Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

አንዳንድ ወቅቶች ከሚገርሙ አጋጣሚዎች ጋር ያገጣጥሙናል፡፡ እኔ የገጠመኝ ግን ከገና በዓል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ አንድ ጊዜ ዓመቱ ትዝ ባይለኝም በግ ለመግዛት ከጓደኛዬ ጋር አዲሱ ገበያ እንሄዳለን፡፡ አሁን ሕንፃዎቹ የተገጠገጡበት ቦታ ይመስለኛል ያኔ የበግ መሸጫ ነበር፡፡ ከታክሲ ወርደን የበግ ገበያው ውስጥ ስንገባ የበግ ዓይነት ለትንግርት ይታያል፡፡ ጓደኛዬ አንድ በጣም የሰባ ሙክት ሳብ ያደርግና በእጁ በሚገባ ከደባበሰ በኋላ ዋጋ ይጠይቃል፡፡ የበጉ ባለቤት ቀጭንና ረዥም አዛውንት፣ ‹‹የመንዝ በግ ነው፡፡ 400 ብር ወዲህ በል . . .›› እያሉ ጣታቸውን ገንዘብ እንደ መቁጠር ሲያንቀሳቅሱ ጓደኛዬ፣ ‹‹ምን አሉኝ? በህልሜ ነው ወይስ በዕውኔ . . . ›› እያለ ሲቆጣ በአካባቢያችን የነበሩ ሰዎች ‹ወይ ስምንተኛው ሺሕ . . .› እያሉ ሲያጉተመትሙ መስማቴ አይረሳኝም፡፡ በእርግጥ በጊዜው እኔም ከመገረም አልፌ መደንገጤን አስታውሳለሁ፡፡

ማን ነበር ‹‹ጉዳያችን መቶ ደመወዛችን ሃምሳ!›› ያለው? በስንት ጭቅጭቅና ንትርክ መካከለኛ የሚባሉ ሁለት በጎችን በ150 ብር ገዝተን በውይይት ታክሲ ጭነን ወደ ቤታችን ስንመለስ፣ የበጎቹን ዋጋ የጠየቁን ሰዎች በመገረም ሲነጋገሩ እኔና ጓደኛዬ በኩራት ተኮፍሰን ነበር፡፡ የውይይታችን ሾፌር ሬዲዮ ሲከፍት፣ ‹‹ዕድሜ ይስጠን ጤና እናያለን ገና . . ›› የሚል ዘፈን ስንሰማ ቆይተን አንድ በውል የዘነጋሁት ቀልደኛ ተተካ፡፡ በቀልደኛው መሠረት ሴትዬዋ እንደኛ የበዓል በግ ሊገዙ ሄደው ዋጋ ሲጠይቁ የበጉ ባለቤት 200 ብር ይላቸዋል፡፡ ሴትየዋ በመበሳጨት፣ ‹‹ምን ዓይነት ጊዜ ላይ ደረስን . . . ›› ሲሉ አንድ ወፈፍ ያደረገው ወጣት፣ ‹‹እማማ ርካሽ ነው ይግዙት . . .›› እያለ ይስቃል፡፡ ሴትየዋ አተኩረው ካዩት በኋላ ‹‹ልጄ አንተማ በጊዜ ለይቶልሃል እኛ ነን መከራ የምናየው . . .›› ሲሉ ውይይት ታክሲያችን በሳቅ ተናጋች፡፡

እኔና ጓደኛዬ ሠፈር ደርሰን በጋችንን በየቤታችን ካስገባን በኋላ አንድ አንድ ለማለት አካባቢያችን ያለ ግሮሰሪ እንሄዳለን፡፡ ስንደርስ ግሮሰሪው ከአፍ እስከ ገደፉ በደንበኞች ተሞልቷል፡፡ እንደምንም ብለን ጥጋችንን ይዘን የመጣልንን ቢራ ፉት ስንል የዓመት በዓል ገበያ ዋጋ ጉዳይ ተነሳ፡፡ አንዱ፣ ‹‹ምን የመሰለ እኔ ነኝ ያለ ወይፈን የሚያህል ሙክት በግ 500 ብር ተገዛ. . . ›› ሲል፣ ‹‹ምን ወይፈን የሚያህል ትላለህ አይቼው የለም እንዴ? እኝህ ሀብታሙ ነጋዴ አይደል እንዴ የገዙት? በሬ በለው እንጂ . . .›› እያለ ያዳንቃል፡፡ ዶሮ በውድ ዋጋ መሸጡ ያብከነከናቸው አንድ አዛውንት ደግሞ፣ ‹‹የዓለም ፍፃሜ ለመቃረቡ ማሳያ የሚሆነው በሃምሳ ሳንቲም እንገዛት የነበረች ዶሮ 25 ብር ማውጣቷ ነው . . .›› ብለው የያዙትን ጂን በአንድ ትንፋሽ ጨለጡት፡፡ ብቻ ግሮሰሪዋ በአንድ እግሯ እስትቆም ድረስ የኑሮ ውድነት ተተነተነ፡፡ በዚህ መሀል ነበር አንድ ነካ የሚያደርገው ሰው ለልመና እጁን እየዘረጋ፣ ‹‹ምን አይታችሁ? ብር አረፋ የሚሆንበት ዘመን ይመጣል፡፡ ያኔ ብዙ ሺሕ ብር ደመወዝ ብታገኙም ልክ እንደ ጉም ይሆንባችኋል . . .›› እያለ ማብራሪያ ሲሰጥ በቅጡ ያዳመጠው አልነበረም፡፡

ይኼንን ሁሉ የምለው ድሮና ዘንድሮን ለማነፃፀር ወይም በድሮ ናፍቆት ዛሬን ለመንቀፍ አይደለም፡፡ ነገር ግን ገበያችንና የኢኮኖሚ ሕግጋቱ ስለማይጣጣሙልኝ ነው፡፡ በቅርቡ ለመኪና ሞተር የውስጥ ዕቃ ብፈልግ ብፈልግ አጣለሁ፡፡ በስንት መከራ በማውቀው ሰው አማካይነት ተፈልጎ ሲገኝ ዋጋው አሥር እጥፍ ጨምሯል፡፡ በአጋጣሚ ዱባይ የሄደ ጓደኛዬ ስለነበር በስልክ ነግሬው ሲመለስ ይዞልኝ መጣ፡፡ እሱ በድርሃም የገዛው በብር ሲታሰብ 100 ብር አይሞላም፡፡ እኔ ግን የተጠየቅኩት ከ3,500 ብር በላይ ነው፡፡ ፍላጎትና አቅርቦት በማይቆጣጠሩት ምስቅልቅሉ ገበያችን ምክንያት ከአልባሳት ጀምሮ እስከ ተለያዩ ሸቀጦች ድረስ የሚደርስብን ብዝበዛ ያናድደኛል፡፡ የነጋዴዎቻችን ብልሹ አሠራር የሚያስተካክለው በመጥፋቱ ሸማቾች ለሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት እንጋለጣለን፡፡

ወደ ገና ገበያ ልመለስና ሰሞኑን ገበያውን በወፍ በረር ለመመልከት ሞክሬያለሁ፡፡ የሰው ልጅ እንደ ዘመኑ ነው የሚኖረውና ከመርካቶ በስተቀር ብዙዎቹን የሕንፃ ገበያዎች (ሞሎች) ተዘዋውሬ ሳይ እዚህ አገር ደፋር ለሆነ ሰው ንግድ ጥሩ ሥራ መሆኑ ገብቶኛል፡፡ ንግድ በጣም ብልህ ሰዎች የሚሳተፉበት የተከበረ ሙያ እንደሆነ አውቃለሁ፡ አሁን ግን እሱም ለዛውን አጥቶ ማንም ደፋር እየገባበት የሚያተራምሰው ከሆነ ጠብሰቅ ያለ ትርፍ አለው ማለት ነው፡፡ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ አንድ ሞል ውስጥ ገብቼ የልጆች ልብስ ሳማርጥ ዋጋው ያስደነግጣል፡፡ በገበያ ዋጋ ትመናም ሆነ ከአምራች እስከ መጨረሻው ተጠቃሚ ድረስ ባለው ሰንሰለት በሚቆረጠው ዋጋ ላይ በቂ ግንዛቤ አለኝ፡፡ አሁን እያየሁት ያለው ግን ደፋሮች ሊዘርፉ የተሰባሰቡበት ይመስላል፡፡ ደንደንና ፈርጠም ያለውን ጎረምሳ፣ ‹‹ምነው ዋጋው ዕቃውን አልመስል አለ?›› ብዬ የልጅ ጃኬት ሳሳየው፣ ‹‹አቅምን አውቆ መኖር ጥሩ ነው፣ ታላቅ ችሎታ ነው . . .›› የሚለው ዘፈን በፉጨት ሲያሰማኝ ማድረግ የነበረብኝ ፀጥ ብሎ መውጣት ነበር፡፡

ከዚህኛው ሕንፃ ወጥቼ በቅርቡ ያለ ሕንፃ ውስጥ ያለ ሞል መሳይ ውስጥ ገባሁ፡፡ አሁንም አያርመኝምና የተጋነኑ ዋጋዎችን እያየሁ አንዲት ቅብጥብጥ መሳይ ቆንጆን፣ ‹‹እህት ለመሆኑ ይኼ የተለጠፈበት ዋጋ ትክክለኛ ነው? ወይስ እየቀለዳችሁ ነው?›› ስላት፣ ከአማኑኤል ሆስፒታል አምልጦ እንደመጣ ወፈፌ በሥጋት እያየችኝ፣ ‹‹ቦሌ የመጣኸው ዛሬ ነው?›› ወይ ብላ ጥያቄዬን ዜሮ አደረገችው፡፡ ወዲያው ዘመናዊና በጣም ትልቅ የሆነውን የሞባይል ስልኳን ከጂንስ ሱሪዋ ኪስ ውስጥ አውጥታ የሆነ ሰው ዘንድ ከደወለች በኋላ፣ ‹‹ውይ ማሚ አሁንስ የሰለቸኝ ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ? በቃ ሰው ለምን አቅሙን አውቆ ሾፕ አያደርግም? ትንሽ ገንዘብ ይዞ እዚህ ይመጣና በኮምፕሌክስ አላሠራ አለኝ እኮ? ማሚ ሙች አሁንስ ሰለቸኝ . . .›› እያለች ስትነፋረቅ ትቻት ወጣሁ፡፡ በዘመነ ሻርክ ክፉና ደጉን ከመነጋገር ለካ ዝም ማለት መልካም ነው፡፡ ከቻሉ ንግዱ ውስጥ ገብቶ ማተራመስ ካልቻሉ ግን ‹‹አንተው ታውቃለህ . . .›› ብሎ ወደ ፈጣሪ ማንጋጠጥ የሚሻል መሰለኝ፡፡ (መሳይ አጥናፉ፣ ከካራ)    

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...