Monday, September 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ልዩነቶችን ከማጦዝ ድርድር ተቀዳሚ የአገር አጀንዳ ይሁን!

  የሰው ልጆች በፈርጀ ብዙ የሕይወት ገጽታዎች ውስጥ በሚያደርጓቸው ግንኙነቶች ድርድር ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ውሳኔዎች ላይ ለመድረስ የሚደረጉ ውይይቶችና ክርክሮች የሚቋጩት በድርድር ነው፡፡ ድርድር ያልተደረገበት ስምምነት ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም፡፡ ካለም በጉልበተኞች የበላይነት የተቋጨ ነው፡፡ ከግለሰብ እስከ ማኅበረሰብ ድረስ በየዕለቱ በሚያጋጥም ውጣ ውረድ ውስጥ ድርድር አለ፡፡ አገሮች በሁለትዮሽም ሆነ በባለብዙ ወገን ግንኙነቶች የሚደርሱባቸው ስምምነቶች ከበርካታ ድርድሮች በኋላ የሚገኙ ናቸው፡፡ በንግድ ዓለም ውስጥ ደግሞ በነጋዴና በሸማች መካከል የሚደረገው የዋጋ ውጣ ውረድ የድርድር አካል ነው፡፡ ድርድር የሕይወታችን ዋነኛ ክፍል ከሆነ ልዩነቶችን በድርድሮች መፍታት ለምን ያቅታል? በአገር የጋራ ጉዳይ ላይ መቼም ቢሆን ልዩነቶች ይኖራሉ፡፡ ልዩነቶችን እያጦዙ አላስፈላጊ ውዝግቦች ውስጥ ከመግባት ይልቅ በድርድር ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ውጤት ማግኘት እየተቻለ፣ ጭፍን ጥላቻ በመፍጠር ለክፉ መፈላለግ የአገራችን ፖለቲከኞች መለያ ከሆነ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

  እጅግ በጣም የተከበረው ሕዝባችን ውስጥ ግን የዘር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የአመለካከት፣ ወዘተ. ልዩነቶች ቢኖሩም መኖራቸው እስካይታወቅ ድረስ በሰላም ተከባብሮ የመኖር ትልቅ ተምሳሌታዊ እሴት አለ፡፡ ልዩነትን ከማቀንቀን ይልቅ ተጋብቶና ተዋልዶ ለዘመናት አብሮ መኖር የቻለው ይህ ኩሩ ሕዝብ ለእናት አገሩ ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ፣ ልዩነት አለኝ ብሎ እርስ በርሱ ሲጣላ ወይም ሲጋጭ ታይቶ አይታወቅም፡፡ አልፎ አልፎ በአንዳንድ ሥፍራዎች መጠነኛ የግጭት አጋጣሚዎች ቢኖሩ እንኳ እዚህ ግባ የማይባል ዓላማ ባላቸው ቡድኖች የሚፈጠሩ ጊዜያዊ ግርግሮች ናቸው፡፡ አንዱ ወገን የሌላውን አክብሮ በሰላም መኖሩና ከዚያም አልፎ ተርፎ የተዋለደው በአርቆ አሳቢነት ላይ የተመሠረተ የጋራ መግባባት መፍጠር በመቻሉ ነው፡፡ ይህ በቃላት ባይገለጽም የምርጥ ድርድር ማሳያ ነው፡፡

  የንግድ ሰዎች የየዕለቱ ግንኙነት በድርድር የተሞላ ነው፡፡ አገሮች ሁሌም ግንኙነታቸው በድርድር ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ ድርድር ማለት በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ በመመሥረት ልዩነትን የሚያጠቡበት ወይም የሚፈቱበት ዘዴ ነው፡፡ ሕዝባችን በዓላትን ሲያከብርም ሆነ የተለያዩ ሥነ ሥርዓቶችን ሲያከናውን አንዱ ሌላውን እንዳያስቀይም ወይም እንዳያስከፋ ተጠንቅቆ ነው፡፡ ድግስ ሲኖር እንኳ ያዘጋጀሁትን ብቻ ብላ አይባልም፡፡ ይልቁንም የአንድ እምነት ተከታይ ሲደግስ ለሌሎች የእምነት ተከታዮች የሚፈልጉትን አዘጋጅቶ ነው፡፡ ይህ በዘመናት ሒደት ውስጥ ሲንከባለል እዚህ የደረሰ ፀጋ ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን ከፍተኛ ተምሳሌት ያለው ፀጋ ከበዓላትና ከድግሶች በላይ በየዕለት ሕይወት ውስጥ ማየት ይቻላል፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ ተምሳሌታዊ እሴት ትምህርት በመውሰድ፣ በፖለቲካው ውስጥ የሚታየውን የዓመታት በሽታ ለማከም አለመቻል ጤና ማጣትን ነው የሚያሳየው፡፡

  ይህ የተከበረ ሕዝብ በአግባቡ የሚመራው ካገኘ ተዓምር መሥራት ይቻላል፡፡ ከዚህ በፊትም አሳይቷል፡፡ ታላቁና ዝነኛው ፀረ ኮሎኒያሊስት ድል በዓደዋ ተራራዎች ላይ ተገኝቶ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች መመኪያ ሊሆን የቻለው፣ በዚህ ኩሩና ድንቅ ሕዝብ ተጋድሎ ነው፡፡ የፓን አፍሪካኒዝም መሠረት የተጣለው ከዓደዋ ድል በኋላ ነው፡፡ አፍሪካውያን የጋራ መሰባሰቢያቸው የሆነውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አሁን የአፍሪካ ኅብረት የሚባለውን ያገኙት በዚህ ቆራጥና ጀግና ሕዝብ ተጋድሎ ምክንያት ነው፡፡ በዘመነ መሳፍንትም ሆነ በተለያዩ ጊዜያት ገዥዎች በደል ቢያደርሱበትም፣ እርስ በርሱ እየተከባበረ ኢትዮጵያችንን እዚህ ያደረሰው ይህ ምሥጉን ሕዝብ ነው፡፡ ይህንን ታላቅና ጨዋ ሕዝብ ለመምራት ትልቅ ሰብዕና ያስፈልጋል፡፡ ከጥላቻና ከመጠፋፋት ፖለቲካ ወጥቶ በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደር የሚችል ፖለቲካዊ ጥበብ የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡ በጥላቻና በክፋት የተዋጠ ፖለቲካ ለዚህ ኩሩ ሕዝብ አይመጥንም፡፡

  ሕዝብ መከበር አለበት፡፡ ሕዝብ የአገሪቱ የመጨረሻው የሥልጣን ባለቤት ነው፡፡ ሕዝብን ለመምራት ዴሞክራት መሆን፣ ከሙስና መራቅ፣ የዕውቀትና የክህሎት ባለቤት መሆን፣ ከተናጋሪነት ባልተናነሰ አዳማጭ መሆን፣ ከሴረኝነት መላቀቅ፣ አገርን መውደድ፣ ባለራዕይ መሆን፣ ለሕግ የበላይነት መታገል፣ ሕገወጥነትን ማስወገድ፣ ለብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም ማንኛውንም መስዋዕትነት መክፈል፣ ከአገር ጠላት ጋር በምንም ዓይነት ሁኔታ አለመተባበር፣ የአገርን ሚስጥር መጠበቅ፣ ወዘተ. ከብዙ በጥቂቱ ይወሳሉ፡፡ በዚህ ዓይነት ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለበት መርህ የሚሠሩ ፖለቲከኞች (ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚዎች) በጠላትነት ከመተያየት አባዜ ውስጥ ወጥተው ለውይይት፣ ለክርክርና ለድርድር በቂ ጊዜ ቢሰጡ ለአገር ጠቃሚ ነው፡፡ አንዱ ሌላውን እየወነጀለ ለመደራደር አለመፈለግ ጊዜ ያለፈበት ኋላቀር ድርጊት ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሴራ ከመጎንጎንና ድክመትን ከመሸፋፈን በመውጣት ሕዝብን ማሳመን አለባቸው እንጂ፣ በተለመደው ትርምኪ ምርኪ ምክንያት መናጀሳቸው ሊቆም ይገባል፡፡ ይህ የሠለጠነ ዘመን የራሱ ብቁ ትውልድ ስላለው ማንንም ማታለል አይቻልም፡፡

  በአጠቃላይ ከአንድ ኢትዮጵያዊ ኩሩ ዜጋ ጀምሮ አገርና የፖለቲካ ፓርቲ የሚመሩ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ድረስ ትልቁ ምሥል መሆን ያለበት ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ጠባቦች ወይም በትምክህት የተወጠሩ ቡድኖች እንደሚፈልጉት የጽንፈኞች መራኮቻ ሳይሆን፣ አገራቸውን በከፍተኛ ስሜት የሚወዱ ዜጎች መገለጫ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሁሉም ዜጎቿ በእኩልነት የሚስተናገዱባት፣ በነፃነት የሚኖሩባት፣ ከበረከቷ እኩል የሚቋደሱባት፣ ማንም ማንንም ሳይንቅ በፍቅር የሚኖሩባትና የሁሉም የጋራ እናት እንድትሆን ከአጓጉል ጭቅጭቅና ንትርክ በመውጣት ለድርድር ቅድሚያ ይሰጥ፡፡ ኢትዮጵያችን ሥልጣንንና እሱ የሚያስገኘውን ሀብት ለመሻማት የሚራኮቱ ብኩኖችን ሳይሆን፣ ለዕድገቷና ለብልፅግናዋ የሚተጉ ልጆቿን ትፈልጋለች፡፡ ስለዚህም ልዩነቶችን ከማጦዝ ይልቅ ድርድር ተቀዳሚ የአገር አጀንዳ ይሁን!               

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  የአውሮፓ ኅብረት ተወካይ በተመድ ጉባዔ ‹‹የትግራይ መንግሥት›› በማለት ላደረጉት ንግግር ማስተካከያ እንዲደረግ ኢትዮጵያ ጠየቀች

  በስዊዘርላንድ ጄኔቭ እየተካሄደ በሚገኘው 51ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...

  በ15 ቢሊዮን ብር የተመዘገበ ካፒታል የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቱን ያሻገረው ስንቄ ባንክ ሥራ ጀመረ

  ከማክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ወደ ባንክ አገልግሎት ከተሸጋገሩ አምስት የማክሮ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ ሕግና ሥርዓት ይከበር!

  በኢትዮጵያ ምድር ጦርነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ፊትን ወደ ልማት ለማዞር ያለው ፍላጎት አሁንም ፈተና እየገጠመው ነው፡፡ ኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት ሲብት በሙሉ...

  የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ አይሁን!

  በጥቂቶች ስግብግብነት ብዙኃኑ ሕዝብ እንዳይጎዳ ተገቢ ሞራላዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ድጋፍ መስጠት ይገባል፡፡ ሰሞኑን መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሱር ታክስና ኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ፣...

  የኢኮኖሚው ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይሆን!

  ጦርነት ውስጥ ያለች አገር ኢኮኖሚ ጤንነት እንደማይሰማው ለማንም ግልጽ ቢሆንም፣ ከጦርነቱ በተጨማሪ በየዕለቱ ገበያው ውስጥ የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ግን አስደንጋጭ እየሆነ ነው፡፡ የብር የመግዛት...