አውሮፓ በዚህ ወቅት በበረዶ ውሽንፍር የምትመታበትና የምትቀዘቅዝበት ቢሆንም፣ እንደ ዘንድሮው ገጥሟት አያውቅም፡፡ የበረዶው አቅም ጎልብቶ አብዛኞቹ የአውሮፓ አገሮች በዚህ ወቅት ከሚኖራቸው የቅዝቃዜ መጠን ጨምረዋል፡፡ የቅዝቃዜ መጠኑ ከኔጌቲቭ 30 ዲግሪ በታች ወርዶም ለሰው ልጆች ሞት ምክንያት ሲሆን፣ ለአንዳንዶች ደግሞ መዝናናትን ፈጥሯል፡፡
‘ያደለው ሙቅ ያኝካል’ እንዲሉ፣ አንዳንዶች በበረዶው ግግር የበረዶ ላይ ጨዋታዎች ለመጫወት ከተለያዩ አገሮች ወደ ሥፍራው ሲያቀኑ፣ በረሃው ካየለበት መካከለኛው ምሥራቅ በጦርነት ምክንያት መሸሸጊያ ፍለጋ የተሰደዱ ሶሪያውያን፣ እንዲሁም አፍሪካውያን የቅዝቃዜው ሰለባ ሆነዋል፡፡
ከአገር አገር የስደተኞች መጠለያ ካምፖች አደረጃጀት የተለያየ ቢሆንም፣ በአብዛኛው ድንኳን በሆኑባቸው ሥፍራዎች ስደተኞች በኢትዮጵያ ብሂል ‹‹ቁር መታን ወይም አፈና ይዟል›› እንደሚባለው በበረዶ ተመተዋል፡፡ በዚህም ሞት ተመዝግቧል፡፡
በአውሮፓ መንገዶች በበረዶ ግግር ሲዘጋጉ የቆሙ መኪኖችንም ለማየት ያዳግታል፡፡ ቅጠሎች፣ ተራሮች፣ ቤቶች፣ የተሰጡ ልብሶች ሳይቀሩ በበረዶ ተሸፍነው በየሚዲያው ታይተዋል፡፡ የበረዶ ግግሩ ለተሽከርካሪዎች መገልበጥ፣ ለአንዳንዶች መውደቅና መሰበር ምክንያት ሆኗል፡፡ የአውሮፕላኖች በረራ ሲስተጓጎል፣ ከ20 በላይ ሰዎችም ሞተዋል፡፡
በስደተኛ መጠለያ ያሉ ስደተኞች ችግራቸውን ያከፋው፣ ከቅዝቃዜው ሊታደጋቸው በሚችል ሥፍራ ባለመስፈራቸው ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ብርዱን የሚከላከሉበት ልብስ፣ ጓንትም ሆነ ጫማ የላቸውም፡፡ ከሚኖሩበት ድንኳን አጠገብ ለጭንቅላታቸው መሸፈኛ ኮፍያ ሆነ ለእጃቸው ጓንት ሳያደርጉ በበረዶ ውሽንፍር እየተመቱ ከወዲህ ወዲያ ሲሉም ተስተውለዋል፡፡ በተለይ ደግሞ በአውሮፓ የተለያዩ አገሮች ድንበሮች የታገቱ ስደተኞች መከራው በርትቶባቸዋል፡፡
ከሳምንት በላይ በዘለቀውና ወደፊትም ይቀጥላል በተባለው ከባድ ቅዝቃዜና በረዶ፣ በፖላንድ በአንድ ቀን ብቻ አሥር ሰዎች ሞተዋል፡፡ ሦስት ስደተኞች በቱርክና ቡልጋሪያ ድንበር ሞተው ሲገኙ፣ ሁለቱ ከኢራቅ አንዱ ከሶማሊያ የተሰደዱ መሆናቸው ታውቋል፡፡ በጣሊያን፣ በቼክ ሪፐብሊክ፣ በሩሲያና በዩክሬንም ሞት ተመዝግቧል፡፡
በረዶው ባየለባቸው የአውሮፓ አገሮች የአውሮፕላኖች በረራ ሲታገድ፣ ቱርክ በሰሜን ምዕራብ የሚገኘው ባህረ ሰላጤዋ በበረዶ ማዕበል በመመታቱ መርከቦች እንዳይንቀሳቀሱ ስትዘጋ፣ በአውሮፓ ኅብረት በርዝመቱ ሁለተኛ የሆነውና ኦስትሪያን፣ ስሎቫኪያን፣ ሃንጋሪን፣ ክሮሺያን፣ ሰርቢያን፣ ሮማኒያን፣ ቡልጋሪያን፣ ሞልዶቪያንና ዩክሬንን አቋርጦ ጥቁር ባህር በሚቀላቀለው ደአቢ ባህር ላይ የሚደረገውን የባህር ትራንስፖርት ሰርቢያ ሙሉ ለሙሉ አግዳለች፡፡
አገሮች የትራንስፖርት እንቅስቃሴን ሲገድቡ የድንበር የለሽ ሐኪሞች ድርጅት ደግሞ፣ በቅዝቃዜው ምክንያት በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአሳሳቢ ደረጃ ውስጥ ይገኛሉ ብሏል፡፡ በአውሮፓ በአደገኛና ሊገለጽ በማይችል ችግር ውስጥ የሚገኙት በተለይ ስደተኞችና በአግባቡ ያልሰፈሩ ሰዎች የበረዶው ሰለባ ሆነዋል ሲልም አክሏል፡፡
በቤልግሬድ ብቻ 2,000 ስደተኞች ያላግባብ የሰፈሩ ሲሆን፣ በሥፍራው የቅዝቃዜው መጠን ኔጌቲቭ 20 ዲግሪ ወይም ኔጌቲቭ አራት ፋራናይት ሆኗል፡፡ በዚህ ሥፍራ ከሚገኙት ስደተኞች አብዛኞቹ ከአፍጋኒስታን፣ ከፓኪስታን፣ ከኢራቅና ከሶሪያ የተሰደዱ ናቸው፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአፍጋኒስታንና የፓኪስታን ስደተኞች በጉምሩክ መጋዘን ውስጥ ሲጠለሉ፣ የዕርዳታ ድርጅቶችም ማሞቂያ፣ ብርድ ልብስ፣ አልባሳትና ምግብ በመጠኑ እያቀረቡ ነው፡፡
በጣሊያን ስድስት ቤት አልባ ሰዎች ሲሞቱ፣ በአገሪቱ ብዙ ጎዳናዎች በበረዶ ግግር በመሸፈናቸው፣ የአየርም ሆነ ምድር ትራንስፖርት ተስተጓጉሏል፡፡ በባህር ላይ መንገደኛችን የሚያሻግሩ (ፌሪ) አገልግሎትም ተቋርጧል፡፡
በሞቃታማነታቸው የሚታወቁት ብዙዎቹ የግሪክ ደሴቶች በበረዶ የተሸፈኑ ሲሆን፣ በእነዚህም ከ62 ሺሕ በላይ ስደተኞች ወደሌላ አገር ለመሸጋገር እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡
የቱርክ አየር መንገድ 650 በረራዎችን ሲሰርዝ፣ በዴንማርክ ከበረዶው ጋር በተያያዘ አደጋዎች መብዛታቸውን ተከትሎ ለዜጎች ቅድመ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፡፡ በሰሜንና በምዕራብ ጀርመን የበረዶ ግግሩ ለብዙ አደጋዎችና ጉዳቶች ሲዳርግ፣ በሃምቡርግ ብቻ ከአየር ፀባዩ ጋር በተያያዘ በሳምንት ውስጥ 415 የአደጋ ጥሪዎች ተደርገዋል፡፡
ከግምት በላይ በሆነው የአየር ፀባይና ቅዝቃዜ ባለፈው ሳምንት በአብዛኞቹ የአውሮፓ አገሮች በሚገኙ አንዳንድ መንደሮች ኤሌክትሪክ ሲጠፋ፣ ቀድሞ ወንዝና ሐይቅ የነበሩ ሥፍራዎች ወደ በረዶ ግግርነት ተለውጠዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ ቃል አቀባይ፣ ‹‹ስደተኞችን ለመርዳት እየሠራን ነው፤›› ቢሉም፣ ብዙዎቹ ስደተኞች በተለይም በባልካን የፖለቲካ ጥገኝነት መጠየቂያ ማዕከል የሚገኙት ለከባድ ችግር ተጋልጠዋል፡፡ ከዚህ ማዕከል ወደ ምዕራብ አውሮፓ ለመሸጋገር የሚመጡ ስደተኞች በቅዝቃዜው ምክንያት እየተጎዱ ሲሆን፣ የጀርመን ፖሊስም በመኪና ተጭነው ሲጓዙ የነበሩ ስደተኞች ሹፌራቸው ጥሏቸው በመጥፋቱ፣ በቅዝቃዜው ተጎድተውና ከመጠን በላይ ቀዝቅዘው ማግኘቱን አስታውቋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አምስት ሕፃናት ነበሩ፡፡
በሩሲያ በ120 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ቅዝቃዜ (ኔጌቲቭ 40 ዲግሪ) ታኅሳስ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. መመዝገቡ ትምህርት ቤቶች ለጊዜው እንዲዘጉ ምክንያት ሆኗል፡፡
በአውሮፓ የተከሰተው ከባድ ቅዝቃዜ በተለይ በየመጠለያ ያሉ ስደተኞችን ጎድቷል፡፡ በመቶ ሺሕዎች ለሚቆጠሩትና እነሱን ለማስተዳደር አውሮፓውያን በተፈተኑበት ጊዜ የተደመረው በረዶ፣ የስደተኞችን ሕይወት ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡
በግሪክ በሊዝቦስ ደሴት የሚገኘው የሞሪያ ስደተኞች ካምፕ በበረዶ ግግር በመሸፈኑ በውስጡ ያሉ አራት ሺሕ ስደተኞች ለጉዳት ተዳርገዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ዕርዳታ ድርጅትም በድንኳን የሚኖሩትን ጨምሮ 120 የሚሆኑ ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ወደ ሆቴል አዘዋውሯል፡፡ ሆኖም አሁንም በድንኳን የሚኖሩ ስደተኞች አሉ፡፡
ስደተኞች ቅዝቃዜውን መቋቋም አቅቷቸው ሲሰቃዩና ሲሞቱ፣ የበረዶ ግግሩ ፈንጠዝያ የፈጠረላቸው ደግሞ የተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮችን ሲያደርጉ ተስተውለዋል፡፡ በሞስኮ ቅዝቃዜው ኔጌቲቭ 27 በደረሰበት ጥር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. 500 የሚደርሱ የብስክሌት ጋላቢዎች በበረዶ ላይ ውድድር አድርገዋል፡፡
የበረዶ ላይ ብስክሌት ውድድሩ እንዳይደረግ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም አጠናቀዋል፡፡ እንቢ በማለት የተሳተፉት ተወዳዳሪዎች አንድም ጉዳት ሳይደርስባቸው ያጠናቀቁ ሲሆን፣ ብርዱን ለመከላከልም በሩሲያ የገና አባት የሚለብሰውን ለብሰው ውድድሩን ማካሄዳቸውም ተዘግቧል፡፡
የምዕራባውያኑን የዘመን መለወጫን አስመልክቶ በየባህሩ በመግባት የመዋኘት (የመጠመቅ) ልምድ ባላቸው አገሮችም፣ ዜጎቻቸው በየባህሩ በመግባት የወቅቱ አየር ያመጣውን በረዶ ሲደሰቱበት ተስተውለዋል፡፡ በካናዳ የውስጥ ሱሪ ብቻ ያደረጉ ወንዶች የበረዶ ላይ ዋና ሲያደርጉ፣ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ዜጎችም የበረዶ ግግር በሳራ ባህር ውስጥ ራቁታቸውን በመግባት በቅዝቃዜው ሲዝናኑ ታይተዋል፡፡