Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርአቅጣጫው የማይገመተው የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ

አቅጣጫው የማይገመተው የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ

ቀን:

(የዓረቦቹና የኢትዮጵያ ሰሞነኛው ሽርጉድ)

በያየሰው ሽመልስ

የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ እንደዚህ ሰሞን ማዕበል በዝቶበትም የሚያውቅ አይመስልም፡፡ የኤርትራው ሰው ወደ ካይሮ አቅንተው ከጄኔራል መኮንኑ አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር መክረዋል፡፡ የኢሳያስና የአልሲሲ ውይይት ማዕከላዊ ትኩረት በመስኖና በዓሳ ሀብት ዘርፍ በጋራ ለመሥራት እንደሆነ በግብፅ መገናኛ ብዙኃን ሲዘገብ ቢቆይም፣ ሁለቱ መሪዎች የቀይ ባህር ኮማንድ ፖስት ለማቋቋም መስማማታቸው ግን የኋላ ኋላ ተጋልጧል፡፡ የወዲ አፎም መንግሥትም ለመጀመሪያ ጊዜ ይህንን ጉዳይ አምኖ ለሕዝብ ይፋ አድርጓል፡፡

- Advertisement -

የመንግሥቱ ቴሌቪዥን ‹‹በቀይ ባህር አካባቢ ያሉ የሽብር እንቅስቃሴዎችን ለመግታት የተቋቋመ ኮማንድ ፖስት ነው›› ሲል የመሪዎቹን ስምምነት አምኗል፡፡ ሕግዴፍ-ሻዕቢያ እንዲህ ያለን መረጃ በሕዝብ ፊት ሲያምን ምናልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከአሁን በፊት የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችም ሆነች ኢራን፣ የኤርትራን ወደቦች ያለገደብ ሲከራዩ ለኤርትራ ሕዝብ አልተነገረውም፡፡ ኤርትራ ከ400 በላይ ሠራዊት የመን አስገብታ እንደምታዋጋ ሕዝቡ አያውቅም፡፡ አሁን ግን ከግብፅ ጋር የገቡትን ውል ለአደባባይ አዋሉት፡፡

የእዚህን ምክንያት የሚገምቱ ሰዎች ሦስት መላምቶችን ያስቀምጣሉ፡፡ አንደኛው መላምት ኢትዮጵያ ለውስጥ ፖለቲካዊ ቀውሷ በተደጋጋሚ ግብፅን እየከሰሰች በመሆኑ፣ ኢሳያስ ከእነ አልሲሲ ጋር የአደባባይ ሽርክና በመፍጠር እነ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ማበሳጨት ፈልገዋል የሚለው ነው፡፡ እናም ኢሳያስ ራሳቸው የጋብዙኝ ጥሪ ለአልሲሲ ማስተላለፋቸውን አንዳንድ ምንጮች በሹክሹክታ ሲያወሩ ይደመጣል፡፡ ካይሮ ከገቡ በኋላም በውኃ ሚኒስትሩ አቀባበል ሲደረግላቸው ሲታይ፣ ነገርየው በፕሬዚዳንት አልሲሲ በኩል ትኩረት እንዳልተሰጠው ጠቋሚ ነው የሚለው መከራከሪያ ይኼኛውን መላምት የበለጠ አጽንኦት አሰጥቶታል፡፡

 በኤርትራ መንግሥት ሠፈር አዲስ አሉባልታ እየተራወጠ እንደሆነ ይደመጣል፡፡ ይኼኛው አሉባልታ ኢትዮጵያ የመኸር ምርቷን ሰብስባ ስትጨርስ ወረራ ልትፈጽምብን እየተዘጋጀች ነው የሚል ነው፡፡ እናም ግብፅን በዚህ ላይ ለማማከር/የሚወራው እውነት ቢሆን እገዛሽ እስከምን ድረስ ነው በማለት የተለመደ ጥያቄዋን ለማቅረብ፣ (በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ በዛ ያሉ ግብፅ ሠራሽ መሣሪያዎች በኢትዮጵያ መማረካቸውን ያስታውሷል)፣ ስለዚህም ለኤርትራ ሠራዊት ‹አይዞን ግብፅ ዛሬም ከእኛ ጋር ናት› የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነው የሚለውም ሁለተኛው መላምት ነው፡፡

ሦስተኛው ምክንያት በአስመራ በኩል ይፋ የተደገረው የቀይ ባህር ኮማንድ ፖስት መቋቋም ጉዳይ ነው፡፡ መቼም ይኼኛውን ጉዳይ ግብፅ አብዝታ እንደምትፈልገው ዕሙን ነው፡፡ ግብፅ በሶሪያ ፖለቲካ ላይ የበሽር አላሳድን መንግሥት ደግፋ ከሩሲያ ጎን መቆሟ የሱኒ እስልምና እናትና አባት ነኝ የምትለዋን ሳዑዲ ዓረቢያን ፀጉር አስነጭቷል (ሳዑዲ የበሽር አላሳድ መንግሥት ከሶሪያ መንበር እንዲፈራርስ እየሠራችና እየፀለየች መሆኑን ልብ ይሏል)፡፡ የነገሥታቱ አገር ለፈርኦኖቹ ታቀርብ የነበረውን ነዳጅ ዘይት ያቋረጠችውም ከዚህ ውዝግብ በኋላ ነው፡፡

እናም ካይሮና ሪያድ ሆድ ተባብሰዋል፡፡ በዚሁ ሰሞን ሳዑዲ ዓረቢያ ጂቡቲ የጦር ሠፈር ልትገነባ እንደሆነ ይፋ አድርጋለች፡፡ ስለዚህ በቀይ ባህር አካባቢ ያለውን የሳዑዲ ዓረቢያን እንቅስቃሴ በቅርበት ለመከታተል በመሻት አብዱልፈታህ አልሲሲ ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር የቀይ ባህር ኮማንድ ፖስት ለማቋቋም እንዲወስኑ አድርጓቸዋል የሚል ግምት አለ፡፡

የሆነ ሆኖ ኤርትራና ግብፅ በወቅታዊ ሽርክናቸው የመሠረቱት የቀይ ባህር ኮማንድ ፖስት አቅጣጫው አይታወቅም፡፡ ኮማንድ ፖስቱ በኢትዮጵያ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ምን ሊሆን እንደሚችል ግን መገመት አይከብድም፡፡

አልሲሲ፣ ሞሴቬኒና ኦማር ጊሌህ

የግብፁ አልሲሲ ወደ ኡጋንዳ ያቀኑት፣ የጂቡቲው ጊሌህም ወደ ካይሮ የተጓዙት በዚሁ ሰሞን ነበር፡፡ የአልሲሲና የሞሴቬኒ የካምፓላ ውይይት በዓባይ ወንዝም ላይ ያተኮረ እንደነበረ የኡጋንዳ መገናኛ ብዙኃን ጽፈዋል፡፡ በእርግጥ የሞሴቬኒ አገር በዓባይ ውኃ አጠቃቀም ፍትሐዊነት ላይ ጠንካራ አቋም እንዳላት ይታወቃል፡፡ የግብፆቹ ፍላጎትም ይህንን ደንዳና አቋም አቅም እንዲያጣ ማድረግ ነው፡፡ ባለባርኔጣው ፕሬዚዳንት ዮሪ ሞሴቬኒ በዚህ ረገድ አቋማቸው ይሸረሸራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው መሆናቸውም በቀላሉ እጅ እንዳይሰጡ ሊያደርጋቸው ይችላል፡፡ ምንም እንኳ በፖለቲካ ዘላቂ ጥቅም እንጂ ዘላቂ ወዳጅ ባይኖርም፡፡

የጂቡቲው ኦማር ጊሌህም ወደ ግብፅ አቅንተው ነበር፡፡ የትንሿ አገር ፕሬዚዳንት ወደ ካይሮ ሄደው የመከሩት ጉዳይ በይፋ ባይገለጽም፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ሊገናኝ እንደሚችል ግን ይገመታል፡፡ ዓረባዊቷ አገር በጂቡቲ እገነባዋለሁ ያለችውን የጦር ቀጣና በተመለከተ ሳይወያዩ እንዳልቀሩ ይታመናል፡፡ አሜሪካንም፣ ቻይናንም፣ ፈረንሣይንም… አስማምታ የጦር ሠፈር የሰጠችው ጂቡቲ፣ በግብፅ ፍላጎትና ግሳጼ ሳዑዲን ትከለክላታለች ተብሎ አይጠበቅም፡፡ የግብፅም ሆነ የሳዑዲ በዚህ ሠፈር ማንዣበብ ግን ከ90 በመቶ በላይ የወጪና ገቢ ንግዷን በምሥራቅ ላደረገችው ኢትዮጵያ እንቅልፍ የሚነሳ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡

ኳታር፣ሳዑዲ ዓረቢያና ኢትዮጵያ

የአውሮፓውያኑ አሮጌ ዓመት መገባደጃ ሰሞን፣ ዓረባውያኑ ከጦቢያ ጋር እፍፍ ያለ ፍቅር ውስጥ ነን ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ወደ ሪያድ ሄደው በተመለሱ ማግሥት የነገሥታቱ ልዑካን ቡድን አዲስ አበባ መጥተው ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ሳይወሰኑም እስከ ጉባ ድረስ ተጉዘው የህዳሴው ግድብ ግንባታን ጎብኝተዋል፡፡ ቡድኑ የተመራው አህመድ አል-ቃቲብ በተባሉት የንጉሣዊ መንበሩ የቅርብ ሰው ነበር፡፡

የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ ሃሚድ አልታኒ ያስከተሉት ቡድን ከአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መንግሥት ጋር አሥራ አንድ ስምምነቶችን ተፈራርሞ ተመልሷል፡፡ የኳታር አየር መንገድ የአስመራ በረራውን አቋርጦ ወደ አዲስ አበባ በሳምንት ሦስት ቀን ሊመጣ ወስኗል፡፡ የኳታሮቹ የቀናት ውሎ በሁለቱም ቤተ መንግሥቶች፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በመሰል አካባቢዎች ነበር፡፡

እንዲህ ያለውን ግንኙነት ወቅታዊ ምክንያት፣ ስትራጂካዊነትና ፖለቲካዊ ዳራ መፈተሽና ለምን ብሎ መጠየቅ ያሻል፡፡

ኳታር

ይህቺ አገር በ1990ው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ከአስመራ ጀርባ እንደነበረች ለአደባባይ የዋለ ሚስጥር ነው፡፡ በወቅቱ የተማረኩ የኤርትራ ወታደሮች ይዘዋቸው ከተገኙ ጦር መሣሪያዎች መካከል በዛ ያሉቱ የኳታርና የግብፅ እንደሆኑ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ ደም በተቃባችበት ጉዳይ ዓረባዊቷ አገር አቀጣጣይ ሆና መቆየቷ ታሪካዊ ጠላትነቷን ያጎላዋል፡፡ ይህም ሳያንስ እ.ኤ.አ በ2008 ኢትዮጵያ የደምና የገንዘብ ዋጋ በምትከፍልበት የሶማሊያ ጦርነት ላይ አልሸባብን ስታስታጥቅና ስንቅ ስትሰፍር ተገኝታለች ተባለ፡፡ የአቶ መለስ ዜናዊ መንግሥትም በዶሃ የነበረውን ኤምባሲውን ዘግቶ ወጣ፡፡ ወትሮም ቢሆን በአዲስ አበባ ኤምባሲ ያልነበራት ኳታር፣ በአስመራና በሞቃዲሾ በከፈተቻቸው ኤምባሲዎች የአፍሪካን ቀንድ በሽብር ልትሞላው እየታገለች መሆኑን ከአዲስ አበባ የሚወጡ መግለጫዎች ሲያትቱ ሰነበቱ፡፡

የሁለቱን አገሮች ግንኙነት የከፋ ጫፍ ያደረሰው ደግሞ በኳታር ልዑላን አይዞህባይነት፣ ዕውቅናና የገንዘብ ምንጭነት የተቋቋመው የአልጄዚራ ቴሌቪዥን የኢትዮጵያ መንግሥትን የሚያበሳጭ ድርጊት መፈጸሙ ነበር፡፡ ‹የኦጋዴንን ጉዳይ የዘገበበት መንገድ ውሸትና ግነት የበዛበት፣ ኦብነግንም የሚያሞካሽ ነው› ተብሎ ቴሌቪዥኑ ከአዲስ አበባ ተጠራርጎ አንዲወጣ ተደረገ፡፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህም ‹ኳታር  ምሥራቅ አፍሪካን ለማተራመስ እየሠራች ነው፣ አልሸባብንም እየደገፈች ነው› በሚለው ክሷ ኢትዮጵያ ገፋችበት፡፡ ኳታርም ከአዲስ አበባ ጋር ያላትን ውል ፈትታ ከአስመራ ጋር ያላትን ሽርክና አጠበቀች፡፡ ይልቁንም ኤርትራንና ጂቡቲን ለማስታረቅ ደፋ ቀና ማለት ቀጠለች፡፡

እ.ኤ.አ. በ2012 ወደ ሥልጣን የመጡት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ  ወገባቸውን አስረው ከከወኗቸው ተግባራት መካከል ይህንን የኳታርን ግንኙነት ማሻሻላቸው እንደሆነ ይጠቀስላቸዋል፡፡ በጥቅምት 2005 ዓ.ም ሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነታቸው ወደ ነበረበት መመለሱ ተነገረ፡፡ የኳታሩ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዳግም ተከፈተ፡፡ ዓረባዊቷ አገርም ለመጀመሪያ ጊዜ አምባሳደር ልካ በአዲስ አበባ ኤምባሲ ከፈተች፡፡

ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ነው እንግዲህ ሰሞኑን ወደ አዲስ አበባ የመጣው የኳታሩ መንግሥት ልዑክ በዛ ያሉ ስምምነቶችን የተፈራረመው፡፡ የአስመራ በረራውን ባልታወቀ ምክንያት ያቋረጠው የኳታር አየር መንገድም ወደ አዲስ አበባ በሳምንት የሦስት ቀን በረራ ለማድረግ የወሰነው ሼኩ የመሩት ቡድን ውደ ኢትዮጵያ ሳይመጣ ነው፡፡

እዚህ ላይ ይህንን ያህል ምላ ተገዝታ ኢትዮጵያን የሙጥኝ ያለችውን ኳታርን ማመን ይቻላል ወይ ብሎ መጠየቅ ያሻል፡፡ አንዳንድ ታዛቢዎች በቀንዱ ፖለቲካ ላይ የማይገመትና የማይታመን ርዕዮት ካላቸው ዓረባውያን መካከል ኳታርን ግንባር ቀደም አድርገው ይጠቅሷታል፡፡ ከኤርትራ ጋር ፍቅር ስለመጨረሷ ውስጥ ውስጡን ሲወራ ቢከርምም ምክንያቱ ግልጽ አልተደረገም፡፡ ተመልሳ ወደ አስመራ ፊቷን ላለማዞሯም ዋስትና የለም፡፡ ከጂቡቲ ጋር የኢሳያስን መንግሥት ለማስማማት ስትጥር ከርማ በመጨረሻ አውሮፕላኗም ወደዚያ እንዳይበር ከለከለች፡፡ ይልቁንም አየር መንገዱ የጂቡቲውን በረራውን መቀጠሉ፣ ሁለቱን አገሮች ስታደራድር የኖረችው አገር በይፋ ወገንተኛ መሆኗን የሚያሳይ ነው ሲሉ የአስመራ ልሂቃን ሲናገሩ ተደመጡ፡፡

እ.ኤ.አ ከ2012 ወዲህ (የሁለቱ አገሮች ወዳጅነት ዳግም ካንሰራራ በኋላ) ኤርትራንና ኢትዮጵያን ለማስታረቅ እየደከሙ ነው ተብሎ በዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ሲወራላቸው ከነበሩ ጥቂት አገሮች አንዷ ኳታር ነበረች፡፡ አሁን ግን ያንን ተልዕኮዋን የት እንዳደረሰችው ሳይታወቅ የኢሳያስን አስተዳደር ችላ ብላ የኃይለ ማርያም ደሳለኝን መንግሥት አቀረበች፡፡ በውክልና ጦርነት (Proxy War) ጦር የሰበቀችባትን ወዳጅ አድርጋ ኢትዮጵያን የተጠጋችው ኳታር የነገ አቅጣጫዋ ወዴት ይሆን? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የማይታመነውንና ተለዋዋጩን የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ባህል በጥልቀት ማወቅ ይጠይቃል፡፡

ከላይ እንደተብራራው ኳታርና ኤርትራ ፍቅራቸውን ካቆሙበት ላለመቀጠላቸው ዋስትና የለም፡፡ ዛሬም ኢትዮጵያ ዋጋ እየከፈለችበት ባለው የሶማሊያ ፖለቲካ ኳታር የራሷን ፍላጎት የሚያስፈጽሙ የጎሳ ቡድኖችን በማደራጀት ላይ መሆኗ ይነገራል፡፡ ሰሞኑን በተጠናቀቀው የአገሪቱ እንደራሴዎች ምርጫም እጇን በረጅሙ እንዳስገባች ሲወራ ከርሟል፡፡ ይህ ለደሃዋ ኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ ፕሮፌሰር አሌክስ ዲ ዎል ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ በውክልና ጦርነት ፍልሚያ በፔትሮሊየም ዶላር ጡንቻቸውን ያፈረጠሙ አገሮችን ኢትዮጵያ ልትቋቋም የምትችልበት አቅም የላትም፡፡ እሷ ወታደር ስትልክ እነሱ ዶላር እያሰረጉ የጎረቤት አገርን ሰላም ከድጥ ወደማጡ ላለማድረጋቸው ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡ ኳታር የዚህ ጉዳይ ዋነኛ ተዋናይት ነች፡፡ እናም በሞቃዲሾ ጉዳይ አዲስ አበባና ዶሃ እንዴት እንደሚደማመጡ አይታወቅም፡፡ እስካሁንም ፍርጥርጥ አድርገው ያወጡት ማብራሪያ የለም፡፡

ሪያድና አዲስ አበባ

ሳዑዲ ዓረቢያ ከኢትዮጵያ ጋር የተሻለ ዝምድና አለኝ ስትል የተደመጠችውም በዚሁ ሰሞን ነው፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም እ.ኤ.አ. 2016 መገባደጃ የመጨረሻ ወራት ወደ ሪያድ ሄደው በተመለሱ ጊዜ፣ የሳዑዲ ሰዎች ዱካቸውን ተከትለው ለይፋዊ ጉብኝት ወደ አዲስ አበባ መጡ፡፡ የሳዑዲ ልዑክ ህዳሴ ግድብ ድረስ ሄዶ ጉብኝት ማድረጉ ግብፅን በእጅጉ አስከፍቷል፡፡ አንዳንድ የካይሮ መገናኛ ብዙኃን ‹ሳዑዲ በግብፅ ላይ ጦርነት እንደማወጅ ያለ ተግባር ፈጸመች› ሲሉ የልዑኩን ጉብኝት አውግዘዋል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ‹ሳዑዲ ለህዳሴው ግድብ የገንዘብ ድጋፍ አደረገች› ሲሉ ጽፈዋል፡፡ የነገሥታቱን አገር ወክለው ልዑካኑን እየመሩ የመጡት ባለሥልጣን ደግሞ ይኼኛውን የግብፆችን (ስለገንዘብ ድጋፍ የተወራችውን) “ዜና” እውነት የሚያስመስሉ ናቸው፡፡

ሰውዬው ሳዑዲ ፈንድ ፎር ዴቨሎፕመንት (SFD) የተባለን ድርጅት በቦርድ ሊቀመንበርነት የሚመሩ ናቸው፡፡ ይህ ተቋም ደግሞ ሳዑዲ ዓረቢያ በውጭ አገሮች ለምታካሂደው ዕርዳታና ድጋፍ ገንዘብ የሚለቅ ነው፡፡ ለዚያም ነው ግብፆቹ ‹ኢትዮጵያ ለምትገነባው ግድብ ከሪያድ ድጋፍ አገኘች› ሲሉ መክረማቸው፡፡ ይህንን ወሬ ግን ሳዑዲዎቹ ውሸት ነው ሲሉ በይፋ ተናግረዋል፡፡

የሆነ ሆኖ ‹ሳዑዲ ለምን በዚህ ሰሞን ህዳሴ ግድብ ድረስ የዘለቀ ሽርጉድ አደረገች? ለምንስ ግብፆቹ ተበሳጩ? ስለምንስ ከወትሮው በተለየ ሁለቱ አገሮች ወዳጅነታቸው የመገናኛ ብዙኃን አጀንዳ ሆነ?› ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ እነሱ ከመምጣታቸው በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሳዑዲ ያመሩት ምናልባትም የባህረ ሰላጤው አገሮች በኤርትራ ከሚያደርጉት ወታደራዊ መስፋፋት ጋር በተገናኘ ውይይት ለማድረግ እንደሆነ ተገምቶ ነበር፡፡ ምንም እንኳ እዚህ ግባ የሚባል ማብራሪያ ባይሰጥበትም፡፡

በእርግጥ ምጣኔ ሀብታዊና ኢንቨስትመንታዊ የጋርዮሽ ግንኙነቶችን ለማጠናከር የተደረገ ጉዞ መሆኑን የመንግሥቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ እውነት ነው ይኼኛውም ጉዳይ በውይይቱ ወቅት መነሳቱ የማይቀር ነው፡፡ ምክንያቱም ሳዑዲ በኢትዮጵያ በዛ ያለ መዋዕለ ሀብት ካላቸው አገሮች አንዷ ነችና፡፡ ይሁንና የሰላምና የፀጥታ ጉዳይ፣ የየመን ጦርነትና የሳዑዲ መራሹ ጣልቃ ገብነት፣ የኤርትራና የባሕረ ሰላጤው አገሮች ወቅታዊ ሽርክና፣ ወዘተ የጠቅላይ ሚኒስትሩና የንጉሡ መወያያ እንደሚሆን አስቀድሞ የተገመተ ጉዳይ ነው፡፡

ለማንኛውም ከአቶ ኃይለ ማርያም የሳዑዲ ጉብኝት በኋላ የንጉሡ መልዕክተኞች አዲስ አበባንና ህዳሴ ግድብን መጎብኘታቸው የግብፅን ጨጓራ ለመላጥ መሆኑ ዕእሙን ነው፡፡ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ከላይ የተገለጸው የካይሮና የሪያድ ፍቅር መጨረስ ነው፡፡ ከዚህ ሃልዮት የሚነሳው ጥያቄ ‹ይህ የሳዑዲ ጠብ እርግፍ ማለት ስትራቴጂካዊ ነው ወይስ ሥልታዊ?› የሚለው ነው፡፡ በዚህ ጸሐፊ እምነትና በአንዳንድ የቀንዱ ፖለቲካ ታዛቢዎች አስተያየት ግን የሳኢዱ ግንኙነት ሥልታዊ ነው፡፡ ዘላቂ ጥቅምን ያላሰላ፣ ግልብ ምክንያትን ያዘለና መነሻውን ወቅታዊ ቁርሾ ያደረገ ነው፡፡

የዛሬ ዓመት አካባቢ በግብፅ መገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን ካገኙ ዜናዎች መካከል ኢትዮጵያንና ግብፅን ለማደራደር ሳዑዲ እየጣረች ነው የሚለው ዋነኛው ነበር፡፡ በዚያን ሰሞን ካይሮና ሪያድ እብስ ያለ ፍቅር ውስጥ ሆነው የደሴት ስጦታ እስከ መለዋወጥ ደርሰው ነበር፡፡ ሆኖም እንደ ቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ዓለምን በሁለት ጎራ የከፈለው የሶሪያ ጦርነት ዱብ እዳ ሆነና ሳዑዲንና ግብፅን ሆድ አባባሳቸው፡፡

ለዚያም ነው ሳዑዲ፣ ግብፅ ከቆመችበት የፖለቲካ ትወራና የዲፕሎማሲ ጥግ በተቃራኒ ሆና መታየት የጀመረችው፡፡ ህዳሴ ግድብ ድረስ በመምጣት ጉብኝት ያደረገችውም ግብፅን በውጭ ጉዳይ ፖለቲካዋ ላይ  ወደ ራሷ ለማምጣት አስገዳጅ መላ በመሻት ነው፡፡ የሳዑዲ አለሁ ባይነት ዘላቂ ጥቅምን ያነገበና ስትራቴጂካዊ ሳይሆን ቅርብ አዳሪነት የተጠናወተውና ሥልታዊ ነው መባሉም ለዚህ ነው፡፡

እናም ሳዑዲም ሆነች ኳታር ከኢትዮጵያ ጋር እየፈጠሩ ያሉትን ወቅታዊና ሥልታዊ አጋርነት፣ ወደ ስትራቴጂካዊነትና ዘላቂ ወዳጅነት በመቀየር በኩል መንግሥት ትልቅ የቤት ሥራ ከፊቱ አለ፡፡ የአቶ ኃይለ ማርያም አስተዳደር አጋጣሚውን ተጠቅሞ ዓረቦቹን ከልማትና ኢንቨስትመንት ባሻገር፣ የሰላምና የፀጥታ ወዳጅ ሊያደርጋቸው ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ጋዜጠኛ ሲሆኑ፣ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...