Thursday, February 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአዲስ አበባ ተፈናቃይ አርሶ አደሮች አሁንም አቤቱታ እያቀረቡ ነው

የአዲስ አበባ ተፈናቃይ አርሶ አደሮች አሁንም አቤቱታ እያቀረቡ ነው

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዘግይቶም ቢሆን ቀደም ሲል ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችን በድጋሚ ለማቋቋም ቢወስንም፣ የአርሶ አደሮች አቤቱታ ግን እየበረታ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ አርሶ አደሮችን በድጋሚ ለማቋቋም በቅርቡ ያቋቋመው ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ በተያዘው በጀት ዓመት 20 ሺሕ አርሶ አደሮችን፣ በአምስት ዓመታት ደግሞ 134 ሺሕ አርሶ አደሮችን ለማቋቋም እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡

በተለይ በዚህ ዓመት 20 ሺሕ አርሶ አደሮችን ለማቋቋም 881 ሚሊዮን ብር በጀት መያዙንም ገልጿል፡፡ ነገር ግን በርካታ ተፈናቃይ አርሶ አደሮችና የአርሶ አደር ልጆች አቤቱታቸውን ለአስተዳደሩ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከቅሬታ አቅራቢ አርሶ አደሮች መካከል የዕድሜ ባለፀጋው አርሶ አደር ሹሚ አበዬና ወጣቶቹ የአርሶ አደር ልጆች እንዳለ ዓለሙና ውርጋ እሸቱ ይገኙበታል፡፡

አቶ ሹሚ የ90 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ናቸው፡፡ ለከተማው አስተዳደር የተለያዩ ቢሮዎች ባቀረቡት አቤቱታ ከ1950 ዓ.ም. ጀምሮ በይዞታነት ይዘው የቆዩት 70 ቀርጥ (17 ተኩል ሔክታር) መሬት፣ እንዲሁም መኖርያ ቤታቸው ያረፈበት 3,000 ካሬ ሜትር ቦታ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ተወስዷል፡፡

የአቶ ሹሚ ቦታ የሚገኘው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ሐና ማርያም አካባቢ ሲሆን፣ ይህ ቦታ ለቻይናው ግዙፍ ኩባንያ ሁጂያን ግሩፕ የጫማ ኢንዱስትሪ ዞን ግንባታ የዋለ ነው፡፡

የዕድሜ ባለፀጋው ቅሬታ የሚያጠነጥነው ይህ ሁሉ ቦታ ተወስዶ በምትኩ የተሰጣቸው 250 ካሬ ሜትር መሆኑ፣ በሕመም ምክንያት ቆመው ማስለካት ባለመቻላቸው በግምት 7,000 ካሬሜትር የሆነ ማሳቸው ሳይለካና ግምቱ ሳይከፈላቸው በመቅረቱ፣ በአሁኑ ወቅት በድህነት ውስጥ ተዘፍቀው መኖራቸውን ነው፡፡

የአርሶ አደር ሹሚ ቅሬታ አስተዳደሩ ያወጣቸው መመርያዎች የሚደግፉዋቸው ቢሆንም፣ ‹‹መመርያዎቹ ተጥሰው ለችግር እንድዳረግ ተዳርጌያለሁ፣ የሕግ የበላይነት ይጠበቅልኝ፤›› የሚል ነው፡፡

መመርያ ቁጥር 12/2004ን በአፈጻጸም ለማጠናከር የወጣው ሰርኩላር የአርሶ አደር የምትክ ቦታ አወሳሰንን በተመለከተ እንዳብራራው፣ አርሶ አደሩ በራሱ ይዞታ ሰፋ ያለ ግቢ ይዞ የሚኖር መሆኑ ታሳቢ በማድረግ የይዞታ አስተዳደር የሽግግር ጊዜ መስተንግዶ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በሚያስተናግደው የቦታ ስፋት ልክ ለአርሶ አደሩም ምትክ ቦታ እንዲሰጥ ያዛል፡፡

በዚህ መሠረት አርሶ አደር ሹሚ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ሊሰጣቸው ሲገባ፣ የተሰጣቸው ግን 250 ካሬ ሜትር ብቻ መሆኑ አግባብ አለመሆኑን ባቀረቡት አቤቱታ ገልጸዋል፡፡

‹‹የተሰጠኝ ቦታ ኤሌክትሪክ፣ ውኃ፣ መንገድ የሌለበት ነው፡፡ በዚህ ቦታ ከልጆቼ ተለይቼ መኖር አልችልም፡፡ ዕድሜዬ የገፋ በመሆኑም ጎጆ መቀለስ ይቅርና ለብቻ መኖርም አልችልም፡፡ ስለዚህ የቀድሞ ካርታ መክኖ ሊሰጠኝ የሚገባው 500 ካሬ ሜትር ቦታ መሠረተ ልማት በተሟላበት አካባቢ እንዲሆን እጠይቃለሁ፤›› ሲሉ አርሶ አደሩ ለተለያዩ የአስተዳደሩ መሥሪያ ቤቶች ባስገቧቸው የአቤቱታ ደብዳቤዎች ገልጸዋል፡፡

ከአቶ ሹሚ በተጨማሪ በምትክ የተሰጣቸው ቦታ መጠን ከለመዱት የአኗኗር ዘይቤ ጋር የማይጣጣም፣ መሠረተ ልማት ያልተሟላለት፣ የካሳ ክፍያውም ቀደም ሲል ከሚያመርቱት የምርት መጠን ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ወደ ድህነት አዘቅት ገብተናል የሚሉ አርሶ አደሮች በርካታ ናቸው፡፡

የአርሶ አደሮቹ ልጆችም እንደ ወላጆቻቸው ሁሉ ቅሬታቸውን በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል ወጣቶቹ እንዳለና ውርጋ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ጨምሮ ለተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡

ሁለቱ ወጣቶች በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በወረዳ ስምንት ቱሉ ቦኬ አካባቢ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ይህ ቦታ ቤተል ተብሎ ይጠራል፡፡

ወጣት እንዳለ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ከ1997 ዓ.ም. በፊት በዚህ አካባቢ ከቤተሰቦቹና ከዘጠኝ ወንድሞቹ ጋር ስፋቱ 24 ሔክታር መሬት በሆነ መሬት ላይ በእርሻ ሥራ ይተዳደር ነበር፡፡

በ1989 ዓ.ም. ቦታው ለልማት በሚፈለግበት ወቅት እሱና ታላቅ ወንድሙ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ በመሆኑ መመርያው በሚያዘው መሠረት 250 ካሬ ሜትር ቦታ ይገባቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ለወላጆቹ ብቻ 500 ካሬ ሜትር ተሰጥቶ ለእሱና ለታላቅ ወንድሙ ቦታው ሳይሰጥ ቀርቷል፡፡

አካባቢው ለልማት በሚፈለግበት ወቅት ከ30 በላይ ወጣቶች ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ደርሶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በወቅቱ ለእያንዳንዳቸው በነፍስ ወከፍ 250 ካሬ ሜትር ቦታና ቤት መሥሪያ በመመርያው መሠረት እንደሚሰጣቸው ተገልጾላቸው ቃልም ተገብቶላቸው እንደነበር፣ ወጣቶቹ በኮሚቴያቸው አማካይነት እንደነበር በጻፉት አቤቱታ ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን ቦታው ሳይሰጣቸው በመቅረቱ ከወላጆቻቸው ጋር የግብርና ሥራቸውን መቀጠል ሳይችሉ፣ በአሁኑ ወቅትም የቤተሰቦቻቸው ጥገኛ ሆነው እየኖሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ወጣት ውርጋ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ጥያቄያችንን ከ1994 ዓ.ም. ጀምሮ ለተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አቅርበናል፡፡ የዜግነት መብታችን እንዲከበርልንና ሕግና ደንብ በሚፈቅደው መሠረት እንድንስተናገድ ብንጠይቅም ሰሚ አላገኘንም፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአቅመ ደካማ ወላጆቻችን ጥገኝነት ሥር እንድንተዳደር ተገደናል፡፡   

‹‹ከዚህ በተጨማሪም በወቅቱ በተከፈለው ካሳ መሥራት የተቻለው የጭቃ ቤት ነው፡፡ የጭቃ ቤቱ በአሁኑ ወቅት በእርጅና ምክንያት በመውደቅ ላይ ይገኛል፡፡ ይህንን ቤት በድጋሚ ለመጠገን ወይም ለመሥራት የግንባታ ፈቃድ በምንጠይቅበት ወቅት በብሎኬት መሥራት አለባችሁ እየተባልን እንገኛለን፡፡ የብሎኬት ቤት ለመሥራት አቅማችን የማይፈቅድ በመሆኑ፣ መኖርያ ቤታችንን እየሸጥን ቀያችንን እንድንለቅ እየተገደድን ነው፤›› ሲል መንግሥት ጉዳያቸውን እንዲያጤን ይጠይቃል፡፡

እነዚህ ወጣቶች እንደሚሉት መንግሥት ከዚህ ቀደም የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችን በድጋሚ ለማቋቋም እንቅስቃሴ መጀመሩን በበጎ ይመለከታሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም መንግሥት የተጠቀሱትን ችግሮች በጥልቀት እንዲመለከት አበክረው ይጠይቃሉ፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በተለይ ከ1980ዎቹ ወዲህ በርካታ ግንባታዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ፡፡ በተለይ በንፋስ ስልክ ላፍቶ፣ ኮልፌ ቀራኒዮ፣ ቦሌ፣ አቃቂ ቃሊቲና የካ ክፍላተ ከተሞች የሚገኙ በርካታ አርሶ አደሮች ለልማት ሲባል ተነስተዋል፡፡

ነገር ግን ከተነሱበት ቦታም ሆነ ከመኖርያ ቤታቸው ሲፈናቀሉ በቂ ካሳና ምትክ ቦታ ባለማግኘታቸው ለከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየተዳረጉ መሆኑን እየገለጹ ነው፡፡

‹‹ባለፀጋ አርሶ አደር ነበርኩ፣ ዛሬ ግን በድህነት ውስጥ እገኛለሁ›› ሲሉ የዕድሜ ባለፀጋው አርሶ አደር ሹሚ በሕይወታቸው ውስጥ የተከሰተውን ለውጥ ይገልጻሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በችግር ውስጥ የሚገኙ አርሶ አደሮችን ሕይወት በድጋሚ ለመለወጥ ሥራዎች ጀምሯል፡፡ እነዚህ አርሶ አደሮች የተጀመረው ለውጥ በአፋጣኝ ተግባራዊ እንዲሆን፣ ከዚያም ባለፈ ያልታዩ በደሎች ታይተው መፍትሔ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የልማት ተነሽ አርሶ አደሮች መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ባካሄደው ጥናት፣ በልማት ከተነሱ አርሶ አደሮች ውስጥ በጥሩ ሁኔታ የሚገኙት ከስድስት በመቶ አይበልጡም፡፡

የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱራዛቅ ያሲን በቅርብ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ተፈናቃዮቹን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማቋቋምና ከዚህ በኋላ የሚፈናቀሉ አርሶ አደሮች ተመሳሳይ ችግር እንዳይገጥማቸው ይደረጋል ብለዋል፡፡    

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ የካቤኔ አባል የሆኑት አንድ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሚያቀርቡትን ቅሬታ እያዳመጡ ነው] 

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር በእጅጉ ስላሳሰበኝ ነው በአካል...

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔና የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የፈጠሩት አምቧጓሮ

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 37ኛው...

የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ትግበራ የፈጠራቸው አሉታዊና አዎንታዊ ጎኖች

የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በዓመት የሚሰጡት የብድር መጠን ላይ የኢትዮጵያ...

ቱግ ቱግ!

የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ለመታደም የመጡ እንግዶችን ሸኝተን ከፒያሳ ወደ...