Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እውነተኛው ታላቅ ቅናሽ ከወዴት አለ?

የሸማቹን መብት ለማስጠበቅ ያስችላሉ የተባሉ ሕግጋቶች ከወጡ ሰነባብተዋል፡፡ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣንን የመሳሰሉ ተቋማት፣ ከንግድ ውድድር ሥርዓቱ  እኩል የሸማቹን መብት ለማስጠበቅ እንዲሠሩ ታስቦበው የተቋቋሙ ናቸው፡፡  

ሸማቾችን ለመታደግ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ያልተገባ ተግባር እንዳይፈጸም፣ ከተፈጸመም ሕግና ዕርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያስችሉ አሠራሮች ስለሸማቾች ጥበቃ በወጣው አዋጅ ውስጥ ተመክተዋል፡፡

ስለሸማቾች ጥበቃና ተያያዥ ጉዳዮች በዝርዝር ከሚደነግጉት አንቀጾች መካከል ለሸማቹ የሚቀርቡ ምርቶችና ሸቀጣሸቀጦች የሚሸጡበጽ ዋጋ በግልጽ በሚታይ ቦታ መለጠፍ እንደሚኖርበት፣ ይህንንም ነጋዴው ወይም አገልግሎት ሰጪው አካል የመተግበር ኃላፊነት እንዳለበት የሚጠቅሰው ይገኝበታል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ማንኛውም የንግድ ድርጅት ለገበያ የሚያቀርበውን ዕቃ ቀድሞ ይሸጥበት ከነበረው ዋጋ ቀንሶ ለመሸጥ ሲፈልግ፣ የዋጋ ቅናሹን መጠን ማስታወቅ ይጠበቅበታል፡፡

ዋናው ነገር ግን ‹‹ታላቅ ቅናሽ›› በማለት ዋጋ ስለመቀነሱ የሚገልጽ የንግድ ድርጅት፣ የዋጋ ቅናሹ ትክክለኛ ስለመሆኑ ማረጋገጫ መስጠት ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ በዘፈቀደ ዋጋ ቀንሻለሁ ብሎ መለጠፍ በሕጉ መሠረት የተከለከለ ነው፡፡ ባስነገረው ወይም በለጠፈው ማስታወቂያ መሠረት ዋጋ ሳይቀንስ ቢገኝ እንደሚያስጠይቀውም   ሕጉ አስፍሯል፡፡  

ከዚህ አንፃር ገበያችንንና ግብይታችን ስንመለከተው፣ በተቀመጠው ሕግ አግባብ መሠረት እየተሠራ ነው ብሎ መናገር አያስችልም፡፡ እንዲህ ያለውን ተግባር የመቆጣጠርና የማስተግበር ኃላፊነት የተሰጠው አካልም ቢሆን ጉዳዩን በተገቢው መንገድ ተከታትሎ እያስፈጸመ ነው ለማለት ያዳግታል፡፡ ‹‹ታላቅ የዋጋ ቅናሽ›› ተብለው በየበዓሉ ሰሞን የሚለጠፉ ማስታወቂያዎችና ሸማቾችን ሆነ ብሎ በማሳሳት ቅናሽ እንዳደረጉ በመጥቀስ የሚለጠፉ መፍሮችን ትክክለኛነት መፈተሽ ተዘንግቷል ማለት ይቻላል፡፡

አዋጁ በወጣ ማግሥት ያልተገባ ዋጋ የሚጠይቁ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር ንቅናቄ በተጀመረበት ወቅት፣ የሚሸጣቸውን ሸቀጣሸቀጦች ዋጋ ለዕይታ ግልጽ በሆነ ቦታ ያላኖረ ክትትል ይደረግበታል እየተባለ ቢፈፍም፣ ‹‹የታላቅ ቅናሽ›› ጉዳይ ግን ቀድሞም ሲሠራበት የቆየ አይመስልም፡፡ በሰሞኑ የገና በዓልም ይህንን ችግር የበለጠ አይተናል፡፡ ጥቂት በማይባሉ የግብይት ሥፍራዎች የዋጋ ቅናሽ ስለመደረጉ የሚገልጹ ማስታወቂያዎች ተገጥግጠው ስናይ ለሸማቾች ጥበቃ የወጣውን አዋጅ እንድናስታውስ ያደርገናል፡፡

አንዳንዱ የዋጋ ቅናሽ በመቶኛ ተሰልቶ፣ ለውጡ መለጠፍ ይኖርበታል፡፡ ሖናም እንዲሁ በደፈናው ‹‹ታላቅ ቅናሽ›› ወይም ‹‹ታላቅ የዋጋ ቅናሽ›› የሚል ጽሑፍ ብቻ የተመቀጠ ነጋዴዎች ሲልጠፉ እናያለን፡፡ በእንግሊዝኛ የታላቅ ቅናሽ አቻ ትርጉም ‹‹ሴል›› እየተባሉ የሚለጠፉ ማስታወቂያዎች ተበራክተዋል፡፡ ስለትክክለኛነታቸው ግን ማረጋገጫ የለም፡፡ የዋጋ ቅናሽ ከሸማቾች የግዥ መሥፈርቶች ውስጥ አንዱ ነውና ማስታወቂያውን፣ አምኖ ወደ ሸመታ መግባቱ አይቀርም፡፡ ነገር ግን ከቅናሹ በፊት የነበረውና የተስተካከለው ዋጋ ልዩነት ምን ያህል እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ልዩነቱ ቢገለጽ እንኳ እውነትነቱን ማን ነው ለሸማቹ የሚያጋግጥለት፡፡

ታላቅ ቅናሽ  የሚል ጽሑፍ የተለጠፈበት ጫማ፣ በጎዳና ላይ ግን ከቅናሹም ባነሰ ዋጋ ሊገኝ ይችላል፡፡ ገበያ ለማግኘት ብቻ ምንም የዋጋ ቅናሽ ሳይደረግ ቅናሽ እንደተደረገ በማስመሰል የሚናገሩ፤ ሲብስም ከቀድሞ መሸጫ ዋጋ በላይ እየጠየቁ ቅናሽ የሚሉና ሸማቾችን የሚያሳስቱ የግብይት ሥፍራዎች ዛሬም፣ ሕግ ወጥቶችም ቁጥጥር አያውቃቸውም፡፡

ለበዓሉ ሲል ሸማቹ መግዛቱ እንደማይቀር በማመንና በመገመት ዋጋ ሳይጠቀሱ ጭምር በስመ በዓል፣ የምርጥ  ዕጥረት ሳያጋጥም በአገር ሰላም ዋጋ የመቆለል ባህሉም እንደባሰበት ነው፡፡ እርግጥ ነው ሻጭ ገበያ እንደሚገኝ ሲያስብ የዋጋ ጭማሪ ማድረጉ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የሚጠቅሱት ፍላጎትና አቅርቦትን ከሚወስኑ ምክንያቶች ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ፍላጎት ከፍተኛ በሆነ ቁጥር የዋጋ መጠን እየቀነሰ መሄዱ ግን የሚጠበቅ የገበያ ባህርይ ነው፡፡

ለዚህም ነው በበዓላት ሰሞን በርካቶች የዋጋ ቅናሽ ማስታወቂያ የሚንጋጉት፡፡ አምራቾችም አዳዲስ ምርት ለማስተዋወቅ ሲፈልጉ ነባሩን ምርት ከገበያ ለማውጣት፣ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ ገበያተኛውን ይስባሉ፡፡ በውጭው ዓለም ይህ የተለመደ ነው፡፡ እስከ 80፣ 90 በመቶ ዋጋ የሚቀንሱ መደብሮች ያጋጥማሉ፡፡ አንዳንዶቹ የተለየ ትዕይንት ለመፍጠር ምርት በነፃ ይሰጣሉ፡፡ ለምሳሌ ዕርቃናቸውን ወደ መደብራችን ለሚመጡ ይህን ያህል ምርት በነፃ እንሰጣቸዋለን በማለት ጉድ ያሰኙ መደብሮች የዜና አውታሮችን ቀልብ በመሳብ በሰበቡም ታዋቂነትን ለማትረፍ በቅተዋል፡፡

በአገራችን የሚታው አብዛኛው የግብይት ሒደት ግን ሸማቾችን በማሳሳት ወይም ተገቢነት የሌለው ስንጥቅ ዋጋ የሚጠይቁ በመሆናቸው ውግዝ ያስብላሉ፡፡ የሸማቾች ጥበቃን የተመለከተውም አዋጅ የወጣው በግብይት ወቅት የሚፈጸሙ ውንብድናዎችን ለመቀነስ ነበር፡፡ በታላቅ ቅናሽ ስም ወይም ሆን ተብሎ በሚፈጠር የምርት አቅርቦት ዕጥረት ዋጋ ሲቆልሉ በተገኙት ላይ የዕርምት ዕርምጃ እንዲወሰድ ገፋ ካለም በሕግ ለመጠየቅ ጭምር በመደንገግ የወጣ ሕግ ነው፡፡ ለዚህ ኃላፊነት የተሰጠው መንግሥታዊ ተቋም ተዋቅራል፡፡ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ነገር ግን በግለጽ የሚታዩ ድርጊቶችን ተከታትሎ ዕርምጃ ባለመወሰዱ ምክንያት በታላቅ ቅናሽ ስም ሸማቾች ያልተገባ ዋጋ እየተጠየቁና እየከፈሉ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በዓላትን ተገን አድርገው በሚዘጋጁ ባዛሮችና በተለያዩ አካባቢዎች በሚዘጋጁ የግብይት ሥፍራዎች ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች የዋጋ ቅናሽ እንደተደረገባቸው በማስታወቂያ ተነግሮ የሚጠራው ዋጋ ግን ከመደበኛው የተለየ ሲሆን አይታይም፡፡ እንዲህ ማድረግ እንደማይቻል ግን በሕግ ተቀምጧል፡፡ አስፈጻሚ አካልም አለ፡፡ ለውጡ ታዲያ የት አለ?

ስለዚህ የታላቅ ቅናሾች ይፈተሽ፡፡ ሕጉም ይፈጸም፤ ይተግበር፡፡ እውነተኛ ቅናሽ የሚያደርጉትን ማበረታታት፣ ይህንኑ በግልጽ በማሳወቅ ለሌሎች ማስተማሪያ የማድረጉ ሥራ ቢኖር ምንኛ በታደልን ነበር፡፡ ሸማቹ ግንዛቤ እንዲኖረው በቂ መረጃ ይሰጠው፡፡ ባለሥልጣኑም ሥልጣኑን ይጠቀም፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት