Monday, March 20, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየገና ዛፍ - ‹‹የሕይወት ዛፍ››

የገና ዛፍ – ‹‹የሕይወት ዛፍ››

ቀን:

‹‹ከደነቶ እሙ ቈጽለ በለሶን›› [እናቱ የበለሶን ቅጠል አለበሰችው]

አብዛኛውን ጊዜ ሲነገር እንደሚሰማው የገና ዛፍ ልማድ ባዕድና ምዕራባዊ ምንጭ እንደሆነ ተደርጎ ነው፡፡ ነገር ግን በብሪቲሽ ሙዚየም ውስጥ የሚገኘው የ13ኛው ምታመት ብራና (መጽሐፍ) እንደሚያስረዳው፣ በ512 ዓ.ም. የነበረው የሶሪያ ንጉሠ ነገሥት አናስታሲዮስ ቀዳማዊ በሰሜናዊቷ ሶሪያ በቱር አብዲ ከተማ፣ የቅዱስ ገብርኤል ገዳምን ባሠራበት ጊዜ ካቀረባቸው መባዎች አንዱ ዛፍ ነበር፡፡

‹‹. . . ሁለት ትላልቅ ዛፎች በተዋበው የመቅደሱ ግራና ቀኝ እንዲቆሙ አደረገ፡፡ በቅርንጫፎቹም ላይ የብርሃን ምልክቶች ተደረጉ፡፡ እንያንዳንዱ ዛፍ አንድ መቶ ሰማንያ ትናንሽ አምፑሎችና ሐምሳ የብር ጌጦች ከላይ እስከታች ተጌጡ፡፡ መስቀሎች፣ ወርቅ፣ ብር ወይም መዳብ እንዲሁም ቀይ እንቁላሎች፣ እንስሳት፣ አዕዋፋት፣ ደወል. . . የዛፉ አካል ሆኑ፡፡››

በግሪክ የተሰሎንቄ አሪስቶትል ዩኒቨርሲቲ የቢዛንታይን አርኪዮሎጂ ፕሮፌሰር የነበሩት ኮንስታንቲን ካሎኪርስ፣ ‹‹Sacred Trees and the Eastern Origin of the Christmas Tree›› በተሰኘው ጥናታቸው እንደሰነዱት፣ በክርስቲያን ቲኦሎጊያና አምልኮ ውስጥ ዛፍ የሚያመለክተው፣ የገነትን ዛፍ (መልካምንና ክፉውን የሚለይ የዕውቀት ዛፍ) ነው፡፡ የተጌጡ ዛፎች (ሞዛይክ ዛፎች) በቀዳሚው ዘመን ኒቆፖሊስ በሚገኘው ቅዱስ ድሜጥሮስ ገዳም፣ በኤጲረስና በተለያዩ ቦታዎችም እንዲሁ ነበሩ፡፡

‹‹በካታኮምቡ በሕይወት ዛፍ (‹‹ዕፀ ሕይወት››) የተመሰለው ክርስቶስ ነው፡፡ ፈኒክስም (የወፍ ዓይነት) በዘላለማዊነት ተመስላለች፡፡ የወይራ ዛፍም የብሉይና ሐዲስ ኪዳኖች ተምሳሌት ሆኗል፡፡››

በመጀመሪያዎቹ የክርስትና አራት ምታመታት፣ የገና በዓል ከጥምቀት ጋር ጃንዋሪ 6 ቀን ይከበር ነበር፡፡ በግሪክ የተለያዩ አካባቢዎች በዓሉ ሲከበር በአብያተ ክርስቲያናቱ መካከለኛ ቦታ በብርቱካን የተጌጡ ሁለት ዛፎችን ያቆሙ ነበር፡፡ ሜትሮፖሊታን ሂሮቴዮስ ቫላኮስ ‹‹The Feasts of the Lord: An Introduction to the 12 Feasts and Orthodox Christology›› በሚለው መጽሐፋቸውም እንዲህ አመሥጥረውታል፡፡ ‹‹የገና ዛፍ፣ የዕውቀት ዛፍን ይበልጡንም የሕይወት ዛፍን እንድናስታውስ ያደርገናል፡፡ ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ጋር ተያይዟልና፤ በዐቢይ ፍሥሐ የምናከብረውም የሕይወት ዛፍ በበረት ከድንግል ማርያም በመወለዱ ነው፡፡››

ከዓመታት በፊት የሶሪያ ኦርቶዶክስ ቅዱስ ኒቆላስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት አባ ዳንኤል ‹‹Christmas Tree … Pagan???- In Defence of the Christmas Tree›› በሚል ርእስ አንድ መጣጥፍ አስነብበው ነበር፡፡ ከበርካታ ዓመታት በፊት በገና ሰሞን በአንድ ቴሌቪዥን ሃይማኖታዊ ፕሮግራም ሲተላለፍ ቀልባቸውን የወሰደው፣ የውይይቱ ርእሰ ጉዳይ ከበዓል ጋር በተያያዘ የአንዳንድ ልማዶች አዝማሚያ በተለይም በወጣቶች ዘንድ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ የሚመለከት ነበር፡፡

አባ ዳንኤል እንዳሉት፣ ተወያዮቹ ‹‹የአዲሱ ዘመን›› (New Age) መንፈሳዊነት አደገኛነትን በተመለከተ ቢስማሙም ከመሃል አንዱ ተወያይ ያነሣው ‹‹… የገና ዛፍም እንዲሁ ከፓጋን (አሕዛብ) የተገኘ ነው፤›› የሚለው ነጥብ አስደንግጧቸዋል፡፡ እውን የገና ዛፍ የፓጋን ነው? ከልጅነታችን ጀምሮ የልደት በዓል በመጣ ቁጥር ስናከብር የምናደርገው የገና ዛፍ መሠረቱ በእርግጥ ከፓጋን ነው? የሚለውን አስተያየት መረመሩና ‹‹ፈጽሞ አይደለም፤ መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፤›› በማለት ማስረጃ እየጠቀሱ እንዲህ ጽፈውታል፡፡

ብዙዎች እንደሚገነዘቡት፣ የገና ዛፍ ወደ አሜሪካ የዘለቀው ከጀርመን በተሰደዱ ዳያስፖራዎች ነው፡፡ ግን የዛፉ ምንጭ ከየት መጣ? ተወያዮቹ እንዳሉት ከፓጋኒዝም ነው? የገና ዛፍ መሠረት ከቀደምት ጀርመኖች አይደለም፤ በጥንታውያን ክርስቲያኖች ትውፊት በሥርዓተ ቅዳሴ ውስጥ የነበረና ከጊዜ በኋላ የደበዘዘ ነው፡፡ በመካከለኛው ዘመን ከቅዳሴ በፊት ወይም በኋላ በምዕራብ አውሮፓ አብያተ ክርስቲያናት ይከናወን ነበር፡፡ በተለይም ከሰሙነ ሕማማትና ትንሣኤ ምስጢር ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ቆይቶም ከታዋቂ ቅዱሳን ጋርም መዛመድ ጀመረ፡፡ በታላላቅ ካቴድራሎች ዐውደ ምሕረት መንፈሳዊ ትርዒቱ (Liturgical dramas) ይቀርብ ነበር፡፡

አንዱ ትርዒት እንደምዕራባዊቷ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት፣ በገና ዋዜማ በሚከበረው የአዳምና ሔዋን በዓል ዕለትም ይቀርብ ነበር፡፡
‹‹የገነት ትርዒት›› (The Paradise play) በገነት ውስጥ በነበረው የአዳምና ሔዋን ታሪክ ላይ የተመሠረተ ነው፤ ይኸው ከገነት ዛፍ፣ ወይም ከዕውቀት ዛፍ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህም የገነት ዛፍ በጀርመናውያን ዘንድ የታወቀና የተለመደ ሆኗል፡፡ በመሠረቱ ዛፎቹ የሚሸበርቁት በብስኩት ሲሆን ቁርባንን የሚያስታውስ ነው፡፡ ቆይቶ ግን ልዩ ልዩ ጣፋጮች ተኩት፡፡

‹‹የእኛ የገና ዛፍ የተገኘው ከፓጋን ‘ጥድ’ (Yule) ዛፍ ሳይሆን በአፕል በተጌጠውና ዲሴምበር 24 ቀን (ታኅሣሥ 28) በአዳምና ሔዋን በዓል ቀን ከሚደረገው የገነት ዛፍ ነው፡፡ የገና ዛፍ መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፤›› በማለት ያለጥርጥር በአጽንዖት ይናገራሉ፡፡

ኢትዮጵያ እና የገና ዛፍ

በኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ጥድን ቆርጠው የገና ዛፍን በማዘጋጀት በዓሉን እያከበሩ ይገኛሉ፡፡ እንደ አውሮፓው ቅኝት ሁሉ፣ እዚህም ከፓጋን (አሕዛብ) ሥርዓት የተወረሰ ነው ብለው የሚያምኑ ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡

የገና ዛፍ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ ሩብ ውስጥ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቤተ መንግሥት እንደነበረ የሰነድ ማስረጃ ቢኖርም ለአገሪቱ መነሻ ነው ብሎ መደምደም ግን ሊያስቸግር ይችላል፡፡

ስለገና ዛፍ መሠረትም ምናልባትም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ውስጥ ካሉ ትውፊቶች ጋር ሊዛመድ የሚችልበት ነገር እንዳለ አንዳንድ ጽሑፎች፣ ድርሳኖች ይጠቁማሉ፡፡ ታላቁ ሊቅ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በ1920ዎቹ በጻፉትና ካለፉ በኋላ በ1948 ዓ.ም. በአለቃ ደስታ ተክለወልድ አማካይነት በታተመው ‹‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› ውስጥ ‹‹በለሶን›› የሚል ቃል እናገኛለን፡፡

‹‹በለሶን፡- ዕፀ አእምሮ [የዕውቀት ዛፍ] የገነት በለስ፤ አዳምና ሔዋን ፍሬውን በልተው ቅጠሉን የለበሱት፣ ኋላም የልደት ዕለት በታምራት መልአክ አምጥቶላት ዳግሚት [ሁለተኛዋ] ሔዋን ለልጇ ለዳግማይ አዳም [ኢየሱስ] ያለበሰችው፤›› በማለት ቃሉን ይፈቱታል፡፡ ከቅዱስ ያሬድ ድጓ (የዜማ መጽሐፍ) የልደት ምንባብ ‹‹ከደነቶ እሙ ቈጽለ በለሶን›› [እናቱ የበለሶን ቅጠል አለበሰችው] በማለትም አክለውበታል፡፡

ስለ በለሶን አንድምታ የአለቃ ኪዳነ ወልድ ‹‹ሥላሴ ቅኔ›› እንዲህ ያፍታታዋል፡፡

‹‹በለሰ ገነት ለአዳም ወሔዋን መቲሮቶሙ

መንክረ ልደት አምላከ መንገሌሆሙ ሰሐበ፤

ወገብርኤልሀ ዜናዌ ቀጸበ፤

እንተ ከመ ዝሰ ግብር እምከመ ለአዳም ተውህበ

ወረከበት ሔዋን ዘኢተረክበ፤

ካዕበ ይስሐብ ኀቤሆሙ አበ

ለበለስ ይምትርዎ ካዕበ፡፡››

የቃል በቃል ፍችውም እንዲህ ነው፡፡ ‹‹የገነትን በለስ አዳምና ሔዋን መቁረጣቸው ወደነርሱ ሳባቸው፣ አስደናቂ የሆነውን የአምላክ መወለድ ወደነርሱ ሳበ፡፡ የምሥራች ነጋሪን ገብርኤልንም የጠቀሰው እርሱ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር ምሥጢር ለአዳም እንደተሰጠ ሔዋንም ያልተገኘውንና ያልተመረመረውን ምሥጢር አገኘች፡፡››

ታላቁ ኢትዮጵያዊ የስድስተኛው ምታመት ታኦሎጎስ (ቲኦሎጂያን) ቅዱስ ያሬድ እንደ አመሠጠረው፣ ‹‹በእንተ ልደቱ ለክርስቶስ አድባር ኮኑ ኅብስተ ሕይወት፤ ወዕፀወ ገዳምኒ ፈረዩ አስካለ በረከት፤ ወማየ ባሕርኒ ኮነት ሐሊበ ወመዓረ፡፡›› ማለትም ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ተራሮች የሕይወት እንጀራ ሆኑ፤ የበረሃ ዛፎችም የበረከት እሸትን አፈሩ፤ የባሕር ውኃም ወተትና ማር ሆነች ይላል፡፡

በምዕራብም ሆነ በምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት እንዳለው ሁሉ፣ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም በአንዳንድ ዐበይት በዓላት እንደ ሆሣዕና፣ ስቅለት፣ ያሉት ከቅዳሴ በኋላ የሚደረጉ ሥርዓቶች አሉ፡፡ አንዱ በበዓለ ስቅለቱ ከስግደት በኋላ የሚደረገው በወይራ ቅጠል ካህኑ፣ ‹‹ይኸን ያህል ስገድ›› እያለ የሚያደርገው ጥብጠባ ይጠቀሳል፡፡ ሊቃውንቱ ስለ በለሶን፣ ስለገና ዛፍ አንድምታ አፍታተው እንደሚገልጹት ይጠበቃል፡፡

የሶርያው ካህን አባ ዳንኤል እንደጻፉት፣ ‹‹ገና ታላቁ ምሥጢረ ሥጋዌ የሚከበርበት ነው፡፡ በዚያም ምሥጢር እግዚአብሔር ቃል፣ ሰው ኾነ (ቃል ሥጋ ኮነ)፡፡ በእኛም ዘንድ አደረ፤›› እንዲል፡፡ አባ ዳንኤል በጽሑፋቸው አያይዘውም፣ ‹‹በገና ዛፋችሁ ተደሰቱ›› ብለው አሳረጉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ዜጎች የተፈተኑበት የኑሮ ውድነት

በኢትዮጵያ በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የኑሮ ውድነት የበርካታ ዜጎችን አቅም...

በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደረጉ ድጋፎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ተጠየቀ

በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደረጉ ድጋፎች ዘላቂነት እንዲኖራቸውና በተቀናጀ መልኩ...

ወደ ኋላ የቀረው የሠራተኞች ደኅንነት አጠባበቅ

በአበበ ፍቅር ለሠራተኞች የሚሰጠው የደኅንነት ትኩረት አናሳ በመሆኑ በርካታ ዜጎች...