በደካማ የሥራ አፈጻጸም ሲወቅሱ የቆዩት የሆርቲካልቸር ልማት ኤጀንሲና የግብርና ኢንቨስትመንትና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ተዋህደ፣ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሆነ መሥሪያ ቤት ተቋቋመ፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ኢንቨስትመንትና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ከክልሎች በውክልና ወስዶ ሲያስተዳድር የቆየውን መሬት እንዲመልስ የተወሰነ በመሆኑ፣ አዲሱ መሥሪያ ቤት መሬት የማስተዳደር ሥልጣን አይኖረውም፡፡ አዲስ የተቋቋመው ‹‹የሆርቲካልቸርና ግብርና ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን›› የተሰኘው መሥሪያ ቤት ባለሀብቶችን መከታተልና መደገፍ ላይ ያተኩራል ተብሏል፡፡
እነዚህ ሁለት ኤጀንሲዎች በአገሪቱ የግብርና ዕድገት በተለይ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በአበባ፣ በጥርጣሬ፣ በቅባት እህሎች እንዲሁም በጥጥ ልማት ትልቅ ለውጥ ያመጣሉ ተብለው የተቋቋሙ ነበሩ፡፡
ነገር ግን ብዙ የተባለለት አበባም ሆነ የእህል ምርት እምብዛም ሆኖ ቀርቷል፡፡ በዚህ ምክንያት የዘርፉ ዋነኛ ተዋናዮች ባገኙት አጋጣሚ መሥሪያ ቤቶቹን ከመውቀሳቸውም በተጨማሪ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም በሥራ አፈጻጸም ደካማነታቸው ወቅሰዋቸዋል፡፡
የእነዚህን ኤጀንሲዎች ድክመት በመለየት ዘርፉን በሚገባው ደረጃ ለመደገፍ አዲስ መዋቅር ሲጠና ቆይቶ በታኅሳስ ወር አጋማሽ ባለሥልጣኑ ተቋቁሟል፡፡ ነገር ግን የመዋቅር ለውጥ ጥናቱ የተካሄደበት መንገድ ያጠራጠራቸው ባለሙያዎች፣ ጊዜው ሳይረፍድ ጥናቱ በትክክለኛ ባለሙያዎች ሊከለስ ይገባል የሚል አስተያየት እየሰጡ ነው፡፡
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የዘርፉ ባለሙያ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ይህ ጥናት የተካሄደው በሆርቲካልቸር ልማት ኤጀንሲ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተርና የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ የቀድሞ ዋና ዳይሬክተር የበላይነት ነው፡፡
‹‹እነዚህ አመራሮች ተወቃሽ እንደ መሆናቸው ጥናቱ በድጋሚ ሊታይ ይገባል›› ሲሉ እኝሁ ባለሙያ ይገልጻሉ፡፡
በተካሄደው ጥናት ከዚህ በፊት በሁለቱ የግብርና ዘርፎች የተፈጠሩ ችግሮች ተለይተው የመፍትሔ አቅጣጫ ተመላክቷል ወይ? ለተፈጠረው ችግርስ ተጠያቂ አካል ተለይቷል ወይ?›› በማለት የሚጠይቁ ባለሙያዎች አሉ፡፡
አዲሱ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤት አዲስ አመራር ተሰይሞለታል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስተር ጽሕፈት ቤት አቶ ያዕቆብ ያላን ዋና ዳይሬክተር፣ አቶ አበራ ሙላትን ደግሞ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አድርጎ ታኅሳስ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. መሾሙ ታውቋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የንግድ ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ያዕቆብ፣ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርጎ ሾሞ ነበር፡፡
የኢንተርፕራይዙ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በቅርቡ የሰበሰቡት ቦርድ፣ አቶ ያዕቆብ መንግሥት ሌላ ኃላፊነት እንደሚፈልጋቸው በመግለጽ ሹመቱ እንዲቀር መደረጉን አመልክተዋል፡፡ እስከዚያው ግን ኢንተርፕራይዙን አቶ መስፍን ተፈራ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው እንዲሠሩ መመደባቸውን አቶ አህመድ አስታውቀዋል፡፡
የአዲሱ የሆርቲካልቸርና የግብርና ኢንቨስትመንት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሸሙት አቶ አበራ፣ የባለሥልጣኑን መቋቋም ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ ነገር ግን በይፋ መግለጫ የሚሰጥ በመሆኑ፣ ዝርዝር ውስጥ ከመግባት እንደሚቆጠቡ አክለዋል፡፡