Monday, October 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየረዥም ርቀት ሩጫ ጀግናው ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ሥርዓተ ቀብር በወታደራዊ ሥርዓት ተፈፀመ

የረዥም ርቀት ሩጫ ጀግናው ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ሥርዓተ ቀብር በወታደራዊ ሥርዓት ተፈፀመ

ቀን:

– ለክብሩ ዘጠኝ ጊዜ ተተኩሷል

በኦሊምፒክ፣ በሉላዊና በአህጉራዊ የአትሌቲክስ መድረኮች በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ ተደራራቢ ድሎቹ ነግሦ የነበረው ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ሥርዓተ ቀብር፣ እሑድ ታኅሣሥ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ፡፡

በሞስኮ ኦሊምፒክና በሌሎች መድረኮች በ5,000 ሜትርና በ10,000 ሜትር ሩጫ ከአሯሯጥ ስልቱና ከአጨራረስ ስኬቱ በመነሣት ‹‹ይፍተር ዘሺፍተር››- ማርሽ ቀያሪው ይፍጠር፣ ‹‹ይፍተር ዘማስተር››- የሩጫው ጌታ ይፍጠር- የሚሉ ቅፅል ስሞችን በዓለም ዙርያ የተጎናፀፈው የአየር ኃይል ሻምበል ምሩፅ፣ ሥርዓተ ቀብሩ እሑድ በስምንት ሰዓት በክብር ዘብና በማርሽ ባንድ ሐዘናዊ ቃና ታጅቦ ከመፈጸሙም ባሻገር፣ ግብዓተ መሬቱ ሲፈጸም ለክብሩ ዘጠኝ ጊዜ የተኩስ ድምፅ ተሰምቷል፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ ከአገር ቤትና ከካናዳ የመጡ ቤተሰቦችና ዘመዶች፣ ወዳጆችና የአሁንና የቀድሞ ሚኒስትሮች፣ የአሁንና የቀድሞ ጄኔራል መኰንኖች፣ ዲፕሎማቶች፣ ልዑላን ቤተሰቦችና አድናቂዎች በተገኙበት ሥርዓተ ቀብር ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የምሩፅን ሀገራዊ ውለታ ያስታወሰ የሐዘን መግለጫ መልእክት በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ርስቱ ይርዳው አማካይነት ተነቧል፡፡ ብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴም ባደረገው ንግግር ምሩፅ የብዙዎች አርአያ እንደነበረ አስታውሷል፡፡

በካናዳ ቶሮንቶ ሐሙስ ታኅሣሥ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ያረፈው ሻምበል ምሩፅ አስክሬን አዲስ አበባ የደረሰው እሑድ ማለዳ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከከፍተኛ ሹማምንት፣ ከስፖርት ማኅበረሰቡና ከቤተሰቡ ጋር በመሆን ተቀብለውታል፡፡ አስክሬኑ ከአውሮፕላን እንደወረደ የክብር ዘብ አጅቦታል፡፡

 እስከ ረፋዱ አምስት ሰዓት በቦሌ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በሚገኝ መኖሪያ ቤት ቆይታ ካደረገ በኋላ፣ በዳግማዊ ምኒልክ ጎዳና በመስቀል አደባባይ በኩል ወደ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በማርሽ ባንድና በክብር ዘብ ዝግታ ጉዞ ሲያደርግ በየመንገዱ የነበሩ እግረኞችና ባለተሸከርካሪዎች ሐዘናቸውን ሲገልፁ ታይተዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያኒቱ እንደደረሰም ጸሎተ ፍትሐቱ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ መሪነት የተከናወነ ሲሆን በካናዳ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማትያስ ዳግማዊ ተገኝተዋል፡፡

‹‹ይፍጠር ዘማስተር›› – ይፍጠር የሩጫው ጌታ

መስከረም 1961 ዓ.ም. (ሴምተምበር 1968) አበበ ቢቂላና ማሞ ወልዴን የያዘው በሜክሲኮ ኦሊምፒክ የሚሳተፈው ብሔራዊ ቡድን፣ የመጨረሻ ጉዞውን ወደ ሜክሲኮ ሲቲ ከማድረጉ በፊት ለልምምድ ቆይታ ያደረገው የኤርትራ ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማ በነበረችው አስመራ ነበር፡፡ ቡድኑ በንግሥተ ሳባ ስታዲየም ልምምድ ሲያደርግ ምሩፅ ይፍጠር የወደፊት ሕይወቱ በር ከፋች አጋጣሚ ፈጠረለት፡፡ በልምምድ ሩጫ ውድድርም ከነማሞ ወልዴ ጋር ተወዳድሮ ለውጤት ባይበቃም አሯሯጡንና አቅሙን ያስተዋሉት ዋና አሠልጣኝ ንጉሤ ሮባ በአየር ኃይል ስፖርት መምሪያ እንዲያዝና ልምምድ እንዲያደርግ አደረጉ፡፡ ቅጥሩንም ፈጸመ፡፡ ለ17 ዓመታት በአየር ኃይል ሲያገለግል እስከ ሻምበልነት ደርሷል፡፡ ከ1978 በኋላም ወደ ስፖርት ኮሚሽን ተዘዋውሯል፡፡

በአዲስ አበባው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስታዲየም፣ ንብ የሚባለውን የአየር ኃይል ስፖርት ክለብን እየወከለ በብሔራዊ ሻምፒዮናና በጦር ኃይሎች ውድድር ባለድል መሆን የጀመረው ምሩፅ፣ ካገኛቸው ሽልማቶች በተጨማሪ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የእጅ ሰዓት መሸለሙ ይታወቃል፡፡

ምሩፅ የመጀመሪያው ኢንተርናሽናል ውድድሩ በ1962 ዓ.ም. በምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታንዛኒያ ውስጥ በ1,500 ሜትር ከኦሊምፒክ ባለወርቁ ኬፕቾግ ኬይኖ ጋር ተወዳድሮ ሦስተኛ የወጣበት ውድድሩ ነበር፡፡ በ1963 ዓ.ም. በአሜሪካ በተካሄደው የአፍሮ አሜሪካን ውድድር በ10 ሺሕ ወርቅ፣ በ5 ሺሕ ሜትር ብር ሜዳሊያ በማግኘት ድሉን አሐዱ ብሎ ጀምሯል፡፡

በ1965 ዓ.ም. በሌጎስ (ናይጄሪያ) በተካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በ10 ሺሕ ወርቅ በ5 ሺሕ ብር አሸንፏል፡፡ በዚያው ዓመት ከሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ከተውጣጡት መካከል የኢትዮጵያ ስፖርት ኮከብ አትሌት ተብሎም ተመርጧል፡፡

የመጀመሪያው የኦሊምፒክ መድረኩ በሆነው 20ኛው ኦሊምፒያድ በሙኒክ ሲካሄድ ምሩፅ በ5 ሺሕና በ10 ሺሕ ሜትር ለመወዳደር ነበር ወደ ሥፍራው ያመራው፡፡ በ10 ሺሕ ሜትር በማጣሪያው አንደኛ ወጥቶ በፍጻሜው ሦስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያን ሲያገኝ፣ በ5 ሺሕ ሜትር ማጣሪያ ‹‹በአሠልጣኞቹ ችግር›› ምክንያት በጊዜ ባለመድረሱ የተነሳ ሳይወዳደር በመቅረቱ ሌላ ሜዳሊያ የማግኘት ዕድሉ ተጨናግፎበታል፡፡

በ1968 ዓ.ም. በሞንትሪያል (ካናዳ) በተካሄደው 21ኛው ኦሊምፒያድ ያለ ጥርጥር በ5,000 እና በ10,000 ሜትር ሁለት ወርቅ ያገኛል ተብሎ ቢጠበቅም፣ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ስፖርታዊ ግንኙነት የነበራት ኒውዚላንድ ከሞንትሪያል ኦሊምፒክ ባለመታገዷ ምክንያት አፍሪካውያን አንካፈልም በማለታቸው ሳይወዳደር ተመለሰ፡፡ በሙኒክ ኦሊምፒክ ምሩፅን ያሸነፈው ፊንላንዳዊው ላሲ ቨረን ዳግመኛ ድሉን ምሩፅ በሌለበት አጣጣመ፡፡

ምሩፅ የኦሊምፒክ ወርቅ ሕልሙን ያሳካው በ1972 ዓ.ም. ሞስኮ ባስተናገደችው 22ኛ ኦሊምፒያድ ሲሆን በሁለቱም ርቀቶች ወርቁን ያጠለቀው ፊንላንዳዊውን ላሲ ቨረንን ድል በመምታት ነበር፡፡

በሞስኮ ኦሊምፒክ ሲሮጥ ዕድሜው የገፋው (በፓስፖርት ዕድሜው 36 ዓመቱ በተለያዩ ሚዲያዎች እስከ 42 የሚያደርሱት) ምሩፅ፣ በ1969 ዓ.ም. እና በ1971 ዓ.ም. በተካሄዱት የዓለም አትሌቲክስ ዋንጫዎች አፍሪካን በመወከል አራት ወርቅ ሜዳሊያ ሲያገኝ ተወዳዳሪዎቹን በቀደመበት ርቀት ያህል በሞስኮ አልደገመውም፡፡ ዕድሜው ገፍቷልና፡፡

በሁለቱ የዓለም ዋንጫዎች፣ በ5,000 ሜትር ውድድሩ ሊያበቃ 500 ሜትር ሲቀር፣ በ10 ሺሕ 600 ሜትር ሲቀር ነበር ማርሽ ቀይሮ በማፈትለክ ያሸነፈው፡፡ በሞስኮ ኦሊምፒክ ግን በሁለቱ ርቀቶች እንደ ቅደም ተከተላቸው 200 ሜትርና 300 ሜትር ሲቀረው ነበር ማርሽ ቀይሮ ድል የመታው ምሩፅ፤ በ1971 ዓ.ም. በዓለም ዋንጫ አፍሪካን ወክሎ ለመካፈል የበቃውም የመጀመሪያው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዳካር (ሴኔጋል) ሲካሄድ ሁለት ወርቅ (በ5 ሺሕና 10 ሺሕ) በማግኘቱ ነበር፡፡

ምሩፅ 1971 ዓ.ም. ወርቃማ ዓመቱ ነበር፡፡ እጅግ የገነነበት ታላቅ ክብርንም የተቀዳጀበት፡፡ በዚያው ዓመት በቼኮዝሎቫኪያ በተዘጋጀው የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ ከተመረጡት ዘጠኝ አትሌቶች አንዱ ምሩፅ ሲሆን፣ ‹‹የኮከቦች ኮከብ›› ተብሎ መመረጡና በተዘጋጀው የተሸላሚዎች መድረክ ከመሃል በከፍታ መቀመጡ ይታወሳል፡፡ የወርቅ ጫማም ተሸላሚ ነበር፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት (የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ) ሻምበል ምሩፅ በቅድመ ሞስኮ ኦሊምፒክ ባገኛቸው አህጉራዊና ኢንተርናሽናል ድሎች ኢትዮጵያን ለታላቅ ግርማ ሞገስ በማብቃት ለፈጸመው አኩሪ ተግባር አምስተኛው የአብዮት በዓል ሲከበር ‹‹የጥቁር ዓባይ ኒሻን››ን ከርዕሰ ብሔሩ ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እጅ መቀበሉ ይታወሳል፡፡

በ800 ሜትር በ1,500 ሜትር መወዳደር የጀመረው ምሩፅ፣ 5 ሺሕና 10 ሺሕ መደበኛ ውድድሮቹ ቢሆኑም በጎዳና ላይ ሩጫዎችም ተደጋጋሚ ድሎች ማግኘቱ አይሳትም፡፡

በተለይ በተከታታይ ዓመታት ድል የተጎናፀፈበት የፖርቶ ሪኮ ግማሽ ማራቶን ውድድር ለዓለም ክብረ ወሰን የበቃበት ነበር፡፡ ጥር 29 ቀን 1969 ዓ.ም. በፖርቶ ሪኮ ኮዓሞ የ21 ኪሎ ሜትር (ግማሽ ማራቶን) ውድድር ምሩፅና መሐመድ ከድር ተከታትለው ሲያሸንፉ፣ ምሩፅ የገባበት 1 ሰዓት 02 ደቂቃ 57 ሰከንድ ያለም ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቦለታል፡፡

በ1972 በፖርቶ ሪኮ ግማሽ ማራቶን አሸንፎ እንደተመለሰ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫም ‹‹የማተኩረው በሞስኮ ኦሊምፒክ ስለሆነ በፖርቶ ሪኮው ድሌ አልኮራም›› ማለቱ አይዘነጋም፡፡

በሞስኮ ኦሊምፒክ ለሦስተኛ ጊዜ ድሉን ለማጣጣም ቋምጦ የነበረው ፊንላንዳዊ ላሲ ቬረን በሞስኮ አየሩ ጥሩ ከሆነ እንደሚያሸንፍ መናገሩን ተከትሎ ምሩፅ በሰጠው አፀፋ ‹‹ሐሩርም ይሁን በረዶ እኔ ከማሸነፍ የሚገታኝ አንዳች ኃይል የለም›› ማለቱ ልበ ሙሉነቱን ያሳየበት አጋጣሚ ነበር፡፡

የሞስኮ ኦሊምፒክ ድሉ ምሩፅን አስደናቂና ትንግርተኛ አትሌት ያደረገው፣ በዘመኑ ኦሊምፒክ እንዳሁኑ በቀጥታ የ10 ሺሕ ፍፃሜ ብቻ ሳይሆን ማጣሪያውን አልፎ በጥቅሉ 20 ሺሕ ሜትር መሮጡ፣ እንዲሁም በ5ሺሕ ለፍፃሜ ድሉ የበቃው ሁለት ማጣሪያዎቹን በድል በመወጣትና በጥቅሉ 15ሺሕ ሜትር በመሮጥ ነበር፡፡ 

ከሞስኮ ኦሊምፒክ ድሉ በኋላ ጥንታዊ ኦሊምፒክ በተመሠረተበት ግሪክ ለኦሊምፒያዊ ሽልማት ከተመረጡ አምስት አትሌቶች ቀዳሚ ሆኖ የኦሊምፒክ ሎሬት አክሊልን ከርዕሰ ብሔሩ የተቀበለው ምሩፅ ይፍጠር ነበር፡፡

በዓለም አትሌቲክስ ታሪክ ‹‹አረንጓዴ ጎርፍ›› የተሰኘ መጠርያ ያተረፈው በ1973 ዓ.ም. የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር በ12 ኪሎ ሜትር በተወዳደረውና በቡድን አንደኛ በወጣው ስብስብ ውስጥ አንዱ የነበረው ምሩፅ ይፍጠር ነበር፡፡ በ1974 እና በ1975 ዓ.ም. በተካሄዱት ተመሳሳይ ውድድሮችም ተሳትፏል፡፡ በሎስ አንጀለስ ኦሊምፒክ በማራቶን ለመወዳደር አልሞ የነበረው ምሩፅ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሶቭየት ኅብረት አልካፈልም በማለቷ ‹‹አጋርነቱን›› ለመግለጽ አገሪቱ እንዳትሳተፍ በማድረጉ ሕልሙ እውን አልሆነለትም፡፡ ከ13 ዓመት በላይ ባስቆጠረው የኢንተርናሽናል ተወዳዳሪነቱ ምሩፅ 271 ጊዜ ድል ማድረጉ ይነገርለታል፡፡

በዓለም ገናና ለሆነው ኃይሌ ገብረሥላሴን ጨምሮ ለኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ለሞሮኮው ሰዒድ አዊታና ሌሎች አፍሪካውያን አርአያ የሆነው ምሩፅ፣ ኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር በ1973 ዓ.ም. በምዕራብ ጀርመን ባደን ባደን ጉባኤውን ሲያካሂድ፣ የዓለም አትሌቶችን ከወከሉ ሁለት አትሌቶች አንዱ ርሱ ነበር፡፡ ሁለተኛው ተወካይ እንግሊዛዊው ያሁኑ የኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ፕሬዚዳንት የያኔው የሞስኮ ኦሊምፒክ የ1,500 ሜትር ባለድል ሰባስቲያን ኮ ነበር፡፡

ከአባቱ አቶ ይፍጠር ተክለሃይማኖትና ከእናቱ ወ/ሮ ለተገብርኤል ገብረአረጋዊ ጥቅምት 5 ቀን 1936 ዓ.ም. በቀድሞ አጠራሩ በትግራይ  ጠቅላይ ግዛት፣ ዓጋመ አውራጃ፣ ዛላምበሳ ወረዳ እመበይቶ በተሰኘ ቦታ  የተወለደውና በ72 ዓመቱ ያረፈው ምሩፅ ይፍጠር የስምንት ልጆች አባት ነበር፡፡

በመኖሪያ ቤቱ በተዘጋጀው የሐዘን መግለጫ መዝገብ ላይ በላይ አቶ በቀለ ወያ እንዲህ ገጠሙ፡፡

‹‹በታሪክ መንገድ – ማርሽ ቀያሪ

በታሪክ ሀገር – ታሪክ ፈጣሪ

በሠራው ሥራ – ህያው ነውና

ሞተ አይባልም – ሲያርፍ አንድ ጀግና፡፡››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...