ሐበሻ ሲሚንቶ አክስዮን ማኅበር ሆለታ አካባቢ በ30 ሔክታር ቦታ ላይ ከ155 ሚሊዮን ዶላር በሚበልጥ ወጪ እያከናወነ ያለው የሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ 95 በመቶ በመጠናቀቁ በሚቀጥለው ወር የሙከራ ምርት፣ ከሁለት ወራት በኋላ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ማምረት እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡
የሐበሻ ሲሚንቶ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን አቢ (ኢንጂነር) እንደገለጹት፣ ከተጠናቀቁት የግንባታ ሥራዎች መካከል የድንጋይ ከሰል፣ በተጓዳኝነት የቀይ አፈር፣ የኖራ ድንጋይና ፑሚስ የሚባሉት ጥሬ ዕቃዎች የሚከማችባቸው እያንዳንዳቸው 240 ሜትር በ44 ሜትር ስፋት ያላቸው ሦስት ትልልቅ መጋዘኖች ግንባታዎች ይገኙበታል፡፡
እያንዳንዳቸው ስድስት ሺሕ ቶን ወይም በአጠቃላይ 24 ሺሕ ቶን የመያዝ አቅም ያላቸው አራት የሲሚንቶ ማጠራቀሚያ ጋኖች ግንባታም ተጠናቋል፡፡ የፋብሪካው ግንባታ ከሚካሄድበት ሁለት ኪሎ ሜትር ያህል ወጣ ብሎ በሚገኝ ሥፍራም፣ ከ200 ሜትር በላይ ጥልቀት ያለው ጉድጓድ ተቆፍሮ የወጣው ውኃም ለፋብሪካው አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ተገልጿል፡፡
አቶ መስፍን እንደሚሉት፣ ከቀሩት አምስት በመቶ ሥራዎች መካከል የፋብሪካውን መሣሪያዎች መፈተሽና ጊዜያዊ ርክክብ ማካሄድ ይገኝበታል፡፡ በመሣሪያዎቹ ላይ ፍተሻ የማካሄድ ሥራ ተጀምሮ አብዛኞቹ ተፈትሸው ጥሩ ይዞታ ላይ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡
ዘመናዊ የጥራት ማረጋገጫ መሣሪያ፣ እንዲሁም 18 ሺሕ ቶን የሚጠጋ የድንጋይ ከሰል፣ ሦስት ሚሊዮን የሲሚንቶ ማሸጊያ ከረጢትና 900 ሺሕ ዶላር የሚያወጡ ልዩ ልዩ መለዋወጫዎች መገዛታቸውንም አቶ መስፍን አስረድተዋል፡፡
ፋብሪካውን ከሌሎች መሰል ፋብሪካዎች ለየት የሚያደረገው ምንድነው? ተብለው የተጠየቁት ጥያቄ አቶ መስፍን፣ እስካሁን ያሉት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች በአብዛኛው በግል ባለሀብቶችና በጥቂት ባለድርሻዎች የተያዙ መሆናቸውን በማስታወስ፣ ሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ ግን ከ16 ሺሕ 500 በላይ ባለአክሲዮኖች የተሳተፉበት በመሆኑ ለየት ይላል ብለዋል፡፡
አሁን ባለው የገበያ ሁኔታ የሲሚንቶ አቅርቦትና ፍላጎት እየጨመረ መሆኑን በተመለከተ፣ የፍላጎቱን ያህል አቅርቦቱ ባለመጨመሩ ምክንያት ፋብሪካው ሳይቸገር ወደ ገበያ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ በዚህም ከ38 በላይ አከፋፋዮችና ነጋዴዎች ከአክሲዮን ማኅበሩ ጋር አብረው ለመሥራት ፍላጎት እንዳሳዩም ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ መስፍን ማብራሪያ፣ ሲሚንቶ ለውጭ ገበያ የማቅረቡን ጉዳይ አክሲዮን ማኅበሩ በቢዝነስ ዕቅዱ ውስጥ አስገብቶታል፡፡ በዚህ መሠረት በአገር ውስጥ ያለው የገበያ ድርሻ ከታወቀ በኋላ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ጎረቤት አገሮች በተለይም ወደ ኬንያና ደቡብ ሱዳን ለማቅረብ ጥናት በመካሄድ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
ፋብሪካው አሁንም በፕሮጀክት ደረጃ ላይ ቢሆንም የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለአካባቢው ማኅበረሰብ ንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ የጥሬ ዕቃ ማውጫ ቦታ ላይ ለተቋቋመው የመንግሥት ክሊኒክ በፀሐይ ኃይል የሚሠራ የኤሊክትሪክ ኃይል የማስገባትና ሕዝብ በብዛት የሚንቀሳቀስባቸውን የውስጥ ለውስጥ መንገዶች የመጥረግና የማስተካከል ሥራዎች ማከናወኑም ተገልጿል፡፡
የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ አዳነ እንደገለጹት ፋብሪካው ሥራውን ሲጀምር በቀን 30 ሺሕ ኩንታል ወይም ሦስት ሺሕ ቶን ኦፒሲ፣ እንዲሁም 45 ሺሕ ኩንታል ፒፒሲ ሲሚንቶ የማምረት አቅም የሚኖረው ሲሆን፣ ወደፊትም አብዛኛው ሕዝብ የሚጠቀምበትን 22.5 የተባለውን ሲሚንቶ ለማቅረብ ሐሳብ አለው፡፡
ፋብሪካዎች ማውጣት ያለባቸው የብክለት ልቀት መጠን የዓለም ባንክ ባወጣው መሥፈርት መሠረት 50 ሚሊ ግራም ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ያስቀመጠችው መሥፈርት ከፍተኛው 150 ሚሊ ግራም ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ የሚያወጣው የብክለት ልቀት መጠን ከፍተኛው 30 ሚሊ ግራም እንደሆነና ይህም ከወጡት መሥፈርቶች ያነሰ እንደሚሆን ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡
የፕሮጀክቱ የኤሌክትሪካልና የኢንስትሩመንት ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ኃይለ ማርያም፣ ፋብሪካው 25 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያስፈልገው፣ ለዚህም የሚሆን የሰብስቴሽንና የኃይል ማሰራጫ ግንባታዎች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡ ከገፈርሳ ግድብ ወደ ሙገር ከሚሄደው 132 ኪሎ ቮልት ኃይል ተሸካሚና አስተላላፊ መስመር 15 ሜጋ ዋት ኃይል እንዲጠቀም እንደተፈቀደለትም ሥራ አስኪያጁ አክለዋል፡፡