ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ እንደገና በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴ ውስጥ ካስገቡት ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል አንዱና ዋነኛው፣ የመንግሥት ሥልጣንን የግል ጥቅም ማስከበሪያና የኑሮ መሠረት የማድረግ ዝንባሌ በመንሰራፋት ላይ በመሆኑ ነው፡፡ ይህንንም ራሱ ኢሕአዴግ በግልጽ አስቀምጦታል፡፡ የመንግሥት ሥልጣንን ለበጎ ዓላማ መጠቀም እየቀረ፣ በዝርፊያ ራስን ለመጥቀም ሲውል የድርጅቱንም ሆነ የሚመራውን መንግሥት ህልውና አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መክተቱን ኢሕአዴግ መገምገሙን አስታውቋል፡፡ መንግሥት ራሱን ከሙስና የመጠበቅና ነፃ የማድረግ ግዴታውን መወጣት ላይ ባሳየው ቸልተኝነት፣ በመንግሥት ውስጥም ሆነ ከመንግሥት ውጪ ባሉ ኃይሎች ሙስና ከልክ በላይ የገዘፈና ሥርዓቱን የሚፈታተን አደጋ እየሆነ እንዲሄድ በር ከፍቷል፡፡ መንግሥት ሰፋፊና ግዙፍ ፕሮጀክቶችን የሚመራ በመሆኑም በኮንትራት አስተዳደር፣ በግዥ፣ በግብር አሰባሰብና በመሬት ዕደላና አጠቃቀም ለከፋ ሙስና መጋለጡ በስፋት ታይቷል፡፡ ይህንን የመሰለ ዕይታ ባለበትና አደጋውን መገንዘብ በተቻለበት ሁኔታ ውስጥ የሕጋዊ ዕርምጃዎች መዘግየት የሕዝቡ መነጋገሪያ ነው፡፡ የመንግሥትንም ግልጽና የማያሻማ ምላሽ ይሻል፡፡
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነት ላይ በተሳተፉ አመራሮች ላይ መንግሥታቸው እየወሰደ ያለውን ዕርምጃ አጠንክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ የሙስና ችግር አለባቸው ተብለው ጥቆማ በሚቀርብባቸው አመራሮች ላይ የተጠናከረ ምርመራ እንደሚካሄድ፣ ማስረጃ እስከቀረበ ድረስም መንግሥት ምሕረት እንደሌለው ገልጸዋል፡፡ በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ለምን ዕርምጃ አይወሰድም ሲባሉ፣ በማስረጃ እስካልተረጋገጠ ድረስ ምንም ማድረግ እንደማይቻል፣ ነገር ግን ማስረጃ ከመጣ መንግሥት አይምርም ብለዋል፡፡
ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ግን፣ ‹‹…በአንዳች ተዓምር ለመንግሥታዊ ኃላፊነት መብቃት ከተቻለ ከፍ ላለ ጥቅም መብቃት ይቻላል የሚል አመለካከት እንዲሰፋ በር ከፍቶ፣ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ወደ መንግሥት ሥልጣን ለመውጣት የሚደረገውን ሩጫ እንዲባባስ አደረገ፡፡ እንደምንም ተሳክቶለት የመንግሥት ሥልጣን ላይ ሊቀመጥ የቻለ ሰው በቀላሉ ከሚገኝ ጥቅማ ጥቅም ጀምሮ በአጭር ጊዜ ሀብት ለማግኘት የሚቻልበት አጋጣሚ እንደሚያሰፋ የተገነዘቡ ሁሉ፣ በዚህ ዕድል ለመጠቀም ዓይናቸውን የማያሹበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ መንግሥታዊ ሥልጣንን መቋደስ ለዚህ ዓይነቱ ዕድል እንደሚያበቃ ግልጽ በሆነበት በዚህ ዘመን ዋናው የሥልጣን መንገድ የሚፈጠረው በድርጅታችን እንደሆነ ይታወቃል… በዚህ የተነሳ የመንግሥት ሹመኛ መሆን የፈለጉ እንደምንም አንገታቸውን ወደ ፓርቲ አመራርነት በማስገባት መረባረብ ጀመሩ፡፡ ድርጅታችንም የሥልጣን ብቻ ሳይሆን ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ማረጋገጫ መሣሪያ ወደመሆን አምርቶ የድርጅታችን የአመራር ጥራት ለአደጋ መጋለጥ ጀመረ፡፡ አድርባዮችና የሥልጣን ጥመኞች ወደ ፓርቲው የኃላፊነት ቦታዎች በመግባት በቀላሉ ወደ መንግሥት ሥልጣን የሚሸጋገሩበት ሁኔታ እየሰፋ በመሄዱም ይዘነው የተነሳነው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት የመገንባት ተልዕኮ ለአደጋ መጋለጥ ጀመረ…›› በማለት በገዛ ራሱ ልሳን አዲስ ራዕይ የቅርብ ጊዜ ዕትም ችግሩን በጥልቀት ተንትኖታል፡፡
ይህንን ችግር በጥልቀት አውቆ ያለፉትን 15 ዓመታት ጉዞውን በጥልቅ ተሃድሶ እገመግማለሁ ያለ ድርጅት የሚመራው መንግሥትም አተያዩ ተመሳሳይ ሊሆን ይገባል፡፡ ችግሮቹን አጥርቶ ማወቁን በአንድ በኩል እየተናገረ፣ በሌላ በኩል ትልልቆቹን ባለሥልጣናት በሚመለከት ማስረጃ ስለመሰብሰብ ሲናገር መደናገር ይፈጥራል፡፡ በአነስተኛና በመካከለኛ ደረጃ ባሉ ሹማምንት ላይ ዕርምጃ መውሰዱን በአደባባይ የሚሰማ ሕዝብ፣ የላይኞቹ ጉዳይ ሲድበሰበስበት ከመገረም በላይ ጥያቄ ያነሳል፡፡ በላይኛው ዕርከን ከሥልጣን የተነሱ ባለሥልጣናት አዳዲስ የሥራ መደቦች እየተፈለጉላቸው ከነጥቅማ ጥቅሞቻቸው ሲሾሙ፣ ከሥልጣናቸው ተነስተው ወደራሳቸው ጉዳይ የገቡ በነፃነት ሲንቀሳቀሱና የመሳሰሉት ትዕይንቶች ሲያጋጥሙ ሕዝቡ ምን እየተከናወነ ነው ማለቱ አይቀሬ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ለራሱም ለሥርዓቱም አደጋ የሆነውን ጉዳይ በስፋት ሲተነትን፣ መንግሥት ደግሞ በአግባቡ ችግሮች ያሉባቸውን ሰዎችና ቦታዎች ለይቶ ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ ተገቢ ነበር፡፡ ያ ባለመሆኑ ግን ‹‹በአንድ አፍ ሁለት ምላስ›› እየተባለ ነው፡፡ በፓርቲ አፍ ሌላ፣ በመንግሥት አፍ ሌላ፡፡
በኢሕአዴግ የጥልቅ ተሃድሶ መድረኮች ላይ ከተነሱ መሠረታዊ ችግሮች መካከል በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀር ባለጉዳዮችን በአግባቡ ያለማስተናገድ፣ በቀጠሮ ማንከራተት፣ በመንግሥት ወጪ የውጭ ጉዞዎችን ማብዛት፣ በሥራ ቦታ አለመገኘት፣ የመንግሥት ሥልጣንን ያላግባብ በመገልገል የአገር ሀብት መዝረፍና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ በሕዝቡ ውስጥ ግን ከዚያም በላይ ብዙ ነገሮች ይባላሉ፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከእነ ቤተሰቦቻቸው ትልልቅ የንግድ ድርጅቶች ውስጥ ይሳተፋሉ፣ ራሳቸውን ከግብር እየሰወሩ የአገር ሀብት ይዘርፋሉ፣ ከመንግሥት ትልልቅ ግዢዎች በሚሊዮኖች ይቀበላሉ፣ በርካታ መሬቶች ይዘው ሕንፃዎች ይገነባሉ፣ ይሸጣሉ፣ ይለውጣሉ፣ ወዘተ ከብዙ በጥቂቱ ናቸው፡፡ እነዚህ እውነት ይሁኑ ሐሰት ጥርት ብለው ሊታወቁ ይገባል፡፡ ንፅህናን የማስታወቅ ኃላፊነት በእያንዳንዱ ኃላፊ ትከሻ ላይ የወደቀ በመሆኑ፡፡ ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማስከበሪያ መደረጉ በኢሕአዴግ በግልጽ ከታመነ፣ በመንግሥት በኩል ደግሞ አጥፊዎችን ለሕግ ለማቅረብ ምን ያዳግታል? ወይስ ሕዝቡ ውስጥ እንደሚባለው መፈራራት ወይም እርስ በርስ ይቅር መባባል አንዱ የግምገማ ገጽታ ሆኗል? ይህ በእጅጉ መልስ ይሻል፡፡
በአጠቃላይ ሙስናም ይባል ኪራይ ሰብሳቢነት ወይም ኃላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት ከሥርዓቱ በተጨማሪ የአገርም አደጋ ነው፡፡ ይህንን አደጋ እያስታመሙ ማስቀጠል የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ አገርን በአግባቡ አለመምራት ሕዝብን ቀፎውን እንደነኩበት የንብ መንጋ በቁጣ ማስነሳት ነው ውጤቱ፡፡ ይህም ባለፉት ጊዜያት ከሚገባው በላይ ታይቷል፡፡ ጥልቅ ተሃድሶው ድርጅቱን ወይም መንግሥትን ለመታደግ የሚደረግ እንቅስቃሴ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ግን የአገርን ህልውና በዘላቂነት ታሳቢ ካላደረገ አደጋ አለው፡፡ ይህንን አደጋ አስወግዶ አገሪቱን ወደ ትክክለኛው የዴሞክራሲ ጎዳና በማስገባት፣ ሥልጣን በምርጫ ብቻ የሚያዝበት ሥርዓት ማምጣት ካልተቻለ ሥጋቱ ይቀጥላል፡፡ በመፈራራት ወይም በእከከኝ ልከክህ እሳቤ ለመቀጠል ማሰብም ሆነ፣ የሕዝቡን ጥያቄ ከተገቢው ጊዜ በላይ በማራዘም መልስ መንፈግ ውጤቱ ጥሩ አይሆንም፡፡ በተለይ በቅርቡ በመልካም አስተዳደር ችግሮችና በሙስና ላይ ጥናት አካሂዶ አስገራሚ መረጃዎችን ማቅረብ የቻለውን የኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ማዕከል ኢንስቲትዩት ይዞ፣ ማስረጃ ፍለጋ ሌላ ቦታ መባዘን ለአገር አይጠቅምም፡፡ ለአገርና ለሕዝብ ዘለቄታዊ ሰላምና መረጋጋት ሲባል ሕግ እንዲከበር መደረግ አለበት፡፡ ማንም ከሕግ በላይ መሆን ስለሌለበት፡፡ ስለዚህም መንግሥት አለባብሶ ማረስን መተው አለበት!