Saturday, June 10, 2023

የቀዝቃዛው ፖለቲካ ቀዝቃዛ ተቃውሞ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የዛሬ 25 ዓመት ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ከወጣ ጊዜ ጀምሮ የመቃወም መብት በመርህ ደረጃ የተከለከለ አይደለም፡፡ በተግባር ግን መቃወም ያለ ብዙ ዋጋ የሚፈጸም እንዳልሆነ በርካታ አብነቶች ይቀርባሉ፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በ1987 ዓ.ም. ሲረቀቅ ለመቃወም ዋና የመሠረት ድንጋይ የጣለው በነፃነት የማሰብ፣ የተለየ ሐሳብ የመያዝ፣ የተለየን ሐሳብ በነፃነት የማራመድ፣ የመደራጀትና መብትና ተያያዥነት ላላቸው ሌሎች መብቶች ዋስትና የሚሰጥ ነው፡፡

በዚህም መሠረት የተቃውሞ ሐሳቦች በተለይ በተለያዩ የግል ሚዲያዎች ከመግለጽ ጀምሮ፣ በ1997 ዓ.ም. በመንግሥት ሥልጣን ለውጥ ለማምጣት ተቃርበው ነበር፡፡ የምርጫው እንቅስቃሴና የሕዝብ ተሳትፎ እንዲሁም የምርጫው ቅስቀሳ የፈጠረው ትኩሳት፣ የኢትዮጵያ የሩብ ዓመት ፖለቲካ ማነፃፀሪያ ሲሆን ይስተዋላል፡፡

ከምርጫው በፊት በቁጥር በርከት ያሉ ተቃዋሚዎች በርካታ ኅብረቶችና ጥምረቶች ሲፈጥሩና ሲፈረከሱ ተስተውሏል፡፡ ቢሆንም እንደ 1997 ዓ.ም. ተቃዋሚዎች ሁለት ጎራ ለይተው ኢሕአዴግን የፈተኑበት ጊዜ አልነበረም ለማለት ያስደፍራል፡፡ በወቅቱ ፌዴራላዊ አስተሳሰብ አራማጆች ሊሰኙ የሚችሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ኅብረት በሚል ስያሜ በአንድ ጥላ የተቀናጁ ሲሆን፣ በአብዛኛው አሃዳዊ መንግሥት (አንድነት) አራማጆች የሚባሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ (ቅንጅት) በሚባል ስያሜ መሰባሰባቸው ይታወሳል፡፡ ሁለቱም የተቃዋሚ ጥምረቶች ሁለት ጎራ ከመፍጠራቸውም ባሻገር፣ የጋራ ትብብር ሲያደርጉና የአንዱን ድምፅ ሌላው እንዳይሻማ ለማድረግ ትብብር ሁሉ ፈጽመው ነበር፡፡

በአንዳንዶች በአሉታዊነት የሚነሱ መጠነኛ ችግሮች የታዩበት ቢሆንም፣ በምርጫው ውጤት ላይ ውዝግብ እስከተነሳ ጊዜ ድረስ ክስተቱ ለፖለቲካ አቅም የደረሰና የኢትዮጵያን ሕዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ በአገሩ ፖለቲካ ላይ በይገባኛል ስሜት እንዲሳተፍ ያነሳሳ ነበር፡፡ በእርግጥ በምርጫው ማግሥት ጥያቄ ቢነሳበትም በኢሕአዴግ በኩል የነበረው ምርጫውን ነፃና ፍትሐዊ የማድረግ ተግባራዊ ዝግጅትም የክስተቱ ዋና መሠረት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ሆኖም የምርጫ ውጤትን መነሻ አድርጎ የተነሳው ውዝግብና ይህንን ተከትሎም በመሪዎች ላይ የተወሰደው የማሰር ዕርምጃ፣ በተለይ የቅንጅት ተወካዮች ፓርላማ አለመግባትና የአዲስ አበባ አስተዳደርን አለመረከብ ተፈጥሮ በነበረው የዴሞክራሲ ጭላንጭል ላይ አሉታዊ ጥላ አጥልቶበታል፡፡

ነገሩ በይቅርታ ያለቀ ቢመስልም፣ በዚሁ አወዛጋቢ ምርጫ ማግሥት የተወሰዱ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ዕርምጃዎች በብዙ ዘንድ ሁኔታው ወደኋላ የሚመለስ እንዳይሆን ተሰግቶ ነበር፡፡   

በኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ ተሳትፎና ትንታኔ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የኢዴፓ እንዲሁም የቅንጅት መሥራች አቶ ልደቱ አያሌው በተለያዩ ጊዜያት በሰጧቸው አስተያየቶች፣ የኢትዮጵያ የተቃውሞ ፖለቲካ በውስጠ ዴሞክራሲ ዕጦት የተተበተበና የሐሳብ ልዩነት የማይስተናገድበት፣ እንዲሁም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዕርዳታ ላይ የተመሠረተና በራሱ የአገር ውስጥ አቅም ላይ ያልተመሠረተ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ፣ የማኅበራትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አዋጅ፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ በከፍተኛ ሁኔታ ይተቻሉ፡፡ የማኅበራትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አዋጅና የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ በተለይ የኢትዮጵያን የተቃውሞ ፖለቲካን በገንዘብም ሆነ በሐሳብ ጽንፈኛ ተብሎ ከሚፈረጀው ዳያስፖራ ለማላቀቅ የረዳ ቢመስልም፣ በራሱ በሁለት እግሩ የሚቆም ሕጋዊ የተቃዋሚዎች ኅብረትና ጥምረት እንዳይኖር ከፍተኛ ድርሻ መጫወቱን ብዙዎች ብዙ ብለውበታል፡፡

የመከለስ አዝማሚያ

በግንቦት ወር 2007 ዓ.ም. የተካሄደው አምስተኛ ጠቅላላ ምርጫ ሁለት ተቃራኒ ውጤቶች አስከትሏል፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ጀምሮ ባለፉት 25 ዓመታት፣ የፓርላማ ውክልና ሙሉ ለሙሉ ማግኘቱ የተገለጸበት የመጀመርያው ክስተት ነው፡፡ በኢሕአዴግ ትንታኔ መሠረት ውጤቱ የተገኘው አስተሳሰቡ በሕዝቡ ውስጥ በመስረፁ ነው፡፡ የምርጫው ውጤት ይፋ ሆኖ ኢሕአዴግ መንግሥት በመሠረተ በጥቂት ወራት ውስጥ ግን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተቃውሞና አመፅ ተቀስቅሷል፡፡

የአዲስ አበባ ዙሪያና ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ የጋራ ማስተር ፕላንን መሠረት ያደረገው በኦሮሚያ አካባቢ የተነሳው ተቃውሞ ለአንድ ዓመት የዘለቀ ሲሆን፣ ወደኋላም በአገሪቱ ሁለተኛው ትልቁ ክልል ወደሆነው አማራ ክልል ቀጥሏል፡፡ ከዚህ በፊት የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ውጤት ተከትሎ የተነሳው ተቃውሞን ጨምሮ መንግሥት አንዳንድ ተመሳሳይ ተቃውሞዎችን ያስተናገደ ቢሆንም፣ ይኼኛው አመፅ የተነሳበት አካባቢ ብዛትና የቆየበት ጊዜ ግን ከሌላው ወቅት የተለየ ነበር፡፡

በአገር ውስጥ በሕጋዊነት የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች የዳር ታዛቢ የሆኑበት ይህ አመፅ፣ በአብዛኛው በመንግሥት በአክራሪነት የሚፈረጁ የውጭ ኃይሎች የተቆጣጠሩት ነበር፡፡ እንደ መሣሪያ ሆኖ በዋናነት ያገለገለውም ማኅበራዊ ሚዲያ በተለይም ደግሞ ፌስቡክ ነበር፡፡ የአገር ውስጥ ተቃዋሚዎች ተቃውሞው በሰላማዊ መንገድና በሰከነ መንፈስ እንዲፈታ ጥያቄ ከማቅረብ ውጪ ተሳትፎአቸው እስከዚህም ነበር፡፡ አመፁ ያስከተለው ቁሳዊ ውድመትና የሕይወት መጥፋት ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ነበር፡፡ በዚህም ደረጃ ኢሕአዴግ ሁኔታውን እንደገመገመ የገለጸ ሲሆን፣ በመንግሥትም በድርጅትም ደረጃ ራሱን ለመፈተሽ ቃል መግባቱም ይታወሳል፡፡

ከዚህ አንፃር የሕዝብን ቀልብ የሳበው የፕሬዚዳንቱ የመስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. የሁለቱ ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን መጀመሪያ የጋራ ጉባዔ የመክፈቻ ንግግር ሲሆን፣ መንግሥት ዘርፈ ብዙ የፖለቲካ ማሻሻያዎች ለማድረግ መወሰኑን ያበሰረ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በፓርላማው ለማሳተፍ የምርጫ ሥርዓቱን ለመከለስ የተገባው ቃል በይበልጥ የሕዝቡን ቀልብ የሳበ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ምርጫው ችግር እንደነበረበት በግልጽ ባያምንም፣ ተቃውሞው የኢኮኖሚ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የሥርዓት ተቃውሞም ጭምር እንደሆነ አምኗል፡፡

በኢሕአዴግ ንድፈ ሐሳብ መተንተኛ መጽሔት አዲስ ራዕይ የመስከረም – ጥቅምት 2009 ዓ.ም. ዕትም ላይ ለቀውሱ መነሻ ሦስት መሠረታዊ ነገሮችን በመነሻነት ያስቀምጣል፡፡ እነዚህም የውስጥ ዴሞክራሲ መላላትና በአድርባይነት እየተተካ መምጣት፣ ሥልጣን የሕዝብ ማገልገያ መሆኑ ቀርቶ ለግለሰብ ጥቅም መዋሉ፣ እንዲሁም ዕድገቱን ተከትሎ የሕዝቡ በተለይ ደግሞ የወጣቶች ፍላጎት መጨመር ናቸው፡፡

‹‹በመናናቅና በጥላቻ ላይ የተመሠረተ አስተሳሰብ ቀላል በማይባል ደረጃ ጉዳት ሲያደርስ ተመልክተናል፤›› ይላል፡፡ ቀጥሎም ‹‹ለጽንፈኛ አፍራሽ ፖለቲካ ዘመቻ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረው በሌላ ሳይሆን ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ጉዟችን ካጋጠመው መደነቃቀፍ ጋር ተያይዞ ነው፤›› በማለት ʻአፍራሽና ጽንፈኛʼ የተባለው የውጭ ኃይል የራሱ ድርጅት በፈጠረለት ምቹ አጋጣሚ የተነሳ በድል አድራጊነት ስሜት መወረሩን ይገልጻል፡፡

ተቃውሞውን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መንግሥት ካቢኔ እንደ አዲስ የተዋቀረ ሲሆን፣ ቀደም ሲል በተቃዋሚዎች ሲቀነቀን የነበረው በምሁራን የመመራት ጥያቄ ተቀባይነት ያገኘ ይመስላል፡፡ የዶ/ር እና የፕሮፌሰር ማዕረግ ያላቸው የተወሰኑ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን በሚኒስትርነት ሾሟል፡፡ በድርጅቶቹም ውስጥ ራሱን እየፈተሸ ይመስላል፡፡

በተቃዋሚዎችና በአንዳንድ ምሁራን ለቀውሱ እንደ ዋና መነሻ ተደርጎ የሚነሳው የልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም ወይም የልማት ሞዴል፣ እንዲሁም የአውራ ፓርቲ ሥርዓትን ግን ከፕሮግራሙ ያስወጣው አይመስልም፡፡ ቀውሱንም ድርጅቱ ሲተነትነው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት በትክክል ባለመፈጸሙ ምክንያት እንጂ፣ የመስመር ችግር ተደርጎ አልተወሰደም፡፡ በተደጋጋሚ ጊዜያት እንደሚያቀርበው ‹‹የአፈጻጸም ችግር››ን ከመጥቀስ ባሻገር ገዥው ፓርቲ የሚያራምደው መስመር አገር ውስጥ በሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች ላይ ያስከተለውን ጉዳት የተመለከተ ወይም ለመመልከት ፍላጎት ያለው አይመስልም፡፡ የምርጫ ሥርዓቱን ለማሻሻል የተነሳበት ምክንያትና ተቃዋሚዎችን በፓርላማ ለማሳተፍ ድርጅቱ የወሰነበት ምክንያትም በዚህ ሰፊ ትንታኔው ላይ አልተካተተም፡፡

ተቃዋሚዎች ምን ይሠራሉ?  

በምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ ሕጋዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቁጥር ወደ 60 የሚጠጋ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ድምፃቸው የሚሰማውና በተለይ በምርጫ ወቅት በንቃት የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡ በቅርቡ በተነሳው ተቃውሞና አመፅም የዳር ተመልካች መሆናቸው በግልጽ ታይቷል፡፡ በአገሪቱ ያሉ ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከምርጫ ውጪ በውስጣዊ ልዩነት ሲወዛገቡ መታየታቸው፣ አልያም አምስት ዓመት ሙሉ ድምፃቸውን አጥፍተው ለምርጫ ብቅ ማለታቸው አዲስ ነገር አይደለም፡፡

‹‹ምርጫ የአምስት ዓመት እንቅስቃሴ የሚቋጭበት ወቅት ነው፤›› የሚሉት የአረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አሥራት ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በነፃነት እንዳይንቀሳቀሱ እክል የፈጠረባቸው ቢሆንም አባላቶቻቸውን በማደራጀት፣ ገንዘብ በማሰባሰብና የተለያዩ ውይይቶችን በማድረግ እንደሚያሳልፉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ የተከሰተው ቀውስ የሥርዓቱ ውጤት መሆኑን የሚያምኑት አቶ ገብሩ፣ ምኅዳሩን የሚያሻሽሉ ዕርምጃዎች ቢወሰዱ በተቃዋሚዎች እንቅስቃሴ ላይ የሚታየውን ክፍተት መሙላት ይችላል የሚል ሐሳብ አላቸው፡፡ ኢሕአዴግ ከተቃዋሚዎች ጋር አብሮ ለመሥራት ያነሳው ሐሳብም ከዚህ በፊት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምክር ቤት አባል የሆኑና ያልሆኑ የሚለውን ቅድመ ሁኔታ ያስቀራል የሚል ተስፋ አላቸው፡፡

ከሦስት ዓመታት በፊት ከአንድነት ፓርቲ ለቀው የወጡት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ከፓርቲ ፖለቲካ ራሳቸውን ካገለሉ ቆይተዋል፡፡ እሳቸው በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ሳሉ የውስጥ ውይይት ይደረግ ነበር፡፡ ነገር ግን አዳራሽ ለማግኘት፣ ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግና የድርጅቱን ልሳን ለማሳተም ይደረግ የነበረው እንቅስቃሴ ከመንግሥት በሚመጣ ጫና ከባድ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

ያም ሆነ ይህ መንግሥት ከተቃዋሚዎች ጋር በጋራ ለመሥራት ያቀረበው ጥሪ አፍዓዊ ሆኖ እንዳይቀር ያሳስባሉ፡፡ ተቃዋሚዎች በተለይ ከመንግሥት ጋር አብረው ቢሠሩ አገሪቱ የተሻለ እንደምትጠቀምም ይገልጻሉ፡፡ መንግሥት ለማሻሻል ያቀደው የምርጫ ሕግ ላይ የራሳቸውን ሐሳብ እንዲያንፀባርቁ፣ እንዲሳተፉና የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማቸው ሊደረግ ይገባል ይላሉ፡፡ ‹‹የምርጫ ሥርዓቱ ችግር ምን እንደሆነ ከተቃዋሚዎች በላይ የሚያውቀው የለም፤›› ያሉት ዶ/ር ነጋሶ፣ ጥሪው ለይስሙላ ሳይሆን የተቃዋሚዎች ድምፅ በግልጽ በሚዲያ ለሕዝብ እንዲቀርብና በገዥው ፓርቲም ሐሳባቸው እንዲደመጥ ይጠይቃሉ፡፡ ምናልባትም በቀጣዩ ምርጫ ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል የሚል አቋም አላቸው፡፡

‹‹ሥርዓቱ ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ አልተሸጋገረም፤›› የሚል አቋም ያላቸው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው፣ ተቃዋሚዎች በምርጫ ወቅት ብቻ እንዲንቀሳቀሱ የሚያደርጋቸው ኢሕአዴግ ራሱ እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡ በተለይ ሚዲያን በእኩልነት ለመጠቀም እንዳይችሉ መንግሥት ገደብ ማድረጉ ትልቅ ችግር እንደፈጠረ ያስገነዝባሉ፡፡ እንደ እሳቸው እምነት ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎች እንዲኖሩ የሚፈልጋቸው በምርጫ እንዲያጅቡትና ቅቡልነትን እንዲያገኝ ብቻ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ቀኖናዊ (የሃይማኖት መልክ ያለው) እንደሆነና አጀማመሩም በማርክሳዊ አስተሳሰብ በጠላትነትና በወዳጅነት ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ‹‹እኛም ከዚህ ሕዝብ ነው የተቀዳነው፤›› የሚሉት ኢንጂነር ይልቃል፣ መከፋፈልና የውስጥ ዴሞክራሲ ችግር የተቃዋሚዎች ባህሪ ብቻ እንዳልሆነ ይሞግታሉ፡፡ ኢሕአዴግም ውስጥ ችግሩ እንዳለ ነገር ግን በሥልጣንና በጉልበት ስለሚፈታው እምብዛም አይታይም ይላሉ፡፡ ከሌሎች ጋር አብሮ የመሥራትና የመተባበር መንፈስ የአንድ ፓርቲ ዋና ዓላማ አለመሆኑንና የጎንዮሽ ሥራ እንደሆነ ያምናሉ፡፡

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ በ‹‹ጠላት››ና በ‹‹ወዳጅ››፣ በ‹‹እኛ›› እና በ‹‹እነሱ›› ጎራዎች የሚገለጽ መሆኑን የሚናገሩት ኢንጂነሩ፣ ከዚህ ባህል በመውጣት የሠለጠነ ፖለቲካ ለማራመድ ፓርቲያቸው አዲስ አስተሳሰብና ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ አካሄድ እንደሚከተል ይናገራሉ፡፡ ‹‹የተለየ ሐሳብ የያዘ ሰው የማጥፋት ባህል መቅረት አለበት፤›› ሲሉም ያጠቃልላሉ፡፡

ቀዝቃዛ ተቃውሞ

የ1997 ዓ.ም. ምርጫን ተከትሎ በተወሰዱ ዕርምጃዎችና በራሳቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች የውስጥ ችግር ምክንያት የተቃውሞው ኃይል ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ መቀዛቀዝ ታይቶበታል፡፡ ʻፖለቲካን እንደ ኮረንቲʼ የመፍራት ባህልም ደግሞ እንዳገረሸ የሚያምኑ በርካቶች ናቸው፡፡

የቅንጅት መሪዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ከታሰሩ በኋላ የተፈጠረው አስፈሪ ድባብ፣ ታሳሪዎች በይቅርታ በመፈታታቸው ያሻሽለዋል ተብሎ ተገምቶ ነበር፡፡ የሆነው ግን ተቃራኒው ነበር፡፡ ብዙዎች ከአገር የተሰደዱ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ነፍጥ ማንሳታቸውን አውጀዋል፡፡ እንደ እነ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ያሉት ፖለቲከኞች ደግሞ ከፖለቲካ ራሳቸውን አግለዋል፡፡ የተቀሩት ኃይሎችም በተለይ አንድነት፣ መኢአድና ኢዴፓ ወደ ቀድሞ ፓርቲያቸው ተመልሰው እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ጥረታቸው ፍሬ ሲያፈራ አይስተዋልም፡፡

በምርጫ 2002 ዋዜማ ተቃዋሚ ኃይሎችን ወደ አንድ የጋራ መድረክ ለማምጣት ለአንድ ዓመት ያህል የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በእነ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ አቶ ገብሩ አሥራትና አቶ ስዬ አብረሃ የቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎች የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ድክመቶች በግልጽ ያሳዩ ነበሩ፡፡ እርስ በእርስ መጠላለፍ፣ በጠላቴ ጠላት መርህ መተባበርና በኢሕአዴግ ጥላቻ ላይ ብቻ መቆም፣ እንዲሁም የጠራ የፖለቲካ ፕሮግራም በአማራጭነት ይዞ ያለመቅረብ የሚሉ ድክመቶች በዋነኛነት ተለይተው ነበር፡፡ እነዚህን ድክመቶች ለማረም ቆርጦ የተነሳው ስምንት የፖለቲካ ፓርቲዎችን የያዘና በብሔርና በኅብረ ብሔር የተመሠረቱ ድርጅቶች አንድ ላይ ያሰባሰበው መድረክ ግን ብዙም ሳይቆይ ውዝግብ ውስጥ መግባቱ ይታወሳል፡፡

በ2002 ምርጫ በአንድነት ፓርቲ ተወካይ መድረክ ካገኘው የአዲስ አበባ አንድ ወንበር ውጪ የተቃዋሚዎቹ ጥረት በምርጫ ውጤት አልታየም፡፡ በምክንያትነትም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር አላፈናፍን ማለቱ ተጠቅሶ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በ2007 በተካሄደው ምርጫም ተቃዋሚዎች ጨርሰው ከፓርላማ የወጡ ሲሆን፣ ብዙዎቹ በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት የመፍጠር ዕድል አደጋ ላይ መውደቁን ገልጸው ነበር፡፡ በኢሕአዴግ በኩል ግን ተቀባይነት ያለው አልነበረም፡፡

በተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደሚገለጸው፣ ሁኔታው በተቃዋሚዎች ድክመት የተነሳ እንደሆነ በመተቸት ኢሕአዴግ አውራ ፓርቲ ሆኖ ለመቀጠል የቀረፀው ስትራቴጂ ድል ተደርጎ በድርጅቱ ንድፈ ሐሳብ መጽሔት ተተንትኗል፡፡ ተቃዋሚዎች ይህንን አይቀበሉም፡፡ ይልቅ ሁኔታውን በውጭ ሆነው ሥርዓቱን በነፍጥ ለመታገል ለወሰኑ ድርጅቶች መልካም ዜና እንደሆነ ተደርጎ ነበር የተገለጸው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ጥናት ማዕከል መምህር አቶ ናሁሰናይ በላይ የፒኤችዲ ዲግሪ ማሟያቸውን በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተግዳሮቶች ላይ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ አቶ ናሁሰናይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአገር ውስጥ የሚገኙ ሕጋዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በነፃነት ለመንቀሳቀስ የሚችሉበት ምቹ ሁኔታ የለም፡፡

‹‹አብዛኞቹ በጠራ ሐሳብ ላይ የመሰባሰብና የውስጥ ዴሞክራሲ ችግር ያለባቸው ቢሆንም፣ በዋናነት ከገዥው ፓርቲ የሚደርስባቸውን ጫና መቋቋም የሚችሉት አይደለም፡፡ የፖለቲካና የገንዘብ አቅምም የላቸውም፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም በአገር ውስጥ ፖለቲከኞች ቁጥጥር ሥር መሆን የነበረበት የተቃውሞ ፖለቲካ ውጭ ባሉ ሰዎች እጅ እንዲዛወር በር ከፍቷል ይላሉ፡፡ እንደ ተመራማሪው እምነት በውጭ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የሚዲያና የገንዘብ አቅም ያላቸው ቢሆኑም፣ የሚያራምዱት ፖለቲካ ኃላፊነት የጎደለውና በአገር ህልውና ላይ አደጋ ሊያደርስ የሚችል ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በጫና ከሕጋዊ ተቃዋሚዎች እጅ እንዲወጣ የተደረገው የተቃውሞ ፖለቲካ ተመልሶ ወደሚመለከተው ሕዝብና በሕግና በኃላፊነት ወደሚንቀሳቀሱ የአገር ውስጥ ኃይሎች የሚመለስበት መንገድ በገዥው ፓርቲ ሊታሰብበት እንደሚገባ ዶ/ር አቶ ናሁሰናይ ያሳስባሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -