Friday, September 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዘንድሮ በአማራና በትግራይ ከ150 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰብል ምርት ይጠበቃል

ተዛማጅ ፅሁፎች

– አትክልት ያመረቱ ገበሬዎች በገበያ እጦት ተቸግረዋል

በዚህ ዓመት በአማራና በትግራይ ክልሎች ከ150 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የግብር ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል፡፡ ይህ የተገለጸው ዓምና በተለያዩ የክልሎቹ ዞኖች ውስጥ ተከስቶ በነበረው ድርቅ ምክንያት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ፣ በዘንድሮው የምርት ዘመን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለመገምገም በተደረገ የመስክ ቅኝት ወቅት ነው፡፡

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከድርቁ አገግመዋል ተብለው ከተለዩት መካከል በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ወረዳ፣ በረኸት ወረዳ፣ ደብረ ብርሃን ከተማ ይጠቀሳሉ፡፡ በሰሜን ወሎ ዞን፣ አበሩ ወረዳ፣ ጉባ ላፍቶ ወረዳ፣ ራያ ቆቦ፣ እንዲሁም የአላማጣ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉና በከፊል ጉዳት ደርሶባቸው ነበር፡፡

አቶ ደረሰ ሀብቴ በምንጃር ወረዳ ኮርማ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ነዋሪ ናቸው፡፡ አቶ ደረሰ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ዓምና ከነቤተሰባቸው የሚተዳደሩበትን ሁለት ጥማድ መሬት አርሰው ከዘሩት ማሽላ ምንም ምርት አላገኙም ነበር፡፡ ዘንድሮው ዝናቡ ጥሩ በመጣሉና በመስኖ ማልማት በመቻላቸውም፣ ማሽላ ሦስት ቆርጥ፣ ጤፍ ሦስት ቀርጥ እንዲሁም ሽንብራ አንድ ቀርጥ መዝራት በመቻላቸው ምርት ሰብስበዋል፡፡ ከማሽላው ብቻ አሥር ኩንታል እንዳገኙ፣ የዘንድሮው ከዓምናው የተሻለ እንደሆነም ገዋጸዋል፡፡

አቶ ተስፋ ባንተሁንም በዚሁ አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚገልጹት በዞኑ ውስጥ ካሉት 15 ወረዳዎች 12ቱ የገጠር ቀበሌዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ ቀበሌዎች ውስጥ ይኖሩ ከነበሩ 1.4 ሚሊዮን ነዋሪዎች ውስጥ 969 ሺዎቹ በድርቁ በመጎዳታቸው ምክንያት ለተረጂነት ተጋልጠው ነበር፡፡ ከ2007 እስከ 2008 በነበሩት ሁለት ዓመታት ውስጥ ከመኸር ወቅት 402 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ቢታቀድም፣ ከዚህ ውስጥ 40 በመቶ ብቻ እንደተሳካ ያብራሩት አቶ ተስፋ፣ በዘንድሮው የመኸር ዘመን  5.4 ሚሊዮን ኩንታል እንደሚገኝ ቢጠበቅም ከዚህ ውስጥ 78 በመቶ ብቻ ሊገኝ መቻሉን አብራርዋል፡፡ ቀሪው ምርት በክልሉ አካባቢዎች በተከሰተው ውርጭ፣ የአፍሪካ አንበጣ በሚባለው ተባይ እንዲሁም በተምች ወረርሽኝ ምክንያት የተዘራው እህል በመውደሙ ሊገኝ አልቻለም ብለዋል፡፡ የአፋር ክልል አዋኝ በሆኑ አካባቢዎችም ዝናቡ ቀድሞ በመውጣቱ የታቀደውም የምርት መጠን ሙሉ በሙሉ መሳካት እንዳልተቻለ፤ በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ 98 ሺሕ ሰዎችም በዕርዳታ እየታገዙ ለመቆየት እንደሚገደዱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በክልሉ ከ2.3 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ተረጂ ሆኖ እንደቆየ ነገር ግን በዘንድሮው ዓመት የተረገጂው ቁጥር ከግማሽ በታች በመቀነስ 650 ሺሕ ብቻ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ተሾመ ዋለ ናቸው፡፡

 በዘንድሮው መኸር በክልሉ 4.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በእርሻ ማሳዎች ተሸፍኖ እንደነበርና ከዚህ ውስጥ 93 በመቶው ሰብል እንደተሰበሰበ ዶ/ር ተሾመ ተናግረዋል፡፡ በመስኖ አማካይነት ከዓመት ዓመት ለማምረት የሚያችል 980 ሺሕ ሔክታር መሬት ተዘጋጅቶ፣ ከዚህ ውስጥ 460 ሺሕ ሔክታሩ እየተዘራበትና ሰብል እየለማበት እንደሚገኝ፤ ቀሪውም የእርሻ መሬት በቅርቡ እንደሚታረስ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ዓምና በኤልኒኖ (የውቅያኖሶች መሞቅ ያከተለው የአየር ፀባይ ለውጥ) ምክንያት በተከሰተው ድርቅ ከተጎዱ የኢትዮጵያ ክፍሎች አንዱ የትግራይ ብሔራዊ ክልል ነበር፡፡ በክልሉ በ2008 በጀት ዓመት ይገኛል ተብሎ ከታሰበውና በ1.3 ሚሊዮን ሔክታር ከተዘራው ሰብል ውስጥ 18 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ነበር ማግኘት የተቻለው፡፡ ዕቅዱ ግን 22 ሚሊዮን የሰብል ምርት ለማግኘት እንደነበር የክልሉ የግብርና እና ገጠር ልማት ቢሮ የሰብልና የአፈር ለምነት ንዑስ የሥራ ሒደት ኃላፊ አቶ  በሪሁን አረጋዊ ገልጸዋል፡፡ በዘንድሮው የመኸር ወቅት በዚያው በ1.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ከተዘራው ውስጥ ከ25 ሚሊዮን ኩንታል ያላነሰ ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸው፣ እስካሁን 91 በመቶው እንደተሰበሰበ አስታውሰዋል፡፡

አቶ በሪሁን እንዳሉት፣ ዓምና የታጣውን የምርት መጠን ዘንድሮ ለማሻሻል በክልሉ ዋና ችግር የሆነው የውኃ እጥረት ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ የውኃ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶችን በመቆፈርና የክረምቱን ውኃ በማቀብ የመስኖ ሥራ በሰፊው እንዲለመድ ሲደረግ ከመቆየቱም ባሻገር ሰብሎችን በመስመር በመዝራት፣ በቂ የማዳበሪያና የፀረ አረም መድኃኒቶችን በማቅረብ ገበሬውን ማገዝ ስለተቻለ የምርቱ መጠን ሊሻሻል መቻሉን አቶ በሪሁን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ በድርቅ ከተጎዱት አካባቢዎች መካከል ደቡባዊ ዞን ራያ አዘቦ፣ ሀውዜን፣ ጎሎ ምሀዳ ወረዳዎችና ቀበሌዎች እንዲሁም በክልሉ ምሥራቃዊ ዞን አዲግራት ወረዳ እና ጋንታ አፈሹም ካለፈው የድርቅ አደጋ እያገገሙ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ዞኖች በተያዘው የመኸር ወቅት ከዝናቡ በተጨማሪ መስኖን በመጠቀም የአካባቢው ገበሬዎች ቶሎ የሚደርሱ የጓሮ አትክልቶችን ማለትም ሽንኩርት፣ ቃሪያ፣ ቲማቲምና ሌሎችንም ጎን ለጎን በማምረት ላይ ይገኛሉ፡፡

በትግራይ የደቡባዊ ዞን የእርሻና የገጠር ደን ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ገብረ እግዚአብሔር ሀገዊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በ2007 እና በ2008 የመኸር ወቅት በ143,300 ሔክታር ላይ ዘር ለመዝራት አቅደን በ130 ሺሕ ላይ የዘራን ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ስድስት ሚሊዮን ኩንታል ለማግኘት ታቦ የነበረ ሲሆን፣ ባጋጠመው የዝናብ እጥረት ምክንያት እርሻዎች በመገልበጣቸው 29 በመቶ ብቻ ሊገኝ ችሏል፡፡

ድርቁን ከመቋቋም ጎን ለጎን እጥርበታማነትን በማስፋፋት ለዚሁ ሲባል ራሱን የቻለ ክላስተር በማቋቋም በ2009 ዓ.ም. 6.5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም ከመኸር ወቅት ብቻ 5.2 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት መገኘቱን አቶ ገብረ እግዚአብሔር በሰጡት መግለጫ ጠቅሰዋል፡፡

በእነዚህ ዞኖችና ወረዳዎች ውስጥ ሪፖርተር ተዘዋውሮ እንደቃኘው ከሆነ ገበሬዎች ሽንኩርት በብዛት ቢተክሉም የገበያ ችግር እያጋጠማቸው ይገኛል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ገበሬዎች ከሰጡት አስተያየትም ይህ ችግር ጉልህ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ አንዳንድ ወረዳዎች ዝናቡ ይብሱን ለዓመታት ዘግይቶባቸዋል፡፡ በዚህ ሳቢያም ከግብርና ወጥተው ወደ ሌላ የሥራ መስክ ፊታቸውን ለማዞር የተገደዱ እንዳሉም እንዳለባቸው የግብርና ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ሰጥተዋል፡፡

 ለሚመረተው ምርት የገበያ ትስስር ባለመፈጠሩ ምክንያትም በደላሎች የመጠለፍ ችግር ይታያል ተብሏል፡፡ ከእርሻ ማሳዎች ወደ ዋና መንገድ የሚወስዱ መጋቢ መንገዶችም ለአምራቾቹ አስቸጋሪዎች ናቸው፡፡

ሌሎችም የእርሻ ሥራን የሚያተጓጉሉ፣ በተለይም በመስኖ ለማልማት እንቅፋት የሚፈጥሩ ልማዳዊ የአኗኗር ዘይቤዎች መቀየር እንዳለባቸው፣ ለችግር ጊዜ ብቻም ሳይሆን፣ ቀስ በቀስ ወደ ካፒታል ማከማቸት የሚያደርስ የቁጠባ ባህል መዳበር የክልሉ መንግሥት በሕዝቡ ውስጥ ማስረጽ የሚፈልጋቸው ሥራዎች መሆናቸውን ኃላፊዎቹ ይናገራሉ፡፡

በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት የዕለት ደራሽ ዕርዳትን ጨምሮ የሴፍቲኔት ፕሮግራም የሚያካልላቸው 9.7 ሚሊዮን ሰዎች እንዳሉ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ይፋ ያደረገው የቅርብ ጊዜ ሪፖርት ይጠቁማል፡፡ በተለይ የዕለት ተደራሽ ዕርዳታ ለማቅረብ አሁንም ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ሲታወቅ፣ ከምግብ እጥረቱ ባሻገር እንደ አጣዳፊ የትውከትና የተቅማጥ (አተት) በሽታ የተከሰተባቸው አካባቢዎች ገና በማገገም ላይ እንደሚገኙ የተመድ ሰብዓዊ ጉዳይ ማተባበሪያ ጽሕፈተ ቤት ሪፖርት ይጠቁማል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ አዲስ ድርቅ ሊቀሰቀስ እንደሚችል ማስታወቁም በመኸር ወቅት የታየውን መንሰራራት ሥጋት ውስጥ ሊከተው እንደሚችል ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች