Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየልደት በዓል ግርዶሽ

የልደት በዓል ግርዶሽ

ቀን:

ለአላፊ አግዳሚ እንዲታዩ በየመደብሩ መግቢያ በር ላይ የተደረደሩ የገና ዛፎች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የከተማዋ አንድ ገጽታ ሆነዋል፡፡ ከመደብሮች ባለፈ የጎዳና ላይ ቸርቻሪዎች መጠናቸው የተለያየ የገና ዛፎችን፣ ማስጌጫ መብራቶችና ኳሶች ለገበያ አቅርበዋል፡፡ የሸማቹ ቁጥርም ጥቂት አይደለም፡፡ በሆቴሎችና መገበያያ ሕንፃዎች የቆሙ ግዙፍ የገና ዛፎችም ይጠቀሳሉ፡፡ በየዓመቱ የልደት በዓል ሲቃረብ ይህንን ድባብ ማስተዋል እየተለመደ መጥቷል፡፡ ከዓመት ወደ ዓመት የገና ዛፍ ሻጮችና የገዥዎችም ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡

የተጠቃሚዎች ቁጥር ከመጨመሩ በተቃራኒው፣ የገና ዛፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የልደት በዓል አከባበር ጋር የተያያዘ አይደለም የሚል ትችትም ይሰነዘራል፡፡ መጤ ከሚባሉ ባህሎች አንዱ እንደሆነ በመግለጽ የገና ዛፍ መበረታታት የለበትም የሚሉ  ወገኖችም አሉ፡፡ ታኅሣሥ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም አዳራሽ የተካሄደው ውይይት ያተኮረውም በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ነበር፡፡ በኢጋ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን የተዘጋጀውን ውይይት የባህል፣ የማኅበረሰብ ጥናት፣ የታሪክ፣ የኪነ ጥበብና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች የታደሙት ሲሆን፣ ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) በልደት በዓል አከባበር ተፅዕኖ እያደረገ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

በውይይቱ የጥናት ወረቀት ካቀረቡት አንዱ የማኅበረሰብ ጥናት ተመራማሪው ዶ/ር ዜና ብርሃኑ፣ ኢንፎርሜሸን ቴክኖሎጂ፣ ዓለም አቀፍ ወይም ድንበር ዘለል የንግድ ተቋሞችና በአገሮች መካከል ያለው ፖለቲካዊ ትስስር መለወጡ ሉላዊነትን እያፋጠኑ መምጣታቸውን ያነሳሉ፡፡ የትኛውም አገርና ማኅበረሰብ ከሉላዊነት ተፅዕኖ ውጪ ሊሆን እንደማይችልም ያክላሉ፡፡ ‹‹በፈጣን የመረጃ ልውውጥና የሰዎች ፍልሰት ምክንያት የባህል መዳቀል ይፈጠራል፡፡ ይህ ተመሳሳይነት ያለው ባህል ለመፈጠሩ አንዱ ምክንያት ይሆናል፤›› በማለትም ይገልጻሉ፡፡

- Advertisement -

የሉላዊነት ፈጣን ሥርጭትን እንደ መነሻ ገልጸው፣ የልደት በዓል አከባበር እንደ ማሳያ ሲወሰድ፣ ኢትዮጵያ እንደ ሌሎች አገሮች በሉላዊነት ተፅዕኖ ሥር መውደቋን ያስረዳሉ፡፡ በዋነኛነት የሚጠቅሱት ምሳሌ የገና ዛፍ ተጠቃሚዎች ቁጥር መጨመሩን ነው፡፡ ቆም ብሎ የገና ዛፍ ለኢትዮጵያውያን የሚሰጠው ትርጉም ምንድነው? ብሎ መጠየቅ እንደሚያስፈልግ ያምናሉ፡፡

ሆቴሎች የተለያዩ አገሮችን ተወላጆችን ስለሚያስተናግዱ እንግዶቻቸው አገራቸው ያሉ እስከሚመስላቸው ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የገና ዛፍን ሊጠቀሙበት ቢችሉም፣ ለተቀረው ማኅበረሰብ ያለው ፋይዳ አጠያያቂ ነው ይላሉ፡፡ ልደት ሲከበር ሃይማኖታዊውና ባህላዊው ሥርዓት የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ብለዋል፡፡

ኢኮኖሚስቱ አቶ ሰለሞን ገብረሥላሴ ያቀረቡት ጥናት፣ ጉዳዩ ለገና ዛፍ ከሚወጣው ወጪ አንፃር ተዳሷል፡፡ ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በተገኘ መረጃ መሠረት፣ እ.ኤ.አ. በ2011 የገና ዛፍን ጨምሮ ሌሎች ከገና ጋር የተያያዙ ቁሳቁሶችን ከውጪ ለማስመጣት 395,106 ዶላር፣ በ2015 ደግሞ 930 ሺሕ ዶላር ወጥቷል፡፡ ወጪው ከዓመት ወደ ዓመት እየናረ መምጣቱን ባለሙያው ገልጸው፣ ሁኔታው እንዲቀየር የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

አቶ ሰለሞን እንደሚሉት፣ በልደት በዓል በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ያለው አከባበር የበለጠ መጉላት አለበት፡፡ ከበዓሉ አከባበሮች አንዱ የገና ጨዋታ ሲሆን፣ የጨዋታውን ባህላዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ለገና ጨዋታ ሩርና ኳስ መሥራት አገር ውስጥ የሚዘጋጁ ምርቶችን ከማበረታታት አንፃር ይታያል፡፡ በሚጫወቱት ቡድኖች ውስጥና ውጪ ትብብርና ፉክክር የመፍጠር ኃይል አለው፡፡ የጨዋታውን ማኅበራዊ ትስስር ለመረዳት ‹‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ የሚለውን አባባል መጥቀስም ይቻላል፤›› ይላሉ፡፡ ስለ በዓሉ አከባበር ውይይት የሚደረግባቸው መድረኮች በመፍጠር እንደ ገና ጨዋታ ላሉ ባህሎች ቦታ መስጠት ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡

የበዓሉን አከባበር በማንፀባረቅ ረገድ ትልቁን ድርሻ የሚወስዱት መገናኛ ብዙኃን እንደሆኑ የገለጸው ሌላው ጥናት አቅራቢ የሙዚቃ ሐያሲ ሠርፀ ፍሬስብሐት ነው፡፡ የግለሰቦችንና የአንድን ማኅበረሰብ የአኗኗር ዘዬ ለመለወጥ በሚዲያ የሚሰራጩ መረጃዎች ጉልበት ቀላል አይደለም፡፡ ሰርፀ እንደሚለው፣ ቀድሞ በቴአትር ቤቶች ዐውደ ዓመትን ምክንያት በማድረግ የሚዘጋጁና የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን ባህል የሚያሳዩ መርሐ ግብሮች በመገናኛ ብዙኃን ሽፋን ይሰጣቸው ነበር፡፡ ከ1990ዎቹ ወዲህ የመገናኛ ብዙኃን አካሄድ መለወጡ፣ በበዓላት አከባበር ተፅዕኖ እንዳደረገም ይናገራል፡፡

ከመገናኛ ብዙኃን በተጨማሪ የማኅበረሰቡ አኗኗር እየተለወጠ መምጣቱም በበዓል አከባበር ላይ የራሱን አሻራ ትቷል ይላል፡፡ እንደ ኮንዶሚኒየም ባሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ያለው አኗኗር ጉርብትናን እንዳቀዘቀዘው ያምናል፡፡ ግላዊ ኑሮ፣ በልደት በዓል አከባበር ብቻ ሳይሆን በሌሎች በዓላት ማለትም በአዲስ ዓመት የአበባአየሽወይ ጭፈራና የቡሔ ጭፈራ መቀዛቀዝም ማስከተሉን ይገልጻል፡፡

ሉላዊነት በበዓላት አከባበር ተፅዕኖ እያሳደረ ስለመሆኑ ከዶ/ር ዜናና ከአቶ ሰለሞን ጋር የተስማማው ሰርፀ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የራሷን መገለጫዎች ይዛ እንጂ የራሷን ጥላ ሉላዊነትን መቀላቀል የለባትም፤›› ይላል፡፡ እንደ በዓላት አከባበር ያሉ ግዙፍነት የሌላቸው ባህላዊ ቅርሶች (ኢንታንጀብል ካልቸራል ሔሪቴጅ) ሲጠፉ ቀስ በቀስ እንደሆነና ቅርሶቹን መጠበቅ የሁሉም የማኅበረሰቡ አካል ኃላፊነት እንደሆነም ተመልክቷል፡፡

ከውይይቱ ታዳሚዎች መካከል የባህላዊ እሴቶች ጥበቃ ትኩረት እንዲሰጠው የጠየቁ ነበሩ፡፡ ባህላዊ እሴቶች ላይ አደጋ ስለመጋረጡ ዘወትር እሮሮ ቢሰማም ተጨባጭ መፍትሔ ሲቀርብ እንደማይታይ የገለጹም ነበሩ፡፡

የሉላዊነት ተፅዕኖ በልደት በዓል አከባበር ብቻ ሳይሆን በሌሎችም እሴቶች ላይ እንደሚታይ የገለጹ አንድ አስተያየት ሰጪ፣ የሉላዊነትን አዎንታዊ ጎኖች ከአሉታዊዎቹ ለይቶ በበጎው ላይ ብቻ ቢተኮር ተመራጭ ነው ብለዋል፡፡

የውይይቱ መነሻ የሆነው የልደት በዓል አከባበርን በተመለከተ አማራጭ የአከባበር መንገዶች ተሰንዝረዋል፡፡ ከአስተያየት ሰጪዎቹ አንዷ፣ የገና ዛፍን በከብቶች ግርግም ቅርፅ መተካት ይቻላል ብላለች፡፡ በአንዳንድ መገበያያ ሕንፃዎች መግቢያ በር በገና ዛፍ ፈንታ የከብቶች ግርግም አስተውለናል፡፡ የልደት በዓልን ሃይማኖታዊ ሥርዓትና ባህላዊ አከባበር ለማንፀባረቅ በጭድ የተሠራ ግርግም ለሽያጭ ያቀረቡም ገጥመውናል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...