‹‹እሮጣለሁ›› የተሰኘው የኢዮብ መኰንን አልበም ገበያ ላይ ከዋለ አንድ ሳምንት ሆኖታል፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ድምፃዊው ሁለተኛ አልበም ሲሆን፣ 14 ዘፈኖች አሉት፡፡ ድምፃዊው በሕይወት ሳለ ጀምሮት የነበረውን አልበም ሳያጠናቅቅ ቢያልፍም በሙያ አጋሮቹና ጓደኞቹ ትብብር ለሕዝብ ጆሮ በቅቷል፡፡
በ1968 ዓ.ም. ጅግጅጋ የተወለደው ኢዮብ፣ ዛየን ባንድ በነበረበት ወቅት በተለይም የአሊ ቢራንና የቦብ ማርሌን ዘፈኖች በማቀንቀን ይታወቃል፡፡ የመጀመሪያ አልበሙ ‹‹እንደ ቃል›› በ2000 ዓ.ም. ከተለቀቀ ጀምሮ አሁንም በተወዳጅነቱ እንደዘለቀ ነው፡፡ በአገሪቱ የሬጌ ሙዚቃ ስልት ቦታ ከሚሠጣቸው ድምፃውያን አንዱ ኢዮብ፣ ባደረበት ሕመም በ2005 ዓ.ም. በ38 ዓመቱ ነበር ያረፈው፡፡
በሕይወት ሳለ ሁለተኛ አልበሙን መሥራት እንደጀመረ ስለተገለጸ፣ ብዙዎች የአልበሙን መላቀቅ በጉጉት ይጠብቁ ነበር፡፡ ካለፈ በኋላም ሙዚቃዎቹ እንደሚለቀቁ ከተገለጸ ቆየት ብሏል፡፡ ታኅሣሥ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ገበያ ላይ የዋለው አልበሙ በቅንብር ዳግማዊ አሊ፣ ሚካኤል ኃይሉና ካሙዙ ካሳ በግጥምና ዜማ ምዕራፍ አሰፋ፣ ኃይሉ አመርጋ፣ ዓለማየሁ ደመቀ፣ ሙሉቀን ዳዊት፣ ኤርሚያስ ታደሰና ሌሎችም ባለሙያዎች ተሳትፈውበታል፡፡ ማስተሪንጉ በአበጋዝ ክብረወርቅ ሺኦታ ተሠርቷል፡፡ አልበሙ ፕሮዲውስ የተደረገው በይሳቃል ኢንተርቴመንት ሲሆን፣ በቮካል ሪከርድስ ይከፋፈላል፡፡
ድምፃውያን ካለፉ በኋላ በሕይወት ሳሉ የጀመሯቸውን ሥራዎች አሰባስቦ ገበያ ላይ ማዋል አንድም ሕዝቡ ከድምፃውያኑ ጋር ዳግም እንዲገናኝ ድልድይ እንደመፍጠር ነው፡፡ ሥራዎቻቸው ህያው ሆነው ዘመን እንዲሻገሩና አድማጭም እንዲያጣጥማቸው ዕድል ይፈጥራል፡፡ በሕይወታቸው መጨረሻ የጀመሩትን ሥራ በማገባደድ ሕልማቸውን እንደማሳካትም ሊታይ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል በአልበማቸው ሽያጭ ቤተሰቦቻቸው እንዲጠቀሙም ያስችላል፡፡ በዕርግጥ ድምፃውያኑ ኖረው የሥራቸውን ውጤት መመልከታቸው ቢመረጥም፣ ቀናቸው ደርሶ ሲያልፉ ውጥናቸውን ከግብ የሚያደርስላቸው መኖሩ መልካም ነው፡፡
የ‹‹እሮጣለሁ›› አልበም ፕሮዲውሰር የይሳቃል ኢንተርቴመንት ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢዮብ ዓለማየሁ እንደሚናገረው፣ ኢዮብ ከማረፉ ከሁለት ዓመት በፊት የአልበሙን ዝግጅት ጀምሮ ነበር፡፡ ካረፈ በኋላ ሙዚቃዎቹን አሰባስቦ የማሳተም ኃላፊነቱ በእሱና በኢዮብ ባለቤት እንዳረፈ ይገልጻል፡፡ ‹‹የተለያዩ አቀናባሪዎች ጋር የነበሩ ፋይሎቹን ማሰባሰብ ጊዜ ወስዷል፤›› ይላል፡፡ የሙዚቃው ባለቤት በሕይወት ሳይኖር ሲቀር ሒደቱ እንደሚከብድ ያምናል፡፡ አልበሙን ለማሳተም እንቅስቃሴ የጀመረው ከኢዮብ ጋር ጓደኛሞች ስለነበሩና ኃላፊነት ስለተሠማው እንደሆነም ያክላል፡፡
ድምፃውያን ካለፉ በኋላ ሙዚቃዎቻቸውን አሰባስቦ የማሳተም ኃላፊነትን የሚወስደው አካል ጉዳይ አጠያያቂ ነው፡፡ በኢዮብ እምነት የሙዚቃ ኢንዱስትሪው ሲያድግ ይሄና ሌሎችም የዘርፉ ችግሮች ይቀረፋሉ፡፡ ድምፃውያን ቢያልፉም ሥራዎቻቸው ለሕዝቡ እንዲደርሱ የማድረግ ጉዳይ ኢንዱስትሪው ሲያድግ ቀላል እንደሚሆንም ይገልጻል፡፡ ‹‹ባለሙያዎች ሲያልፉ ሙዚቃቸውን ለሕዝብ ማድረስ ከዘርፉ ችግሮች አንዱ ነው፡፡ ፕሮፌሽናል ስቱዲዮዎች ሲበራከቱና ኢንዱስትሪው ሲያድግ ይስተካከላል፤›› ይላል፡፡ አሁን ባለው አሠራር የኢዮብ አልበም ተጠናቆ እንዲለቀቅ ማድረግ ፈታኝ እንደነበር ገልጾ፣ ‹‹ሥራውን የጀመርኩት ኃላፊነት ስላለብኝ ለራሴ የገባሁት ቃል ስለነበረና እንደ ጓደኝነቴም እሱን ለመዘከር ነው፤›› ይላል፡፡
የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዳዊት ይፍሩ እንደሚናገሩት ዘፋኞች ካለፉ በኋላ አልበማቸውን ለአድማጭ ማድረስ፣ ድምፃውያንን በሥራዎቻቸው ለማስታወስና ቤተሰቦቻቸው በገቢው ተጠቃሚ እንዲሆኑም ያስችላል፡፡ ‹‹ከዚህ በፊትም ድምፃውያን ካለፉ በኋላ በጥበቡ ዘርፍ ህያው መሆናቸውን ለማሳየት ተመሳሳይ ጥረቶች ተደርገዋል፤›› ይላሉ፡፡ እንደ ምሳሌ ከሚጠቅሱት አንዱ ጥላሁን ገሠሠ ነው፡፡ አልበሙ ሳይወጣ ሕይወቱ ቢያልፍም፣ አንዱን ዘፈን ቴዎድሮስ ታደሰ እንዲዘፍን ተደርጎ ተለቋል፡፡ የምሥራቅ እዝ የፖሊስ ኦርኬስትራ አባላት ወደ ኤርትራ ሲሄዱ በፈንጂ ሕይወታቸው ሲያልፍ ከድምፃውያኑ የአንዷን አልበም ለማሳተም የተደረገውን ጥረትና የሚካያ በኃይሉን ሥራዎች ለማሳተም መሞከሩንም ይጠቅሳሉ፡፡
ሙዚቀኞች ካለፉ በኋላ ሥራዎቻቸውን በማሳተም ቤተሰቦቻቸውን ከአልበሙ ሽያጭ ተጠቃሚ የማድረግ ሐሳብ ሁሌ ሲለካ እንደማይችል ሙዚቀኛው ይገልጻሉ፡፡ ‹‹የሙዚቃው ኢንዱስትሪ ደከም ባለበት በአሁኑ ጊዜ ከአልበም ሽያጩ ቤተሰብ ይጠቀማል ማለት ዘበት ነው፤›› ይላሉ፡፡ ሆኖም ድምፃውያን ካለፉ በኋላ ሥራዎቻቸው ሕዝብ ጆሮ እንዲደርሱ ማድረግ መበረታታት እንዳለበት ያምናሉ፡፡ ለአድማጮች ድምፃውያኑ በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ ምን ሊሠሩ ይችሉ እንደነበር አመላካች ነው ሲሉም ይናገራሉ፡፡
‹‹ሥራዎቹን ለሕዝብ ሲያቀርብ የኖረ ባለሙያ ሙዚቃዎች ባክነው እንዳይቀሩ አልበማቸው መታተማቸው መልካም ነው፡፡ ጥላሁን ከ400 በላይ ሥራዎች አውጥቷል፡፡ አሁንም ያልወጡ ሥራዎቹ ለሕዝብ ቢቀርቡ ጥሩ ነው፤›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ የሙዚቀኞች ሥራ በማለፋቸው ምክንያት ተዳፍኖ እንዳይቀር ኃላፊነቱን የሚወስድ አካል አስፈላጊ መሆኑንም ያክላሉ፡፡
የድምፃውያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ፀጋዬ እሸቱ በበኩሉ፣ ድምፃውያን ካለፉ በኋላ ሥራዎቻቸው ታትመው ጥሩ ገቢ ከተገኘ ቤተሰቡ ተጠቃሚ ቢሆንም፣ ትዝታ ቀስቃሽ እንደሆነም ያምናል፡፡ ዘፋኞቹ ከሞቱ በኋላ አልበሞች ሲወጡ የድምፃውያን ቤተሰቦችንንና ወዳጆችን ሐዘን የሚቀሰቅሱበት አጋጣሚ ሰፊ እንደሆነ ይገልጻል፡፡
ፀጋዬ ድምፃውያን ካለፉ በኋላ ሥራዎቻቸውን ለሕዝብ በማቅረብ ረገድ የሚጠቅሰው ጥላሁን ገሠሠን ነው፡፡ አልበሙን ለሕትመት በማብቃት ረገድ የጥላሁንን ባለቤት ጥረት አያይዞም ያነሳል፡፡ ስለ አልበሙ ሲገልጽ ‹‹አልበሙን ሳዳምጠው ሐዘንን በመጠኑ ይቀሰቅሳል፤›› ይላል፡፡ ድምፃዊው ጉዳዩን የሚመለከትባቸው ሁለት ጽንፎች ከአልበም ሽያጭ ቤተሰብ ሊያገኘው የሚችለው ገቢና በአልበሙ ምክንያት የሚቀሰቀሰው ትዝታ ናቸው፡፡
የኢዮብን አልበም በተመለከተ በግጥምና ዜማ ከተሳተፉት ባለሙያዎች አንዱ ኤርሚያስ ታደሰ እንደሚናገረው፣ የአልበሙ 80 በመቶው ኢዮብ በሕይወት በነበረበት ወቅት ቢጠናቀቅም ክፍተቶች ነበሩ፡፡ እነዚህ ክፍተቶችም ተሞልተውና መስተካከል ያለባቸው ተስተካክለው አልበሙ ከፍጻሜ በቅቷል፡፡ ስለ አልበሙ ኢዮብ ዓለማየሁ ሲገልጽ፣ ‹‹ሙዚቃዎቹ ኢዮብን የሚገልጹ ስለፍቅርና በጎነት የሚሰብኩ ናቸው፤›› በማለት ነው፡፡ ‹‹እሮጣለሁ›› የሚለው የአልበሙ መጠሪያ ድምፃዊው በሕይወት ሳለ የመረጠው ነው፡፡
አልበሙን ፕሮዲውስ ያደረገው ይሳቃል ኢንተርቴመንት ከአልበሙ የሚያገኘው ገቢ እንደሌለ ሥራ አስኪያጁ ይገልጻል፡፡ የአልበሙ ገቢም ለቤተሰቦቹ ይሆናል፡፡ አስተያየታቸውን የሰጡን ባለሙያዎች ከሚስማሙበት ሐሳብ አንዱ ድምፃውያን ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ሥራዎቻቸው ገበያ ላይ ሲውሉ ሕዝቡ ለአልበሙ ትልቅ ቦታ መስጠቱ ነው፡፡
ኢዮብ እንደሚለው፣ የኢዮብ መኰንን አልበም በጉጉት ይጠበቅ ስለነበረ ከሕዝቡ ጥሩ ምላሽ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አልበሙ አድማጭን ዳግም ከኢዮብ ጋር የሚያስተሳሰር እንደሚሆንም ይገልጻል፡፡ በአልበሙ ከተካተቱት ሙዚቃዎች አስራ ሁለቱ ኢዮብ የዘፈናቸው ሲሆኑ፣ የተቀሩት ሁለቱ ተመሳሳይ ድምፅ ባላቸው ዘፋኞች ክፍተታቸው ተሞልቷል፡፡
በአልበሙ ዝግጅት ወቅት ከድምፃዊው የሙያ አጋሮች ጎን የኢዮብ ባለቤት ወይዘሮ ቲና ተዓርም ነበረች፡፡ አልበሙ ይወጣል ተብሎ ከተጠበቀበት ጊዜ የዘገየው መሞላት የነበረባቸው ክፍተቶች በመኖራቸው መሆኑን ትገልጻለች፡፡ ምንም እንኳን ኢዮብ በሕይወት ኖሮ አልበሙ ቢወጣ የበለጠ ትደሰት እንደነበር ብትናገርም፣ ‹‹አልበሙ በመጠናቀቁ የተሰማኝን ደስታ ለመግለጽ ይከብደኛል፤›› ትላለች፡፡ በተጨማሪም ኢዮብ በታመመበት ወቅትና ከኅልፈቱ በኋላም ከጎኑ የነበሩ የሙያ አጋሮቹንና ሕዝቡንም ታመሰግናለች፡፡ አልበሙ የኢዮብን ምልከታ እንደሚያሳይ ገልጻ፣ ሳይለቀቅ በመቆየቱ ጥያቄ ያቀረበው ሕዝብ እንደሚደሰትበት ተስፋ ታደርጋለች፡፡
‹‹እሮጣለሁ›› አልበም እንደወጣ ገዝታ እንዳዳመጠችው የምትናገረው ወጣት፣ ‹‹ሁለተኛ አልበሙ ሊወጣ እንደሆነ ከሰማሁ ቆይቻለሁ፡፡ ‹‹ተው ያልሽኝን›› የሚለው ነጠላ ዜማው በሬዲዮ ተለቆ አልበሙ ሊወጣ ነው ሲባል በጣም ደስ ብሎኝ ነበር፡፡ አልበሙ እንደወጣም ከአዟሪ ገዝቻለሁ፤›› ትላለች፡፡ የኢዮብ አድናቂ የሆነችው ወጣት፣ የኢዮብ ፎቶ ያለበት የአልበሙ ፖስተር በየሙዚቃ ቤቱ ተለጥፎ ስታይ ልዩ ስሜት እንደተሰማት ትናገራለች፡፡
‹‹እንደ ኢዮብ ሁሉ የሌሎችም ያለፉ ድምፃውያን አልበሞች ቢወጡ ለድምፃውያኑ ክብር መስጠት ነው፤›› ትላለች፡፡ በዚህ ረገድ ድምፃውያኑ ማናጀር ካላቸው በማናጀራቸው በኩል ካልሆነም ቤተሰቦቻቸው ኃላፊነቱን ቢወስዱ መልካም ነው ትላለች፡፡ በእርግጥ ድምፃውያኑ በማለፋቸው ብቻ ሥራቸው ገበያ መዋል አለበት ብላ አታምንም፡፡ ስለዚህም የሙዚቃው አሠራርና ይዘት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ትላለች፡፡ ጥራቱ ከተጠበቀ በድምፃዊው ማለፍ ያዘኑ አድናቂዎቹ በሥራው እንደሚደሰቱ ትናገራለች፡፡ ‹‹በሕይወት ያሉ ድምፃውያን ከቀድሞ ሥራቸው መሀከል ተወዳጆቹን መርጠው አዲስ አልበም ሲያወጡ ያለፈውን ትዝታ ስለሚቀሰቅስብኝ በደስታ አልበሙን ከሚገዙ ሰዎች መሀከል ነኝ፡፡ ከነዚህ አልበሞች እኩል ያለፉ ድምፃውያንን የሚያስታውሱኝ አልበሞች ቢወጡም ከመግዛት ወደ ኋላ አልልም፤›› ትላለች፡፡