ መሆናቸውንና በአጀንዳዎቹ ላይም የጋራ መግባባት እንደተደረሰባቸው አረጋግጧል፡፡ በዚህ ሒደት አመራሩና አባላት የሕዝብን ምሬት ያስከተሉ ችግሮችን በዝርዝር በመገምገም መንስዔያቸውና መፍትሔያቸው ላይ የተሟላ መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡ ግምገማውን መሠረት በማድረግ የሰው ኃይል ምደባ ማስተካከያዎች እንዲደረጉና በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የመንግሥት የአመራር ምደባ በውጤታማነት ላይ ተመሥርቶ እንዲፈጸም ተደርጓል። ተሃድሶውን ይበልጥ የማጥለቅ ሥራዎች በተጠናከረ ሁኔታ የሚፈጸሙበትንም አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ላይ የተሳተፉ አመራሮች ላይ እየወሰደ ያለውን ዕርምጃ መንግሥት አጠናክሮ እንደሚቀጥል፣ የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነትን ችግር ለመታገልና በዚህ ተግባር ላይ ተሳትፈው የተገኙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ሥር ራሱን የቻለ የምርመራ ቢሮ መቋቋሙን በዚሁ ሳምንት አስታውቀዋል፡፡

እነዚህ ዕርምጃዎችና አቅጣጫዎች እንዳሉ ሆነው በድምሩ ሲታይ አሁን ላይ ሆኖ በእርግጠኝነት መናገር ወይም መከራከር የሚቻለው በዳግም ተሃድሶው የአፈጻጸም ሒደት ላይ እንጂ በውጤቱ ላይ ሊሆን አይችልም። አሁን ላይ ሆኖ ስለተሃድሶው ስኬት ወይም ውድቀት ለመደምደም መሞከር ችኮላ ነው የሚሆነው። ሒደቱ በራሱ እዚህም እዚያም እልባት የሰጣቸው ችግሮች ይኖሩ ይሆናል። ተሃድሶው ግን ከዚህም በላይ የገዘፉ ዘላቂ ግቦች የተቀመጡለት ነውና እስካሁን ባስገኛቸው የቁጥቁጥ ውጤቶቹ የሚያኩራራ አይደለም። ገና የተጀመሩትን ውይይቶች አድማስ ማስፋት፣ ይበልጥ ማጥለቅና በአዲስ አስተሳሰብ መተግበር የሚጠይቅ ነውና ለውጥ አላመጣም ተብሎ የሚኮነንም አይደለም።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...