Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትይድረስ አሸባሪነትን ለሚዋጉ ሁሉ

ይድረስ አሸባሪነትን ለሚዋጉ ሁሉ

ቀን:

በጳውሎስ ደሌ

      ወቅቱ ከሞላ ጎደል መላውን ዓለም የሚያስተባብርና በመላው ዓለም የተገጣጠመ የዓመት በዓል ሰሞን ነው፡፡ እንዲህ ያለም ሆነ በተወሰነ አገር ብቻም የሚከበር ዓውደ ዓመት ስለገበያ ዋጋ፣ ስለምግብና ጤንነት፣ ስለ‹‹ሕገወጥ› እርድ፣ ስለቆዳና ሌጦ ገበያ ብቻ የሚወራበት አይደለም፡፡ የአውሮፓውያኑ የ2016 መሰናበቻና የ2017 መባቻ ሰሞን ደጋግመን እንደተገነዘብነው ዓውደ ዓመት የደስታ የፌሽታ የፈንጠዝያ ብቻ ሳይሆን የሥጋትም፣ የጥርጣሬም፣ የሰቀቀንም፣ የጥንቃቄም፣ የመከላከያም፣ የዝግጁነትም ወሬና ተግባር ወቅት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በአገራችን ደረጃ ሳይቀር ‹‹የዘንድሮው [የ . . .  በዓል] በሰላም ተጠናቀቀ›› ማለት ድረስ የዘለቀና ‹‹የለመደበት›› ዜና መስማት ጀምረናል፡፡ እንዲህ ዓይነት የሰቀቀን፣ የሥጋትና የፍርኃት ወግ በተለይም የአንዳንድ የመገናኛ ብዙኃንን ኤዲቶሪያል ፖሊሲ ከመጠናወቱ የተነሳ ‹‹የ .  . . የብሔራዊ ፈተና በሰላም ተጠናቀቀ›› ማለት ዓይነት ወሬ የሰማነው፣ ከ2008 ዓ.ም. ክረምት የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና በፊት ነው፡፡

አሸባሪነት ዓለምን እያመሳት ነው፡፡ በአሸባሪነት ላይ የሚካሄደውም ጦርነት በተለይም “War on Terror” የሚባለው የፀረ አሸባሪነት ትግሉም ችግሩን ከማባባስ የተለየ ፋይዳ ሲሰጥ አልታየም፡፡ አሸባሪነት ምንጩና ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን ከፍተኛ ወንጀል ነው፡፡ ሰዎችን በነሲብ የሚያጠቃ ሽብር የትግል ሥልትና ዘዴም ሊሆን አይችልም፡፡

- Advertisement -

ኢትዮጵያም አሸባሪነትን መከላከልና መዋጋት ያለባት መሆኑ የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ አገራችን በተቻለ መጠን ዓለም አቀፋዊ አሸባሪነት ዓይን ውስጥ እንዳትገባ መከላከል፣ ለአሸባሪነት ጥቃት የለማ ምክንያት ወይም ሰበብ አለመሆኗን ማረጋገጥ፣ አሸባሪነት በአገር ውስጥ ቅጣዩን ለማብቀልና ለማመስ በውጭ ያሉ ዜጎቻችንና ጥቅሞቻችንን ዓላማ ለማድረግ የሚመቸው ሁኔታ እንዳይፈጠር መታገል ይገባናል፡፡

ከዚህ በመነሳት መጀመሪያ አሁን በገነነው ዓለም አቀፋዊ አሸባሪነት ላይ ለጥቆም ይኼንኑ ለመከላከል በሚያስችለን ውድ ሀብታችን ላይ አንድ ነገር ማለት ፈለግሁ፡፡ ሐሳቤ እንደሚስተናገድልኝም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

የትኛውም ዓይነት ፅንፈኝነት (የፖለቲካም ሆነ የሃይማኖት) ተቻችሎ ለመኖር አያመችም፡፡ መራራ ስሜት እያከማቸና የጎሪጥ እያስተያየ ለፀብ ያዘጋጃል፣ ያነሳሳል፡፡ ከዚያም አልፎ የጥቃት ቀጥተኛ ማካሄጃ ሊሆን ይችላል፡፡ የዚህ ዓይነት የፅንፈኝነት ዝንባሌ በየትኛውም ሃይማኖት ውስጥ እንደየሁኔታው ሊከሰት የሚችል ነው፡፡ የዚህ የዚህ ሃይማኖት ጠባቂ፣ አስፋፊና ወታደር ነን ባይ ኃይሎች ከእነሱ ውጪ የሆኑ ባለእምነቶችን ያሳደዱበትና የጨፈጨፉበት ታሪክ በዓለማች ውስጥ በክርስትናም በእስልምናም በኩል ተካሂዷል፡፡ በአንድ ሃይማኖት ውስጥ ልዩነት ያበቀሉ ወገኖች “ከሃዲ አሳሳቾች” እየተባሉ በአውሮፓም፣ በእስያም፣ በኢትዮጵያም እየታደኑ የተገደሉበት ዘመን ነበር፡፡

ይህ አሮጌ ዘመን ዛሬ በጥቅሉ የታለፈ ቢሆንም፣ ዛሬም 21ኛውን ክፍለ ዘመን ወደ ቀድሞው ዘመን መመለስ የሚሹ ጥንተኞች ጥፋት ያደርሳሉ፡፡ ከልማትና ከፀጥታ አውታር የራቀ ወይም ሕጋዊ አስተዳደር የተቃወሰበት የግርግር ሥፍራ ውስጥ ጣቢያ እያበጁና እየተሹለከለኩ፣ ሃይማኖት ከ“ማረም”ና ከማስቀየር አልፈው በጥንታዊዎቹ በድንጋይ ወገራ፣ በጅራፍ ግርፊያ፣ በአካል ቅርጠፋና በአንገት ስየፋ ቅጣቶች ሕዝብን ያርበደብዳሉ፡፡ የጠላት ቀጣና የሚሉትን አካባቢ ደግሞ በፈንጂና በጥይት ያተራምሳሉ፡፡

የዚህ ዓይነቱ ጥንተኛ ፅንፈኝነትና አሸባሪነት ዛሬ ዋና መነገጃ ሆኖ ያለው እስልምና ነው፡፡ ለአሸባሪዎች ምቹ መነቃቂያ ድባብ ሆኖ የጠቀማቸው ምላሽ ያጣው የፍልስጤም ጥያቄና ከዚያ ጋር ተያይዞ የተፈጠረው ፀረ እስራኤልና ፀረ አሜሪካ ሙቀት ነው፡፡ ከዚያ ሌላ ከነዳጅ ጥቅም ጋር የተያያዘ ጭፍራ የማበጀት ትግልና ጣልቃ ገብነት አለ፡፡

በጊዜያት ውስጥ እስላማዊ ፅንፈኞች ፀረ ምዕራብ ጣልቃ ገብነትንና ፀረ እስራኤልነትን መታወቂያቸው እያደረጉት መጡ፡፡ ፀረ እስራኤልና ፀረ አሜሪካ ፖለቲከኞችም ሃይማኖታዊ ፅንፈኝነትን በመሣሪያነት ይጠቀሙበት ገቡ፡፡ በፍልስጤሞች የትጥቅ ትግል ውስጥ ለትኩረት ማግኛነትና ለማስገደጃነት ይውል የነበረው እገታና ፈንጂ ጠመዳም ተስፋፍቶና ከፍቶ ለተለያየ ዓላማ ማስፈጸሚያ ይውል ጀመር፡፡ እንዲያውም የፍልስጤም ጉዳይ አድሎኛ አያያዝና ዓለም አቀፋዊ ሽብርን በወታደራዊ ዘመቻ የማጥፋት ሙከራ ለሽብር መስፋፋት የማዕዘን ድንጋይ ሆነው እያገለገሉ ነው፡፡ በዛሬው ጊዜ ፍትሕ ላጡት ፍልስጤማውያን እቆረቆራለሁ የማይል፣ የአሜሪካን ኃያላዊ ሚናንና የአሜሪካ ተቀፅላነትን የማይቃውም፣ ምዕራባዊ የባህል “ዘበናይነት”ን እንደ ጠንቅ/እንደ ርኩሰት የማያይ “እስላማዊ” አሸባሪነት የለም ማለት ይቻላል፡፡

በዛሬው ዓለማችን ውስጥ የሁለት ልዕለ ኃያላን ፍጥጫ ባለመኖሩ የተባበሩት መንግሥታትም ፍጥጫዎችን የማቻቻል ታህል የተፅዕኖ አቅም ስለሌለው፣ የእስራኤልና የፍልስጤም ጉዳይ የመፍትሔ ተስፋ እንኳ ካጣ ቆይቷል፡፡ ፍልስጤሞች በትጥቅ ትግል ቢሉ በሕዝብ አመፅ፣ ከዚያ መስመር ወጥተውና የእስራኤልን መንግሥትነት አውቀው በአቤቱታና በድርድር ቢሞክሩም ጠብ የሚል ነገር ያጡት፣ ስቃይና ግብግብ የማይለወጥ ኑሮ የሆነባቸው አለኝታ የለሾች ናቸው፡፡ እስራኤልን አላቅም ባዩና መፍትሔ መሆን የማይችለው ፅንፈኛው ሐማስ በጋዛ ምርጫ አሸንፎ የመንግሥት መሪ ለመሆን መቻልም (ፋታህ ሲመራው የቆየው አገር አልባ መንግሥታቸው በንቅዘት መዛሉ ተደምሮበት) የዚሁ የተስፋ ማጣት ውጤት ነበር፡፡ የአሜሪካና የአውሮፓ ተገን ያላት እስራኤል ግን ለስግብግብነቷ ተቆጪና ቆንጣጭ የለሽ እንደሆነች አለች፡፡ ይህ ሁኔታ ሁለት ፅንፍ የወጡ ብልሽቶችን አስክትሏል፡፡

በእስራኤል ውስጥ አነሰም በዛ ፍትሕን የሚሞክር ፖለቲከኛ ወደ ሥልጣን እንዳይመጣ የቀኝ አክራሪነት ምንተፍረት የለሽ ዓይናውጣነት በእስራኤል ፖለቲካ ውስጥ እንዲንሰራፋ፣ የእስራኤል ሌበር ፓርቲ ተከፋፍሎ ከቀኝ ክንፎቹ እምብዛም የማይሻል አቅመ ቢስ እንዲሆን አድርጓል፡፡ እስራኤል በፍልስጤሞች ላይ የምታሳርፈው በትርና ሸፍጥ መከለያ አጥቷል፡፡ ሐማስን የውስጥ አርበኛ ያህል ማስፈራሪያና ማሳበቢያ አድርጎ በመጠቀም “ብልጠት” ውስጥ ተውጣለች፡፡ የሐማስን የሮኬት ትንኮሳ ጋዛን ወሮ ለማጋየት ተገቢና በቂ ምክንያት አድርጋ ይዛዋለች፡፡ ሰላማዊ ድርድሯ ሁሉ ወደ 1967 ይዞታ መመለስ ብሎ ነገር የማይታሰብበት ሆኗል ብሎ ማለት አይገልጸውም፡፡ ከዚህ ቀደም እንዳልነው እህሉን ሁሉ በመጋዘኑ ተቆጣጥሮ በሽማግሌ ስንስማማ ድርሻህን ትወስዳለህ፣ እስከዚያ ግን እኔ መብላቴን እቀጥላለሁ ከሚልና (በልቶ ለመጨረስ ከቆረጠ) ነጣቂ የማይለይ ነው፡፡ የድርድር ድራማዋ ባለበት ረግጦ ሲሰናከል ወይም ቁርቁሱ በሞቀ ጊዜ ደግሞ ሰው እየሰፈሩ የፍልስጤሞችን መሬት መቀነስ ይቀጥላል፡፡ እየተጠናቀቀ ያለውም ይኼው ነው፡፡

ይኼ የእስራኤል ጋጠወጥ አድራጎት በዙሪያዋ የሚከምረው ዓረባዊ እስላማዊ ብግነትና የይሁዲ ጥላቻ ሌላው ብልሽት ነው፡፡ ብግነት ሄዶ ሄዶ ሊያመጣ የሚችለውን ጣጣ አርቆ የሚያይ ጠፍቷል፡፡ የተፃራሪዎቿን እንቅስቃሴ ጓዳ ጎድጓዳ በስለላዋ ልትቆጣጠር እንደምትችል አድርጋ የምታምነውና የአሜሪካና የአውሮፓ ድጋፍ ባልታሰበ የኢኮኖሚ ቀውስ ሊንኮታከት የሚችልበት አደጋ ብቻዬን ቢያስቀረኝስ የሚሉ አዙሮ ማየት የተዘነጋት እስራኤል፣ የሚበግኑ ጠላቶቿ አድፍጠው ያልተጠበቀ ጅምላ ጨራሽ ጥቃት የሚሰነዝሩበትን ቀን መለማመን የያዘች ትመስላለች፡፡ እስከ አሜሪካ የተዘረጋ የገንዘብ መረብ ባለው ግዢ የእስራኤልን የመሬት ይዞታ ከፍልስጤሞች ወደ ይሁዳዎች የማዞር የኖረ ሥልት አልበቃ ብሎ፣ የቤንጃሚን ኔትንያሁ መንግሥት አመፃ ላይ የተገኘ ፍልስጤማዊን የቤተሰብ ቤት የማፍረስ ዘዴ ሲጨምርበት ታይቷል፡፡ ይኼን ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጽም፣ ከዚህም ርቆ ሄዶ ጠቅላላ በእስራኤል ውስጥ ያሉትን ፍልስጤሞች እንግዶች የሚያደርግ (እስራኤልን የይሁዳዎች አገረ መንግሥት ብሎ የሚያወጅ) ሕግ እስከ መንደፍ ህሊና ሲያጣ፣ ታሪክ አገሬ ብሎ የመኖር ትውልዳዊ መብትን የሰጠው ለአንድ ወገን ብቻ አይደለም ብሎ እንኳ የገሰጸው የለም፡፡ ሩሲያ የዩክሬይንን ተገንጣዮች ደገፈች፣ “ግዛት” ነጠቀች” ብለው ማዕቀብ ለማድረግ የፈጠኑት ለሕዝብና ለሉዓላዊ መብት “አሳቢዎቹ” አሜሪካና አውሮፓ፣ እስራኤል ይኼን ሁሉ ስትሠራና ሮኬት ተወነጨፈብኝ በሚል ሰበብ መከላከያ ኃይል በሌለው የጋዛ ሕዝብ ላይ የአየርና የምድር ጦር ደጋግማ ስታዘምት አለመቆጣታቸው ቅሌታቸው ነበር፡፡ አንዳንዶቹ (ስዊድን፣ ፈረንሣይ፣ ወዘተ) በየአገራቸው ፍልስጤምን እንደ አገረ መንግሥት የማወቅ ውሳኔ ማፅደቅም (ተግባራዊ ውሎ የለውምና) የምንተፍረት ወግ እንዲያም ሲል የሽብር ዒላማነትን ለመቀነስ ቢበጀኝ የተባለ የከንፈር ቀለም ዓይነት ነገር ነው፡፡ ከአንጀት ፍትሐዊ መፍትሔ ቢሹማ ፍልስጤሞች የሚያደርጉት ከማጣታቸው ብዛት በጭፍን እልህ ሰልስለው ያጋጣማቸውን ይሁዳ በስለትም፣ በጥርስም ቦጭቆ እስከ መበቀል ድረስ የሚሠሩትን እስከሚያጡ ድረስ ተመልካች ባልሆኑና የ1967 ዓ.ም. ቅድመ ጦርነት ይዞታን በመሠረታዊ መስማሚያነት ተቀበዬ በማለት እስከ ማዕቀብ የሚደርስ ጫና በእስራኤል ላይ ባደረጉ ነበር፡፡

የፍልስጤሞች የህልውና ጥያቄ ተደፍቆ እስከቆየ ድረስ ሕፃናትን የማይምር የአሸባሪ ሥልት ይቅርና ከዚህም የባሰ መበቀያ ቢገኝ መጠቀምን ተገቢ የሚያደርግ፣ በሚዛናዊ ህሊና አሸባሪነትን ለመፃረርና ለማምከን የማያስችል የበደልና የብግነት ምሰሶ በምድራችን ላይ ተተክሎ ይቆያል፡፡ በስመ ፀረ አሜሪካ እስራኤል ትግል ንፁኃን በፈንጂ ሲበሉ የሚያርር እንደሚኖር ሁሉ “እሰይ” የሚልም ይኖራል፡፡ “ሽብርተኝነት”ን የሚያበረታታና የሚያስቀጥል የጋራ ምክንያትና ቁጣ መኖሩ ይቀጥላል፡፡ ሽብርን በተለያየ መልክ የሚደግፉ መንግሥታት፣ ባለሀብቶችና የሃይማኖት ፅንፈኛ ቡድኖች መኖራቸው አይዳከምም፡፡ ትርምስ በተከሰተበት የእስልምና አካባቢ ውስጥ በብርሃን ፍጥነት የፅንፈኞችና የሽብር ውጥኖች ብቅ ማለታቸው ከዚህ ሁሉ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡

አክራሪነትም ሆነ ለዘብተኝነት በየሃይማኖቶች ውስጥ የሚታዩ ዝንባሌዎች ቢሆኑም ዛሬ እስልምናን ተመርኩዞ የሚታየውን የአክራሪነትና የሽብር እንቅስቃሴ ከዕድገት መጓደል፣ ከፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ከአሜሪካ ጣልቃ ገብነት፣ ከእስራኤልና ከፍልስጤም ቅራኔና ምዕራባዊ የበላይነትና የባህል አላሻቂነትን ከመቃወም ጋር የቅርብ ግንኙነት አለው፡፡ እንዲያውም የፍልስጤም ጉዳይ አያያዝና ዓለም አቀፋዊ ሽብርን በወታደራዊ ዘመቻ የማጥፋት ሙከራ ለሽብር መስፋፋት የማዕዘን ድንጋይ ሆነው እያገለገሉ ነው፡፡ በዛሬው ጊዜ ፍትሕ ላጡት ፍልስጤማውያን እቆረቆራለሁ የማይል፣ የአሜሪካን ኃያላዊ ሚናንና የአሜሪካ ተቀፅላነትን የማይቃወም፣ ምዕራባዊ የባህል ዘበናይነትን እንደ ጠንቅ የማያይ እስላማዊ አሸባሪነት የለም ማለት ይቻላል፡፡

ይህን መሳዩን ዓለም አቀፋዊ አሸባሪነት ፖለቲካዊ መሠረት የሚያደርግ መፍትሔ በቅርብ ይመጣል ብሎ ተስፋ ማድረግ ያስቸግራል፡፡ በእስራኤል ያለው ወግ አጥባቂ መንግሥት በሠፈራ ተስፋፊነትን ከሰላም ንግግር ጋር አብሮ ሊያስኬድ የሚሻ አሿፊ ነው፡፡ ይህንን ሹፈት ‹‹ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ›› በቁርጠኛ ተግሳፅ ማረቅ አልቻለም፡፡

ዋና መቀፍቀፊያውን ኋላ በቀሩና በተቃወሱ አካባቢዎች አድርጎ ደሃና ሀብታም አገር የማይባልበት መረብ እያበጀና እየተስፋፋ የመጣው አክራሪ አሸባሪነት በበኩሉ፣ በምዕራብ አገሮችና ዜጎች ላይ የሚፈጥረው ማብቂያ ያጣ መንሸቅሸቅ እስልምናና ሙስሊሞችን በአሉታዊ ስሜትና በአደጋ ምንጭነት እንዲታዩ እያደረገ ነው፡፡ ወደ ስምንት ዓመት ግድም ያደረገው የዓለም የገንዘብና የኢኮኖሚ ቀውስ ያስከተለው የኑሮ ድቆሳ፣ የወግ አጥባቂ ፖለቲካ ግፊትና ገዢነት መደረቡ ደግሞ ሁለቱንም ተመጋጋቢ ችግሮች አያባባሰ ነው፡፡

በአውሮፓ ውስጥ በካርቱን ሥዕል ተረብ የእስልምና ዕምነት ነብይ መንካት፣ በመስጊዶች ማማዎችና ከራስ እስከ እግር በሚሸፍኑ የሙስሊም ሴቶች አለባበስ ላይ እየተንፀባረቁ ያሉ ቅዋሜዎች፣ በሆላንድ ክስ ላይ የሚገኘው ግሪን ዊልደርስ እስልምና ላይ ያካሄደው ነቀፋ፣ በአሜሪካም መንታዎቹ ፎቆች ከወደሙበት ሥፍራ በአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ መስጊድ የመሥራት ሐሳብ የቀሰቀሰው ቅዋሜና አንድ ቄስ ኃፍረት ሳይሰማው የመስከረም አንድ የሽብር ጥቃት በሚታሰብበት ዕለት በሺዎች የሚቆጠሩ የቁርዓን መጸሕፍትን አቃጥላለሁ ብሎ ለመዛት መቻሉ፣ እየዳበረ ያለውን አደገኛ ዝንባሌ ጫፍ ጫፉን የሚጠቁሙ ናቸው፡፡

የተፈጠረው መራራ ስሜት ‹‹ጠላታችን እስልምና ሳይሆን አልቃይዳ ነው›› በሚል ግንዛቤ የማይመለስ ሆኗል፡፡ ታላቁ የሽብር ጥቃት በተፈጸመበት የኒውዮርክ አካባቢ መስጊድ የመሥራትም ነገር በየትም ሥፍራ መሬት ገዝቶ የዕምነት ቤትን በመሥራት መብት ብቻ የሚታይ አልሆነም፡፡ ሙስሊሞች ይኼንን ልብ ባይሉና መብታችን ነው ብለው ቅዋሜ በተነሳበት አካባቢ ሊያንፁ ቢሞክሩ፣ የአሜሪካ መንግሥትም ተመልካች ወይም መብት አስከባሪ ቢሆን ጭፍንና ተተናኳይ ቅዋሜ አድጎና ተባዝቶ የአገሪቱን የሃይማኖት ሰላም እንዲረብሽና የእስልምና ተከታዮችም ለአደጋ እንዲጋለጡ ዕድል መስጠት መሆኑ (ይህም በምላሹ ለአክራሪ አሸባሪነት መዛመት ማገዙ አይቀሬ ሀቅ ነው፡፡

ቄሱ ቁርዓንን አቃጥሎ ቢሆን ኖሮ በዓለም ይቀሰቀስ የነበረው ቁጣ አሜሪካን ብቻ በመለብለብ የሚወሰን አይሆንም ነበር፡፡ የሌላውን የእምነት መጽሐፍ በተቃውሞ መግለጫነት በአደባባይ ማቃጠል መብት ተደርጎ በአሜሪካ መወሰዱም ማቃኛ እስካላገኘ ድረስ አሜሪካ በውስጧ አደገኛ እሳት አዳፍና ትቆያለች፡፡

ኢራቅ ውስጥ አሁን እየታየ ያለው ሁኔታ ፀረ እስራኤል አሜሪካ አሸባሪነትን በጭፍኑ ክርስቲያንነትን ጠላት ወደ ማድረግ እንዳይዞር ያሳስባል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ያለው እስልምናና ሙስሊሞችን እንደ አደጋ ማየትም በአጋዥነት እስከ ቀጠለ ድረስ ውሎ አድሮ በምዕራቡ ሠፈር ከፀረ ስደተኞች ዝንባሌ ጋር ተያይዞ በሙስሊሞች ላይ ግብታዊ ጥቃት ማድረስና ማባረር ሊከሰት የሚችል ነው፡፡ ይህ በሌላው ማዕዘን የሚያስነሳው ጥፋት ደግሞ የባሰ ነው፡፡ ከዚህ ልቆም አክራሪነትና አሸባሪነት ከባዮሎጂያዊና ከኑኩሌር የፍጅት ጦር መሣሪያዎች ጋር ተያይዞ ጠቅላላ ዓለም መውጫ የሌለው ችግር ውስጥ እንዳትገባ ያስፈራል፡፡

ከዚህ አሳሳቢ ችግር አኳያ በአገራችን ያለው የሃይማኖት ሰላም ምን ያህል ውድና ብርቅ ሀብት እንደሆነ መገንዘብ አይከብድም፡፡ ይህ ሀብት እንደምን ተጠብቆ ሊቆይልን ቻለ? ይህ ጥያቄ ታሪካዊ ኃላፊነታችንን ለማወቅ የሚያስችል ይመስለኛል፡፡

ባለብዙ ሃይማኖት በሆነቸው ኢትዮጵያ ውስጥ (በነበረን የዕድገት ደረጃ የማያስገርም) ብዙ ነገር ሆኗል፡፡ በኃይል ሃይማኖት ማስለወጥ፣ እምቢ ያሉትን መግደል፣ አንዱን እምነት ነውር አድርጎ ሌላውን ተከባሪና ትክክል ማድረግ፣ ከሥር በዋሉ ሃይማኖቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በመንግሥታዊ ሃይማኖትም ውስጥ በተፈጠሩ የእምነት አንጃዎች ላይ ተካሂዷል፡፡ ምንም ተደረገ ምን አባቶቻችንና እናቶቻችን ሁሉንም ችለውና ተቻችለው እያሳለፉ አብሮ በመኖር የሃይማኖት ሰላምን አቆይተውልናል፡፡ ይህንን ትልቅ ውለታ የአሁኑ ትውልድ ማክበሩን የሚያረጋግጠው የተላለፈለትን የሃይማኖት ሰላም ቅርስ ተንከባክቦ መጠበቅ ከቻለ ነው፡፡     

የአሁኑ ዘመን ትውልድ ከቀደመው ብዙ የሚለይ እንደመሆኑ የሃይማኖት ሰላም እንክብካቤ የሚጠይቀውም ተግባር ተቻችሎ ከመኖር የበለጠ ነው፡፡ የአገርን ነፃነት ሊማርክ የመጣ ጠላትን ለመመለስ ከሚደረግ ሕዝብና እምነት ከማይለይ የነፃነት ተጋድሎ ባሻገር፣ የትኛውም ሃይማኖት ፖለቲካን ካቀነቀነ ወይም እምነትና የፖለቲካ ፓርቲነት ተዛምደው ሃይማኖታዊ ፖለቲከኝነት ከተያዘ፣ አልፎም በአገር ደረጃ ወይም በክፍለ አገር ደረጃ ሃይማኖት መንግሥታዊ ሥልጣን ልሁን ካለ፣ ወይም የመንግሥት ወገንተኝነት ልቀዳጅ ካለና ከተቀዳጀ መዘዝ ይኖረዋል፡፡ መላ አገር ከሞላ ጎደል የአንድ እምነት ተከታይ በሆነበት ሁኔታ እንኳን መንግሥታዊ ሥልጣኑ ሃይማኖታዊ ከሆነ ሃይማኖታዊ ጭቆና ወይም አድልኦ መከተሉ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ንዑሳን በሆኑ ሌሎች ሃይማኖቶች ላይ ብቻ ሳይሆን መንግሥታዊ ከሆነው የአንድ ሃይማኖት መስመር ወጣ ብለው በበቀሉ የዚያው እምነት ክፍሎች ላይም የሚያርፍ ነው ይኼንን ሀቅ መንግሥታዊ ሃይማኖት የመሆን እውነታ ባለበት ቦታና ታሪክ ውስጥ ሁሉ (በእስልምናም በክርስትናም) እናገኘዋለን፡፡

እናም ሃይማኖት ፖለቲካዊ እንዳይሆን፣ ወይም ሃይማኖት መንግሥታዊ እንዳይሆን፣ ወይም መንግሥት ወደ አንዱ ወይ ወደ ሌላው ሃይማኖት እንዳያጋድል መጠበቅ አንዱ ዋነኛ ተግባር ነው፡፡ በዚህ ላይ ሥልጣን ላይ የወጣ ፓርቲ ለፖለቲካ ድጋፍ የሃይማኖት መድረክን ከመጠቀም መራቁና ይኼም ቀጣይነት ማግኘቱ ሃይማኖት ፖለቲካን እንዳይፈተፍት ይከላከላል፡፡ ከዚህ ሌላ የአገሪቱን ሃይማኖቶች አያያዝ የበለጠ ፍትሐዊ ማድረግ፣ በጎረቤት አገሮች ያሉ ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ የሰላም ችግሮች እንዲወገዱ ጠንክሮ መታገል፣ ሃይማኖትን ተከልለው የሚቦተልኩ ቡድኖችና ሃይማኖታዊ መንግሥታት ሰላማችን እንዳይበጠብጡ መጠበቅ፣ እንዲሁም ከየትኛውም የዕምነት ክፍል በኩል የሌላ እምነት ተከታዮችን የማስገለልም ሆነ የማጥላላት ወይም የመተናኮል እንቅስቃሴ እንዳይመጣ (ማለትም የሃይማኖት መከባበር ሁሉም የሚተነፍሰው ምግባር እንዲሆን) አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ይገባል፡፡

አሸባሪነትን የመከላከልና የመዋጋት የትኛውም ዓይነት ዝግጁነትና የተግባር እንቅስቃሴ የአሸባሪነትን ወንጀል ልቅምና ጥረት አድርጎ ማስቀመጥን ታሳቢ ብቻ ሳይሆን ቅድመ ሁኔታ ያደርጋል፡፡ በእንዲህ ያለ ሕግ ላይ የተመሠረተ ግብ ማኅበራዊ ግንዛቤና የሕዝብ ንቃት ሳናደርግ፣ በዚህ ላይ ያልተድበሰበሰና ለትርጉም ያልተጋለጠ ሕዝባዊ ንቃትና ተቀባይነት ሳንገነባ አሸባሪነትን ለመዋጋት አንችልም፡፡

የአገራችን የፀረ አሸባሪነት ሕግ ሲበዛ ቦርቃቃ ነው፡፡ ከሌሎች መካከል በአፈጻጸም ሲጎሳቆል የሚታየውም በዚህም ምክንያት ጭምር ነው፡፡ ተቃውሞና ትችት፣ የተለየ ሐሳብ ሁሉ ጠላቶቻችን የሚሉት ነው፣ ሌላ ሥውር ዓላማ አለው፣ ድርጅታችንን ለአደጋ ያጋልጣል እየተባለ በአሸባሪነት ከመፈረጅ የሚከለክለው ግንዛቤና ንቃት የለንም፡፡ የፀረ አሸባሪነት ሕጋችን ገዢው ንቃትና አፈጻጸም በሰላማዊ ስብሰባና ሠልፍ ውስጥ የሚነሳን ድንገተኛ ሕገወጥነት እንኳንስ በአሸባሪነት ለመፈረጅ፣ በገዛ ራሱ ባህሪ ላይ ተመሥርቶ ሕገወጥ ድርጊት አድርጎ በተራ ወንጀል ለመክሰስ ሕገ ሐሳቡ ነበረ ወይ? የሚል ጥያቄ መመለስን ይጠይቃል፡፡

በሕግ ተለይተው የተመለከቱ ጥፋቶች ሁሉ ቅጣት የሚያስከትሉ የወንጀል ድርጊቶች ናቸው፡፡ የወንጀል ድርጊቶች ሁሉ ግን አሸባሪነት አይደሉም፡፡ በኅቡዕ መደራጀት፣ ሰላማዊ ያልሆነ ትግል ሁሉ ሕገወጥ ናቸው እንጂ የግድ የአሸባሪነት ወንጀል አይደሉም፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...