Monday, September 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ከሕዝብ ንቃተ ህሊና ጋር የሚመጣጠን ምላሽ ያስፈልጋል!

  ያለንበት ዘመን በዓለም ዙሪያ በርካታ ለውጦችን እያስተናገደ ነው፡፡ ቀዝቃዛው ጦርነት አክትሞ በሊበራሎች የበላይነት ይመራ የነበረው የምዕራቡ ዓለም፣ አሁን ደግሞ ዋነኛ በሚባሉት አገሮች ውስጥ እያቆጠቆጠ ባለው ‹ፖፑሊስት ሙቭመንት› እየተቀየረ ነው፡፡ በእነዚህ አገሮች ቀድሞ የሚታወቁት የፖለቲካና የዲፕሎማሲ አካሄዶች እየተቀየሩ፣ በፊት ከፍተኛ ስምና ዝና የነበራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች እየተገፉ ነው፡፡ በዘመናችን አሜሪካን ጨምሮ በምዕራብ አውሮፓና በአንዳንድ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች በመንግሥታትና በተቋማት ላይ ባኮረፉ ዜጎች የሚደገፉ አዳዲስ አስተሳሰብ ያነገቡ ሰዎች እየታዩ ነው፡፡ ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዚህ ምሳሌ ማሳያ ሲሆኑ፣ በቅርቡ በብዙ የአውሮፓ አገሮች ተመሳሳይ ግለሰቦች ወደ ሥልጣን ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ሲያኮርፍ የነበሩ አስተሳሰቦች ይለወጡና አዳዲስ መሪዎች ብቅ ይላሉ፡፡ ለወቅቱ ጥያቄዎች ምላሽ እንዳላቸው ቃል ይገባሉ፡፡ የሕዝብን ስሜት ይኮረኩራሉ፡፡

  ባለፈው አንድ ዓመት በአገራችን የተከሰተው ደም አፋሳሽ ሁከት ለጊዜው ቢበርድም፣ ለሁከቱ መነሻ የሆነው የሕዝብ ጥያቄ አሁንም አለ፡፡ ምንም እንኳ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› ውስጥ መግባቱንና በዚህም ለለውጥ የሚረዱ ምልክቶች መታየታቸውን ቢገልጽም፣ አሁንም ከዘመኑ አስተሳሰብና ከሕዝቡ ንቃተ ህሊና ጋር የሚመጣጠን ምላሽ ይጠበቃል፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ፣ በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄ መድረኮች በተቀመጠላቸው አቅጣጫ መሠረት መቀጠላቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ ሒደቱ እንዳለ ሆኖ የፍጥነቱ ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በይደር የታለፉ የሕዝብ ጥያቄዎች በተቻለ ፍጥነት መፈታት አቅቷቸው፣ ከተግባር ይልቅ ንግግር ሲቀድም መሰላቸት ይመጣል፡፡ ተስፋ መቁረጥ ይከተላል፡፡ ይኼ ለአገርም ሆነ ለሕዝብ አይበጅም፡፡

  ሕዝብ የመታደሱ እንቅስቃሴ ላይ ተስፋ የሚያደርገው ከዚህ በፊት ይፈጸሙ የነበሩ አስከፊ ተግባራት ሲወገዱ ነው፡፡ የመታደሱ እንቅስቃሴ አካል የሆኑት የባለሥልጣናት ሹም ሽርና ጥፋተኞችን በሕግ የመጠየቅ ዕርምጃዎች እንደ በጎ ሲወሰዱ፣ ሕዝብ በሌላ በኩል ያነሳቸው ጥያቄዎችና የተፈጠሩበት ቅሬታዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱለት እየጠበቀ መሆኑ ግንዛቤ ሊኖር ይገባል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ላይ ጠንክሮ መሥራት ካልተቻለና ውጤት ካልተገኘ ብጥብጦችና ሁከቶች ገጽታቸውን ቀይረው ሊመጡ ይችላሉ፡፡ ሰዎችን ከኃላፊነት ቦታ ማንሳትና አዳዲስ ፊቶችን ማሳየት መልካም ሆኖ ሳለ፣ በዚያኑ ልክ በሙስና ውስጥ እስከ አንገታቸው የተዘፈቁትንና ሕዝብ ሲያስመርሩ የነበሩትን፣ በሕገወጥ መንገድ ፍትሕ ሲያዛቡና ምሬት የፈጠሩትን ዋነኛ ተዋናዮች ዝም ማለት ትክክል አይሆንም፡፡ ፍትሐዊም አይደለም፡፡ በተጨማሪም የተሃድሶ እንቅስቃሴው ብዙ እየተወራለት ተግባር ሲዘገይ ተዓማኒነት ይጠፋል፡፡

  ሕዝብ በተለይ የአገሪቱን ከፍተኛ ቁጥር የያዘው ወጣት ኃይል ከዘመኑ ጋር በማይመጥን የአመራርና የአስተሳሰብ ዘይቤ መመራት አይፈልግም፡፡ የዘመኑ ሰው በዘመኑ አስተሳሰብ መመራት አለብኝ ሲል ንቃተ ህሊናው ጎልብቷል ማለት ነው፡፡ ሰላሳ ሚሊዮን ያህል ዜጎች በትምህርት ገበታ ላይ በሚገኙበት፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት በጣም እየጨመረ ባለበት፣ የዜጎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፍላጎቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉ በመጡበት፣ የአኗኗር ዘይቤዎች በጣም እየተለወጡ ባሉበት፣ ወዘተ የለውጥ አስፈላጊነት ጎልቶ ይታያል፡፡ ይህንን በከፍተኛ ደረጃ እያደገ የመጣ የለውጥ ፍላጎት ማርካት የሚቻለው ከዘመኑ ጋር በሚመጥን አስተሳሰብና ተግባር እንጂ፣ ከሁለት አሥርት ዓመታት በፊት በነበረ የርዕዮተ ዓለም ወይም የችግር መፍቻ ዘዴ አይደለም፡፡ ለአገር እስካዋጡ ድረስ አማራጮችን ማየት ተገቢ ነው፡፡

  በፖለቲካው መስክ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱን የማጎልበት ጉዳይ በፍፁም መዘንጋት የለበትም፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ተነሳሽነት ሊኖር ይገባል፡፡ ኢሕአዴግ በጣም ከሚተችባቸውና ከሚወገዝባቸው ችግሮች መካከል ይኼው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጉዳይ ዋነኛው ነው፡፡ ከሕዝብ ጋርም ሆድና ጀርባ የሚያደርገው ይኼው ነው፡፡ ሕዝብ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ኖሮ የሚፈልገውን በነፃነት መምረጥ የሚችለው በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲኖሩ ብቻ ነው፡፡ የእነዚህ ዓይነቶቹ ፓርቲዎች መኖር የሚጠቅመው አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲፈጠር፣ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል እንዲሰፍን፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በተግባር እንዲረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፣ በብሔራዊ ጉዳዮች የጋራ መግባባት እንዲፈጠር፣ ወዘተ ነው፡፡ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ በእውነተኛ መንፈስ እንዲጎለብት ከተፈለገ፣ ኢሕአዴግ ግማሽ መንገድ ድረስ በመሄድ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር መነጋገር ወይም መደራደር አለበት፡፡ አርዓያነትም ሊያሳይ ይገባል፡፡ ይህ የዘመኑን ጥያቄ ለመፍታት ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡

  አሁን ወቅቱ የተግባር ነው፡፡ ዓለም በፍጥነት እየተለወጠ ነው፡፡ በአገሪቱ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት በማንኛውም መስክ የሚታዩ ድክመቶችን ማረም፣ የተበላሹትን ማስተካከል፣ ለሕዝብ ፍላጎት መገዛት፣ የሕዝብ ተሳትፎን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደግ፣ ከሕዝብ ጋር በግልጽ መነጋገር፣ በአገሪቱ በሰላም ተቻችሎ ለመኖር የሚረዱ የፖሊሲና የስትራቴጂ ለውጦችን ማከናወን፣ የሕዝብን የልብ ትርታ እያዳመጡ ለለውጥ የሚረዱ ማናቸውንም ዕርምጃዎች ለመውሰድ መዘጋጀት፣ ለወጣቶች የአገር ፍቅር መንፈሳቸውን የሚያሳድጉ ሥራዎችን ማከናወን፣ ማሳተፍና የመሳሰሉት ጠቃሚ ሐሳቦች ይካተታሉ፡፡ ጥልቅ ተሃድሶው ድርጅቱን ከገባበት አጣብቂኝ ውስጥ ከማውጣት በላይ አገሪቱን የሚጠቅምና ሕዝቡን የሚያረካ ይሁን፡፡ በእግር ኳስ የባከነ ሰዓት እንደሚባለው ሁሉ ጊዜን በሚገባ በመጠቀምና ውጤት በመጨበጭ በተነፃፃሪ ሁሉንም ዜጋ ለማስደሰት መትጋት ጠቃሚ ነው፡፡ ያለንበት ዘመን ጊዜ ባለፈባቸው አስተሳሰቦች እንደማይመራ የዓለም በርካታ ክስተቶች እያሳዩ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሕዝቡ ንቃተ ህሊና ጋር የሚመጣጠን ምላሽ ይጠበቃል!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ለትግራይ የተገዛው ነዳጅ ከጅቡቲ መግባት ጀመረ

  ድርድርን በሚመለከት የአሜሪካ መንግስት አቋም እንደማይዝ ተገለጸ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች...

  አዲስ አበባና ኦሮሚያ ወሰን ለማካለል ተስማሙ

  ኮዬ ፈጬ፣ ቱሉዲምቱ፣ ጀሞ ቁጥር 2 ወደ ኦሮሚያ ለቡ፣ ፉሪና...

  መንግስት 8 የስኳር ፋብሪካዎችን ለጨረታ አቀረበ

  መንግስት ስኳር ኢንተርፕራይዞችን ወደግል ለማዛወር በወጣው ጨረታ ባለሐብቶች እንዲሳተፉ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በኢትዮጵያ ላይ የቀጠለው የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት

  ምዕራባውያን አገሮች በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በዲፕሎማሲም...

  የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የድጎማ በጀት ለፖለቲካ ሥራ ማስፈጸሚያ እንደሚውል የሚያሳይ ሪፖርት ቀረበ

  ለመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ የበጀት ድጎማ ከመደበኛው ሥራ ይልቅ ከዋናው...

  መንግሥት የሥራ ግብር ምጣኔን እንዲቀንስ ተጠየቀ

  የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) መንግሥት የሠራተኛውን የኑሮ ጫና...

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የአመራሮች ምርጫና ቀጣይ ዕቅዶቹ

  የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲጠበቅ የነበረውን...

  በ15 ቢሊዮን ብር የተመዘገበ ካፒታል የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቱን ያሻገረው ስንቄ ባንክ ሥራ ጀመረ

  ከማክሮ ፋይናንስ ተቋምነት ወደ ባንክ አገልግሎት ከተሸጋገሩ አምስት የማክሮ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ ሕግና ሥርዓት ይከበር!

  በኢትዮጵያ ምድር ጦርነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ፊትን ወደ ልማት ለማዞር ያለው ፍላጎት አሁንም ፈተና እየገጠመው ነው፡፡ ኢትዮጵያ አዲሱ ዓመት ሲብት በሙሉ...

  የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ አይሁን!

  በጥቂቶች ስግብግብነት ብዙኃኑ ሕዝብ እንዳይጎዳ ተገቢ ሞራላዊ፣ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች ሲወሰዱ ድጋፍ መስጠት ይገባል፡፡ ሰሞኑን መንግሥት በኤሌክትሪክ የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች ሱር ታክስና ኤክሳይስ ታክስን ጨምሮ፣...

  የኢኮኖሚው ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይሆን!

  ጦርነት ውስጥ ያለች አገር ኢኮኖሚ ጤንነት እንደማይሰማው ለማንም ግልጽ ቢሆንም፣ ከጦርነቱ በተጨማሪ በየዕለቱ ገበያው ውስጥ የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ግን አስደንጋጭ እየሆነ ነው፡፡ የብር የመግዛት...