Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየልዩ ፍላጎት ክህሎት ላላቸው ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ መስጠት ይጀመራል

የልዩ ፍላጎት ክህሎት ላላቸው ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ መስጠት ይጀመራል

ቀን:

የልዩ ፍላጎት ክህሎት ላላቸው ባለሙያዎች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት መስጠት ሊጀመር መሆኑ ተገለጸ፡፡

የአካል ጉዳተኞች የልማት ተሳትፎ ተጠቃሚነት፣ በዘላቂ ልማት ግቦችና የልማት ዕቅዶች የማካተትና የመተግበር ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ለመወያየት፣ ላይት ፎር ዘ ወርልድ ባዘጋጀው መድረክ የተገኙት በትምህርት ሚኒስቴር የልዩ ፍላጎት ትምህርት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዓለማየሁ ወልደቂርቆስ እንደተናገሩት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ መስጠት በሚጀመረው የልዩ ፍላጎት ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት፣ መምህራን ወይም መምህራን ያልሆኑ ባለሙያዎች መፈተን ይችላሉ፡፡

በሚኒስቴሩ አጠቃላይ ትምህርት የሙያ ብቃትና ዕድሳት ዳይሬክቶሬት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለመሥራት ካቀዳቸው አንዱ፣ አካል ጉዳተኞች በመማር ማስተማሩ ሒደት የሚገጥማቸውን የመግባባት ክፍተት፣ ብቃት ባላቸው የልዩ ፍላጎት መምህራን መሙላት መሆኑን ያስታወሱት ባለሙያው፣ ሙያው ያላቸውን በመፈተንና የብቃት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀት በመስጠት በዘርፉ ያለውን ክፍተት ለመሙላት እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

እንደ አቶ ዓለማየሁ፣ የብሬልም ሆነ የምልክት ቋንቋ ከሚችሉት አብዛኞቹ መምህራን ቢሆኑም፣ ከመማር ማስተማሩ ሒደት ውጭ በማስተርጎምም ሆነ በሌላ ሥራ ያሉትም የብቃት መመዘኛውን መፈተንና የምስክር ወረቀት ማግኘት ይችላሉ፡፡

ተበታትኖ የነበረውን የልዩ ፍላጎት ትምህርት ለማቀናጀት የልዩ ፍላጎት ትምህርት ስትራቴጂ በ1998 ዓ.ም. መነደፉን በማስታወስ፣ ከአተገባበር ጋር የተያያዙ ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮችን በማስተዋል በ2004 ዓ.ም. ሌላ ስትራቴጂ መነደፉን፣ ይህም መድልኦ ሳይኖር ልጆች እንዲማሩ ለማስቻል መሆኑንና አሁን ላይ በተደረሰው አምስተኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት ፕሮግራምም ፖሊሲውን ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አሁን እየተተገበረ ባለው አምስተኛው የትምህርት ዘርፍ ልማት ፕሮግራም ፍትሐዊና አካታች የሆነ ትምህርትን ለመስጠት የሚረዳ መዋቅር መዘርጋቱና በዚህም የልዩ ፍላጎት ትምህርትን የተመለከተ ዳይሬክቶሬት መቋቋሙ፣ አካል ጉዳተኞች በመማር ማስተማሩ ሒደት ተሳታፊ እንዳይሆኑ የሚያግዱ ችግሮችን ለመቅረፍ ያስችላልም ብለዋል፡፡

በአገሪቱ የሚገኙ የጤና፣ የትምህርት፣ የመንገድና ሌሎች ግንባታዎች ለአካል ጉዳተኞች እምብዛም ተደራሽ አይደሉም፡፡ አገሪቱ በሁሉም ዘርፎች አካል ጉዳተኞችን የሚያሳትፉ መሠረተ ልማት እንዲኖር የተለያዩ ፖሊሲዎችን ብታስቀምጥም ትግበራው ብዙ ይቀረዋል፡፡

በአገሪቱ ከሚገኙት ዩኒቨርሲቲዎችም ስድስት ያህሉ ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ሲሆኑ ሌሎቹ አመቺ አይደሉም፡፡ ሆኖም አገር አቀፍ ፈተናዎች ድርጅት ሁሉንም ተማሪዎች የሚመድበው በአገሪቱ ባሉ ዩኒቨርሲትዎች ነው፡፡ ይህም የአካል ጉዳተኞችን በትምህርት የመሳተፍ ዕድል ፈትኖታል፡፡ ይህንን አስመልክቶ ምላሽ የሰጡት ባለሙያው፣ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ለአካል ጉዳተኞች የሚመች መሠረተ ልማት ባይኖራቸውም፣ አካል ጉዳተኞች በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች የሚመደቡበት ሁኔታ እንዲቀየር ቢከራከሩም ሰሚ አላገኙም፡፡ እንደ ትምህርት ሚኒስቴርም አካል ጉዳተኞች ለእነሱ በሚያመቹ ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ እንዲመደቡ፣ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች አካል ጉዳተኞችን የሚያስተናግዱ መሠረተ ልማት ሲያሟሉ ደግሞ ምደባውን በሁሉም የማድረግ ሥራ ቢቀጥል እንደሚሻልም ይመክራሉ፡፡

አካል ጉዳተኛ ልጆች በተለይም በገጠር ያሉት ከማኅበረሰቡ ግንዛቤ አንፃር ከቤት እንደማይወጡ፣ በዚህም ምክንያት ትምህርት እንደማያገኙ በመድረኩ የተነሳ ጥያቄ ነበር፡፡ አቶ ዓለማየሁ እንደሚሉት፣ ሁሉም ሕፃናት ትምህርት ቤት እንዲሄዱ ቅስቀሳው ይሠራል፡፡ ችግሩ ግን አካል ጉዳተኞቹ ትምህርት ቤት ቢመጡም በቂ የሠለጠነ የሰው ኃይል ባለመኖሩ የሚያስተናግዳቸው አለማግኘታቸው ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲዎች ያሉ ተማሪዎች ተመርቀው የሚወጡት የንድፈ ሐሳብ ትምህርት እንጂ የተግባር ስለማይቀስሙ ተማሪዎቹን ለመርዳትም ይቸግራቸዋል፡፡ ከሥልጠና ብቃት ማነስ ጋር ተያይዞ ሊያስተምር የሚችል ካለመኖሩም በተጨማሪ የማበረታቻ ጉዳይ ሁሌም እንዳከራከረ ነው፡፡

የክፍል ጥበት ሌላው ችግር ሲሆን፣ ተማሪዎቹ ግን ለመማር ፍላጎት እንዳላቸው ማየታቸውን አቶ ዓለማየሁ አክለዋል፡፡

በተደረገ ዳሰሳ አንዳንድ ቦታ ላይ አንድ ዓይነት የአካል ጉዳት ለምሳሌ ሸሽቾ በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ 500 መስማት የተሳናቸው ተማሪዎች በመኖራቸው፣ በአማራ ክልል ደግሞ ዓይነ ስውራን በብዛት በመታየታቸው ክልሎቹ የአካል ጉዳቱ እንደሚፈልገው ምላሽ፣ ለመምራን ሥልጠና እንዲሰጡ መምከራቸውን ተናግረዋል፡፡

የአካል ጉዳተኛውን ታሳቢ ያደረጉና አካታች የሆኑ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በየሴክተር መሥሪያ ቤቱ ቢኖሩም ተቀናጅተው አለመሥራታቸው ችግር እንደሆነም ተነግሯል፡፡ በዘርፉ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኔትወርክ መፍጠራቸውን የላይት ፎር ዘ ወርልድ ከፍተኛ የኢንክሉዥን አማካሪ ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሤ ሲገልጹ፣ የድርጅቱ ከፍተኛ ፕሮግራም ኦፊሰር አቶ አብርሃም ወርቁ በበኩላቸው፣ የአካል ጉዳተኛውን ችግር ለመቅረፍም ሆነ በሁሉም ልማቶች ለማካተት በዘርፉ የሚሠሩ ሁሉ መቀናጀት እንዳለባቸው መክረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...