Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየገና መልዕክት

የገና መልዕክት

ቀን:

የዘንድሮውን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ምክንያት በማድረግ የሃይማኖት አባቶች ካስተላለፉት መልዕክቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ዕለት ከወደላይ የተላለፈው ዓቢይ መልዕክት ሰላምና በረከት በምድር ላይ ሆነ የሚል እንደሆነ ማስተዋል አለብን፡፡

በዓለ ልደተ ክርስቶስ የበረከት ቀን ከመሆኑም ሌላ የዕርቅ፣ የእኩልነትና የአንድነት በዓልም ነው፡፡ ከብዙ ጊዜ መለያየትና መራራቅ በኋላ፣ ፈጣሪ የሰዎችን ሥጋ አካሉ አድርጎ በሰዎች መካከል በአካል መገኘት ከዕርቅ ሁሉ የበለጠ ዕርቅ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ በዕለተ ልደተ ክርስቶስ መላዕክትና ሰዎች ፈጣሪያቸው በተወለደበት ዙሪያ ተሰባስበው በእኩልነትና በአንድነት ሲዘምሩና ሲያመሰግኑ ማየትና መስማትም የፍጡራንን እኩልነትና አንድነት ያረጋገጠ ሌላው ክስተት ነበር፡፡ ሰማያውያንና ምድራውያን ለሰው ልጅ ህልውና ወሳኝ የሆነውን ‹‹ሰላም በምድር ይሁን›› እያሉ በአንድ ቃል መዘመራቸውም ለሰማያውያኑም ሆነ ለምድራውያኑ ከሰላም የበለጠ ትልቅ ጸጋ የሌለ መሆኑ የሚያስገነዝብ ነበር፡፡

ከዚህም ጋር ‹‹የሺሕ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ›› እንደሚባለው የሁሉም ማሰሪያ ስለሆነ የድሮ ነጋዴ ለንግድ ሲወጣ ስንቁን በትከሻው ተሸክሞ እንደሚጓዝ ሁሉ፣ ዛሬም የልማት ነጋዴ ሕዝባችን ሰላምን በልቡ ቋጥሮ መጓዝ  ይኖርበታል፡፡

ሁሉም ችግሮች ከሰላም በታች መሆናቸውን ሁሉም ማኅበረሰባችን መገንዘብ አለበት፤ ሁሉም ለአንድነት፣ ለእኩልነት፣ ለፍትሕ፣ ለወንድማማችነት፣ ለመተማመንና ለመከባበር መስፈን የማያወላውል አቋም ሊይዝ ይገባል፡፡

የቀደሙት አባቶቻችን ኢትዮጵያን ታላቅ አገር እንድትሆን ያበቋት አንድነታቸውን ጠብቀው በጋራ ስለሠሩ ነው፤ ያለ አንድነት ታላቅነትም፣ ኃያልነትም፣ ልማትና ዕድገትም ፈጽሞ እንደማይገኝ ሳይታለም የተፈታ ነውና ሕዝባችን ይህንን በውል ማጤን ይኖርበታል፡፡

ነገረ ሕይወት ከተሰበከባቸው የዓለማችን አገሮች ኢትዮጵያ ቀዳማዊ አገር እንደመሆኗ መጠን፣ በእግዚአብሔር ከተሰጣት የቅድሚያ ኃላፊነት አንፃር በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ሁሉ፣ እንደ ድሮው ደማቁ የአንድነት ታሪኳና ተደናቂው ሥልጣኔዋ፣ እንደዚሁም ጽኑ ሰላምዋና ልማቷ ጠብቃ በማስጠበቅ አስተማሪነትዋ ጎልቶ እንዲወጣ ‹‹ችግሮች ሁሉ ከሰላም በታች ናቸው›› የሚለውን ጠንካራ የሰላም አስተሳሰብ መርሕ በማድረግ ሁሉም በአንድነት፣ በኃላፊነት፣ በቅንነትና በተቆርቋሪነት አገሩን እንዲጠብቅና እንዲያለማ መልዕክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

  • ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

***********

ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም በበረት ውስጥ መወለዱን ስናከብር እናቶችንና ሕፃናትን በማስታወስ ሊሆን ይገባል፡፡ የወለዱ እናቶችን እንኳን ማርያም ማረቻችሁ በማለትና የተወለዱትንም ሕፃናት እንኳን ተወለዳችሁ፣ እንኳንም በሰላም ወደዚች ምድር መጣችሁ በማለት ልንቀበላቸውና ልንከባከባቸው ይገባል፡፡ የሕፃናት መብት ይከበር፡፡ ከሁሉ በላይ ሕፃናት የሚሹት ፍቅርን ነውና እናፍቅራቸው፡፡ የልደት በዓል የቤተሰብ በዓል ነውና “ኢየሱስ፣ ማርያምና ዮሴፍ  ቤተሰቦቻችንን ባርኩልን ብለን እንጸልይ፡፡”

በአሁኑ ጊዜ መንግሥት፣ ኢትዮጵያ ሀገራችንን በበቂና በተሻለ ሁኔታ ለማስተዳደር  በተያያዘው የተሐድሶ ጉዞ የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን በማየት ላይ እንገኛለን፡፡ ይህንንም ማስፈጸም እንዲችሉ ለተለያዩ ኃላፊነቶች የተመረጡ ሰዎች እንደተመደቡ ይታወቃል፡፡ በእኛ እምነት የእነርሱ ለዚህ ታላቅ ኃላፊነት መመረጥ በክብር ከፍ ለማለት ሳይሆን፣ የሕዝቦችን ጥያቄዎችን በተገቢው ሁኔታ መልስ ለመስጠትና ለማስተዳደር መሆኑ እናምናለን፡፡ ስለሆነም ሁላችንም በመልካም አስተዳደር ፍትሐዊ የሆነ ሥራዎችንና ውጤቶችን እንደምንጠብቀውና እንደምንመኘው ለተግባራዊነቱ በትኩረት እንደሚሠሩና እንደሚያስፈጽሙ ታላቅ እምነት አለን፡፡

በማያያዝም መንግሥት አሁን ወደታች በመውረድ የኅብረተሰቡን ችግሮች ለማስተካከልና ለመቅረፍ በሚያደርገው ውይይት ሰምቶ ዝም ብሎ ማለፍ ከሆነ አመርቂ ውጤት ሊገኝ ስለማይችል፣ በቁርጠኝነት የተነሳበትን ዓላማና ለሕዝቡ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም በመተማመን ነው፡፡ የሰላሙ ንጉሥ ሰላሙን ለምንወዳት ለአገራችን ለኢትዮጵያና ለሁላችን እንዲሰጠን እንጸልይ፡፡

  • ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ፣ ሊቀጳጳሳት ዘካቶሊካውያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚደንት፣ የምሥራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት ሊቀመንበር

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...