ከሁለት ዓመት በፊት ‹‹ሃይማኖታዊ መንግሥት ማቋቋም›› የሚል ፖለቲካዊ ግብ በማስቀመጥ ሲንቀሳቀሱ ተገኝተዋል ተብለው ክስ ተመሥርቶባቸው ሲከራከሩ የከረሙት የቢላል ሬዲዮ ዋና አዘጋጅን ጨምሮ 20 ተከሳሾች፣ ማክሰኞ ታኅሳስ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. የቅጣት ውሳኔ ተላለፈባቸው፡፡
በወቅቱ በሽብር ተግባር ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በመታየት ላይ የነበሩትን እነ አቡበከር አህመድንና እነ ኤልያስ ከድር የተባሉ ተከሳሾችን ከእስር ለማስፈታት ሲንቀሳቀሱ፣ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው በክሱ ላይ የተጠቀሱት የቢላል ሬዲዮ ዋና አዘጋጅ ካሊድ መሐመድና ጋዜጠኛ ዳርሰማ ሶሪን ጨምሮ 20 ግለሰቦች ናቸው፡፡
በወቅቱ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የነበሩትና ‘የሙስሊሙ ማኅበረሰብ መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ’ እየተባሉ የሚጠሩትን እነ አቡበከር አህመድን መንግሥት ማሰሩ ትክክል እንዳልሆነ እየገለጹ፣ ፍርደኞቹ ቅስቀሳ ያደርጉ እንደነበር የቅጣት ውሳኔው ያስረዳል፡፡
ሕዝበ ሙስሊሙን ወደ አመፅ በማስገባት የሽብር ተግባር በመፈጸምና በመንግሥት ላይ ጫና በመፍጠር፣ መንግሥት አማራጭ ሲያጣ እንዲፈታቸው ለማድረግ በራሪ ወረቀቶችን አዘጋጅተው እንደነበር ክሱ ይጠቁማል፡፡ በአዲስ አበባ፣ በጅማና በወልቂጤ ከተሞች በራሪ ወረቀቶችን በመበተን፣ ሕገወጥ ሠልፎችን በማዘጋጀት የአመፅ ቅስቀሳ ለማድረግ ሃያዎቹም ፍርደኞች ተሳትፎ ማድረጋቸውን
ፍርድ ቤቱ በቅጣት ውሳኔው ዘርዝሮ አቅርቦ ነበር፡፡
የቢላል ሬዲዮ ዋና አዘጋጅ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ አበባ አንዋር፣ ቤኒንና አወልያ መስጊዶች በተካሄዱ አመፆች ላይ በመገኘት ኅብረተሰቡን ለአመፅ የሚያነሳሱ ቅስቀሳዎችን ማለትም ‹‹ድምፃችን ይሰማ፣ የታሰሩ ኮሚቴዎች ይፈቱ፣ የአህባሽ አስተምህሮን መንግሥት በኃይል ሊጭንብን አይገባም…›› በማለት ሲሳተፉ እንደነበር ክሱ ያብራራል፡፡ ሌሎቹም ፍርደኞች ተመሳሳይ ድርጊቶችን በተናጠልና በቡድን በመሆን መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ማስፈሩን፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ታኅሳስ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. የሰጠው የቅጣት ውሳኔ ያስረዳል፡፡
ዓቃቤ ሕግ እንደ ክሱ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ ማስረዳቱን ፍርድ ቤቱ ገልጾ፣ ፍርደኞቹ እንዲከላከሉ ውሳኔ ሰጥቶ ነበር፡፡ ፍርደኞቹም የተከላከሉ ቢሆንም፣ የዓቃቤ ሕግን ክስና የምስክሮች ቃል ማስተባበል እንዳልቻሉ ተነግሯቸው የጥፋተኝነት ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡ በመሆኑም ከፍርደኛ ዳርሰማ ሶሪ ባንቃሺ በስተቀር ሁሉም ፍርደኞች ካቀረቡት የቅጣት ማቅለያ ሐሳብ፣ ከእያንዳንዳቸው ሁለት ማቅለያ ተወስዶላቸዋል፡፡
ዳርሰማ ሶሪ ግን ሦስት ማቅለያ ተወስዶለታል፡፡ በመሆኑም ፍርደኞቹ እያንዳንዳቸው በአምስት ዓመት ከስድስት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ፣ ዳርሰማ ሶሪ ግን በአራት ዓመታት ከአምስት ወራት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡