Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመንግሥት የአገር ውስጥ የመርከብ ወኪሎችን በአግባቡ እንዲቆጣጠር ጥሪ ቀረበ

መንግሥት የአገር ውስጥ የመርከብ ወኪሎችን በአግባቡ እንዲቆጣጠር ጥሪ ቀረበ

ቀን:

– የወጪ ንግድ ሸቀጦችን በጂቡቲ ወደብ በኮንቴይነር ለማሸግ ብቻ ከ100 ዶላር በላይ ይጠየቃል

– የመርከብ ጭነት አስተላላፊዎች ችግሩ የመንግሥት እንደሆነ ይገልጻሉ 

የወጪ ንግድ ሸቀጦችን በጂቡቲ ወደብ በኮንቴይነር ውስጥ አሽጎ ለመላክ በአንድ ኮንቴይነር 110 ዶላር የሚጠየቀው ወጪ ተገቢነት የለውም ያሉ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ለዚህ ድርጊት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ያሏቸውን የውጭ መርከብ ኩባንያዎችን በመወከል    በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ወኪሎችን መንግሥት በአግባቡ እንዲቆጣጠር ጥሪ አቀረቡ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ምንጮች እንዳብራሩት፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የባዶ ኮንቴይነር እጥረት ባይኖርም ባዷቸውን ወደ ጂቡቲ ለሚጓጓዙ ኮንቴይነሮች የሚከፈለው የትራንስፖርት ወጪ ሳያንስ፣ ወደ ጂቡቲ ወደብ የሚላኩ ሸቀጦችን በኮንቴይነር ውስጥ ለመጫን የሚከፈለው 110 ዶላር አግባብነት የጎደለው ነው ብለዋል፡፡ እንዲሁም በጂቡቲ የሚገኙ የመርከብ ወኪሎች የሚያስከፍሉት ታሪፍ በመሆኑ፣ ምርቶቹን እዚሁ በማሸግ መላክ እንዲቻል መንግሥት በተለይም ዘርፉን የሚቆጣጠረው የማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣን፣ የበላይ የሆነው የትራንስፖርት ሚኒስቴርና ሌሎችም የመንግሥት አካላት ትኩረት እንዲሰጡበት ጠይቀዋል፡፡

የወጪ ንግድ ሸቀጦች ወደ ውጭ ሲላኩ በአገር ውስጥ ሳሉ በኮንቴይነር ባለመታሸጋቸው ምክንያት ከሚወጣባቸው የውጭ ምንዛሪ ወጪ ባሻገር፣ ምርቶቹ እስከ ጂቡቲ ወደብ በመኪና ተጭነው ሲጓጓዙ የሚደርስባቸውን የሥርቆት ወንጀል (ቅሸባ) ለማስቅረት የሚቻልባቸው ዕድሎች እየታጡ እንደሚገኙ የዘርፉ ተዋናዎች ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ባሻገር በላኪና በምርት ተቀባይ መካከል ብዙውን ጊዜ ንትርክ የሚያስነሳውን የክብደት መቀነስ ችግርም ለመቀነስ እንደሚረዳ ተጠቅሷል፡፡ ወጪ ሸቀጦች በአገር ውስጥ በኮንቴይነር ታሽገው ቢወጡ ያላግባብ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ ከማስቀረት በተጨማሪ (በብር የሚከፈል በመሆኑ)፣ የሸቀጦች ደኅንነትና የጥራት ደረጃ  በአግባቡ ተፈትሾና ተረጋግጦ እንዲወጣ ለማድረግ እንደሚያስችል ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ፡፡

በየዓመቱ ከ200 እስከ 300 ሺሕ ቶን የሚገመት የቡና ምርት፣ እንዲሁም ከ300 እስከ 400 ሺሕ ቶን የሚገመቱ የቅባትና ጥራጥሬ እህሎችና ቅመማ ቅመሞች ወደ ውጭ እንደሚወጡ ሲገመት፣ ከዚህ ውስጥ እስከ 90 በመቶው ጂቡቲ ወደብ ከደረሱ በኋላ በኮንቴይነር እንደሚጫኑ ይገለጻል፡፡  

የኢትዮጵያ የመርከብ ጭነት አስተላላፊዎችና የመርከብ ኩባንያ ወኪሎች ማኅበር ፕሬዘዲንትና የማክፋ ቢዝነስ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ አሰፋ ስለጉዳዩ በሪፖርተር ተጠይቀው ችግሩ መኖሩን ገልጸዋል፡፡ ምርቶች በአገር ውስጥ በኮንቴይነር ውስጥ እንዲጫኑ ቢደረግ የተዘረዙት ጠቀሜታዎች እንዳሉ ገልጸው፣ ለወጪ ሸቀጦች የሚውል ኮንቴይነር በአግባቡ አቀናጅቶ የማቅረብ ችግር ከፍተኛ በመሆኑ፣ የመርከብ ወኪሎች ኮንቴይነር ለማቅረብ እየተቸገሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ማኅበሩ ይህንን ችግር እንዲፈታና ምርቶችም በአገር ውስጥ በኮንቴይነር ታሽገው የሚቀመጡበትን ቀልጣፋ አሠራርና ቅንጅት እንዲፈጥር ሲወተውት ቢቆይም ምላሽ እንዳላገኘ አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም በላይ መንግሥት ለሌሎች ዘርፎች የሚሰጠውን ማበረታቻና ከቀረጥ ነፃ ዕድል ለጭነት አስተላላፊዎችም ሆነ ለመርከብ ወኪሎች ባለመስጠቱ ዘርፉን ችላ ለማለቱ አስረጂ አድርገውታል፡፡ በመሆኑም መሬት በተመጣጣኝ የሊዝ ዋጋ ቢያቀርብና የመርከብ ኩባንያዎችና ወኪሎች የኮንቴይነር ማከማቻዎችን እንዲገነቡ ቢያስችል፣ የኮንቴይነር መጫኛና ማውረጃ መሣሪያዎችን ከቀረጥ ለማስገባት እንዲቻል ቢፈቅድ፣ ባዶ ኮንቴይነር ወደ ጂቡቲ መላክ ሊቀንስ የሚያስችሉ መፍትሔዎች እንደሚሆኑ አቶ ሙሉጌታ ጠቅሰዋል፡፡

በዘርፉ ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች በአገር ውስጥ መርክብ ወኪሎች ላይ ከሚያቀርቡት የሰላ ትችት መካከል ‹‹የወኪል ወኪል›› ሆነው የሚሠሩ፣ ዋናዎቹ ወኪሎች በእጅ አዙር የሚያሽከረክሯቸው በመሆናቸው ለላኪዎች ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት ኃላፊነታቸውን ከመወጣት ይልቅ የሚያጉላሉና አላስፈላጊ ወጪ የሚያስከትሉ ሆነዋል በማለት የሚያሰሙት ይገኝበታል፡፡ መንግሥት ትክክልኛ ወኪሎች እነማን እንደሆኑ በማጣራት ቁጥጥር እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

በሌላ በኩል አቶ ሙሉጌታ እንደሚከራከሩት፣ የወኪል ወኪል ወይም የሦስተኛ ወገን ሆኖ መሥራት በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በመላው ዓለም የሚሠራበት የተለመደ አሠራር ከመሆኑ ባሻገር፣ የአገር ውስጥ ወኪሎች ትክክለኛና ሕጋዊ አሠራርን ተከትለው ይሠራሉ፡፡ ይህንን የማያደርጉ ካሉና ያላግባብ ዋጋ የሚያንሩ ከሆነ ግን መንግሥት ተከታትሎ ዕርምጃ መውሰድ እንደጠበቅበት ተናግረዋል፡፡ ያልተገባ ዋጋ የሚጠይቁ የመርከብ ወኪሎች አሉ ቢባል እንኳ ጭነቱን የሚሰጣቸው ላኪ አንዱን የመርከብ ድርጅት ከሌላው አወዳድሮ የሚመርጥ በመሆኑ፣ እንዲህ ያለው ትችት ብዙም እንደማያስኬድ ገልጸዋል፡፡

ስለጉዳዩ የማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣንን ለማነጋገር ሪፖርተር ያደረገው ጥረት ሊሳካ አልቻለም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...