Tuesday, February 27, 2024

የሰማያዊ ፓርቲ የቀድሞ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መከላከያ ምስክሮቹን ማሰማት ጀመረ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በሽብር ተግባር ወንጀል ተጠርጥሮ የተከሰሰው የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ ሐሙስ ታኅሳስ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. የመከላከያ ምስክሮቹን ማሰማት ጀመረ፡፡

የፍልስፍና ምሁሩን ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋንና የሕግ ሙሁሩን ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያምን ጨምሮ አሥር መከላከያ ምስክሮች እንዳሉት ያስመዘገበው አቶ ዮናታን፣ የመከላከያ ምስክሮቹ ክሱን ለሚመረምረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የምስክርነት ቃላቸውን ከመስጠታቸው በፊት የተከሳሽነት ቃሉን ሰጥቷል፡፡

ከፌስቡክ ጓደኞቹ ጋር ባደረጋቸው ውይይቶች የሰጣቸው አስተያየቶች እንደ ወንጀል ተቆጥረው ክስ እንደተመሠረተበት የተናገረው አቶ ዮናታን እንደ፣ ፖለቲከኛና ሐሳቡን በነፃነት እንደሚያራምድ ማንኛውም የኅብረተሰብ አካል ድርጊቱ ጥፋት ነው ብሎ እንደማያምን አስረድቷል፡፡ ባለው የፖለቲካ ኃላፊነት በፌስቡክም ሆነ በተለያየ መንገድ ማለትም ለመገናኛ ብዙኃንም ተመሳሳይ ሐሳብ እንደሚናገር የገለጸው አቶ ዮናታን፣ ዓቃቤ ሕግ ኅብረተሰቡን ለአመፅ የሚያነሳሳ ጽሑፍ እንዳሰራጨ አድርጎ ክስ ማቅረቡ ስህተት መሆኑን ተናግሯል፡፡ ምናልባት አለመረዳት ሊሆን እንደሚችልና ፍርድ ቤቱም ግንዛቤ ሊወስደው ይችላል የሚል እምነት እንዳለው አክሏል፡፡ የጻፈው ጽሑፍ ግን ለሕዝብ ቢደርስ ችግር እንደሌለውም ተናግሯል፡፡

በፌስቡክ ገጹ የጻፋቸው፣ የተወያየባቸውና ሐሳቡን ያካፈለባቸው መጣጥፎች መንግሥት ስለሶማሊያና ጋምቤላ በተደጋጋሚ የገለጻቸው ሐሳቦች እንደሆኑም አቶ ዮናታን ተናግሯል፡፡ ‹‹ሐሳቤን መግለጽ ካልቻልኩ፣ ካልተወያየሁ፣ ካልተናገርኩና ካልተቃወምኩ ታዲያ ለምን ፖለቲከኛ ሆንኩ?›› በማለት የጠየቀው አቶ ዮናታን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ይቅርታ በጠየቁበትና በኦሮሚያ ክልል የተፈጠሩ ሁከቶች በመልካም አስተዳደር ዕጦት መሆኑን በገለጹበት ጉዳይ፣ በእሱ ላይ ወንጀል ሆኖ መከሰሱ ተገቢነት እንደሌለው አስረድቷል፡፡

የተከሰሰው ከፌስቡክ ገጽ በወጣ ጽሑፍ እንጂ በኦሮሚያ በተደረገው ረብሻ እንዳልሆነና ዓቃቤ ሕግም ምንም ዓይነት ማስረጃ እንዳላቀረበ ገልጿል፡፡ ፌስቡክ የጓደኛን ልክ (ብዛት) ስለሚመጥን ዓቃቤ ሕግ በክሱ እንዳለው ሕዝብን ለማነሳሳት ገደብ እንዳላለፈ አስረድቷል፡፡

አቶ ዮናታን በዝርዝር የተከሳሽነት ቃሉን ከሰጠ በኋላ ጠበቃው ምስክሮቹ የሚመሰክሩበትን ጭብጥ አስይዘው እንደጨረሱ፣ ዶ/ር ያዕቆብ በቅድሚያ የሙያ ምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

የ72 ዓመቱ የሕግ ምሁር ዶ/ር ያዕቆብ ለፍርድ ቤቱ በሰጡት የሙያ ምስክርነት እንደገለጹት፣ አቶ ዮናታን የተከሰሰው በሽብር መሆኑን ያውቃሉ፡፡ ‹‹ክቡራን ዳኞች እንደሚያውቁት ሽብርተኝነት ከባድ ወንጀል ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ወንጀል በመሆኑ ድርጊቱን የፈጸመ አካል የትኛውም አገር መክሰስ ይችላል፡፡ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤትም ሊያጠቃልለው በውይይት ላይ ነው፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ወደ ዮናታን ክስ ሲመለሱ ግን ከጥቂት ሰዎች ጋር በፌስቡክ መገናኘቱ የሽብር ወንጀል ነው ወይም ፈጽሟል ለማለት እንደሚከብድ ተናግረዋል፡፡ በአሜሪካ ናይን ኢለቨን (9/11) የተፈጸመውን የሽብር ተግባር ያስታወሱት ዶ/ር ያዕቆብ፣ በናይጄሪያ 200 ልጃገረዶች ከታገቱት፣ በኡጋንዳ፣ በኬንያና በተለያዩ አገሮች ከተፈጸሙት የሽብር ወንጀሎች አንፃር ዮናታን በፌስቡክ የሽብር ተግባር ፈጽሟል ማለት ‹‹ድርጊቱን ያሳንሰዋል›› ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት ድንጋጌንና ተቀብላ ያፀደቀቻቸውን የሰብዓዊና የዴሞክራሲ መብቶችንም የሚጥስ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የፌስቡክ ንግግር፣ ውይይትና ሐሳብ መስጠት ለሽብር አስተዋጽኦ ያደርጋል ማለት እንደሚከብድም ገልጸዋል፡፡ በእሳቸው እምነት አቶ ዮናታን በፌስቡክ የጻፈውና የተጻጻፈው በሕገ መንግሥቱ በተፈቀደው የንግግር ነፃነት ውስጥ የሚወድቅ መሆኑን  ነው፡፡ ሰውን የሚያዋርድ፣ ሕግን የጣሰና ባህልን የሚያንኳስስም እንዳልሆነ አክለዋል፡፡

ንግግር ተፈጥሯዊ ከመሆኑ አንፃር ያልተጠቀሰበት ዓለም አቀፋዊ የስምምነት ቃል ኪዳን ሰነድ እንደማይገኝም ጠቁመዋል፡፡ በእርግጥ ሐሳብን መግለጽ፣ መነጋገርና መጻፍ ፍፁም ስላልሆነ ገደብ እንዳለውም የገለጹት ዶ/ር ያዕቆብ፣ አቶ ዮናታን የጻፈው ግን በተከለከሉት ወይም ገደብ በተጣለባቸው ውስጥ እንደማይካተት አስረድተዋል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበበትን ክስ ማንበባቸውንና እሳቸው እንደገባቸው ሐሳብን በነፃነት መግለጽ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ሁለተኛ መከላከያ ምስክር ሆነው የቀረቡት የፍልስፍና ምሁሩ ዶ/ር ዳኛቸው ናቸው፡፡ ሐሳብን በነፃነት መግለጽ ምን ማለት እንደሆነ እንዲያስረዱ ተጠይቀው እንደገለጹት፣ ሐሳብን በነፃነት መግለጽ እንደሚቻል ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ ሲረቀቅ በ1948 (እ.ኤ.አ.) አብራ አርቃቂ እንደነበረች አስረድተዋል፡፡ በ1953፣ በ1969 እና በ1982 (እ.ኤ.አ.) በተደረጉ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ ጉባዔዎች ላይም ተሳታፊ እንደነበረችም አስረድተዋል፡፡

ንግግር በይዘቱ እንደማይፈተሽ የገለጹት ዶ/ር ዳኛቸው ማንም ሐሳቡን የመጻፍ፣ የማውጣት፣ የመሳተፍ፣ የማጋራትና የማቅረብ መብት እንዳለውና መንግሥትና ሕዝብም የማወቅ መብት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ሰዎች እርስ በርሳቸው ሐሳብ መለዋወጥና መወዳደር መብታቸው መሆኑንም አክለዋል፡፡ ዴሞክራሲ ድምፅ ይፈልጋል፡፡ የአቶ ዮናታንን ጽሑፍ ሲያነቡት (የክስ ቻርጁን) እምነቱን ማስቀመጡን ተገንዝበዋል፡፡ እሳቸው በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ስምንት ዓመታት መጻፋቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ስህተት ወንጀል እንዳልሆነ፣ አቶ ዮናታን ሲሳሳት ስህተቱን መቀበል ወይም አለመቀበል መብት መሆኑን የገለጹት ዶ/ር ዳኛቸው፣ ስህተት የሚሆነው አቶ ዮናታን ከጻፈው ጽሑፍ ላይ ይወሰድና ሌላ ስህተት ሲፈጸም መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከድርጊት ወደ ሽብር ይኬዳል እንጂ፣ ከሐሳብ ወደ ሽብር መሄድ ከፈረሱ ጋሪው እንዲሉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሐሳብ እንደማይወሰን፣ የመለመን፣ የማሞገሥና የመተቸት መብት የተፈቀደ መሆኑንና ይዘት ሊመዘን እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ አቶ ዮታናታንም የተጠቀመበት መሣሪያ በግል ሐሳብን መግለጽ በመሆኑ፣ ከንግግርና ከጽሕፈት የሚመጣን ስህተት ማገድ ሳይሆን መፍቀድ መሆኑን ብዙ ፈላስፎች የሚስማሙበት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ በዮናታን ጽሑፎች ላይ ሞራል የሚነካ ነገር አለማየታቸውንም አክለዋል፡፡ ሪፖርተር በበዓል ምክንያት ማተሚያ ቤት እስከገባበት ሐሙስ ታኅሳስ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ አቶ ዮናታን በመከላከያ ምስክርነት ካቀረባቸው አሥር ሰዎች የሁለቱን ብቻ መስተናገድ ችሏል፡፡ የቀሪዎቹን መከላከያ ምስክሮች ቃል ማካተት አልተቻለም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -