Wednesday, March 22, 2023

ናይል በሚዲያዎች ዕይታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹እ.ኤ.አ. በ2040 በውኃ እጦት የሚሰቃዩ አሥር ተቀዳሚ አገሮች የትኞቹ ናቸው?››

ጋዜጠኛና ጸሐፊው ዳንኤል ካሊናኪ ይህን ጥያቄ ያቀረበው ናይል ቤዚን ኢንሺየቲቭ (ኤንቢአይ) እ.ኤ.አ. ከታኅሳስ 12 እስከ 16 ቀን 2016 በሩዋንዳ ኪጋሊ አዘጋጅቶት ለነበረው ክልላዊ የሚዲያ ሥልጠና ተሳታፊዎች ነው፡፡ ከኤርትራ በስተቀር የኢንሺየቲቩ አባል አገሮችን የወከሉ የሚዲያ ባለሙያዎች በዝርዝሩ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ ያሏቸውን አገሮች መጥቀስ ጀመሩ፡፡ በተለይ የግብፅና የሱዳን ጋዜጠኞች አገሮቻቸው በዝርዝሩ ውስጥ እንዳሉ እርግጠኛ የነበሩ ይመስላሉ፡፡ በኋላ ላይ ካሊናኪ ሙሉውን ዝርዝር ሲያቀርብ አንድም አፍሪካዊ አገር በዝርዝሩ አልተካተተም፡፡ ዝርዝሩ ውስጥ ያሉት አገሮች ባህሬን፣ ኩዌት፣ ፍልስጤም፣ ኳታር፣ የተባበሩት የዓረብ ኤምሬቶች፣ እስራኤል፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኦማንና ሊባኖስ ናቸው፡፡

ከዚህ እውነታ በተቃራኒ የናይል ተፋሰስ አገሮች የሚዲያ ውጤቶችን በግርድፉ ያየ ሰው፣ በውኃ እጥረትና የናይል ውኃን በጋራ ለመጠቀም ስምምነት ባለመኖሩ የተነሳ አገሮቹ ወደ ጦርነት የማምራት ዕድላቸው ሰፊ እንደሆነ እንዲያስብ ሊገደድ ይችላል፡፡

ለዳንኤል ካሊናኪ ይህ የእውነታና የምልከታ ልዩነት መነሻ የናይል ጉዳይን ከመጠን ያለፈ የፖለቲካ ጉዳይ አድርጎ ማየትና አሉታዊ የሚዲያ ዘገባዎች ናቸው፡፡ ካሊናኪ በእነዚህ ዘገባዎች ግጭት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ የጠቆመ ሲሆን፣ ከኤክስፐርቶች ይልቅ በርካታ ባለሥልጣናት ሽፋን እንደሚያገኙ፣ የመንጋነት ባህሪ እንደሚስተጋባ፣ እነዚህ ሚዲያዎች ወገንተኝነት የሚንፀባረቅባቸውና እውነታውን በሚያጣምሙ ጋዜጠኞች እንደሚመሩ አስገንዝቧል፡፡

በካርቱም ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር አታ ባታይኒ ከዳንኤል ካሊናኪ ጋር ተመሳሳይ የሆነ አቋም አላቸው፡፡ በቅርቡ በሱዳን ዋድ መዳኒ በናይል ላይ ተደርጎ በነበረ ዓውደ ጥናት እንደገለጹት፣ የናይል ጉዳይ ከመጠን ባለፈ የፖለቲካ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ዶ/ር ባይታኒ፣ ‹‹ተመራማሪዎችና ምሁራን የፖለቲካ መደቡ በናይል ላይ ያለው ግንዛቤ እንዲሰፋ ማገዝ ይችላሉ፡፡ በበርካታ አገሮች የአመራር ክፍተት አለ፡፡ ዋነኛው ትኩረት የፖለቲካ መሪነትን ማስቀጠልና የአጭር ጊዜ ጥቅም ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውኃና መሬት ሀብት ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ጌጤ ዘለቀም በተመሳሳይ፣ ‹‹በተለመደው መንገድ መቀጠል አንችልም፡፡ የሳይንስ ማኅበረሰቡ በመውጣት የተሻሉ መንገዶችን ለፖለቲከኞቹ መንገር አለበት፤›› ብለዋል፡፡

በናይል ላይ የሚደረገው የሐሳብ ልውውጥ በፖለቲካው መደብ የበላይነት መካሄዱ የራሱ ችግር እንዳለው የገለጹት የምሥራቃዊ ናይል ቀጣና የቴክኒክ ጽሕፈት ቤት የማኅበራዊ ልማትና ኮሙዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ውባለም ፈቃደ፣ ‹‹የእኛ ጥረት በናይል ላይ የሚደረገውን የሐሳብ ልውውጥ በዋነኝነት ወይም በብቸኝነት የፖለቲካ ወይም የደኅንነት ችግር አድርጎ ከማየት የተፈጥሮ ሀብት ማኔጅመንት ችግር አድርጎ ወደማየት ማሻገር ነው፡፡ ጉዳዩ ከመጠን በላይ የፖለቲካ ገጽታ ሲላበስ ትክክለኛ መረጃ መጣመሙ አይቀርም፡፡ የፖለቲከኞችን መረጃ መሞገትና ስህተት ሲሆን ማስተካከል የብልህ ጋዜጠኛ ግዴታ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ለአንዳንዶች የናይልን ጉዳይ የፖለቲካ ወይም የደኅንነት ጉዳይ አድርጎ ማየት ለጉዳዩ ተገቢ የሆኑ አካላትን ከውሳኔ አሰጣጥ ሒደቱ ያገላል፡፡ በስቶኮልም ዓለም አቀፍ የውኃ ኢንስቲትዩት የድንበር ተሻጋሪ ውኃ ማኔጅመንት ክፍል ፕሮግራም ማናጀር ዶ/ር አና ካስካዎ ከእነዚህ አስተያየት ሰጪዎች የሚካተቱ ናቸው፡፡ ዶ/ር ካስካዎ፣ ‹‹የናይል ጉዳይ የፖለቲካ ጉዳይም መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ነገር ግን ከዚህ የባሰው ጉዳይ የደኅንነት ጉዳይ ተደርጎ መካለሉ ነው፡፡ ይኼ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ምክንያቱም በውሳኔ አሰጣጡ ሊሳተፉ የሚገባቸውን አካላት ይቀንሳል፤›› ብለዋል፡፡

በግብፅ የካይሮ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስና የፖለቲካ ሳይንስ ፋኩልቲ ሌክቸረር ዶ/ር ራውያ ቶፊቅ ግን በዚህ ግምገማ አይስማሙም፡፡ ዶ/ር ቶፊቅ፣ ‹‹የናይልን ጉዳይ የፖለቲካ ጉዳይ አድርጎ በማየትና የቴክኒክ ጉዳይ በማድረግ መካከል ግልጽ ልዩነትን ሁሌም ማግኘት አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡ ዶክተሯ መንግሥታት በተፈጥሯቸው እንደ ሁኔታው በፖለቲካ ወይም በቴክኒክ ጉዳዮች ሊሳተፉ ከሚችሉ ተቋማትና ግለሰቦች እንደሚዋቀሩም አስታውሰዋል፡፡ ‹‹አንዳንዶች የትብብር አጀንዳው ላይ ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት ይኖራቸዋል፡፡ ሌሎቹ ግን ያን ያህል ጉጉት ላይኖራቸው ይችላል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

ይሁንና ተፋሰሱን የሚገጥመው ችግር ናይልን የፖለቲካ ወይም የደኅንነት ችግር አድርጎ በማየት የተገደበ አይደለም፡፡ እንደ የውኃ ፍላጎት ማደግ፣ የሕዝብ ብዛት መመንደግ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ያሉ ችግሮች የናይልን ህልውና ጭምር እየተፈታተኑ ስለመሆኑ የተፋሰሱ ውሳኔ ሰጪዎችና ነዋሪዎች በቂ ትኩረት አለመስጠታቸው፣ እንደ ኤንቢአይ ያሉ ክልላዊ ተቋማትን እያስጨነቀ ይገኛል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1999 ከተቋቋመ ጀምሮ ኤንቢአይ ከሚዲያ ጋር በቅርበት ይሠራል፡፡ የኪጋሊው የሚዲያ ሥልጠናም ኤንቢአይ ሚዲያው ይህን ችግር ተገንዝቦ ለተከታዮቹ ይህንኑ እንዲያሰራጭ ለማንቀሳቀስ የወሰደው የቅርብ ጥረት አካል ነው፡፡

ቁጥራቸው እያደገ ያለና አሳማኝ ማስረጃዎችን የያዙ በርካታ የጥናት ውጤቶች ይህን አደገኛ አዝማሚያ ለመቀልበስ አስቸኳይ የተቀናጀ ዕርምጃ እንደሚያስፈልግ ይደመድማሉ፡፡ በዚህም ሚዲያ ተፋሰሱ በአጭርና በረጅም ጊዜ ሊገጥም ስለሚችለው አደጋ ለሕዝቡ የማስጠንቀቅ ኃላፊነት ተሸክሟል፡፡ ሚዲያው በዚህ ኃላፊነት ለአሁኑ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውልድ ፍላጎት ጭምር መቆም እንዳለበትም ተመልክቷል፡፡ በሥልጠናው ላይ የቀረቡትን ጨምሮ በርካታ ጥናቶች ናይልን እየገጠሙት ያሉት በርካታ ችግሮች እየተባባሱ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የኢንትሮ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ፣ ‹‹የአካባቢ ሥነ ምኅዳሩንና የብዝኃ ሕይወት ሀብቶቻችንን በፍጥነት እያጣን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተጨማሪም እያደገ ከመጣውና ናይልን እየፈተኑ ከመጡ ተግዳሮቶች መካከል ከተሜነትና የኢንዱስትሪ መስፋፋት፣ እንዲሁም የድርቅ ተደጋግሞ መከሰት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በከፊል ሕዝቡን በማስተማር እነዚህን ችግሮች አገሮቹ እንዲቋቋሙ ለማድረግ ሚዲያው ኃላፊነት ወድቆበታል፡፡

የኤንቢአይ ሴክሬታሪያት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢኖሰንት ንታባና (ኢንጂነር) እንደሚገልጹት፣ የአምስት ቀናቱ የሚዲያ ሥልጠና ዓላማ የተፋሰሱ አገሮች ጋዜጠኞች ናይልን እየገጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችና ስላሉት አቅሞችና ተስፋዎች ጥልቅ መረዳት እንዲኖራቸው ማገዝ ነው፡፡ ንታባና ይህ በተፋሰሱ ዘላቂ ትብብርን ለማስፋፋት ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

በቅርቡም ኢንትሮ ለምሥራቃዊ ናይል ጋዜጠኞች ተመሳሳይ ሥልጠና ሰጥቶ ነበር፡፡ አቶ ፈቅአህመድ ኢንትሮ በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበ ቢሆንም፣ እነዚህ እንቅስቃሴዎች ወደ ሕዝቡ እንዲደርሱ በሚፈለገው ደረጃ ሚዲያው ሽፋን አለመስጠቱን ተናግረዋል፡፡

ንታባናም ሆኑ አቶ ፈቅአህመድ በናይል ጉዳይ ተቀዳሚው የሚዲያ ኃላፊነት የአገሮቹን የጋራ ተጠቃሚነት በማውጣት ትብብርን ማስፋፋት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ እስካሁን ኤንቢአይ የናይል ውኃ ሁሉንም አባል አገሮች ተጠቃሚ በሚያደርግበት መንገድና አገሮቹ እርስ በርስ መተማመንና መግባባት እንዲኖራቸው ለማድረግ በርካታ ጥረቶችን አድርጓል፡፡ እነዚህ ጥረቶች ሲደረጉ ዋናው ታሳቢ የተደረገው ነገር የናይል ወንዝ የሁሉም አገሮች የጋራ ንብረት መሆኑ ነው፡፡

‹‹የጋራ ኢንቨስትመንት ፕሮግራሞችን አዘጋጅተናል፣ ድንበር የለሽ ትንታኔ ሠርተናል፣ የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ለመቋቋም የሚያስችሉ ፖሊሲዎችና አሠራሮችን አዘጋጅተናል፣ የነገ ውሳኔ ሰጪ ወጣት ኤክስፐርቶችን በማሠልጠን ስለናይል የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው አድርገናል፣ ኤክስፐርቶችና ፖሊሲ አውጪዎች በበርካታ የቴክኒካዊ ጉዳዮች እንዲመክሩና ለስምምነት መሠረት እንዲጥሉ አድርገናል፣ በናይል ላይ የመረጃና የእውቀት ቋት ገንብተናል፤›› በማለት አቶ ፈቅአህመድ ኢንትሮ ከሠራቸው ውጤታማ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ከፊሉን ዘርዝረዋል፡፡

ንታባና ኤንቢአይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ትብብር ለመፍጠር በሚያደርገው ጥረት ሚዲያ ቁልፍ አጋሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ግንዛቤ ለማሳደግ፣ ትኩረት የሚደረግባቸው አካላትን ተደራሽ ለማድረግና የሕዝቡን አስተያየት ለመቅረጽ ከሚዲያ የተሻለ ሌላ አካል ለማግኘት እንደማይቻልም አስገንዝበዋል፡፡

‹‹ያለሚዲያ እገዛ የናይል ትብብር ግቡን አይመታም፤›› የሚሉት ዶ/ር ውባለም በበኩላቸው፣ ሚዲያው ትብብርን ለማስፋፋት የሚያደርገውን ጥረት በራሱ ወይም ለሌሎች መድረክ በመፍጠር ሊወጣው እንደሚችል አመልክተዋል፡፡ እነዚህ ባለድርሻ አካላት የግል ቢዝነስ ዘርፉ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ሲቪል ማኅበራት፣ ሃይማኖታዊ ተቋማትና መሰል አካላትን እንደሚጨምሩም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

የሱዳን የውኃ ሀብቶች የቴክኒክ ክፍል ኃላፊና የቀድሞ የውኃ ሀብት ሚኒስትር ሰይፈልዲን አብደላ (ፕሮፌሰር) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በናይል ላይ ላለው ትብብር የስኬት ተምሳሌት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ­‹‹ውይይቶችና ድርድሮች በርካታ ጊዜያት መውሰዳቸው እውነት ነው፡፡ ምክንያቱም ከታሪካዊ ጉዳዮች ጋር የተቀላቀሉ በመሆኑ ቀላል አይደለም፡፡ ከባህልና ከፖለቲካ ጋር የሚያያዙ በርካታ ጉዳዮችም ከድርድሩ ጀርባ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን በኤንቢአይ ትብብር አሁን የተሻለ ቁርጠኝነት በማሳየት ላይ በመሆናችን በትክክለኛ የትብብር አቅጣጫ ላይ እንገኛለን፤›› ሲሉ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

ሰይፈልዲን በግድቡ ጉዳይ የሱዳን ዋና ተደራዳሪም ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ግድቡ እንደ ሱዳን ላሉ የታችኛው ተፋሰስ አገሮች በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በሙሉ ስሜትና መተማመን የሚገልጽ ሱዳናዊ ኃላፊ ማግኘት አይቻልም፡፡ ይህ እምነት ከየት እንደመጣ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹የግድቡን ጥቅም ሁሌም የማወሳው ከቴክኒካዊ የኋላ ታሪኬ በመነሳት ነው፡፡ አብዛኞቹን የዓባይ ገባሮችና የኢትዮጵያን ተዳፋት ቦታዎች መርምሬያለሁ፡፡ ከቴክኒክ አንፃር በሦስቱ አገሮች ፍላጎቶች መካከል ተቃርኖ አላየሁም፡፡ እንዲያውም በተቃራኒው እንደሚደጋገፉ አረጋግጫለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ሰይፈልዲን በሙያቸው የግድብ ኢንጂነር ሲሆኑ በሱዳን ግድቦች በተለያዩ ኃላፊነቶች ለበርካታ ዓመታት ሠርተዋል፡፡

የግድቡ ተፅዕኖ ግምገማ ጥናት በሒደት ላይ ይገኛል፡፡ አንዳንዶች የግድቡ ግንባታ በማለቅ ላይ ባለበት በዚህ ወቅት የተፅዕኖ ግምገማ ጥናት ላይ ድርድር የማድረጉ አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ ይህ ጥያቄ ሰይፈልዲን ከጋዜጠኞች ከሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ውስጥ እጅግ የተደጋገመው ነው፡፡

‹‹በዚህ ጉዳይ ላይ ሚዲያው ያለው ግንዛቤና አረዳድ የተሳሳተ ነው፡፡ በግድቡ አካላዊ ቅርፅና እኛ እየተደራደርን ባለበት ጉዳይ መካከል ልዩነት አለ፡፡ የግድቡን ዲዛይን በተመለከተ ተነጋግረን የመፍትሔ ሐሳብም አቅርበናል፡፡ ኢትዮጵያም በቀና ልቦና ሁሉንም የመፍትሔ ሐሳቦች በተግባር ፈጽማለች፡፡ አሁን እየተደራደርን ያለነው በግድቡ የመጀመሪያ ሙሌትና ግድቡ ሥራ ላይ በሚውልበት ሁኔታ ላይ ነው፤›› ሲሉም አብራርተዋል፡፡

የሥልጠናው ተሳታፊ ኤክስፐርቶች በተፋሰሱ አገሮች መካከል አልፎ አልፎ የሚታየው ውጥረት በአብዛኛው የሚነሳው በተሳሳተ መረጃ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ትክክለኛ መረጃ እውቀት በማይኖርበት ወቅት ክፍተቱ በአላዋቂነት፣ በፍራቻ፣ በሐሜትና በመሳሰለው ሊሸፈን እንደሚችልም ጠቅሰዋል፡፡

የማንኛውም ሚዲያ ዋና ሥራ ትክክለኛ፣ እውነተኛና ተጨባጭ መረጃ መስጠት ነው፡፡ በናይል ጉዳይ ላይ የሚሠራ ሚዲያም ከዚህ አንፃር የተለየ ሚና አይኖረውም፡፡ በናይል ጉዳይ ተገቢ የሆነ ድርሻ ያላቸው አካላት ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉና የሚዲያውን አገልግሎት አጥብቀው ይሻሉ፡፡ ነገር ግን የናይል ጉዳይ ካለው ስስና አሳሳቢ ባህሪ አንፃር ሚዲያው ተጨማሪ ኃላፊነት እንዳለበት ይታመናል፡፡ ከዚህ አንፃር በተለይ ብሔራዊ ሚዲያው ስለናይል በቋሚነት ለሕዝቡ መረጃ የመስጠት፣ የማስተማር፣ የማነሳሳትና የማንቀሳቀስ ተጨማሪ ኃላፊነት እንዳለበት አቶ ፈቅአህመድ ይከራከራሉ፡፡ ዶ/ር ውባለምም በተመሳሳይ የናይል ጉዳይን ሳይንስንና ተጨባጭ ኩነቶችን ተመሥርቶ ለመጻፍ ሚዲያው ተጨማሪ ጥረቶችን ሊያደርግ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የኋላ ታሪክና ምርመራ ማድረግ ተፈላጊ ባህሪ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ውባለም ገለጻ ሚዲያው የሕዝብ ድጋፍን በማንቀሳቀስ፣ የሕዝቡን አመለካከትና አስተያየት በመቅረጽ አዋቂ፣ ብሩህና ደፋር መሪዎችን ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡ በተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የተፋሰሱ አገሮች አንፃራዊ ተጠቃሚነትን በማጉላት ትብብር የመፍጠር ሚናም ሊኖረው እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ የተለያዩ የናይል ባለድርሻ አካላትን በማገናኘት ድልድይ ሆኖ ሊሠራ እንደሚችልም አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ይሁንና ይህንን የማስተማር ሚና በአብዛኛው ሚዲያው አይወጣውም፤›› ሲሉ ዶ/ር ውባለም ምልከታቸውን አካፍለዋል፡፡

ከዚህ በተቃራኒ ሚዲያው አሉታዊ ሚና ሊጫወት እንደሚችልም ተመልክቷል፡፡ ዶ/ር ውባለም፣ ‹‹ጠባብ በመሆን፣ ልዩነቶች፣ የማይቻሉ ጉዳዮችና ቅሬታዎች ላይ በማተኮር›› ይህን አሉታዊ ሚና ሚዲያው ሲጫወተው ማየት አዲስ ነገር እንዳልሆነ ይከራከራሉ፡፡

የናይልን ጉዳይ በተመለከተ በተለይ ዓለም አቀፍ ሚዲያው ግጭት ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል፡፡ ‹‹ጎጂ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡ ኤንቢአይ ከተቋቋመ ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ነገር ግን እነዚህን ስኬቶች የሚሸፍን ኃላፊነት የሚሰማው ዓለም አቀፍ ሚዲያ ማየት አልተቻለም፡፡ ዓለም አቀፍ ሚዲያው የተለየ አጀንዳ ሊኖረው ይችላል፡፡ ምናልባትም እንደ ክልላዊ አልያም ብሔራዊ ሚዲያ ኃላፊነት ላይሰማቸው ይችላል፡፡ አሳዛኙ ነገር ክልላዊና ብሔራዊ ሚዲያውም ግጭት ላይ ሲያተኩር ነው የሚታየው፤›› በማለት ዶ/ር ውባለም የዓለም አቀፍ ሚዲያው ተፅዕኖ ወደ ሌሎች ሚዲያዎች መተላለፉን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በአብዛኛው ዓለም አቀፍ ሚዲያው የናይል ጉዳይን ስሜት ቀስቃሽ ጉዳይ አድርጎ የሚያቀርበው ሲሆን፣ ውስብስቡን የናይል ጉዳይ ከግጭትና ከቀውስ ጋር ብቻ አስተሳስሮ ሲስለው ይስተዋላል፤›› በማለት አቶ ፈቅአህመድ በተመሳሳይ ያክላሉ፡፡

በሌላ በኩል የናይል ጉዳይን የሚሸፍኑ የሚዲያ ተቋማት በብሔራዊ ጥቅም ስም ገለልተኝነታቸውን እያጡ እንደሆነ የሚያስጠነቅቁም አሉ፡፡ በግብፅ ሚኑፊያ ዩኒቨርሲቲ የሶሲዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር ሞሐመድ ሞሄይድን፣ ‹‹ሚዲያውን በንቃት ነው የምከታተለው፡፡ ከልምድ እንዳየነው የናይል ተፋሰስ አገሮች የሚዲያ ተቋማት ለሕዝቡ የሚሰጡት መንግሥት ሕዝቡ እንዲያውቅ የሚፈልገውን ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ ዋና ዓላማቸውም ሕዝቡን ወደ አንድ የተወሰነ አቅጣጫ እንዲያስብ ማድረግ ነው፡፡ ተመራጩ መንገድ ግን የሚዲያ ሚና የመንግሥት ይፋዊ መረጃን እንዲሞግትና እንዲጠይቅ ይጠብቃል፤›› ብለዋል፡፡ ንታባና ግን ሚዲያው የኤንቢአይን የትብብር አጀንዳ ለማስፈጸም በአጋርነት ሲንቀሳቀስ የሙያ ደረጃውንና ሥነ ምግባሩን ሳይቀንስ እንዲሆን ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

‹‹ብሔራዊና ክልላዊ ሚዲያ ሕዝቡን የማስተማር የተለየ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ከናይል ዓውድ አንፃር ገንቢ ጋዜጠኝነት ማለት ጥያቄ የማይቀርብባቸውንና በሳይንስ የተረጋገጡ የናይል አደጋዎችን ለሕዝቡ ማስተማር ማለት ነው፡፡ ይኼ ከወገንተኝነት ጋር አይገናኝም፡፡ ሕዝባዊ አገልግሎት ነው፤›› በማለት ዶ/ር ውባለም ይሞግታሉ፡፡

አቶ ፈቅአህመድ ሚዲያው የናይል ጉዳይን ከውኃ ጉዳይ ጋር ብቻ አቆራኝቶ እንደሚያይም ተችተዋል፡፡ ዶ/ር ውባለም በዚህ ይስማማሉ፡፡ ‹‹ናይል ውኃ ብቻ ማለት አይደለም፡፡ ሕይወት የሚደግፍ ሥርዓት ነው፡፡ ናይል ማለት ምግብ፣ ኢነርጂ፣ ኃይል፣ የውኃ ትራንስፖርት፣ ጂኦፖሊቲክስ፣ የዱር እንስሳት፣ ባህልና ሌላ ሌላም ነገር ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የተወሰኑ የሚዲያ ባለሙያዎች በ‹‹ናይል ጉዳዮች›› ላይ ስፔሻሊስት መሆን እንዳለባቸው ዶ/ር ውባለም ገልጸዋል፡፡

የሚዲያ ባለሙያዎች ያልዳሰሷቸውና ያልደረሱባቸው በርካታ የናይል ጉዳዮች እንዳሉም አቶ ፈቅአህመድ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ጂኦፖለቲካዊ፣ ጂኦስትራቴጂካዊ፣ ከሕግ ጋር የተያያዙ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና መሰል የናይል ጉዳዮችን ሌሎች ወገኖችን ሳያስቀይም ሚዲያው ሊጽፍና ሊያስተምር ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

ኤንቢአይ/ኢንትሮ ናይልን በተመለከተ ላለው መረጃና እውቀት ዋነኛው ማዕከል ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡ ሚዲያው በናይል ጉዳይ የተሻለ ግንዛቤና እውቀት እንዲኖረው ሥልጠና ከመስጠት ባሻገር፣ በናይል ጉዳይ የላቀ ዘገባ ላቀረቡ ጋዜጠኞች በየሁለት ዓመቱ የሚሸልምበት የናይል ሚዲያ ሽልማት ፕሮግራምንም እ.ኤ.አ. በ2015 ጀምሯል፡፡                          

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -