Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየደሴውን ሼክ ኑሩ ይማምን በመግደል የተጠረጠሩ 14 ተከሳሾች ጥፋተኛ ተባሉ

  የደሴውን ሼክ ኑሩ ይማምን በመግደል የተጠረጠሩ 14 ተከሳሾች ጥፋተኛ ተባሉ

  ቀን:

  ከሦስት ዓመታት በፊት በአማራ ክልል ደሴ ከተማ ሸዋበር መስጊድ አካባቢ ሰኔ 27 ቀን 2005 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት አካባቢ አዛውንቱን ሼክ ኑሩ ይማምን በሁለት ጥይት ተኩሶ በመግደል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው 14 ተከሳሾች፣ ሐሙስ ታኅሳስ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ጥፋተኛ ተባሉ፡፡

  ተከሳሾቹ ድርጊቱን የፈጸሙት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀናለ)፣ 38(1)ን እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3(1)፣ 6 እና 7ን በመተላለፍ መሆኑን ገልጾ፣ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ (የአሁኑ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ) ያቀረበለትን ክስ ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት፣ ሁሉም ተከሳሾች ጥፋተኛ ሆነው ማግኘቱን በውሳኔው ገልጿል፡፡

  ፍርደኞቹ በሕገ መንግሥቱ የተከበረውን የሃይማኖትና የእምነት ነፃነት መብትን በመቃረንና በኃይል እንዲቀየር በማስገደድ፣ የደሴ ከተማ ሕዝብ ሰላማዊ ሠልፍ እንዲወጣ ወረቀት በመበተን ጭምር ሲያስተባብሩ እንደነበር፣ ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ገልጿል፡፡

  አዲስ አበባ ከሚገኘው ‹‹ድምፃችን ይሰማ ቡድን›› ጋር ተናበው መሥራት እንዳለባቸው በመግለጽና በተለያዩ መንገዶች አመፅ ቀስቃሽ ድርጊቶችን በመፈጸም፣ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ሸጎሌ መስጊድ ከሚገኙ ግብረ አበሮቻቸው ጋር የሚገናኝ ቡድን በመላክ ሲወያዩና የአመፅ ድርጊት ለመፈጸም ተዘጋጅተው እንደነበር ፍርድ ቤቱ በውሳኔው መዝገብ አስፍሯል፡፡

  ፍርደኞቹ ሃይማኖታዊና አይዶሎጂያዊ ዓላማቸውን ለማራመድ በማሰብና ለማስፈጸም በህቡዕ በመደራጀት፣ እነሱ ለፈለጉት ዓላማ ሌሎችን በመመልመልና በማደራጀት፣ ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው ቡድኖች ጋር በህቡዕ ግንኙነት በመፍጠር፣ በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለማሳደርና ኅብረተሰቡን ለማስፈራራት ሲንቀሳቀሱ እንደነበር፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በሰነድና በሰዎች ምስክሮቹ ማስረዳቱን ውሳኔው ይገልጻል፡፡

  ነሐሴ 4 ቀን 2004 ዓ.ም. በደሴ ከተማ አረብ ገንዳ መስጊድ ላይ ባደረጉት የአመፅና ረብሻ ጥሪ፣ ከአዲስ አበባ ወልዲያ የሚወስደውን መንገድ በመዝጋት የሕዝብ ትራንስፖርት እንዲቋረጥ በማድረግ፣ ሕግና ሥርዓት ለማስከበር በተሰማሩ የፖሊስ አካላት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውም መረጋገጡን ውሳኔው ይጠቁማል፡፡

  ፍርደኞቹ በሚያደርጓቸው ህቡዕ ስብሰባዎች ከእነርሱ አስተሳሰብ፣ አስተምህሮና እምነት ውጪ ናቸው ባሏቸው የሃይማኖት አባቶችና ግለሰቦች ላይ ፍርኃትን ለመፍጠር በማቀድ፣ በተደጋጋሚ ጊዜ ተሰብስበው ከተወያዩ በኋላ የማስፈራሪያ መልዕክት ሰኔ 19 ቀን 2005 ዓ.ም. ማስተላለፋቸውን ዓቃቤ ሕግ በሰነድና በሰው ማስረጃው ማረጋገጡን ውሳኔው ያስረዳል፡፡

  ‹‹ልብ ያለው ልብ ይበል›› በሚልና ‹‹የማስጠንቀቂያ ደወል፣ ከዚህ ሌላ ማስጠንቀቂያ አይኖርም፣ ከኢስላም ጠላቶች ጋር የምታደርገው ትብብር በገንዘብ የማይተመን ዋጋ ያስከፍልኃል›› የሚል ዛቻ በሟች ሼክ ኑሩ ላይ ማስተላለፋቸውንም ዓቃቤ ሕግ በሚገባ ማስረዳቱን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ገልጿል፡፡

  በተለያዩ የሃይማኖት አባቶች ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው በገለጹት መሠረት፣ በሌሊት በቤታቸው ወረቀት እንዲበተን ካደረጉ በኋላ ሰኔ 27 ቀን 2005 ዓ.ም. ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት አካባቢ ሼክ ኑሩን በሁለት ጥይት መትተው መግደላቸውን፣ ዓቃቤ ሕግ በሰውና በሰነድ ሊያረጋግጥ በመቻሉና ፍርደኞቹ መከላከያ ምስክር ያሰሙ ቢሆንም፣ የዓቃቤ ሕግን ማስረጃ ሊያስተባብሉ ባለመቻላቸው ሁሉም ጥፋተኛ መባላቸው ተገልጿል፡፡

  ፍርድ ቤቱ ግራ ቀኙ የቅጣት ማክበጃና ማቅለያቸውን ከጥር 9 ቀን 2009 ዓ.ም. በፊት እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ በመስጠት፣ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለጥር 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ 

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...