Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሰመራ ኤርፖርት ማሻሻያ ፕሮጀክት በ268 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተካሄደ ነው

የሰመራ ኤርፖርት ማሻሻያ ፕሮጀክት በ268 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተካሄደ ነው

ቀን:

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የአፋር ክልል ዋና ከተማ በሆነችው ሰመራ የሚገኘውን ኤርፖርት የማሻሻያ ግንባታ በ268 ሚሊዮን ብር ወጪ በማካሄድ ላይ ነው፡፡

ከ1990ዎቹ ጀምሮ የሰመራ አውሮፕላን ማረፊያ ሜዳ መደበኛ ያልሆኑ የአነስተኛ አውሮፕላን በረራዎች ሲያስተናግድ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የማሻሻያ ሥራ በማከናወን፣ ሁለት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የጠጠር የአውሮፕላን ማረፊያና አነስተኛ ጊዜያዊ ተርሚናል ገንብቶ በታኅሳስ 2006 ዓ.ም. መደበኛ በረራ አገልግሎት ማስተናገድ ጀምሯል፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቦምባርዲየር Q400 አውሮፕላን በሳምንት ሦስት ቀን መደበኛ በረራ መስጠት ጀምሮ፣ የአካባቢው ሕዝብ የአየር ትራንስፖርት ፍላጎት በማደጉ አየር መንገዱ በየዕለቱ የበረራ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የኮሙዩኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድም ተክሉ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የአፋር ክልል የኢኮኖሚ ዕድገትና ያሉትን የቱሪስት መስህቦች በመመልከት እንዲሁም የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር መቀመጫ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ፣ የሰመራ ኤርፖርትን ማሻሻል አስፈላጊ እንደሆነ ታምኖበታል፡፡ በአፋር ክልል ኢንቨስትመንትና የቱሪስት ፍሰት እያደገ እንደመጣ አቶ ወንድም ያስረዳሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በክልሉ በጨው ምርት፣ በፖታሽ ማዕድንና በወርቅ ፍለጋ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ተሰማርተው ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ላይ ይገኛሉ፡፡ የፌዴራል መንግሥትም ይህን በመመልከት በክልሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ከፍተኛ ሙቀት ባለበት በዚህ ክልል የመከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅት ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን በገባው ውል መሠረት፣ የአስፋልትና የሲሚንቶ ኮንክሪት መንገዶች በመገንባት ላይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትም ክልሉን በአየር ትራንስፖርት ለማገናኘት የሰመራ ኤርፖርትን ደረጃ ለማሳደግ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ የኤርፖርት ማሻሻያ ሥራ የመጀመሪያ ክፍል የሆነው የአውሮፕላን ማረፊያ ሜዳውን ከጠጠር ወደ ኮንክሪት አስፋልት ማሳደግ ነው፡፡ በመሆኑም ድርጅቱ ያወጣውን ጨረታ አገር በቀል ኩባንያ የሆነው አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን አሸንፎ፣ የአውሮፕላን ማኮብኮቢያና ማረፊያ ሜዳውን በአስፋልት ኮንክሪት በ268 ሚሊዮን ብር ለመሥራት ውል ፈርሞ ግንባታውን በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

የአውሮፕላን ማረፊያው 2.5 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 60 ሜትር ስፋት እንዳለው የገለጹት አቶ ወንድም፣ ቦይንግ 737 የመሳሰሉ ጄት አውሮፕላኖችን ማሳረፍ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሚሰጠው ዕለታዊ መደበኛ አገልግሎት ምቹ እንደሚሆን፣ መደበኛ ያልሆኑ በረራዎች አገልግሎት የሚሰጡ የግል አየር መንገዶችም በኤርፖርቱ መጠቀም እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡

በአፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን የሰመራ ኤርፖርት ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛቸው ጌጤ፣ የአውሮፕላን ሜዳ ግንባታ ሥራው መስከረም 2008 ዓ.ም. መጀመሩንና በአሁኑ ወቅት የግንባታው 70 በመቶ መጠናቀቁን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በኮንትራት ውሉ ግንባታው በነሐሴ 2009 ዓ.ም. ሙሉ በሙሉ መጠናቀቅ ያለበት ቢሆንም፣ ሰመራ 12ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ኅዳር 2010 ዓ.ም. የምታስተናግድ በመሆኗ አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን የአውሮፕላን ማረፊያ ሜዳውን ግንባታ ቀደም ብሎ በሰኔ 2009 ዓ.ም. ለማጠናቀቅ ርብርብ በማድረግ ላይ መሆኑን አቶ ግዛቸው ተናግረዋል፡፡ ሳባ ኢንጅነሪንግ የተባለው አገር በቀል ኩባንያ የፕሮጀክቱ አማካሪ ነው፡፡

የሰመራ ኤርፖርት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል አምባቸው፣ የሰመራ ኤርፖርት የአውሮፕላን ማረፊያ ሜዳ በመገንባት ላይ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚሰጠው መደበኛ የበረራ አገልግሎት ሳይስተጓጎል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት የኤርፖርት ግንባታውን እንደ ራሱ ፕሮጀክት በመመልከት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑንም አቶ ዳንኤል ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ለሰመራ ኤርፖርት ዘመናዊ የመንገደኞች ተርሚናል ግንባታ ለማካሄድ የዲዛይን ሥራ ተጠናቆ ግንባታውን የሚያካሂድ ኮንትራክተር ለመቅጠር ጨረታ መውጣቱን ከአቶ ወንድም ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በአንድ ጊዜ 170 መንገደኞች ማስተናገድ የሚችል ዘመናዊ ተርሚናል ግንባታ በ2009 ዓ.ም. እንደሚጀመር የገለጹት አቶ ወንድም፣ ተርሚናሉ የአካባቢውን ኅብረተሰብ አኗኗርና ባህል የሚያንፀባርቅ እንደሚሆን አክለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቭዬሽን ባለሥልጣን በበኩሉ የአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ በመገንባት ላይ ነው፡፡ ናሽናል ኦይል ካምፓኒ (ኖክ) የአውሮፕላን ነዳጅ ማቅረቢያ ጣቢያ ለመገንባት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት 22 ኤርፖርቶችን ያስተዳድራል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 20 የሚሆኑት የአስፋልት መንደርደሪያ ያላቸው ሲሆኑ፣ አራቱ (አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ መቀሌና ባህር ዳር) ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ናቸው፡፡ ሁለቱ በጠጠር ሜዳ በረራዎችን ያስተናግዳሉ፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የኤርፖርቶችን ቁጥር ወደ 30 ለማሳደግ፣ ከዚህ ውስጥ 25ቱን የአስፋልት ሜዳ ያላቸው እንዲሆኑ ድርጅቱ ሰፊ ሥራ በማከናወን ላይ መሆኑን አቶ ወንድም ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሰመራ፣ የሐዋሳ፣ የጂንካ፣ የሮቤ፣ የሽሬ፣ የደምቢዶሎና የነቀምቴ ኤርፖርቶች ግንባታ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ በላሊበላ፣ በባህር ዳርና በጎንደር ኤርፖርቶች የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ የአገር ውስጥ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት አቶ ወንድም፣ የአገር ውስጥ መንገደኞች ፍሰት በየዓመቱ 20 በመቶ በማደግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2008 ዓ.ም. ከሦስት ሚሊዮን በላይ መንገደኞችን በአገር ውስጥ በረራዎች አጓጉዟል፡፡ አየር መንገዱ 20 የአገር ውስጥ በረራ መዳረሻዎች አሉት፡፡ ‹‹ይህ የሕዝቡ የመክፈል አቅም መጨመሩን ያሳያል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው አገሪቱ ተከታታይና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስገንዘብ በመቻሏ ነው፤›› ያሉት አቶ ወንድም፣ የክልል ኤርፖርቶች ከገቢ አንፃር ለድርጅቱ ትርፋማ ባይሆኑም መንግሥት ካስቀመጠው የአየር ትራንስፖርትን በሁሉም ክልሎች ተደራሽ የማድረግ አቅጣጫ በመነሳት፣ ድርጅቱ በክልሎች ኤርፖርቶችን መገንባትና የማሻሻል ሥራ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡

‹‹በቀጥታ በገንዘብ ተጠቃሚ ባንሆንም የአየር ትራንስፖርት የክልሎችን የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ዘርፎችን የሚያነቃቃ በመሆኑ የክልል ኤርፖርቶች ላይ ኢንቨስት እናደርጋለን፡፡ የሐዋሳ ኤርፖርት ግንባታ ሲጀመር ለአዲስ አበባ ካለው ቅርበት አንፃር አስፈላጊነቱ ላይ ጥያቄ ያነሱ ወገኖች ነበሩ፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት የሦስት ቀናት በረራ አገልግሎት መስጠት ጀምሮ ዛሬ በየዕለቱ እየበረረ አውሮፕላኑ ሙሉ ነው፡፡ ኤርፖርቱ ከጅምሩ ለክልሉ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፤›› ያሉት አቶ ወንድም፣ በክልል የሚገነቡ ኤርፖርቶች በገንዘብ የሚያስገቡት ገቢ ሳይሆን መታየት ያለበት ለክልሎች ንግድ፣ ኢንቨስትመንትና ቱሪዝም ዕድገት በሚያደርጉት አስተዋጽኦ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በሰመራ ከተማ ከኤርፖርቱ በተጨማሪ ዘመናዊ ሁለገብ ስታዲየም፣ የእንግዳ ማረፊያዎችና መንገዶች በመገንባት ላይ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል፡፡                

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...