Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመሬት የማስተዳደር ኃላፊነቱን ያጣው ኤጀንሲ ትኩረቱን ባለሀብቶችን መደገፍ ላይ አደረገ

መሬት የማስተዳደር ኃላፊነቱን ያጣው ኤጀንሲ ትኩረቱን ባለሀብቶችን መደገፍ ላይ አደረገ

ቀን:

– ለባለሀብቶች የተላለፈ መሬት ሙሉ በሙሉ ባለመልማቱ 11.3 ቢሊዮን ብር ታጣ

ከክልሎች በውክልና የወሰደውን የእርሻ ኢንቨስትመንት መሬት መልሶ ለክልሎች እንዲያስረክብ የታዘዘው የኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ ትኩረቱን ለባለሀብቶች ኤክስቴንሽን አገልግሎት መስጠት ላይ አድርጓል፡፡

በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 283/2005 የተቋቋመው የኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ በውክልና የወሰደውን መሬት ለክልሎች እንዲመልስ ታዟል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ በመሩት ውይይትና የእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ በተካሄደው ጥናት፣ መሬት የማስተዳደር ኃላፊነት ለክልሎች እንዲመልስ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

‹‹ቀደም ሲል መሬት በውክልና በመግባቢያ ሰነድ ከከልሎች ተወስዶ በፌዴራል ደረጃ ለባለሀብቶች የሚሰጥበትና የሚተዳደርበት ሥርዓት በሕገ መንግሥቱ ከተደነገጉ መሠረታዊ ጉዳዮችና አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በኅብረተሰቡ ዘንድ ብዥታ እየፈጠረ በመሆኑ፣ መሬት የማስተዳደርና ለባለሀብት የማስተላለፍ ተግባር በክልሎች ባለቤትነት ይፈጸም፤›› ሲል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስተባባሪነት የተካሄደው ጥናት ያመለክታል፡፡

የፌዴራል መንግሥት በዚህ ረገድ የክልሎችን አቅም ለመገንባት፣ ከክልሎች ጋር ተቀናጅቶና ተባብሮ ኢንቨስትመንቱ የተሳለጠ የማድረግ ሥራ እንዲሠራ ውሳኔ ተላልፏል፡፡ በዚህ ውሳኔ መሠረት በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ሥር የሚገኘው የኢትዮጵያ ግብርና ኢንቨስትመንትና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ትልቁን ሥራውን አጥቷል፡፡ የፌዴራል መንግሥት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው መሬቱ በቀጥታ በክልሎች ቢተዳደር የተሻለ የአሠራር መሻሻል ይኖራል የሚል አስተያየት ከተለያዩ አቅጣጫዎች በመሰንዘሩ ነው፡፡

በዚህ መሠረት ኤጀንሲው ታኅሳስ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ይፋ ባደረገው የሰፋፊ ግብርና ኢንቨስትመንት ኤክስቴንሽን አገልግሎት አተገባበር ማኑዋል ረቂቅ ሰነድ፣ የግብርና ኢንቨስትመንትን እንደሚደግፍ ገልጿል፡፡

የዚህ የኤክስቴንሽን አገልግሎት ተግባራዊ ለማድረግ ያስፈለበትን ምክንያት የባለሀብቱን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለማሻሻል፣ የባለሙያና የሠራተኞች ክህሎት ለማሳደግ፣ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ለማሻሻል፣ የኤክስፖርት ምርቶችን ማሳደግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

በፌዴራልና በክልሎች 2.5 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ለባለሀብቶች ቢተላለፍም፣ ዘርፉ በበርካታ አስተዳደራዊ ችግሮች በመተብተቡ ምርታማነት ሊያድግ አልቻለም፡፡ ኤጀንሲው ባዘጋጀው ረቂቅ ሰነድ ላይ ከተላለፈው መሬት ውስጥ በአጠቃላይ ወደ ልማት የገባው 983,537.06 ሔክታር መሬት ሲሆን፣ የተገኘው ምርት 1,647,021 ቶን ነው፡፡ የተላለፈው መሬት በሙሉ ቢለማ የሚጠበቀው ምርት 2,770,000 ቶን ይሆን እንደነበር ረቂቅ ሰነዱ ያመለክታል፡፡ ነገር ግን ሊመረት ይገባ የነበው 1.2 ሚሊዮን ቶን ምርት ሳይመረት ቀርቷል፡፡ ይህ ምርት በገንዘብ ሲተመን 11.3 ቢሊዮን ብር መሆኑንና ይህ ገንዘብ መታጣቱንም ሰነዱ አመልክቷል፡፡

በዚህ መሠረት ኤጀንሲው መሬት ከማስተዳደር ይልቅ ትኩረቱን ባለሀብቶችን መደገፍ ላይ አድርጓል፡፡ የኤክስቴንሽን አገልግሎቱን ተግባራዊ ለማድረግ በፌዴራልና በክልሎች ዓብይ ኮሚቴዎች እንደሚቋቋሙና ረቂቅ ሰነዱም በአሁኑ ወቅት በውይይት ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ሙላት አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...