Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በ16 ሚሊዮን ብር ዕዳ ተከሰሱ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የጉምሩክና የኢኮኖሚ ወንጀል ዳይሬክቶሬትንና የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን ከውጭ አገር በሕጋዊ መንገድ የገባ የአርማታ ብረት ያላግባብ መውሰዳቸው በፍርድ ቤት በመረጋገጡ፣ ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ዕዳ እንዲከፍሉ በአስመጪው ድርጀት የክስ አቤቱታ ቀረበባቸው፡፡

ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀጥታ ክስ ፍትሐ ብሔር ችሎት በሁለቱ የመንግሥት ተቋማት ላይ የክስ አቤቱታ ያቀረበው፣ ወሪ ጄኔራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ነው፡፡

ማኅበሩ በክስ አቤቱታው እንደገለጸው፣ ከውጭ አገር ብረት አስመጪ ከሆኑ ድርጅቶች ላይ በመግዛት ዓለም ገና በሚገኘው መጋዘኑ ያከማቻል፡፡ በተለይ ትኩረት አድርጎ የሚገዛቸው የአርማታ ብረቶችን በመሆኑ ‹‹የአርማታ ብረቶች ችርቻሮ ንግድ›› የሚባል የችርቻሮ መሸጫ ሱቅ ተክለሃይማኖት አካባቢ በመክፈት እየነገደ መሆኑን ለችሎቱ አስረድቷል፡፡

ማኅበሩ የዕለት ተዕለት ሥራውን በማከናወን ላይ እያለ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሚያዚያ 4 ቀን 2005 ዓ.ም. ዓለም ገና በሚገኘው መጋዘኑ በመሄድ፣ 670,460 ኪሎ ግራም (670.46 ሜትሪክ ቶን) የአርማታ ብረት በሕገወጥ መንገድ የገባ መሆኑን በመግለጽ እንደወሰደበት በአቤቱታው አመልክቷል፡፡ በወቅቱ በነበረው የአንድ ኪሎ አርማታ ብረት ዋጋ 24 ብር መሆኑን የጠቀሰው ማኅበሩ፣ ወለዱንና ላለፉት አራት ዓመታት እየናረ የመጣውን የዋጋ ግሽበት ሳይጨምር የ670.46 ሜትሪክ ቶን ብረት ዋጋ 16,091,040 ብር መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

ባለሥልጣኑ ከማኅበሩ ብረቶቹን የወሰደው መሐመድ ከድር አብዲ የተባለ ግለሰብ ከቀረጥና ግብር ነፃ መብት ተጠቅሞ በሕገወጥ መንገድ ያስገባው በማስመሰል ቢሆንም፣ ብረቶቹ በማኅበሩ መጋዘን ውስጥ የተከማቹት በምን ሁኔታ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ሰነድም ሆነ ማስረጃ ሳይኖር እንደሆነ ማኅበሩ በክስ አቤቱታው አስረድቷል፡፡

ብረቶቹ የተከማቹት በሕገወጥ መንገድ ከውጭ አገር በማስገባት ነው ቢባል እንኳን፣ በወቅቱ ድርጊቱን የማጣራት ሥልጣን የነበረው የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሆኖ ሳለ፣ ባለሥልጣኑ ‹‹ውክልና አለኝ›› በማለት የፈጸመው ድርጊት ትክክል እንዳልነበር ማኅበሩ በአቤቱታው አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የአርማታ ብረቶቹ በሕገወጥ መንገድ የገቡ መሆናቸውንና መንግሥትም ሊያገኝ ይገባ የነበረውን የተጨማሪ እሴት ታክስና የግብር ክፍያዎች ማጣቱን በመግለጽ በመዝገብ ቁጥር 165434 ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የክስ አቤቱታ ያቀረበ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ጥቅምት 8 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጠው ብይን ማኅበሩ ብረቶቹን በመጋዘኑ ያከማቸው በሕጋዊ መንገድ ከአስመጪዎች በመግዛት መሆኑን ከቀረቡለት ሰነዶችና ምስክሮች ማረጋገጡን ገልጾ፣ የቀረበውን የወንጀል ክስ ውድቅ ማድረጉን ማኅበሩ ባቀረበው የክስ አቤቱታ ላይ ገልጿል፡፡

ከሳሽ ወሪ ጄኔራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተወሰደበት የአርማታ ብረት ያላግባብ መሆኑን በፍርድ ቤት ጭምር ያረጋገጠ መሆኑን በመግለጽ፣ የአርማታ ብረቱ በተወሰደበት ጊዜ ባለው ዋጋ ሳይሆን አሁን በወቅታዊው ዋጋ ተሰልቶ በገንዘብ ከነወለዱ፣ ወይም ብረቱ በወቅቱ በነበረው ዋጋ ተሰልቶና ብረቱንና የዋጋውን ልዩነት ገንዘብ ከነወለዱ እንዲከፈለው ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የጉምሩክና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጥያቅ ያቀረበ ቢሆንም፣ ሊቀበለው እንዳልቻለ በክስ አቤቱታው ገልጿል፡፡

በመሆኑም የክስ አቤቱታው የቀረበለት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀጥታ ክስ ፍትሐ ብሔር ችሎት፣ ማኅበሩ ያቀረበለትን የክስ አቤቱታ ተመልክቶ ክፍያው እንዲፈጸምለት ትዕዛዝ እንዲሰጥለት አመልክቷል፡፡

ፍርድ ቤቱ የቀረበለትን የክስ አቤቱታ ተመልክቶ ሁለቱ የመንግሥት ተቋማት የካቲት 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀርበው እንዲያስረዱ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች