Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዘመነኛው የገና ምልክት

ዘመነኛው የገና ምልክት

ቀን:

የገና በዓል ሲቃረብ የደብተር ገጾችን (ያሮጌ ወይም የሚማሩበትን) በምላጭና በመቀስ በተለያየ ቅርጽ እየቀደዱ የገና ዛፍ (ፅድ) ማስዋቢያ ጌጣጌጦችን መሥራት፣ የሲጋራ ብልጭልጭ (ብርማውን የኒያላና ወርቃማውን የሮዝማን) ወረቀቶች፣ የከረሜላ መጠቅለያዎችንም አጠራቅሞ ለፅድ ማስዋቢያነት በመልክ በመልክ መሥራት የብዙዎች የገናና የልጅነት የትምህርት ቤት ትዝታ ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ ገና በትምህርት ቤት በቤትም የሚከበርበት መንገድ በተለይም ከገና ዛፍ ጋር በተያያዘ በብዙ መልኩ ተቀይሯል፡፡ የተቆረጠ የፅድ ዛፍ መንገድ ላይ ሰው ይዞ ወይም መኪና ላይ ተጭኖ አይታይም፡፡ የገና ዛፍ ማስዋቢያዎችን ለመሥራት ተማሪዎች የደብተር ገጾችና የሲጋራ ብልጭልጭ ወረቀቶችን በመቆራረጥ ሲጠመዱም አይገኙም፡፡ ጥድ ላይ ጣል ጣል የሚደረግ ጥጥ ፍለጋም አይገባም፡፡  

ትላንት የተከበረውን የገና በዓል አስመልክቶ የተዘጋጁ መዝናኛ ፕሮግራሞችን ለማስተዋወቅ በየጎዳናው ከተሰቀሉ ማስታወቂያዎች አብዛኞቹ ለጀርባ ሥዕል የተጠቀሙት በተለያዩ ጌጣጌጦች ያሸበረቀ የገና ዛፍ ነው፡፡

የተለያዩ የገበያ ስፍራዎችም በሰው ሠራሽ ገና ዛፎችና ማስዋቢያዎቻቸው አሸብርቀውና ተብለጭልጨው ተስተውለዋል፡፡ ለከርሞ የልደት ማስዋቢያ ቁሳቁሶችን፣ የውበት መጠበቂያ ቅባቶችና ሌሎች መዋቢያዎች በስፋት የሚሸጡበት ቦምብ ተራ፣ በገና ዛፍና በማስዋቢያዎቹ የተጨናነቀው በዓሉ ከመድረሱ 15 ቀናት አስቀድሞ ነበር፡፡ ሆቴሎች የፈረንጆቹን ገናና አዲስ ዓመት አስታከው በየደጃፋቸው የገና ዛፍ ሲያቆሙ፣ ሬስቶራንቶችና ካፌዎች ደግሞ አንዳንዶቹ የገና ዛፍ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ጌጣጌጦችን ብቻ በመጠቀምም ቢሆን ቤቶቻቸውን አስውበው ታይተዋል፡፡

ሞሎች ትላልቅ የገና ዛፎችን በየመግቢያቸው ሲያደርጉ፣ አንዳንድ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ለበዓሉ ድምቀት ሰጥተውት ከርመዋል፡፡ አንዳንድ የገበያ ማዕከላት በተለይም በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ ደጃፋቸው ላይ ባስቀመጧቸው የገና ዛፎች ፉክክር የያዙና ፉክክሩም ከፍተኛ ድምፅ ካላቸው ስፒከሮች በሚለቀቅ ሙዚቃም የታጀበ ይመስላል፡፡ ትንንሽ ልብስ መሸጫዎችና መደብሮች ሁሉ እንደየ አቅማቸው የገና ዛፍ አቁመው አሸብርቀዋል፡፡ ከዚህ ቀደም እምብዛም ባልተስተዋለ መልኩ ቁመታቸው ከ10 ሜትር ያላነሰና ውስጣቸው ክፍት ሆኖ ዙሪያቸው በተለያዩ መብራቶችና ማስዋቢያዎች ያሸበረቀ የገና ዛፍ ከታየባቸው ቦሌ መድሃኔዓለም አካባቢ ማፊ ሲቲ ሞልና በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ዋና በር መግቢያ ይጠቀሳሉ፡፡

እዚያው ቦሌ መድሃኔዓለም አውሎ ቢዝነስ ሴንተር መግቢያ ላይ ከሌሎቹ ለየት ብሎ በደረቅ ሳር በተሠራ ጎጆ ቤት የክርስቶስን ውልደት ለማስታወስ ተሞክሮም ነበር፡፡ በሚሊኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው አዲስ ሾፒንግ ፌስቲቫል ደግሞ ለገበያ የቀረበ በጭድ የተሠራ የከብቶች በረት አስተውለናል፡፡ በረቱ የክርስቶስን መወለድ ከሚያሳይ ሥዕልና በመስቀል ቅርጽ የተሠራ መብራት ያሸበረቀ ነው፡፡ ከበዓሉ በኋላ ቦታ እንዳይዝ ተጣጥፎ መቀመጥም ይችላል፡፡ የገና ዛፍ በሆቴል፣ በንግድ ማዕከላት፣ በሬስቶራንቶችና ካፌዎች እንደታየው ሁሉ፣ የልደት በዓል ካለሱ እንደማይሆን ሁሉ እንደ አንድ የገና አስቤዛ በየገበያ ቦታው ግለሰቦች ሲሸምቱትም ታይቷል፡፡ ከከተማ ዘልቆ በገጠር አንዳንድ አካባቢዎች ገናን ለማስዋብ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ይኸው ዛፍና ማስዋቢያው፣ በብዙ ቦታዎችና በሰዎች ቤትም መታየት የጀመረው ለፈረንጆች ገና በዓሉ ከሚከበርበት ዕለት አስቀድሞ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ገና በዓል አከባበር መገለጫ ያልነበረው የገና ዛፍ፣ ለክርስቶስ ልደት (ገና) ማድመቂያነት መዋል ከጀመረ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ በመጠንም በስፋትም ጎልቶ መታየት የጀመረው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ነው፡፡

ገና ያለ ገና ዛፍ?

ለመጀመሪያ ጊዜ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በጀርመን እንደተሠራ የሚነገርለትን የገና ዛፍ ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ወደ ሌሎች አገሮች እንዲስፋፋ አድርጎታል፡፡ ዛፍን የተለያዩ ቀለማት ባላቸው ጌጣጌጦች ማስዋቡ በዓሉ በሚከበርበት ወቅት ያለውን የአየር ፀባይ አመላካች (winter)፣ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ በረዶም በማይጥልበት፣ አረንጓዴ ተክሎችም መልካቸውን በማይቀይሩበት፣ ቅጠሎች በማይረግፉበትና ከበረዶ ግግሩ የተነሳ ኮፍያ፣ ጓንት፣ ቡትስ(ከጥጥ የተሠራ)  ካፖርት በማይለበስበት በዚህ ወቅትም ቢሆን፣ የገና ዛፍ ከኢትዮጵያም ዘልቋል፡፡ እዚህ እዚያ ጋር ብቻ ተብሎ በማይጠቀስ መልኩ የገና ዛፎች በስፋት ታይተዋል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድንና የሰው ልጆችን ለማዳን መምጣትን የሚያመላክቱ ጌጣጌጦችም ነበሩ፡፡

የገና ዛፍ መጠቀምን ከሉላዊነት ተፅዕኖ አንፃር የሚመለከቱት አሉ፡፡ ባህሉ በኢትዮጵያ ያለውን የልደት በዓል አከባበር እንደማያሳይ በመግለጽ፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ያለው የበዓሉ አከባበር እንዲጎላ የሚያሳስቡም አሉ፡፡ ባለፈው ሳምንት ‹‹ባህልን ከአሉታዊ የሉላዊነት ተፅዕኖ የሚታደግ መፍጠር›› በሚል ርዕስ በተለያየ ሙያ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች መወያያ መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ የባህል፣ የማኅበረሰብ ጥናት፣ የኪነጥበብ፣ የኢኮኖሚና ሌሎችም ባለሙያዎች የታደሙት ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የልደት በዓል አከባበር ማጉላት እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡

የገና ዛፍ ማስጌጫዎች ምን ያህል የኢትዮጵያን ሕዝብ ይገልጻሉ? በሚል የተነሳው ጥያቄ፣ ከአገሪቱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አንፃር ተቃኝቷል፡፡ ኢኮኖሚስት ሰለሞን ገብረሥላሴ፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን ጠቅሰው፣ እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ የገና ዛፍና ተያያዥ መገልገያዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት የወጣውን ወጪ ያስቀምጣሉ፡፡ ከ2011 እስከ 2015 ባሉት ዓመታት በተከታታይ 395,106፣ 425,145፣ 797,388፣ 905,367 እና 930 ሺሕ ዶላር ወጪ ወጥቷል፡፡

ወጪው ከዓመት ወደ ዓመት በእጅጉ መጨመሩን ባለሙያው ገልጸው፣ የገና ዛፍና ሌሎችም የገና ዛፍ ግብዓቶች እንዳይበረታቱ መንግሥት አንዳች ነገር ማድረግ አለበት ይላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ማኅበረሰቡ አገሪቱን ሊገልጹ ለሚችሉ የገና አከባበር ሥርዓቶች ትኩረት እንዲሰጥ ያሳስባሉ፡፡ በእርግጥ ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ በተለያዩ ተቋሞችና በየቤቱ ስላለው የበዓሉ አከባበር ጥያቄ የሚያነሡ ብዙዎች ናቸው፡፡ አንዳንድ ልማዶች ልብ ሳይባሉ ከዓመት ወደ ዓመት እየተስፋፉ መምጣታቸውም ይገለጻል፡፡ ባህላዊ እሴቶችን በማስተዋወቅ ረገድ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋሞች ምን ያህል ሠርተዋል? የሚል ጥያቄም ይሰነዘራል፡፡

የገና በዓል በመጣ ቁጥር ቤታቸውን በገና ዛፍና በተለያዩ ማስዋቢያዎች ማሸብረቅ የሚያስደስታቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ቤት ከፍተኛ ጸሐፊ ወ/ሮ አዜብ አክሎግ፣ የገና በዓልን በገና ዛፍ የማስዋብ ልምዳቸው የተጠነሰሰው ልጅ እያሉ ከወንድማቸው ጋር ፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን ይሄዱ በነበረበት ጊዜ እንደሆነ ያስታውሳሉ፡፡ በወቅቱ እንደዛሬው አርቴፊሻል የገና ዛፍና የተብረቀረቁ ጌጣጌጦች ስላልተስፋፉም፣ ጽድ በመቁረጥ በቤት ውስጥ ከወረቀት የሚሠሩ ጌጣጌጦችንና ጥጥ ለማስዋቢያነት ይጠቀሙ ነበር፡፡ ‹‹ዛሬ ላይ ነገሮች ቀለዋል፡፡ ዛፍም ማስዋቢያውም ከገበያ ይገኛል›› የሚሉት ወ/ሮ አዜብ፣ የገና ዛፍ ለበዓል ቤት ከማድመቂያነት ባለፈ ስላለው ትርጉም እንደማያውቁ ይናገራሉ፡፡ የገና ዛፉን የገዙት የዛሬ ሰባት ዓመት አካባቢ በ100 ብር እንደነበር፣ ዛፉን በአግባቡ በማስቀመጥ በየዓመቱ እንደሚጠቀሙበት በየዓመቱ ግን ለማስዋቢያ የሚሆኑ ጌጣጌጦች እየገዙ እንደሚጨምሩበትም ነግረውናል፡፡ ‹‹በጣም ደስ ይለኛል፡፡ በልጅነቴ አየው የነበረው ገና በመጣ ቁጥር ብዙ ነገር እንዳደርግ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ አሁን ሰው ሰራሽ ዛፍ ብጠቀምም የበለጠ የሚያስደስተኝ የተፈጥሮ የጽድ ዛፍ ብጠቀም ነበር፡፡ ሽታው፣ ብዙ ነገሩ ከአእምሮዬ አይወጣም፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

ከፈረንጆቹ ገና ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ነው ከሳሎን ቤት የገና ዛፍ ያደረገችው፡፡ የቤቱ ጣሪያ ቀረብ ያለ ነው፡፡ ሸብርቆ የቆመው የገና ዛፍ ግን ለረዥም ኮርኒስም ትልቅ የሚባል ነው፡፡ የሁለት ልጆች እናት የሆነችውና በሠላሳዎቹ መጀመሪያ የምትገኘው ወጣት ምንም እንኳ ‹‹ለልጆቹ ብዬ ነው ያደረግኩት›› ብትልም ባለፈች ባገደመች ቁጥር አንድ ነገር ወደዚያ እያደረገች ዛፉን ለማስዋብ የምታደርገው ጥረት ያደረገችው ለልጆቹ ብቻም ሳይሆን ለራሷም ስትል እንደሆነ ይናገራል፡፡

የዛፉ አጋጊያጥ፣ የፖስት ካርድ አደራደሯ ጊዜ ሰጥታ በፍላጎት እንዳደረገችው ምስክር ነው፡፡ እንደ እሷ በልጆች አሳብበው በግልጽም የገና በዓል እንዴት ያለ ገና ዛፍ ይሆናል? በሚል ትኩረት ሰጥተው የገና ዛፍ የሚገዙም ብዙዎች ናቸው፡፡ ስለ ገና ዛፍ አንድምታ በቂ መረዳት ያላቸው፤ ስለ ሉላዊነትና ስለምዕራባዊያን ተፅዕኖም በደንብ የሚያውቁ ብዙዎችም በዓሉ ያለ ገና ዛፍ ገና ገና የሚላቸው አይመስልም፡፡ በቤት ውስጥ በተለይም በሆቴሎችና ሕንፃዎች ከተጌጡና ካሸበረቁ ትልልቅ የገና ዛፎች ጎን ቆምና ቁጭ ብሎ ፎቶግራፍ መነሳትም የብዙዎች ደስታ ይመስላል፡፡ ለዚህ ፌስቡክ ምስክር ሊሆን ይችላል፡፡ መሠረቱና ትርጉሙ ከእኛ ጋር ግንኙነት የለውም ቢባልም እዚህም እዚያም የሚታየው ነገር ገና ያለ ገና ዛፍ እንዴት? እንደተባለ ያሳያል፡፡  

በከተማይቱ በሚገኙ አንዳንድ የገበያ ማዕከላት መግቢያ ላይ ትልልቅ የገና ዛፎች ቆመዋል፡፡ ቤተልሔም አሰፋ ትባላለች፡፡ የሆሊ ኤቨንት ኦርጋናይዘር ማርኬቲንግ ማኔጀር ስትሆን ከማፊ ሲቲ ሞል ፊት ለፊት የቆመው 16 ሜትር ርዝማኔ ያለውን የገና ዛፍ የሠሩት እሷና የሥራ ባልደረቦቿ እንደሆኑ ትናገራለች፡፡ የገበያ ማዕከሉን በተለያዩ ጌጣጌጦችና መብራቶች አስውበውታል፡፡ ከመግቢያው ላይም የገና አባት ቁጭ ብለው ለልጆች የተለያዩ ሥጦታዎች የሚሰጡበትና ፎቶ የሚነሡበትን በበረዶ የተሸፈነ ቦታ አዘጋጅተዋል፡፡

ቦታውን በበረዶ የተሸፈነ ለማስመሰል 30 ኩንታል ጨውና አንድ ኩንታል ስኳር ተጠቅመዋል፡፡ አርቴፊሻል ፅዱን የገዙት ግማሹን ከቻይና ቀሪውን ደግሞ ከመርካቶ ነው፡፡ የዛፉ ላይ የሚሰቀሉትን ጌጣጌጦች ከቻይና ማስመጣታቸውን ቤተልሔም ተናግራለች፡፡ ዕቃዎቹን ለመግዛት አጠቃላይ የወጣው ወጪ 170,000 ብር ሲሆን፣ ዛፉን ለማቆም 10 ቀናት እንደፈጀባቸው ቤተልሔም ትገልጻለች፡፡

ቀናት ፈጅቶ ከፈረንጆቹ ገና በፊት የተጠናቀቀው ዛፉ 9 ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ነው፡፡ ውስጡም ክፍት ሲሆን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበትን በረት ለማስመሰል ተሞክሯል፡፡ የማርያምና የዮሴፍን ምሥል የያዘ ቅርፅ ከአንደኛው ጥግ ቆሟል፡፡ ከምሥሉ አጠገብ ኢየሱስ ክርስቶስ በትንሽ አልጋ ተኝቶ ይታያል፡፡ ከጎናቸውም በጎች አሉ፡፡ በዓሉ እንደዚህ ባማረ መልኩ እንዲያልፍ ዲኮር የማድረግ ሐሳቡን ያመነጨው የድርጅቱ ባለቤት ሲሆን፣ በሥራው ላይ 11 ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡ ለሥራቸውም ወደ 250,000 ብር እንደተከፈላቸው ቤተልሔም ገልጻለች፡፡ የገና ዛፍ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ እንደ ቤተልሔም የገቢ ምንጭ የሆናቸውም ብዙዎች ናቸው፡፡   

የገና ዛፍ ገበያ

ፒያሳ ከወትሮው የተለየና የልደት በዓልን ገጽታ መላበስ የጀመረችው ከሳምንታት በፊት ነው፡፡ ለወትሮው የልጆች ልደት ቁሳቁሶች፣ ጌጣጌጥና መጻሕፍት ይሸጡ የነበሩ ነጋዴዎች ፊታቸውን ወደ ገና ዛፍ፣ ኳሶችና መብራት አዙረዋል፡፡ አመሻሽ ላይ ነጋዴዎቹ የገዥዎችን ቀልብ በሚስብ መልኩ በማይክራፎን ታግዘው ዕቃዎቻቸውን እያስተዋወቁ ይቸበችባሉ፡፡ ‹‹ለረዥም ጊዜ የሚያገለግል የገና ዛፍ›› እያሉ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የሚያስተዋውቁ ሻጮች ዕረፍት ሲያደርጉ የበዓል ሙዚቃ ይለቃሉ፡፡ በአካባቢው የገና ዛፍ፣ ፖስት ካርድ፣ ቀያይ ኮፍያና ሌሎችም ቁሳቁሶች ለማግኘት ብዙ መጓዝ አያስፈልግም፡፡ ጎዳናውም መደብሩም የገና ዛፍና ተያያዥ ቁሳቁሶች ነው፡፡  

የገና ዛፍና ማስዋቢያዎቹ ከትላልቅ እስከ ትናንሽ የገበያ ስፍራዎች በተለያዩ ዋጋዎች ተሸጠዋል፡፡ ዋጋቸው እንደ ጥራታቸው፣ በያዙት የቅርንጫፍ ብዛት፣ ቁመትና ዓይነት፣ እንዲሁም እንደሚሸጡበት አካባቢ ይለያያል፡፡ በሚሊኒየም አዳራሽ ተዘጋጅቶ በነበረው አዲስ ሾፒንግ ፌስቲቫል ላይ ጥቂት የማይባሉ የገና ዛፍና ጌጣጌጦች እየተሸጡ ነበር፡፡ በረዶ እና አረንጓዴ የሚባሉ የዛፍ ዓይነቶች ለሽያጭ የቀረቡ ሲሆን፣ በረዶው ዋጋ ከአረንጓዴው ዛፍ ትንሽ ወደድ ይላል፡፡ ሜትር ከ10 ርዝመት ካላቸው ጀምሮ የተለያየ መጠን ያላቸው ዛፎች ባዛሩ ከተከፈተ ከታኅሳስ 14 ጀምሮ ተሽጠዋል፡፡ 1 ሜትር ከ10 ቁመት ያላቸው ዛፎች በ1000፣ 1 ሜትር ከ50 1600፣ ሜትር ከ80 አረንጓዴው 2500 በረዶው ደግሞ 2700 ሲሸጡ ከርመዋል፡፡ በዚህ ዋጋ የሚሸጡት የራሳቸው መብራት ያላቸውና በሶኬት የሚሠሩት ናቸው፡፡ ከዚያ ውጪ ያሉት ከ350 ብር ጀምሮ ነበሩ፡፡ በዛፎቹ ላይ የሚሰቀሉ መብራቶች ደግሞ እንደ ዓይነታቸው ከ40 እስከ 400 ብር ድረስ ተሽጠዋል፡፡ በቦምብተራ እንደየዓይነታቸው ከ150 ብር ጀምሮ ሲሸጡ፣ በሾላ፣ በቂርቆስና በሳሪስ ገበያ ከ200 እስከ 2000 ብር ሲጠሩ ነበር፡፡

የገና ዛፍ ሲሸጥባቸው ከነበሩ የንግድ ማዕከላት አንዱ መገናኛ የሚገኘው ሸዋ ሃይፐር ማርኬት ሲሆን፣ የተለያዩ መጠን ያላቸው የገና ዛፎች ከ4 ሺሕ ብር እስከ 24 ሺሕ ብር ድረስ ተሸጠዋል፡፡ የእነዚህ ዛፎች አብዛኛው ገዥ ግለሰቦች ሳይሆኑ ድርጅቶች ናቸው፡፡

የሸዋ ሃይፐር ማርኬት ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሰሚራ ሸረፋ እንደሚሉት፣ ዛፎቹ በብዛት የገቡት በትዕዛዝ ሲሆን፣ ዋጋቸውም ውድ የሚባል አይደለም፡፡ ዛፎቹን ያስገቡትም በብዛት በትዕዛዝ ስለሆነ እንጂ፣ ለገበያው ብለው አይደለም፡፡ እሳቸው ባሉበት መሸጫ ግለሰቦች ብዙም ትኩረት አይሰጡትም፡፡ ትኩረት ሰጥተው እየገዙ ያሉትም ሞሎች፣ ሆቴሎች፣ ኤምባሲዎች፣ ባንኮችና ትላልቅ ተቋማት ናቸው፡፡ እንደ ወ/ሮ ሰሚራ ብዙኃኑን ተጠቃሚ ለመድረስ በቅናሽ ያቀረቡት እንቁላል፣ ዘይት፣ ዱቄት፣ ዶሮና ለበዓሉ የሚሆኑ የምግብ ምርቶችን ነው፡፡

የገና ዛፍና አካባቢ

የገና በዓል ለማክበር በአብዛኛው አገሮች ጥቅም ላይ የሚውለው የገና ዛፍ ሰው ሰራሽ ቢሆንም የተፈጥሮ የሚጠቀሙም አሉ፡፡ የተፈጥሮውን መጠቀሙ የአየር ንብረት ለውጥ ያመጣል፣ ጽድ እንዲመናመንና ያለአግባብ እንዲጨፈጨፍ ያደርጋል በሚል ብዙዎች ወደ ሰው ሰራሽ ሲያዘነብሉ፣ በኢትዮጵያም ከዓመታት በፊት ለገና በዓል ጽድ ቆርጠው የተያዙን መቅጣት በመጀመሩ፣ አሁን ላይ በብዛት የሚታየው ሰው ሰራሹ ነው፡፡ ሆኖም ሰው ሠራሹ ዛፍ አካባቢን የመበከል አቅሙ ከተፈጥሮው የጎላ እንደሆነ ዘጋርዲያን አስፍሯል፡፡

እንግሊዝ ሰው ሰራሽ የገና ዛፎች ከበዓሉ በኋላ በሚወገዱበት ሁኔታ አየር ስለሚበክሉና መሬት ስለሚጎዱ የተፈጥሮ ዛፍ መጠቀምን መርጣለች፡፡ ለዚህም በየዓመቱ 12 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ እስከ 8 ሜትር የሚደርሱ ጥዶች ይተከላሉ፡፡ ሥፍራው ዛፍ በተነሳ ቁጥር መልሶ የሚተከልበት ነው፡፡ የተተከሉት የገና በዓል ከመድረሱ በፊት ባለው አንድ ሳምንት የሚሸጡ ሲሆን፣ ከዚህም 165 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚገኝ ዘጋርዲያን ዘግቧል፡፡ አንዳንድ አብቃዮች ከነሥሩ የሚሸጡ ሲሆን፣ ይህም የገና በዓሉ ካለፈ በኋላ መልሶ ለመትከል ይረዳል፡፡ በኖርዌይ ሰው ሰራሹን ዛፍ ለመከላከል ሰዎች ዛፉን ከደጃቸው እንዲያበቅሉ ዘር ይሰጣል፡፡ ይህን ማድረግ ያልቻሉ አገሮች ደግሞ በአግባቡ የሚወገድበትን ዘዴ ዘርግተዋል፡፡

ሰው ሰራሽ የገና ዛፎች ከፕላስቲክ የሚሠሩ ከመሆናቸው የተነሳ በአፈር ለምነት ላይ ያላቸው ተፅዕኖም ከባድ ነው፡፡ የአፈርን ለምነት ከመቀነስ እስከ መበከልም ይደርሳሉ፡፡

በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፅድን መቁረጥ ከተከለከለበት ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የፕላስቲክ ገና ዛፎች በብዛት እየገቡ ነው፡፡ ሰው አንዱን ዛፍ ለረዥም ዓመታት የማስቀመጥ ልምድ ቢኖረውም፣ እንዴት እንደሚወገድ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሲሰጥ አልተስተዋለም፡፡ ይህን አስመልክተን ያነጋገርናቸው በአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ነጋሽ መብራት፣ ከዚህ ቀደም በስስ ፌስታል እንጂ በዚህ ዙሪያ ምንም እንዳልተሠራ ተናግረዋል፡፡ የብክለቱ ሁኔታ እየታየ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሊሰጥ እንደሚችልም ግን አክለዋል፡፡ 

በምሕረተሥላሴ መኰንንና በሻሂዳ ሁሴን

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...