Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዝንቅወጣቱ ጥግ ይዞ ሁለት ሊትር ስፕራይት ከሚይዘው የፕላስቲክ ዕቃ የገና ዛፍ እየሠራ...

ወጣቱ ጥግ ይዞ ሁለት ሊትር ስፕራይት ከሚይዘው የፕላስቲክ ዕቃ የገና ዛፍ እየሠራ ይታያል

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ዋና የንግድ ስፍራዎች ከውጭ በሚገቡት ሰው ሠራሽ የገና ዛፎች ሲጨናነቁ፣ ወጣቱ ደግሞ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ ጥግ ይዞ ሁለት ሊትር ስፕራይት ከሚይዘው የፕላስቲክ ዕቃ የገና ዛፍ እየሠራ ይታያል፡፡ ለቋሚውም ሸምበቆ ይጠቀማል፡፡ የአንዱ ዋጋም 60 ብር ነው፡፡ ፎቶ በዳንኤል ጌታቸው

* * *

ጉርሻ

- Advertisement -

ከሠፊው ገበታ ከማዕዱ ቆርሶ

‹‹አፈር ስሆን›› አፈር ለብሶ

እጅ ወደ አፍ ደርሶ

ደግሞ ተደጋግሞ መልሶ መላልሶ

‹‹ስሞት ስቀበር ስሄድ ባጥንቴ

ደጋግሞ ለምኖ እያለ በሞቴ››

ብላ ጠጣ ብሎ እንዳልደጋገመ

የፍቅር ጀምበር መሽቶ ከጨለመ

ወዳጅነት ርቆ ሲሆኑ ባላንጣ

ከዳኝ ካደኝ ፀብ ሲመጣ

‹‹በሞቴ›› ብሎ ከአፉ በጣለው ጉርሻ

‹‹እጄ ይጣልህ›› አለው መጥላት ሲሻ

ታሪኩ ከበደ ‹‹ምክረ ሰይጣን›› (2008 ዓ.ም.)

* * *

ባንክ የዘረፈው የገና አባት

በፈረንጆች አዲስ ዓመት መግቢያ በገናቸው በዓል ሰሞን የንግድ ማዕከሎች እንዲሁም ጎዳናዎች በገና ዛፎች፣ በሚሸጡ የስጦታ ዕቃዎች በተንቆጠቆጡበት አንድ ዕለት በአሜሪካዋ ቴኒስ በምትገኝ ከተማ የገና አባት አለባበሱን እንደ (ገና አባት ያደረገ ሌባ) ከባንክ ይገባና እየተዘዋወረ የሞቀ ሰላምታ ለባንክ ሠራተኞች፣ ደንበኞች እየሰጠ ከረሜላም እያደለ ይቆይና በመጨረሻ እውነተኛ ማንኘቱ ይገልጣል፡፡ ወደ አንዱ የባንክ ገንዘብ ከፋይ ጠጋ ብሎ ቁራጭ ወረቀት ይሰጣል፡፡ ጽሑፉ ገንዘብ የሚጠይቅና መሣሪያ መያዙንም የሚገልጽ ነበር፡፡ ባንክ ዘራፊው የገና አባት የተወሰነ ገንዘብ ዘርፎ ከባንኩ መውጣት ቢችልም፣ ከባንኩ ደጃፍ እልፍም ሳይል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡ 

* * *

ፑቲን ከጃፓን የቀረበላቸውን የውሻ ስጦታ አልፈልግም አሉ

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለእንስሳት ባላቸው ፍቅር ይታወቃሉ፡፡ በዚህ ረገድ ብዙ ከመባሉ ባሻገር ፈረስ ሲጋልቡ፣ ከዶልፊን ጋር ሲዋኙና ትንሽ ነብር አቅፈው የሚያሳይ ፎቶዎቻቸው የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ስቦ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. 2010 ላይም ከቡልጋሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ውሻ በስጦታ መልክ ተበርክቶላቸዋል፡፡ በተጨማሪም ዬኒ የተሰኘች ውሻም አላቸው፡፡ ይኼን በመመልከት ይመስላል የጃፓን መንግሥት በቅርቡ ጃፓንን ለጎበኙት ፑቲን ወንድ ውሻ ለማበርከት ቢፈልግም ሩሲያ ይኼን አልፈቀደችም፡፡ ዬኒ የተሰኘችውን ውሻቸውም እ.ኤ.አ. 2012 ላይ በጃፓን የተበረከተች ነች፡፡ ጃፓን አሁን ደግሞ ለዩኒ ተጨማሪ የሚሆን ወንድ ውሻ በስጦታ ለፕሬዚዳንቱ ላበርክት ብትልም ፑቲን ‹‹ይኼን የውሻ ዲፕሎማሲ አልፈልግም›› ማለታቸውን ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡

* * *

በገና ዛፍ ላይ የሚደረጉ ማስዋቢያዎችና ተምሳሌትነታቸው

ሆሊ

‹‹ሆሊ›› ወይም በአገርኛው የእሾህ አክሊል እየተባለ የሚጠራው ተክል በግንዱ ላይ በያዘው እሾህ፣ በትናንሽ አረንጓዴ ቅጠሎቹና ቀይ አበባዎቹ ይታወቃል፡፡ በጣም ጠንካራ ግን ቀጭን ግንድ ያለው ሲሆን፣ ወደ 400 የሚጠጉ ዝርያዎችም አሉት፡፡ ቀይ ፍሬ፣ አረንጓዴ ቅጠልና ግንዱ ላይ እሾህ ተደርጎለት ለገና ዛፍ ማስዋቢያ ከፕላስቲክ የሚሠራው የተፈጥሮ ዛፉ አምሳያ፣ የኢየሱስ ክርስቶስን ዘለዓለማዊነት፣ በእሱ መወለድና መሞት ለሰው ልጆች የሰጠውን የዘለዓለም ሕይወት ያሳያል፡፡ በግንዱ ወይም በቅጠሎቹ ጫፍ ላይ ያለው እሾህ ኢየሱስ ሲሰቀል በጭንቅላቱ ላይ የነበረውን የእሾህ አክሊል ለማስታወስ ነው፡፡ በዛፉ ላይ ያለው ቀይ አበባ ወይም ፍሬ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን ያፈሰሰውን ደም ይወክላል፡፡

ስጦታ

በገና የሚሰጡ ስጦታዎች ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን የተሰጠ ስጦታ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡ እሱም ሕይወቱን ሰጥቶ ሰዎችን ስለማዳኑ በስጦታ ይታወሳል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም በግርግም በተወለደ ጊዜም ሦስቱ ሰብአ ሰገል (የጥበብ ሰዎች) ለሕፃኑ ይዘው የሄዱትን እጣን፣ ከርቤ፣ ሽቶና ወርቅ ስጦታዎች ለማስታወስ ሰዎች ስጦታን ይለዋወጣሉ፡፡  

ሚስትሊቶይ

ሚስትሊቶይ የራሱ ሥር ሳይኖረው በሌሎች ዛፎች ላይ ተጣብቆ የሚያድግ ነው፡፡ ይኼ በሰው ሠራሽ ተሠርቶ ለገና ዛፍ ማስዋቢያ የሚውል ሲሆን፣ አሠራሩም ለስላሳ፣ ራሱን ችሎ የማይቆም ተደርጎ ነው፡፡ ይኼም የሰው ልጆች ያለ ፈጣሪያቸው መቆም እንደማይችሉ ለማመላከት ነው፡፡

የገና ዛፍ ማስዋብ

በ18ኛው ክፍለ ዘመን ገና ዛፍን በተለያዩ ጌጦች ማስዋብ በፈረንሣይ፣ በጀርመንና በኦስትሪያ እንደተጀመረ ይነገራል፡፡ የገና ዛፍ የፓጋን እምነት ተከታዮች ነው የሚል መከራከሪያ ቢኖረም፣ በሌላ ወገን ያሉት የገነት የሕይወት ዛፍ ምሳሌ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የገና ዛፍ ቅርንጫፎች ሙሴ በነደ እሳት በቁጥቋጦ ውስጥ ከፈጣሪው ጋር የተነጋገረውንና የሕይወት ዛፍ የሆነውን ክርስቶስ ለማስታወስ ነው፡፡

ሻማና መብራት

በገና ዕለት የሚለኮሰው ነጭ ሻማ የክርስቶስን ንጹህነት ለማሰብ ሲሆን፣ ይኼ በአብዛኛው በኤሌክትሪክ ብርሃን ተተክቷል፡፡ መብራቱም ሆነ ሻማው የሚወክሉት የክርስቶስን ብርሃንነት ነው፡፡

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...