Friday, July 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዘቢዳር ቢራ በጣት የሚከፈት ጠርሙስ በማስተዋወቅ ገበያውን ተቀላቀለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቤልጂየሙ ቢራ ጠማቂ፣ ዩኒብራ ኩባንያና በጀማር ሁለገብ ኢንስትሪ አክሲዮን ማኅበር ባለቤትነት የተቋቋመው ዘቢዳር ቢራ፣ ከመነሻው በዓመት 350 ሺሕ ሔክቶሊትር ቢራ የሚያመርት ፋብሪካውን በደቡብ ክልል አስገንብቷል፡፡ በ150 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ በተገነባው ፋብሪካ የተጠመቀው ቢራ ለገበያ መቅረብ ጀምሯል፡፡

የዘቢዳር ቢራ ፋብሪካ ግንባታ፣ ዩኒብራ ከተቀላቀለው በኋላ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ሲካሄድ መቆየቱ ታውቋል፡፡ በዚህ ዓመት ለገና በዓል ዋዜማም ቢራው ለገበያ ቀርቧል፡፡ ቢራው ታኅሳስ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ይፋ በተደረገበት ወቅት፣ ጋቨን ብራውን የዘቢዳር ቢራ ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዳብራሩት፣ እስካሁን ከተለመደው የቢራ ጠርሙስ ለየት ያለ አዲስ አቀራረብ አስተዋውቋል፡፡ ያለ ጠርሙስ መክፈቻ በጣት የሚከፈተው የዘቢዳር ቢራ፣ የገብስ ብቅል፣ ጌሾና ውኃ ብቻ በመጠቀም እንደሚመረት ያስታወቁት ሚስተር ብራውን፣ ቢራው በጊዜያዊነት በደቡብ ክልልና በአዲስ አበባ ከገበያ እንደሚቀርብ ገልጸዋል፡፡

የቢራ ኢንዱስትሪው በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት እንደመሆኑ፣ በገበያው ውስጥ ያለው ፉክክር ያሠጋው እንደሆነ የተጠየቁት ሚነስተር ብራውን፣ ዘቢዳር ቢራ ገበያውን ያለ ችግር መቀላቀል የሚችልባቸው የገበያ ስትራቴጂዎችን ይዞ እንደመጣና የገበያ ችግር ሥጋት እንደማይሆንበት ገልጸዋል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አገሪቱ የቢራ ገበያ በያመቱ ከ15 እስከ 20 በመቶ እያደገ ይገኛል፡፡ ይህ መሆኑም ብቻ ሳይሆን ቢራ ለመጠጣት የሚያስችል ገቢ የሚያገኙ ሰዎች ቁጥር መበራከትም በኢንዲስትሪው ለሚንቀሳቀሱ ኩባንያዎች ቁጥር መጨመር አስተዋጽኦ እንዳደረገ ይታመናል፡፡

በዩኒብራ የ60 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ፣ ከሦስት ዓመት በፊት በተደረገ ድርድርና ስምምነት መሠረት ወደ ሥራ በመግባት ምርቱን ለገበያ ያበቃው ዘቢዳር ቢራ፣ በጀማር ሁለገብ የ40 በመቶ ባለቤነት የተዋቀረ ነው፡፡ ጀማር ሁለገብ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር፣ ከ1100 ያላነሱ ባለአክሲዮኖች የመሠረቱት አክሲዮን ማኅበር ሲሆን፣ የባንክና የኢንሹራንስ ኃላፊዎች፣ የሆቴል ባለንብረቶችና ሌሎችም የተሳተፉበት እንደሆነ የዘቢዳር ቢራ፣ የብራንድ ማናጀር ወ/ሮ ራዕይ መሰለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ዩኒብራ ኩባንያ እ.ኤ.አ. በ1960 የተመሠረተ የቤልጂየም ቢራ ጠማቂ ኩባንያ ሲሆን፣ በምሥረታው ማግሥት ወደ አፍሪካ በመምጣት ፋብሪካዎችን እንደተከለ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ስኮል የተሰኘውን የቢራ ብራንድ በአፍሪካ በባለቤትነት የሚያስተዳድረው ዩኒብራ፣ በቢራ ጠመቃ በቤልጂየም ከሚታወቁ ትልልቅ ኩባንያዎች መካከል ይጠቀሳል፡፡

በጉራጌ ዞን ዘቢዳር ማሲፍ ከተባለው ተራራ መጠሪያውን የተዋሰው ዘቢዳር ቢራ፣ በጉብርየ አካባቢ ለሚገኙ ከ200 በላይ ነዋሪዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም የፋብሪካው ኃላፊዎች ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ቢጂአይ ኢትየጵያ፣ ዳሸን ቢራ፣ ሐይኒከን ቢራ፣ ሜታ ቢራ፣ ሐበሻ ቢራ እንዲሁም ዘቢዳር ቢራ በአገሪቱ ያሉትን 11 የቢራ ፋብሪካዎች የሚያስተዳድሩ ሰባቱ ኩባንያዎች ሆነዋል፡፡ መንግሥት በቢራ ኢንዱስትሪው ውስጥ ለመግባት ፍላጎት ያላቸው አዲዲስ ኩባንያዎችን የመቀበል ፍላጎቱ እየቀነሰ መምጣቱን ባለፈው ዓመት ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ ይህም ለገበያው ተመጣጣኝ ምርት ማቅረብ የሚችሉ ፋብሪካዎች ከመተከላቸውና የመጠጥ ኢንዱስትሪውንም ከዚህ በላይ ማስፋፋት የሕዝቡን የጤና ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሚሆን የመንግሥት ኃላፊዎች መጥቀሳቸው ይታወሳል፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች