Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

​በአፋር ክልል በአፍዴራ ጨው ማምረቻ አካባቢ የሚገኘውና ‹‹ፍልውኃ›› የሚባለው የቱሪስት መስህብ

ትኩስ ፅሁፎች

ፎቶ በመስፍን ሰለሞን 

**********

ጎህ ሲቀድ ማለዳ

            ነፍስ አጥምዶ ሞጋች

የድምቀት እልልታ – የመደነቅ አጋች

ጉድ መጣ ከሰማይ!

ከልቦና ሌባ፣ ከጠላቂ ፀሐይ፡፡

ከጉብታው ማዶ፣ ከተራራው አናት

ጨረሩን በትኖ – ባ’መዳይ ያፈናት፣

በጥጋጥግ ቅባት – በረቂቅ ሰሌዳ፣

ደ’ሞ እንደ ጠዋት – ልክ እንደማለዳ፡-

በብርሃን ዋግምት

በሊቀ ሊቅ ድግምት

በጀንበር ማቅለጫ፣ በንፋስ ገበቴ

በአድማስ አግጣጫ በልቦና ቤቴ፣

ማነው ሊቀ-ጠበብት? ምትሐት ለቅላቂ

ሽቅብ ወደ ሕዋ – ቁልቁል በጩላቂ

በአፍዝ አደንግዝ፣ አድማስን አላቂ

      መርቀቅህ የበዛ – በጥበባት ፍዳ

እጠብቅሃለሁ – በንጋት ማለዳ

የዛሬዋ ጀንበር – በምጥህ ተወልዳ

  • ካሳሁን ወልደዮሐንስ፣ ማርገጃ (2006)

********

በፖል ዳንሰኞች የታጀበ ቀብር

በታይዋን የቀድሞው ፖለቲከኛና የቻይ አስተዳደር ካውንስል አፈ ጉባዔ ቱንግ ሲያንግ በ76 ዓመታቸው ሲሞቱ ቀብራቸው በአልቃሽ ሳይሆን በፖል ዳንሰኞች (በቆመ ብረት/ጣውላ ላይ እየተሽከረከሩ የሚደንሱ) ነበር የታጀበው፡፡

የቀብር ሥነ ሥርዓቱ የተለያየ ቀለም ባላቸው ጂፕ መኪኖች የታጀበ ሲሆን፣ እያንዳንዱ መኪና አናት ላይም የቆመ ብረት ተገጥሞ ነበር፡፡ 50 ያህል ዳንሰኞችም ኃፍረታቸውንና ጡታቸውን ብቻ በመሸፈንና ከመኪናው አናት በመሆን በብረቱ ላይ እየተሽከረከሩ በመደነስ ቀብሩን አጅበዋል፡፡ ሲኤንኤን እንደሚለው፣ የሟች ልጅ የአባቱ ቀብር በፖል ዳንሰኞች እንዲታጀብ ያደረገው አባቱ ቀብራቸው ያሸበረቀ እንዲሆን ይመኙ ስለነበር ነው፡፡

***********

ኤሚሬትስ ወደ ዱባይ የሚያደርገውን በረራ ያስተጓጎለ እባብ

የኤሚሬትሱ በረራ ቁጥር ኢኬ 0863 ከአማን ወደ ዱባይ ሊያደርግ የነበረውን በረራ በአውሮፕላኑ ዕቃ መጫኛ ስፍራ (ካርጎ) እባብ በመገኘቱ ሰረዘ፡፡

ቢቢሲ እንዳሰፈረው፣ በረራው የተሰረዘው ተሳፋሪዎች አውሮፕላኑ ውስጥ ከመግባታቸው አስቀድሞ፣ ፍተሻ በሚደረግበት ወቅት እባቡ በመገኘቱ ነው፡፡ ኤሚሬትስ የእባቡን ዝርያም ሆነ የጎጂነት አቅሙን ከመናገር ተቆጥቧል፡፡

**********

ዩጋንዳዊው ከገንዘባቸው ጋር ተቀበሩ

እ.ኤ.አ. ከ2006 እስከ 2016 በዩጋንዳ ፐብሊክ ሠርቪስ በከፍተኛ ፐርሶኔልነት ያገለገሉት የ52 ዓመቱ ቻርልስ ኦቦንግ በሥራ ዘመናቸው ሲቆጥቡት የነበረው ገንዘብ አብሯቸው መቀበሩን የዩጋንዳው ዴይሊ ሞኒተር ዘገበ፡፡ ዘገባው እንደሚያመለክተው ሰውየው ገንዘቡ የምድራዊ ሀጢያታቸው ይሠረዝላቸው ዘንድ እንደሚረዳቸው ቻርልስ ኦብንግ ያምናሉ፡፡ እንዴት ቢባል ያጠራቀሙት 200 ሚሊዮን የዩጋንዳ ሽልንግ ፈጣሪን በፍርድ ቀን ይምራቸው ዘንድ ለመደለል ይረዳቸዋል፡፡ ግለሰቡ የሞቱት በፈረንጆች ገና ዋዜማ ሲሆን ባለቤታቸው ይህን ከገንዘባቸው ጋር አብሮ የመቀበር ኑዛዜያቸውን እንዲፈጸም እንድታደርግ እማኞችን መርጠው ነበር፡፡ ሰውየው እንደ ቃላቸው ከገንዘባቸው ጋር ቢቀበሩም በተወሰኑ ቤተሰቦችና የጎሳ መሪዎች ሐሳብ ገንዘቡ በመጨረሻ ከመቃብር እንዲወጣ ሆኗል፡፡ ወንድማቸው እንደገለጸው ደግሞ ከዚህ ቀደም ሌላ ወንድማቸውም ካጠራቀሙት ገንዘብ ጋር ተቀብረዋል፡፡

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች