Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምየእስራኤል ፖሊሶች ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ላይ ያደረጉት የሙስና ምርመራ

የእስራኤል ፖሊሶች ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ላይ ያደረጉት የሙስና ምርመራ

ቀን:

አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር በወንጀል ተጠርጥሮ በፖሊሶች ምርመራ ተደረገበት ሲባል መስማትና ማየት ለአፍሪካውያን ብርቅ ይሆናል፡፡ በአፍሪካ ጠቅላይ ሚኒስትሮችም ሆኑ ፕሬዚዳንቶች በተለይ በሥልጣን ላይ እያሉ ለሚፈጽሙት በደል፣ ወይም ለተጠረጠሩበት ወንጀል እምብዛም ሲጠየቁ አይስተዋሉም፡፡

ለእስራኤላውያኑ ግን እንዲህ ዓይነቱ አሠራር ሕዝብን በታማኝነት ከማገልገል ይቆጠራል፡፡ በመሆኑም በጥፋት የተጠረጠረም ሆነ ያጠፋ ባለሥልጣን፣ ሥልጣኑን መብት አድርጎ ከሕግ የበላይነት ሊያመልጥ አይችልም፡፡ ለዚህም የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በሙስና ተጠርጥረው ለሦስት ሰዓታት ያህል ለፖሊስ ቃላቸውን የሰጡበት የሰሞኑ ክስተት አንዱ ማሳያ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ የተጠረጠሩባቸውን ወንጀሎች በተመለከተ በፖሊስ ከመጠየቃቸው አስቀድሞ፣ ለስምንት ወራት ያህል በድብቅ ምርመራ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ በዚህም ጊዜ 50 ያህል ምስክሮች የተጠየቁ ሲሆን፣ ኔታንያሁ ለምርመራ የቀረቡትም ይኼ ከተጠናቀቀ በኋላ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጀሩሳሌም ፖስት እንዳሰፈረው፣ ኔታንያሁ በሙስና ከተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች አንዱ በሆነው፣ ‹‹ከነጋዴዎች ጥቅማ ጥቅም ማግኘት›› ተጠያቂ ሆነዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ኔታንያሁ በሙስና መጠየቅ አለባቸው የሚሉ የተቃዋሚዎችን ጥያቄዎች ተከትሎ ፖሊስ ምርመራ እንደሚያደርግ ሲያስታውቅ፣ ለፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውና ለመገናኛ ብዙኃን ‹‹ወሬ እየጨማመራችሁ አታጋኑ፣ ምንም አይፈጠርም፣ ምክንያቱም ምንም አልነበረም፤›› በማለት የተናገሩት ኔታንያሁ፣ በፖሊስ የተጠየቁት ጥያቄና የሰጡት ምላሽ ግልጽ ባይወጣም፣ ‹‹የሠራሁት ወንጀል የለም›› ሲሉ ለሚዲያ ተናግረዋል፡፡

በእየሩሳሌም በሚገኘው መኖሪያቸው ፖሊስ ላቀረበላቸው ጥያቄ መልስ የሰጡት ኔታንያሁ፣ በሺዎች የሚቆጠር ዶላር የሚያወጡ ያልተገቡ ስጦታዎች ከአገር ውስጥና ከውጭ ነጋዴዎች ተቀብለዋል ተብሎ በየሚዲያው ተሠራጭቷል፡፡ ከዚህ ቀደምም ለአገሪቱ የተበረከቱ ስጦታዎችን ለግል ጥቅማቸው ወስደዋል ተብለዋል፡፡

ከረዥም ጊዜ በፊት ጀምሮ ከቱጃር እስራኤላውያንና የውጭ ዜጎች ስጦታ ማግኘት በሚለውና ከዚሁ ጋር በተያያዙና ባልተጠቀሱ ጉዳዮች የተጠየቁት ኔታንያሁ፣ ለሊኩድ ፓርቲ ሕግ አውጭዎች፣ ‹‹ሁሉንም የሚዲያ ዘገባ አድምጠናል፡፡ በቴሌቪዥን ጣቢያ ስቱዲዮዎችና በተቀዋሚ ፓርቲዎች ቢሮዎች የነበረውን የደስታ መንፈስ አይተናል፡፡ ለፈንጠዝያው ትንሽ ዘግየት እንዲሉ እፈልጋለሁ፡፡ እናንተ አቧራ ብታስነሱም እኛ እስራኤልን መምራት እንቀጥላለን፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

የኔታንያሁ ተቃዋሚዎች ከዚህ ቀደም የተለያዩ ወንጀሎችን ሠርተዋል እያሉ ቢወነጅሏቸውም፣ አንዱም ውንጀላ ማስረጃ ተገኝቶበት ለፍርድ አላበቃቸውም፡፡ ሆኖም ከወራት በፊት በተቃዋሚዎች በተነሱ ጥያቄዎች ሳቢያ የአገሪቱ ፀረ ሙስና ክፍል ፖሊሶች፣ ኔታንያሁን ለተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች ምላሽ እንዲሰጡ አድርገዋል፡፡

ኔታንያሁ ከተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች መካከል ከጀርመን የተገዛው ሰርጓጅ መርከብ ተጠቃሽ ነው፡፡ ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ሰርጓጅ መርከቡ ከጀርመን ሲገዛ የኔታንያሁ የግል ጠበቃ ድርድር ውስጥ ተሳትፏል የሚል ነው፡፡

የኔታንያሁ የግል የሕግ አማካሪ ዴቪድ ሺምሮን ከጀርመን የጦር መሣሪያ አምራቹ ኩባንያ ጋር ድርድር አድርገዋል ቢባሉም፣ ከሰርጓጅ መርከቡ ግዥ ውል ጀርባ ያለው ቴይሰንክሩፕ ኩባንያ፣ ከግዢው ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ማጭበርበር እንዳልተፈጸመ አሳውቋል፡፡

ሆኖም ይኼ ምስክርነት ናታንያሁን ከመጠየቅ አላዳነም፡፡ የጥቅም ግጭት በሚፈጥር አሠራር የጦር መሣሪያ ግዢ አፅድቀዋል ተብለው ተጠይቀዋል፡፡

ከካርበን ልቀት ፈቃድና ከታክስ ጋር በተያያዘ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው ስምንት ዓመት እስራት ከተፈረደባቸው ፈረንሣዊ አርናውድ ማያምራን፣ እ.ኤ.አ. በ2009 ለነበራቸው የምርጫ ቅስቀሳ ገንዘብ ተቀብለዋል የተባሉ ቢሆንም፣ ‹‹ፍፁም ውሸት›› ብለውታል፡፡ ቢሯቸው በሰጠው መግለጫም፣ ገንዘቡን የተቀበሉት እ.ኤ.አ. በ2001 መሆኑን፣ በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳልነበሩና ገቢ የተደረገው 40 ሺሕ ዶላርም የእስራኤል ገጽታን በውጭው ዓለም መገንባትን ጨምሮ ለማኅበረሰብ አቀፍ ሥራዎች ማስፈጸሚያ እንደዋለ አሳውቋል፡፡

የሕዝብ ገንዘብ ያላግባብ ለግል ጥቅም ማዋልም ሌላው ኔታንያሁን ያስጠየቀ አጀንዳ ነው፡፡ በእንግሊዝ ለነበራቸው የአንድ ቀን ቆይታ ሚስታቸውን ይዘው በመሄድ 127 ሺሕ ዶላር ያወጡትን ጨምሮ ሌላም የሕዝብ ገንዘብ አባክነዋል ተብለውም ተወንጅለዋል፡፡

ኔታንያሁ በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ በፖሊስ የተጠየቁባቸው ጉዳዮች ከወር በፊት ጀምሮ በሚዲያውና በተቃዋሚዎች ሲብላሉ የከረሙ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ከዓመታት በፊት ተነስተው ማስረጃ ባለመገኘቱ የተዘጉ ናቸው፡፡

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ለሦስት ሰዓታት በቆየው የፖሊሶች ጥያቄና በእሳቸው ምላሽ ዙሪያ ዝርዝር መረጃ ለሕዝብ ይፋ አልሆነም፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ለኔታንያሁ ያልተገባ ስጦታ አበርክተዋል የተባሉት የአሜሪካ ቢሊየነርና የዓለም ጂዊሽ ኮንግረስ ፕሬዚዳንት ሮናልድ ላውደር ይገኙበታል፡፡

ላውደር ለኔታንያሁ ያልተገባ ስጦታ ከመስጠት ባለፈም፣ ኔታንያሁ ባደረጉዋቸው ጉዞዎች ያልተገባ ገንዘብ ጥቅም ላይ እንዲውል አድርገዋል ተብለው በፖሊስ ተጠይቀዋል፡፡

ላውደር የኔታንያሁ የጥንት ወንጅ ሲሆኑ፣ እ.ኤ.አ. በ1990ዎች እስራኤል ከሶሪያ ጋር ለነበራት ድርድር ኔታንያሁ ግንባር ቀደም ተደራዳሪ ሆነው እንዲቀርቡ ያደረጉ ቱጃር ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...