Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የናይል ጉዳይ ከመጠን ያለፈ የፖለቲካ አጀንዳ እንዲሆን ያደረገው ሚዲያው ነው››

ዶ/ር ውባለም ፈቃደ፣ የምሥራቃዊ ናይል ቀጣና ቴክኒክ ጽሕፈት ቤት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ

ዶ/ር ውባለም ፈቃደ የናይል ቤዚን ኢንሺየቲቭ (ኤንቢአይ) አንድ አካል የሆነውና መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የምሥራቃዊ ናይል ቀጣና የቴክኒክ ጽሕፈት ቤት (ኢንትሮ) ሶሻል ዴቨሎፕመንት ኤንድ ኮሙዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊ ናቸው፡፡ ዶ/ር ውባለም የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በአግሪካልቸራል ኢኮኖሚክስ አጠናቀዋል፡፡ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን (ፒኤችዲ) ደግሞ በዴቨሎፕመንት ፕላኒንግና በስፓሽያል ፕላኒንግ በቅደም ተከተል አግኝተዋል፡፡ በተመድ የፕሮጀክት አገልግሎቶች ጽሕፈት ቤት ተመልምለው ኤንቢአይን በቅድሚያ የተቀላቀሉት የጋራ መተማመንና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ (ሲቢኤስአይ) ፕሮጀክት ዋና ልዩ ባለሙያ ሆነው ነው፡፡ የሲቢኤስአይ ፕሮጀክት ዋና ዓላማ በዓባይ ተፋሰስ አገሮች መካከል ውይይት መፍጠርና ይህም የሐሳብ ልውውጥ እንደ የግሉ የንግድ ዘርፍ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ሲቪል ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማትና ሚዲያ የመሳሰሉ ሌሎች ባለድርሻ አካላትን እንዲያካትት ማድረግ ነው፡፡ ዶ/ር ውባለም ኤንቢአይን ከመቀላቀላቸው በፊት በበርካታ የአፍሪካ አገሮች በተመራማሪነት፣ በመምህርነት፣ በአማካሪነትና በተዛማጅ ጉዳዮች አገልግለዋል፡፡ በአውሮፓም በስፓሽያልና ዴቨሎፕመንት ፕላኒንግ እንዲሁም ማኔጅመንት ዘርፍ ሠርተዋል፡፡ በአሜሪካ የግጭት ማኔጅመንትን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች በገለልተኛ አማካሪነት አገልግለዋል፡፡ በሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኘው ዓለም አቀፍ የዴቨሎፕመንትና ግጭት ማኔጅመንት ማዕከል የፕሮጀክት አስተባባሪ ሆነውም አገልግለዋል፡፡ ዶ/ር ውባለም በቅርቡ በሱዳን ዋድ መዳኒ እንዲሁም በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄዱ ዓውደ ጥናቶችና የሚዲያ ሥልጠና ተገኝተው ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፣ ሰፊ የሥራ ልምዳቸውንም አካፍለዋል፡፡ ሰለሞን ጎሹ የናይል ጉዳዮችን በተመለከተ በመዘገብና መረጃ በማስተላለፍ ላይ ዶ/ር ውባለምን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ቢሯችሁ በዋነኛነት የሚያከናውናቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ውባለም፡- በዋነኛነት የኤንቢአይ የምሥራቅ ናይል ሰብሲዲያሪ አክሽን ፕሮግራምን (ኢንሳፕ) እናስፈጽማለን፡፡ ኢንሳፕ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳንና ሱዳንን ያቅፋል፡፡ እርግጥ ነው ግብፅ እ.ኤ.አ. ከሰኔ ወር 2010 ጀምሮ በኤንቢአይ (ኢንሳፕ) ያላትን ተሳትፎ አቋርጣለች፡፡ ነገር ግን ኤንቢአይ በሚያዘጋጃቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ትሳተፋለች፡፡ ለአብነትም የናይል የሚኒስትሮች ስብሰባና በዓመት ሁለት ጊዜ በሚካሄደው የናይል ዴቨሎፕመንት ፎረም ያላትን ተሳትፎ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ኢንሳፕ የምሥራቅ ናይል አገሮችን አንድ ላይ በማሰባሰብ ያላቸውን ልዩ አቅም ለመጨመር ይሠራል፡፡ የእነዚህ አራት አገሮች የሕዝብ ብዛት በአጠቃላይ ከተፋሰሱ 11 አገሮች የሕዝብ ብዛት ጋር ሲነፃፀር 50 በመቶ የሚይዝ በመሆኑ የሚያንሰራራ አካባቢያዊ ገበያ መፍጠር ይችላሉ፡፡ እነዚህ አገሮች በታሪክ፣ በባህልና በኃይድሮሎጂም የተቆራኙ ናቸው፡፡ በአካባቢው ከውኃ ኃይል የማመንጨት ከፍተኛ አቅም ያለ በመሆኑ ለኃይል ንግድም የተመቸ ነው፡፡ የግብርና ምርትን የማሳደግ አቅምም እንዲሁ አለ፡፡ ውኃን በተሻለ ሁኔታ በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ ይቻላል፡፡ አካባቢው ተስፋዎች እንዳሉት ሁሉ የራሱ ተግዳሮቶችም አሉት፡፡ የውኃ አቅርቦት ከቦታ ቦታና ከጊዜ ጊዜ የተለያየ ነው፡፡ 86 በመቶ የሚሆነው የናይል ውኃ ከኢትዮጵያ ከፍታማ ቦታዎች የሚመነጨው በዓመት ውስጥ በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ይህ ንዑስ ተፋሰስ ከተራዘመ ድርቅና ከከፍተኛ ጎርፍ ትልቅ ጉዳት ይደርስበታል፡፡ ይህ ሁኔታ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ይበልጥ ተወሳስቧል፡፡ በአካባቢው በትነት ሳቢያ ከፍተኛ የሆነ የውኃ እጦት ይከሰታል፡፡ በዚህ ንዑስ ተፋሰስ ነው የናይል ውኃ የሰሐራ በረሃን የሚቀላቀለው፡፡

ኢንሳፕ በመሠረታዊነት ሁለት አካባቢዎች ላይ አተኩሮ ይሠራል፡፡ እነዚህም የውኃ ሀብት ኢንቨስትመንት ዝግጅት ትብብርና የአባል አገሮች ትብብርን ማቀናጀት ናቸው፡፡ ይህም ለአስተዳደር የሚሰጠውን የጽሕፈት ቤት አገልግሎት ድጋፍ ይጨምራል፡፡ የሚዘጋጁት የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ማኅበራዊ ጠቀሜታ ያላቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ ዋናው ዓላማ ነው፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ድህነትን የሚያስፋፉ ከሆነ፣ በአካባቢው ማኅበረሰብ ወይም በኅብረተሰቡ በአጠቃላይ መካከል ልዩነቶችን የሚፈጥሩ ከሆነ አሳዛኝ ነው የሚሆነው፡፡ ምንም እንኳን ሐሳቡ መልካም ቢሆንም፣ ዕቅዱ በትህትናና በጥንቃቄ ካልታጀበ በቸልተኝነት ማኅበራዊ ግጭቶችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ ለዚህም ነው እነዚህ ፕሮጀክቶች ያለ ኅብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ እንዲከናወኑ የማንፈልገው፡፡ ሕዝቡ በተለይ ፕሮጀክቶቹ በቀጥታ የሚመለከቱት ሕዝብ ማማከር፣ መረጃ መስጠትና ቅሬታውን የሚያቀርብበት መድረክ ማመቻቸት ይገባል፡፡ በተቻለ መጠን የሕዝቦችን መልሶ መስፈር ለማስቀረት መጣር ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ማድረግ የግድ በሚልበት ወቅት ትርጉም ያለውን ተሳትፎ ለማጎልበት መልሶ ማስፈሩን ከሕዝቡ ጋር ማድረግ ነው እንጂ እነሱ ላይ ማድረግ አያስፈልግም፡፡ በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ሕዝቡ እንዲያሳልፍ መረጃው በራሳቸው ቋንቋ ሊዘጋጅና ተደራሽ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ስናጠቃልለው የእኔ ክፍል ማኅበራዊ ልማትን ለማስፋፋትና ለማጠናከር፣ እንዲሁም የኮሙዩኒኬሽን ልማት ላይ ይሠራል፡፡ ይህም ማኅበራዊ ፍትሕ፣ ማኅበራዊ ቁርኝት፣ የፆታ እኩልነት፣ የድህነት ቅነሳና ተሳትፎን ይጨምራል፡፡ እነዚህን በተለያዩ መንገዶች ለማስፋፋት እንጥራለን፡፡ ድንበር ተሻጋሪ የፖሊሲ ቀረፃዎችን እንደግፋለን፡፡ የባለድርሻዎችን ተሳትፎ ለማጠናከር የአቅም ግንባታ ሥልጠና እንሰጣለን፣ መድረኮችንም እናመቻቻለን፡፡      

ሪፖርተር፡- ከእነዚህ ባለድርሻ አካላት መካከል አንዱ የሆነውን የሚዲያ ሚና በናይል ጉዳዮች ላይ እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር ውባለም፡- የናይል ትብብርን ለማጠናከር የጋራ ፍላጎቶችን በማሳደግ ሚዲያ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ሚና አለው፡፡ ናይል የፖለቲካ ድንበሮችን አያውቅም፡፡ በኢንትሮ ʻድንበር የለሽ ትንታኔʼ  የሚል ፕሮግራም አለን፡፡ የፖለቲካ ድንበሮች ባይኖሩ ናይልን እንዴት እንጠቀመው ነበር? አንድ ቦታ ላይ የሚፈጸም ነገር የላይኛውን ወይም የታችኛውን ተፋሰስ አገሮችን እንዴት ይነካል? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ እንሞክራለን፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የሚደረግ ምክክር፣ ዕቅድና ድርድር በጠንካራ፣ ብቃት ያለውና ታማኝ የመገናኛ ዘዴ መታገዝ ይኖርበታል፡፡ ሚዲያ የሕዝብን አስተያየትና አመለካከት በመቅረፅ፣ እንዲሁም ሕዝቡ ለአንድ የተወሰነ አጀንዳ ድጋፍ እንዲሰጥ ወይም እንዲቃወም ለማንቀሳቀስ ቁልፍ ሚና ይጫወታል፡፡     

ሪፖርተር፡- በናይል ተፋሰስ አገሮች የሚሠራ ሚዲያ የናይልን ሳይንስ በአግባቡ ተረድቶ ሪፖርት እያደረገ ነው ብለው ያምናሉ?

ዶ/ር ውባለም፡- በአካባቢው የሚስተዋለው አንዱ መሠረታዊ ችግር ያለመታደል ሆኖ የሚዲያውን ባህል የተመለከተ ነው፡፡ የሚዲያው ባህል ገና በማደግና በመውጣት ላይ ያለ ነው፡፡ ናይልን የተመለከቱ ሳይንሳዊና እውነታን የተመለከቱ ዘገባዎችን ሲሠራ በአብዛኛው ቅድመ ታሪክና ምርምር አያደርግም፡፡ ስለዚህ ብዙ ጊዜ በርካታ የእውነታ መፋለሶች ይታያሉ፡፡ የማረም አጋጣሚ ቢኖርም የተሳሳቱ ምልከታዎች ግን አይታረሙም፡፡ ሚዲያው የማስተማር ሚናውን በአግባቡ እየተወጣ ነው ማለትም አይቻልም፡፡          

ሪፖርተር፡- በበርካታ የጥናት ሥራዎችም ላይ ስለሚዲያው ሚና ሲያወሱ የሚዲያን አጀንዳ የመቅረፅ ሚና ይገልጻሉ፡፡ በናይል ተፋሰስ ትርጉም ያለው ሚና ለማምጣት ሚዲያው እንዴት ነው አጀንዳን መቅረፅ ያለበት?

ዶ/ር ውባለም፡- አጀንዳ የመቅረፅ ሒደት ችግሮችና አማራጭ መፍትሔዎች የሕዝብ ትኩረት የሚያገኙበት ወይም የሚያጡበት ሒደት ነው፡፡ አጀንዳዎች ያላቸው አንፃራዊ ጠቀሜታ ቅርፅ የሚይዝበት ሒደትም ነው፡፡ ነገር ግን ተቃራኒውም እውነት ነው፡፡ ነገሮች አጀንዳ መሆናቸውን እንዲያቆሙም ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፡፡ የሚዲያ ተጠቃሚው ሕዝብ አጀንዳዎችን ከአዕምሮው ሳያወጣ እንዲያስብባቸው ለማድረግ ሚዲያዎች ይወዳደራሉ፡፡ ከዚህ አንፃር አጀንዳ መቀንበብም (Framing) በጣም አስፈላጊ ቴክኒክ ነው፡፡ ለተመሳሳይ ጉዳይ አሉታዊ ወይም አዎንታዊ ገጽታ ማላበስ ይቻላል፡፡     

ሪፖርተር፡- የተሻለ አጀንዳ ቅንበባ በናይል ጉዳይ የሚዲያን ገንቢ ሚና ይጨምራል ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ውባለም፡- በተለያዩ የሚዲያ ውጤቶች ስለናይል የሚጻፉትን ሁሌም እገመግማለሁ፡፡ አንድ አዝማሚያ በግልጽ ይታያል፡፡ ዓለም አቀፍ ሚዲያው ወደ ናይል ፊቱን የሚያዞረው የግጭት ጽሑፍ ለማቅረብ ብቻ ነው፡፡ እጅግ ትልቅ የሆነ አውዳሚ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ለ11 አገሮች የሕይወት መሠረት የሆነን ታላቅ ጉዳይ ስሜት ቀስቃሽ አድርጎ ብቻ ማቅረብ ተገቢ አይደለም፡፡ ሚዲያ የአንድን ጉዳይ አሉታዊ ገጽታ ብቻ በመጻፍና ጠባብ አቅጣጫ በመከተል፣ ልዩነት ላይ ብቻ አተኩሮ፣ ስለማይቻለውና ቅሬታ ስለቀረበበት ጉዳይ ብቻ ሁሌም በመጻፍ ጎጂ ጎን ሊላበስ ይችላል፡፡ ነገር ግን ሚዲያ የተለያዩ አካላት ያላቸውን የጋራ ስሜት በማውጣት የማቀራረብ ሚናም መጫወት ይችላል፡፡ ለአብነትም ሚዲያው አንድ አማካይ ግብፃዊ ዜጋ ራሱን በአንድ አማካይ ኢትዮጵያዊ ዜጋ በመተካት ዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነ ግብርና እንዴት እንደሚከናወን ማሳየት ይችላል፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ ከፍታማ ቦታዎች የሚኖረው ገበሬ ሕይወት ምን እንደሚመስልና ለሕይወቱ የሚያሠጉ በርካታ አደጋዎችን እንዴት በየቀኑ እንደሚጋፈጥ ግንዛቤ መፍጠር ይችላል፡፡ በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የኢትዮጵያ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አገሪቱ በምታገኘው ዝናብ ጥሩነት ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ ስለዚህ የግብፅ የሚዲያ ባለሙያዎች ኢትዮጵያዊ ገበሬ ወይም አማካይ ዜጋ ምን እንደሚመስል፣ ምን ዓይነት የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት አቅርቦት እንደሚያገኝ፣ የሚያገኘው ንፁህ የመጠጥ ውኃ ምን ያህል እንደሆነ ለአንባቢዎቻቸው ማሳየት አለባቸው፡፡ በሁሉም አቅጣጫ ጉድለት ነው የሚያገኙት፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ የሚዲያ ባለሙያዎችም ከግብፅ የውኃ አቅርቦት ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነው በናይል ላይ የተንጠለጠለ ስለመሆኑ ለአንባቢዎቻቸው ማሳየት አለባቸው፡፡ ግብፅ በሰሃራ በረሃ መሀል ላይ እንደምትገኝም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ፍራቻቸው ተገቢ እንደሆነ መረዳት ይጠይቃል፡፡ ሚዲያችን ጉዳዮችን በገንቢ ሁኔታ መቀንበብ አለበት፡፡ በጣም ከባድ የሚመስል ጉዳይ እንደገና ተቀንብቦ ገንቢ ገጽታ በመያዝ ከአንድ ወንዝ የሚጠጡ ጎረቤት አገሮችን ለማቀራረብ ሊውል ይችላል፡፡ ለምሳሌ ያህል ብዙ ሰዎች ታላቁ የህዳሴ ግድብ አሉታዊ ገጽታ ያለው ፕሮጀክት እንደሆነ ቀንብበው ለማሳየት ይሞክራሉ፡፡ በአብዛኛው የሚጎላው ግድቡ የታችኛው ተፋሰስ አገሮችን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጎዳ ተደርጎ ነው፡፡ በተወሰነ መልኩ ይህ የታሪኩ አንድ አካል ሊሆን ይችላል፡፡ የወንዙን የተፈጥሮ ፍሰት አቋርጠህ ግድብ ስትሠራ አካባቢያዊና ሌሎች ሊጠገኑ የሚችሉ ተፅዕኖዎች መኖራቸው የማይቀር ነው፡፡ ምንም ዓይነት ጉዳት አያስከትልም ማለት ከሳይንስ አንፃር ትክክል አይደለም፡፡ በሌላ በኩል በአሉታዊ ገጽታ ላይ ብቻ በማተኮር ጉዳዩን አጋኖ ማቅረብ ስህተትና ከሞራል አንፃርም ተቀባይነት የሌለው ነው፡፡

የጉዳዩን ሁሉንም ገጽታዎች ሚዛናዊና ፍትሐዊ በሆነ አስተማማኝ እውነት፣ ቁጥሮችና ማስረጃዎች በማቅረብ ማሳየት ኃላፊነት የሚሰማው የሚዲያ ባለሙያ ግዴታ ነው፡፡ ታላቁ የህዳሴ ግድብ በጎ ገጽታዎችም አሉት፡፡ በአንድ በኩል ተፋሰሱ ከአንድ ይልቅ ሁለት ትልልቅ ግድቦች ቢኖሩት መልካም ነው፡፡ ይህ እ.ኤ.አ. ከ1976 እስከ 1988 አጋጥሞ እንደነበረው ዓይነት የተራዘመ ድርቅ ዳግም ቢከሰት ለመቋቋም በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ አራቱ አገሮች ድርቅ የመቋቋም አቅማቸው ሁለት ግድቦች በመኖራቸው ይጨምራል፡፡ ይህ ግን የሚቻለው አገሮቹ በህዳሴ ግድቡ መግባቢያ ስምምነት ሰነድ ላይ እንደፈጸሙት በመተባበር ግድቦቹን ሥራ ላይ የሚያውሉ ከሆነ ነው፡፡ በምሥራቅ ናይል ሥራ ላይ ያሉ ግድቦች የሚሠሩበትን መንገድ ማቀናጀት የግድ ነው፡፡ ለዚህና ለሌሎች አሳማኝ ምክንያቶች አገሮቹ ወደዱም ጠሉም በትብብር መሥራታቸው የግድ ነው፡፡ ይኼ የምርጫ ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገር ግን አገሮቹ ትብብሩን ወደ መሬት ለማውረድ ማድረግ ባለባቸው ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ቁጭ ብለው በመነጋገር መስማማት አለባቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ሚዲያው በተፋሰሱ አገሮች ውሳኔ አሰጣጥ ሒደት ላይ እንዴት ተፅዕኖ መፍጠር ይችላል?

ዶ/ር ውባለም፡- አገሮቹ ጥረቶቻቸውን ማቀናጀትና ዕቅዶቻቸውን በአመክንዮ መምራት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ በላይኛው ተፋሰስ አገሮች ከፍታማና ቀዝቃዛ ቦታዎች የውኃ ማከማቻ መሠረተ ልማት በመገንባት የውኃ ትነትን በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ውኃ ማትረፍ ይቻላል፡፡ ነገር ግን የታችኛው ተፋሰስ አገሮች ውኃቸው ከግዛታቸው ውጪ በመቀመጡ ከሥነ ልቦና አንፃር ላይረጋጉ ይችላሉ፡፡ ይህን ለመፈጸም ፍጹም የሆነ መተማመንና እምነት መፍጠር አለብህ፡፡ ሚዲያው ኩነቶችንና ክስተቶችን በመዘገብ ራሱን ሳያጥር እንዲህ ዓይነት መረጃዎችንና ሳይንሳዊ ግኝቶችን ፈልቅቆ በማውጣት ለኅብረተሰቡ እንዲደርስ በማድረግ አገልግሎት ሊሰጥ ይገባል፡፡ ምን እንደሚቻል ፖሊሲ አውጪዎችን ጨምሮ ለሕዝቡ በማስተማር ላይ ትኩረት የሚያደርግ ልማታዊ ኮሙዩኒኬሽን የተባለ ራሱን የቻለ ዘርፍ አለ፡፡ ኅብረተሰቡ ውኃን እንዴት በአግባቡ መጠቀም እንደሚቻልና በግብርና ንግድ ውኃን እንዴት ማትረፍ እንደሚችል ሚዲያው በአግባቡ ቢያስተምረው፣ መሪዎችም ድፍረት የተሞላበትና አዳዲስ ውሳኔዎችን ለመውሰድ ይበረታቱ ነበር፡፡ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት፣ የሕዝቡን አመለካከት በመቅረፅና በማንቀሳቀስ ብሩህና ደፋር መሪዎችን ለመፍጠርም ቁልፍ ሚና ሊጫወት ይችላል፡፡ በየትኛው የኢኮኖሚ ዘርፍ የተፋሰሱ አገሮች ከሌላኛው የተሻለ ተፈጥሯዊ የሆነ አንፃራዊ ተጠቃሚነት እንዳላቸው በማሳየት የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ማጉላትም ይችላል፡፡ ሚዲያ በናይል ባለድርሻ አካላት መካከል ግንኙነት እንዲኖር ድልድይ ሆኖም ሊያገለግል ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- እ.ኤ.አ. በ1999 ኤንቢአይ ከተቋቋመ ጀምሮ ከሚዲያ ጋር በቅርበት ይሠራል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ብሔራዊ ሚዲያዎች ስለናይል በሚጽፉበት መንገድ ላይ በሒደት መሠረታዊ ለውጥ አይተዋል?

ዶ/ር ውባለም፡- ኤንቢአይ ገና ሥራ ሲጀምር እኔ በባለድርሻ አካላት መካከል መተማመን እንዲፈጠር በሚሠራው የሲቢኤስአይ ፕሮጀክት ውስጥ እሠራ ነበር፡፡ በቅድሚያ ከሠራናቸው ሥራዎች አንዱ የናይል የሚዲያ ባለሙያዎችን ከሁሉም አባል አገሮች በማሰባሰብ እንዲገናኙ ማድረግ ነበር፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ናይልን ለመሸፈን ፍላጎት ያላቸውና እየሸፈኑ ያሉ ባለሙያዎችን ክልላዊ የሚዲያ ኔትወርክ እንዲፈጥሩ ሐሳብ አቀረቡ፡፡ በዚህም መሠረት የናይል ሚዲያ ኔትወርክ (ኤንኤምኤን) ተቋቋመ፡፡ ይህን ኔትወርክ ስኬታማ ለማድረግ በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ፕሮጀክቱ የመጀመሪያውን ተነሳሽነት ወስዷል፡፡ በእኛ ድጋፍና የገንዘብ ዕርዳታ ኔትወርኩ የተለያዩ ስብሰባዎችን አድርጓል፡፡ ነገር ግን ለኤንኤምኤን የምናደርገው ድጋፍ ሊቀጥል አልቻለም፡፡ ፕሮጀክቱ ራሱ ከሦስት ዓመት በኋላ ተዘግቷል፡፡ ከዚያ በኋላ ኔትወርኩ ጠፍቷል፡፡ ነገር ግን እኛ አስበን የነበረው ተነሳሽነቱና ንቅናቄው አንዴ ከተጀመረ የሚመለከታቸው አካላት ያስቀጥሉታል የሚል ነበር፡፡ እኛ አስፈላጊ የሆኑ መረጃ፣ ዳታና ዕውቀት መቅሰሚያ ሥራዎችን እናቀርባለን፡፡ ነገር ግን ከዚያ አልፈን የሚዲያ ባለሙያዎች በቋሚነት እንዲገናኙ ማድረግ አንችልም፡፡ በዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ በመታገዝ ኔትወርኩን ለመፍጠር አሁንም እየጣርን ነው፡፡ ሚዲያው አሁንም ገና ያልተጫወተው ብዙ ሚና አለ፡፡ የተወሰኑ የሚዲያ ባለሙያዎች በናይል ጉዳዮች ላይ ስፔሻሊስት መሆን አለባቸው፡፡

ናይል ማለት ውኃ ማለት አይደለም፡፡ ናይል ሕይወት የሚደግፍ ሥርዓት ነው፡፡ ናይል ማለት ምግብ፣ ኢነርጂ፣ ኃይል፣ የውኃ ትራንስፖርት፣ ጂኦፖሊቲክስ፣ የዱር እንስሳ፣ ባህልና ሌላ ሌላም ጉዳይ ነው፡፡ ናይል በሚዲያ በበቂ መንገድ ካለመሸፈኑም ባሻገር ተገቢ ባልሆነ መንገድም እየቀረበ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ የሚዲያ ዋናው ሚና ትክክለኛ፣ እውነተኛና ተጨባጭ መረጃ መስጠት ነው፡፡ ሚዲያው ይህን ካደረገ ተጠቃሚው በሒደት በመረጃው ምን ማድረግ እንዳለበት ያውቃል፡፡ ያለሚዲያው የናይል ትብብር ግቡን ሊያሳካ አይችልም፡፡ ሚዲያውን እንቀርፀዋለን ወይም የሚሠራበትን ባህል በአዲስ እንለውጠዋለን ብለን አናስመስልም፡፡ በምሥራቅ ናይል እየተካሄዱ ያሉ በርካታ ኢንቨስትመንቶች ላይም ተፅዕኖ ለማድረግ አንሞክርም፡፡ በክፉም ሆነ በበጎ ጎኑ ሚዲያው የራሱ ችግሮች አሉበት፡፡ ነገር ግን በርከት ያለ ትክክለኛ መረጃ ቢኖረን ትብብሩ በተሻለ መጠናከሩ የማይቀር ነው፡፡ ሚዲያው በሚሸፍነው ጉዳይ ላይ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ለማካተት ቢጥር፣ አስቦና አቅዶ ወይም በቸልተኝነት የተሳሳቱ መረጃዎች እንዲካተቱ ወይም ጠቃሚ መረጃዎች እንዳይካተቱ ማድረጉን ቢቀንስ፣ ወይም ከተቻለ በጠቅላላ ቢያስወግድ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ኤንቢአይ ወይም ኢንትሮ ያሏቸውን የዕውቀት ሀብቶች፣ መረጃዎችና ኤክስፐርቶች በመንተራስ እንዲሁም በራሱ ጥረት በሚያገኛቸው መረጃዎች ገንቢ ሚና መጫወት ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ሚዲያው ሊጫወት ከሚገባው ከዚህ ተመራጭ ሚና በተቃራኒ በናይል ጉዳይ ላይ የሚደረገው የሐሳብ ልውውጥ በበላይነት የሚከናወነው ከፍተኛ ስሜታዊነት በሚስተዋልባቸው፣ ግጭትና ውጥረት በሚያነሳሱ ፖለቲከኞች ነው፡፡ የእነዚህ ፖለቲከኞች ድምፅ ደግሞ በናይል ላይ ካለው ሳይንሳዊ መረጃ ይልቅ ለሚዲያው ቅርብ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በክልሉ ያለው የፖለቲካ ባህል ሳይለወጥ የሚዲያውን ባህል እንዴት መቀየር ይቻላል?

ዶ/ር ውባለም፡- ይኼ ለምርጫ አስቸጋሪ ነው፡፡ ቁርጥ ያለ መልስ የለኝም፡፡ ነገር ግን እውነትነት የሌለውን መረጃ የመዋጊያ ብቸኛ መንገድ ትክክለኛ መረጃ ማቅረብ ነው፡፡ የናይል ጉዳይ በከፍተኛ ሁኔታ የፖለቲካና የደኅንነት ጉዳይ ሆኖ እየቀረበ በመሆኑ እስማማለሁ፡፡ የሐሳብ ልውውጡ በፖለቲካ መደቡ የበላይነት እየተካሄደ ነው፡፡ እኛ እየጣርን ያለነው ናይልን በዋነኛነት ወይም በብቸኝነት የፖለቲካና የደኅንነት ችግር አድርጎ የማየት የሐሳብ ልውውጡን ወደ የተፈጥሮ ሀብት ማኔጅመንት ችግር ለማሸጋገር ነው፡፡ ከመጠን ባለፈ የፖለቲካ ገጽታ ሲላበስ ትክክለኛ መረጃ መጣመሙ የማይቀር ነው፡፡ ይህን ለማስተካከል ሚዲያው ከባድ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሚዲያው ይህን ቢያንስ ማስተካከል ወይም ደግሞ ማረም ይችላል፡፡ ፖለቲከኛ የቱንም ነገር ሊናገር ይችላል፡፡ የተሳሳተ ነገር ከተናገረ የመሞገትና ትክክለኛውን መረጃ ማቅረብ የአንድ ብልህ ጋዜጠኛ ግዴታ ነው፡፡ እርግጥ ነው ትክክለኛ መረጃ የሚሰጡ ጥሩ ፖለቲከኞችም አሉ፡፡     

ሪፖርተር፡- የናይል ጉዳዮች አስፈላጊ ባልሆነ መንገድ የፖለቲካ ጉዳይ ሆነው እየቀረቡ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ፡፡ ከዚህ አንፃር በጉዳዩ ላይ ያለውን ዓለም አቀፍ ፍላጎት እንዴት ይገመግሙታል?

ዶ/ር ውባለም፡- ናይል በጣም ጠቃሚ ተፋሰስ ነው፡፡ ስትራቴጂካዊ አቀማመጥ ባለው ክልል የሚገኝ ነው፡፡ በታሪክ ኃያላን ነገሥታት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ዋና ዋና ጦርነቶችን በክልሉ አድርገዋል፡፡ ስለዚህ የናይል ትብብር ውጤት ላይ ዓለም አቀፍ የኃይል ግንኙነቱ በእርግጠኝነት አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን ይኼ ብቸኛው ወሳኝ ምክንያት አይሆነም፡፡ የናይል ጉዳይ ከመጠን ያለፈ የፖለቲካ አጀንዳ እንዲሆን አንዱ አስተዋጽኦ ያደረገው ራሱ ሚዲያው ነው፡፡ ለምሳሌ ሚዲያው ‘የውኃ ደኅንነት’ የሚል አባባል ይጠቀማል፡፡ ይህንን ማንም አይረዳውም፡፡ የውኃ ደኅንነቱ የተጠበቀ አገር ምን ማለት ነው? ምን ያህል ውኃ ነው የአንድን አገር የውኃ ደኅንነት የሚያረጋግጠው? ከናይል አገሮች የየትኛው የውኃ ደኅንነት ነው የተሻለ የተረጋገጠው? ይኼ ጽንሰ ሐሳብ ሕጋዊ፣ ፖለቲካዊ ወይስ ኢኮኖሚያዊ ነው? ከየት ነው የመነጨው? ሚዲያው ከመጠቀሙ በፊት ሊረዳው ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- ናይልን በተመለከተ ሚዲያው የሚሰጠው አብዛኛው ሽፋን አሉታዊ ገጽታዎች ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ በከፊል የሚገለጸው መጥፎ ዜናዎች ከጥሩ ዜናዎች ይልቅ ይሸጣሉ በሚለው ነው፡፡ ሚዲያው ለበጎና ገንቢ ጉዳዮች ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጥ ምን እንዲያደርግ ያሳስባሉ?

ዶ/ር ውባለም፡- የግጭት ዜናዎች የበለጠ ይሸጣሉ፡፡ የግጭት ዜናዎች ይበልጥ የሚስቡን በተወሰነ መንገድ ግጭቱ እኛን ይነካል ብለን ስለምናስብ ነው፡፡ ነገር ግን እንደ አንድ የሠለጠነ የሰው ልጅ ከዚያ ወጣ ብለን ማሰብ ይኖርብናል፡፡ ኤንቢአይ ባለፉት ዓመታት በርካታ ነገሮችን ሠርቷል፡፡ ነገር ግን ስለእነዚህ ስኬቶች የሚያወራ ኃላፊነት የሚሰማው ዓለም አቀፍ ሚዲያ አይታይም፡፡ ዓለም አቀፍ ሚዲያው የተለየ አጀንዳ ሊኖረው ይችላል፡፡ ምናልባትም እንደ ብሔራዊ ወይም ክልላዊ ሚዲያ ኃላፊነት አይሰማው ይሆናል፡፡ አሳዛኙ ነገር ብሔራዊና ክልላዊ ሚዲያውም ግጭት ላይ ማተኮሩ ነው፡፡ ለዚህ የተዘጋጀ መፍሔ የለኝም፡፡ ነገር ግን በጎ ጎኖችን ደጋግሞ በመጻፍ አዲስ ባህል መፍጠር ይቻላል ብዬ አምናለሁ፡፡ መጥፎ ዜናዎችን መጻፍ በሒደት ባህል እንደሆነ ሁሉ ገንቢ ዜናዎችን መጻፍም ባህል ሊሆን ይችላል፡፡ በተወሰነ ሁኔታ የሚዲያ ሥራ ጥበብ የሚጠይቅ ነው፡፡ በጣም በፈጠራ የታደሉ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ባለሙያዎች ካሉ የሚጻፈው ነገር አንባቢን እንዲስብ ማድረግ ቀላል ነው የሚሆነው፡፡

ሪፖርተር፡- በብሐራዊ ጥቅምና በሚዲያ ኃላፊነት መካከል ያለውን ግንኙነት እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር ውባለም፡- ከተጨባጭ ሁኔታና በጥብቅ ከእውነታው ጋር የሚስማማ ከሆነ ብሔራዊ ስሜት ጥሩ ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- በአጠቃላይ የሚዲያ ሚናን በተመለከተ ሁለት መሠረታዊ ክርክሮች ይሰማሉ፡፡ በአንድ በኩል ሚዲያ ተጨባጩን እውነታ ከመዘገብ የተለየ ሚና የለውም በሚል የሚከራከሩ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ገንቢ ወይም የሌላ የተሻለ ግብ ማግኛ መንገድ አድርገው ሚዲያውን የሚያዩ፣ ሚዲያ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ወይም አገር ለመቀየር የሚያስችል ሥራ ሊሠራ ይገባል የሚሉ አሉ፡፡ ከየትኛው ወገን ጋር ይስማማሉ?

ዶ/ር ውባለም፡- የማንኛውም ሚዲያ የመጨረሻ ዓላማ እውነትን መናገር ነው፡፡ ስለሚዲያ ገንቢ ሚና ስናወራ ሚዲያ የተፋሰሱ አገሮች ስለሚገጥማቸው የጋራ አደጋ የማስጠንቀቂያ ሥራ መሥራት አለበት ማለታችን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ብሔራዊና ክልላዊ ሚዲያ የተለየ ኃላፊነት ኖሮበት ሕዝቡን ማስተማር አለበት፡፡ እነዚህን ትምህርቶች የሚሰጠው ደግሞ ክርክር የማይቀርብባቸው ሳይንሳዊ መረጃዎችን ተመርኩዞ ነው፡፡ ይኼ ወገንተኝነት የሚንፀባረቅበት ሥራ አይደለም፡፡ እንዲያውም ሕዝባዊ አገልግሎት ነው፡፡ በዚህ ሒደት የሚዲያ ነፃነት ጥያቄ ውስጥ ሊገባ አይችልም፡፡ የተለያዩ ሐሳቦችን ማስተናገድ አለበት፡፡ ይህ ሲባል ግን ማንም እየመጣ የፈለገውን እንዲል መፍቀድ አለበት ማለት አይደለም፡፡፡ ይኼን ስል ቅድመ ምርመራ ይደረግ ለማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የተባለውን አንባቢያን የሚያነፃፅሩበት ታሪካዊ ዳራና ሌሎች ጠቃሚ መረጃዎች፣ ቁጥሮችና ዳታዎች አብረው መቅረብ አለባቸው፡፡ ሚዲያው የተለያዩ ድምፆችን ሲያስተናግድ እነዚህ ድምፆች ለጉዳዩ ተገቢነት ያላቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ መልካም ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሥራቸውን በነፃነት ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲያከናውኑ ዋስትና የሚሰጣቸው ሕግ የለም›› አቶ አመሐ መኮንን፣ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች

ለበርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በፍርድ ቤት በመሟገት የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጠበቃና የመብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን የፈረንሣይና  የጀርመን መንግሥታት በጋራ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የላቀ...

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....

‹‹ሥራችን ተከብሮ እየሠራን ነው ብዬ አስባለሁ›› ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር

ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነቶች ሲሠሩ የቆዩትና በ2014 ዓ.ም. የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን በዋና ኦዲተርነት እንዲመሩ የተሾሙት  ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ በኦዲት ክፍተቶች ላይ...