Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርሕዝቡ እንዳያዝን መሬቱ እንዳይባክን

ሕዝቡ እንዳያዝን መሬቱ እንዳይባክን

ቀን:

በሳሙኤል ረጋሳ

ጊዜ እየጨመረ በሄደ ቁጥር የሕዝብ አቋም እሱ ራሱ እንደሚፈጽመው ጉዳይ ወይም በሌሎች እንደሚፈፀምለት ጥያቄ መጠን የእርካታ ወይም የመከፋት ስሜት ግልጽ እየሆነ ይሄዳል፡፡ በአብዛኛው ሕዝባዊ ፍላጎት የሚረካው መንግሥት ያሉትን ችግሮች አውቆ መፍትሔያቸውን በቃል ሳይሆን በተግባር ሲያሳይ ነው፡፡

ከሰሞኑ ሲጠበቅ የነበረው የአዲስ አበባ ዙሪያ አርሶ አደሮች የመፈናቀያ ካሳ ጉዳይ ፍንጭ እየታየ ነው፡፡ በመሠረቱ ለአርሶ አደሮች የሚከፈለው ገንዘብ ካሳ ነው? ወይስ መንግሥት ብቸኛ መተዳደሪያ ይዞታቸውን በተለያየ ምክንያት የወሰደባቸው አርሶ አደሮች ሌላ የሚያኖር ገቢም ሆነ ጥሪት ስለሌላቸው ሥራቸውን ወደ ሌላ መስክ ቀይረው ለዘለቄታ የሚያኖር የሕይወት ዋስትና ነው? ይኼ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊና የሥነ አዕምሮ ጫና የሚያሳድር የይዞታ ማስለቀቅ ሥራ ውጤቱ የሚለካው በሕዝቦች ውስጥ በሚያስከትለው የፖለቲካ ጣጣና አመፅ መሆኑን በተጨባጭ አይተናል፡፡

- Advertisement -

 ቀደም ሲል በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የተነሳውና ወደ ሌሎችም ተዛምቶ የበርካቶችን ሕይወትና ንብረት ሊያጠፋ የቻለው የሁካት መነሻ ነው፡፡ ይኼ ጥያቄ መነሳት እንደሚችል ተገምቶ በሕገ መንግሥቱ ቅድሚያ መፍትሔ ተቀምጦለታል፡፡ ሕገ መንግሥቱ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ስለምትገኝ ለመስፋፋትም ሆነ ለሌሎች አገልግሎቶች በክልሉ ላይ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጫና ስለምትፈጥር፣ ክልሉ ልዩ ጥቅም እንዲያገኝ ደንግጓል፡፡ ይኼ ድንጋጌ የኢሕአዴግ መንግሥትን ያህል ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡ ነገር ግን የመጀመሪያዎቹ የፈጠሩትን ሕገ መንግሥት የኋለኞቹ ሊያሳምሩት ባለመቻላቸው ጉዳዩ አገራዊ የሆነ ፖለቲካዊ ቀውስ ፈጥሯል፡፡ መንግሥት ገቢ የሚያስገኙለትን የሊዝ፣ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት የመሳሰሉት ሕጎች ወጥተው ተደጋጋሚ ማሻሻያ ጭምር ተደርጎላቸዋል፡፡ ይኼ የአዲስ አበባ አካባቢ አርሶ አደርን ያላግባብ መፈናቀልን ያስቀራል ወይም መፍትሔ ያበጅለታል የተባለው ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ግን የመንግሥትን በር በኃይል እስኪያንኳኳ ድረስ ሰሚ አላገኘም፡፡ ይኼ ጉዳይ በቂ ጥናትና በሕዝብ ጥምር የተደገፈ የመፍትሔ ሐሳብ ያስፈልገዋል፡፡ በተወሰኑ ባለሥልጣናት ወይም ካድሬዎች የሚቀርብ መፍትሔ በምንም መልኩ የተሟላ ሊሆን አይችልም፡፡ በአሁኑ ወቅት የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት መዋቅሮችን በአዲስ አደረጃጀት በከፍተኛ ምሁራን አዋቅረዋል፡፡ ይኼ ጥሩ ሐሳብ ነው፡፡ ጥሩ ሐሳብ የሚሆነው ካልተማረ የተማረ ይሻላል ከሚለው ተለምዶአዊ አባባል ነው፡፡ ነገር ግን የማስተርስና የዶክትሬት ዲግሪ በያዙ ሰዎች መዋቅሮችን በመሙላት ብቻ ተዓምር ይኖራል ማለት የበዛ የዋህነት ነው፡፡

አዲሱ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሥራውን መጀመር ያለበት ሕዝቡን ያስመረሩና መፍትሔ የሚያስፈልጋቸውን ችግሮች ለይቶ አውጥቶ ተግባራዊ የመፍትሔ ሐሳብ በማምጣት ነው፡፡ ከእነዚህ ችግሮች ውስጥ የመጀመሪያው መሆን ያለበትና አስፈላጊ ያልሆነ መስዋዕትነት የተከፈለበት የፊንፊኔ ዙሪያ ጉዳይ ነው፡፡ ታዲያ ምነው እስካሁን ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም ሆነ፡፡ ቄሱ ካልተናገሩ የመጽሐፉ ዝምታ እኮ ዘለዓለማዊ ነው፡፡ መጽሐፉ ለብቻው አይናገርም፡፡

ይኼንን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ የያዘ አጀንዳ ወደ ጎን በመተውና ባለመፈጸም የክልሉም ሆነ የፌዴራል የሕግ አውጪ አካላት በቅድሚያ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ አሁን ከሚሰማው ፍንጭ የፊንፊኔ ዙሪያ ተፈናቃይ ገበሬዎች በአንድ ሔክታር እስከ አምስት መቶ ሺሕ ብር ድረስ ተከፍሎ ከይዞታቸው እንደሚለቁ እየተነገረ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ሰፊ ማሳ አለው የሚባል ገበሬ ያለው ይዞታ ሁለት ሔክታር ቢሆን ነው፡፡ ይኼ ገበሬ አንድ ሚሊዮን ብር ድረስ ያገኛል፡፡ ሚሊየነር ሆነ እንበል፡፡ አንድ ሚሊዮን ብር በአሁኑ የአገራችን የኑሮ ሁኔታ አንድ ሰፊ ቤተሰብ ለማስተዳደር የሚታሰብ አይደለም፡፡ ቦታ ፈልጎ አንድ አነስተኛ የቤተሰብ መኖሪያ ቤት ለመሥራት ብቻ አንድ ሚሊዮን በቂ የሚባል ገንዘብ አይደለም፡፡ መንግሥት ለእነዚህ ሰዎች የሚከፍለው ክፍያ ሊከብደው ይችላል፡፡ መሬቱን ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ገበሬው የሚበቃውን መቋቋሚያ ለማስከፈል ግን በጣም ቀላል ነው፡፡

እስካሁን ድረስ በማስፋፊያ አካባቢ የተሠሩ የግል ቤቶችም ሆኑ ኮንዶሚኒየሞች የሚገኙት አብዛኛዎቹ በመጀመሪያዎቹ መሥራቾች እጅ ሳይሆን፣ በተደጋጋሚ ተሸጠውና ተለውጠው፣ በርካታ ነጋዴዎችንና ደላሎችን ባለብዙ አሥር ሚሊዮን ብር ባለቤት አድርገው፣ ባለይዞታ የነበሩትን አርሶ አደሮችና ቤተሰቦችን አደህይተውና ከአካባቢው አባረው ነው፡፡

አንድ ከአካባቢው የተፈናቀሉ ዕድሜዬ 80 ዓመት ነው ያሉት አባት ምሳሌያዊ አነጋገር እንሆ፡፡ ‹‹ፆም በሁለት ይከፈላል›› አሉ አዛውንቱ፡፡ ‹‹ሁለት ሰዎች በተለያየ ምክንያት ፆማቸውን ይውላሉ፣ ምግብ ሳይበሉ፡፡ አንደኛው ሀብታም አንደኛው ደሃ ናቸው፡፡ ሀብታሙ ሰው ያልበላው ሃይማኖቱ የሚያዘውን የፅድቅ ፆም ሊያደርስ ነው፡፡ ደሃው ያልበላው የሚላስ የሚቀመስ ከቤቱ አጥቶ ነው፡፡ ሁለቱም ፆም ውለዋል፡፡ ረሃቡ እኩል ነው ስሜቱ ይለያያል፡፡ መሠረቱም ለየቅል ነው፡፡ ለነፍሱ ሲል በፈቃዱ የፆመው የገነትን መግቢያ በር ለመክፈት እየሞከረ በመሆኑ፣ የረሃብ ስሜቱ የሰማይ ቤት ተስፋውን ያለመልመዋል፡፡ ወደ ቤቱ ሲመለስ ፆም በመዋሉ የሚዘጋጅለት ምርጥ ምግብ፣ በማኅበራዊ ኑሮው ፆሙ የሚያስገኝለት ትልቅ ሥፍራና ፍላጎቱን በማሸነፉ የሚሰማው ውስጣዊ ደስታ በሰማይም በምድርም የሚያስገኝለት ትርፍ ካለመብላቱ ጋር ሲያስበው ነፍሱ በሀሴት ትሞላለች፡፡ ደሃው ሰው ግን ፆሙን የዋለው በማጣቱ እንጂ በፍላጎቱ ባለመሆኑ የረሃብ ስሜቱ ትልቅ ነው፡፡ ገብቶም የሚቀስመው ነገር ባለመኖሩ ውስጡ ይሟሟታል፡፡ የዛሬው ፆም መዋልን ነገ የሚከተለው በዛሬው ረሃብ ላይ የሚጨመር ሌላ ረሃብ መሆኑን ሲያስበው ሰማይ ተደፍቶበት ቢያድር አይከፋውም፡፡ ፋሲካ በማይከተለው የሁልጊዜ ረሃቡ ዕድሉን እንዲያማርርና ለዚህ ያበቃውን ምክንያት እግዚአብሔርና ሰውን እንዲጠይቅ ይገደዳል፤›› አሉ አዛውንቱ፡፡ እንግዲህ ሁለቱም በተግባር የደጸሙት አንድ ዓይነት ረሃብ መራብ ነው፡፡ መሠረቱና ውጤቱ በግለሰቦቹ ላይ የሚያስከትሉትን ውጤት ባለ ህሊና ሁሉ ሊገምተው ይችላል፡፡

የአዛውንቱ የምሳሌያቸው መነሻ የሆነው ከመሬቱ ላይ የተነሳውን ገበሬና የእሱን ይዞታ ወስዶ በሚሊዮኖች ሸጦ የተነሳውን ከተሜ ከግምት የሚያስገባ ነው፡፡ ሁለቱም ባለ ይዞታዎች ነበሩ፡፡ ሁለቱም ይዞታቸውን ለቀው ከአካባቢው ሄደዋል፡፡ አንደኛው የለቀቀው እንደ ሀብታሙ ፆመኛ በተስፋና በደስታ ነው፡፡ ገበሬው የለቀቀው ደግሞ እንደ ፆመኛው ሀብታም ሳይሆን፣ እንደ ፆም አዳሪው ደሃ በደነዘዘ ስሜት፣ በሐዘንና በተስፋ መቁረጥ ነው፡፡

ታዲያ ይህን ችግር ይፈታል ተብሎ የተቀመጠው የሕገ መንግሥት ድንጋጌ ያስገኛል የተባለው ልዩ ጥቅም ምንድነው? ለማንና ለመቼስ ነው የተቀመጠው? ይኼ ችግር የሚፈታው ለአካባቢው መንገድ ስለተሠራ፣ ትምህርት ቤት ስለተከፈተ፣ የባቡር ሐዲድ ስለተዘረጋ፣ ወዘተ አይደለም፡፡ ይኼ ጠቀሜታው ለአፈናቃዩ እንጂ ለተፈናቃዩ አይደለም፡፡ ተፈናቃዩማ አካባቢውን ለቆ ይሄዳል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሲተረጎም ከፆመኛው ሀብታም ወስዶ ለፆም አዳሪው ደሃ የድርሻውን የሚከፍልበት አሠራር ሊያበጅ ይገባዋል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ እነዚህ አርሶ አደሮች ወደየትም ሳይሰደዱና የመንግሥትን ወጪ ሳይጠይቁ ባሉበት ቦታ ወደ ከተሜነት ተለውጠው በተስፋና በደስታ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ መንግሥት ከገበሬዎቹ የሚረከበውን ማሳ በጨረታ የሚሸጠው እያንዳንዱን ካሬ ሜትር ከአሥር ሺሕ ብር በላይ ነው፡፡ ታዲያ መንግሥት በእያንዳንዱ ካሬ ሜትር አንድ ሺሕ ብር ለገበሬው ካሳ (የሕይወት ዋስትና) ጭማሪ ቢጠይቅና በትክክል ገበሬው የሚጠቀምበትን አቅጣጫ ቢያስቀምጥ፣ ባለሀብቱም ሆነ ገበሬው ሁለት ሔክታር መሬት ሲለቅ የሚገኘውን ገንዘብ ሲያሰላው ራሱን ሊያመው ይችላል፡፡ የደላላውና የመሬት ነጋዴው ገቢ ግን በመንግሥት በኩል የማይተላለፍ ስለሆነ አስልቶትም አያውቅም፡፡ በሁለት ሔክታር መሬት ላይ ያሉ ንብረቶችም ሆኑ ባዶው መሬት በእነዚህ ሕገወጦች በኩል ሲተላለፉ ለገበሬው ይከፈል ከተባለው አያንስም፡፡

ለገበሬው በሔክታር አምስት መቶ ሺሕ ብር ሲከፈል ገንዘቡ ትንሽ አይደለም፡፡ ነገር ግን መንግሥት ቆሜለታለሁ የሚለውን ገበሬ ከመተዳደሪያውና ከቄዬው ሲያስነሳው ኑሮው ሊሻሻል ወደሚችልበት ደረጃ ወይም እንዲቆይ አስፈላጊውን ሁሉ የማድረግ ግዴታ  አለበት፡፡ ሁለት ሔክታር ወይም ከዚያ በታች ይዞታ ያለው ገበሬ በካሬ ሜትር ተሰልቶ የሚደርሰውን ገንዘብ መንግሥት ለልማት በሚውል መንገድ እንዲጠቀሙበት ሊረዳቸውና ሊያስተምራቸው ይገባል፡፡ ገበሬዎች ተደራጅተውና መሬት ተጫርተው በሊዝ ገዝተው ኮንዶሚኒየም ሠርተው እንዲኖሩበትና እንዲያከራዩት ቢደረግ፣ በኢንዱስትሪው መንደር ግንባታ ውስጥ ገንዘባቸውን ኢንቨስት በማድረግ ለራሳቸውና ለልጆቻቸው ዘላቂ ሥራ ቢያመቻቹ፣ ቦንድና አክስዮን በመግዛት ቢሳተፉና ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎች ቢመቻቹላቸው ያገኙት ገንዘብ ተመልሶ ለልማት ዋለ ማለት ነው፡፡

እነዚህና መሰል አሠራሮች መንግሥት ባቀደው የመዋቅራዊ ለውጥና የአዲስ አበባ ዙሪያን ወደ ከተማ ሕይወት በመለወጥ ሒደቱ ላይ ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል፡፡ ፆመኛውና ፆም አዳሪው እኩል ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ የፍትሕ፣ የእኩልነትና የመብት ጉዳዮችም በፅኑ መሠረት ላይ ይቆማሉ፡፡ የጥልቁ ተሃድሶም አንድ ዋነኛ መገለጫ ሊሆን ይችላል፡፡ ያለነገር በጥልቀት የሚለው ቃል አልተጨመረም፡፡ ነገር ግን አሁን በሚታየው ፍንጭ መሠረት በሔክታር ይከፈላል ተብሎ የታሰበው ገንዘብ አርሶ አደሩን በቁጥር በመሸንገል ዘለቄታ በሌለው ተስፋ ገብቶ ገንዘቡን የሚያባክነው እንጂ፣ መሠረታዊ ለውጥ አውጥቶ ሕይወቱን ለመምራት የሚበቃ ገንዘብ አይደለም፡፡ ይኼ ገንዘብ ለልማት የሚውል አይሆንም ማለት ነው፡፡

መንግሥት አንድን ባለመብት ያለፍላጎቱ ከይዞታው ሲያስለቅቅ በካሳ መልክ ጉርሻ ሰጥቶ መሆን የለበትም፡፡ በመሠረቱ አንድ ሰው ይዞታውን በግዴታ መልቀቅ ያለበት ለመንግሥታዊ የአገልግሎት ተቋማትና መሠረተ ልማት ብቻ ሲሆን ነው ሕጉ የሚደነግገው፡፡ ለመንግሥትና ለግል ኢንቨስተሮች ወይም ለተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚለቀቅ ቦታ ከላይ በተጠቀሰው መሠረት የገበሬውን ተስፋ ብሩህ በማድረግ በፈቃደኝነት መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ሁሉ አፈጻጸም የሚረዳው በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ ሆኖ ሳለ በጎን በተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በሚወጣ ሕግ መሆን የለበትም፡፡ የከተማ ነዋሪ ተከራዮችም ሆኑ ባለይዞታዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ሲለቁ እኮ የተሻለ ቤት ወይም ቦታና የቤት መሥሪያ ገንዘብ እየተከፈላቸው ነው፡፡ ታዲያ የኢሕአዴግና የአርሶ አደሩ ወዳጅነት ከመቼው ቀዝቅዞ ነው አቋም የተቀየረው?

ሌሎች ከፊንፊኔ ዙሪያ መሬት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚመጡ የዘለቄታ ችግሮችም አብረው መታሰብ አለባቸው፡፡ የፊንፊኔ ዙሪያ አርሶ አደሮች የያዙት መሬት በአገሪቱ ውስጥ እጅግ ለም ከሚባሉት የጤፍና የስንዴ አምራች አካባቢዎች ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡ ይኼ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች እጅግ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ለአዲስ አበባ ካላቸው ቅርበት አንፃር ለከተማይቱ ነዋሪዎች በቀላሉ መኪና ባይገባ እንኳ በእንስሳት ተጭኖ በፍጥነት እህል ያቀርባሉ፡፡ በተለይም የአዲስ አበባ ሕዝብ ዋና ምግብ ጤፍ ደግሞ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል በብዛትም ሆነ በጥራት የሚመረት አይደለም፡፡ የአደአና የበቾ ጤፍን የመሳሰሉ በብዛታቸውና በጥራታቸው ወደር የማይገኝላቸው ዝርያዎች ምንጫቸው የአዲስ አበባ አካባቢ መሬትና ገበሬ ነው፡፡ የእነዚህ አካባቢዎች የጤፍ ምርት በመሬት ጥበት ምክንያት ለወደፊት በእጅጉ እንደሚቀንስ ይታመናል፡፡ እነዚህ ማሳዎች በልማትና በኢንቨስትመንት ስም አምራችነታቸው ለዘለቄታ እየቀረ ነው፡፡

ለደረቅ ወደብ ግንባታ፣ ለሰፋፊ የአበባ እርሻዎች፣ ለሕንፃዎች፣ ለመንገዶች፣ ለካምፖች፣ ለድርጅቶች፣ ወዘተ ግንባታዎች የሚሰጡ የእርሻ መሬቶች ለዘለቄታው ወደ ማሳነት ሊመለሱ አይችሉም፡፡ የሕዝብ ቁጥር በየዓመቱ በሚሊዮን የሚጨምር ሆኖ ሳለ በብዛትና በጥራት የሚያመርቱ ብርቅዬ የማይተኩ ማሳዎቻችን ከአገልግሎት ውጪ ማድረግ ትኩረት የሚያሻው የወቅቱ አጀንዳ መሆን አለበት፡፡ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ መሬቶች በጥናት ላይ ተመሥርቶ ከአዲስ አበባ ርቀውም ቢሆን ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ የኢንዱስትሪ ምርቶች ፍለጋ የቀለብ ምርቶቻችንን ማሳጣት የለበትም፡፡ ሁለቱም በየፈርጁ ይስተናገዱ፡፡ ሰፋፊ ጭንጫ መሬቶች እያሉ ምርጥ ማሳዎች መምከን የለባቸውም፡፡ ሁኔታዎች በዚህ ከቀጠሉ የአደአና የበቾ ምርጥ የጤፍና የስንዴ ዝርያዎች ሲጠፉ የማየት ዕድል የሚገጥማቸው በርካታ የዚህ ዘመን ሰዎች ይኖራሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዙሪያ ሕዝቡንም መሬቱንም በአግባብ እንጠቀምበት፡፡ ሕዝቡም መሬቱም እየባከነ ነው፡፡ ለወደፊት አዳዲስ የማያፈናቅሉ ሥራዎች የሚካሄዱ ከሆነ፣ መንግሥት የሚወስነው ውሳኔና ደንብ መነሻው ከሕዝብ የሚመነጭ መፍትሔን የሚያካትት መሆን አለበት፡፡ ብዙው ሕዝብ ለጥቂቶች ሥልጣን ሰጥቷል፡፡ ሥልጣን ማለት ማዘዝ ለአንዱ፣ መታዘዝ ለብዙው ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ጥቂቶች የተስፋ መንገድ መቀየስ አለባቸው፡፡ ያኔ ሁሉም በፍቅርና በመቻቻል ይኖራል፡፡ ያኔ መንግሥትና ሕዝብ ሊበጠስ በማይችል ገመድ ይተሳሰራሉ፡፡

መቼም በአገራችን አሁን አሁን መንግሥትን መተቸት ተገቢ የመሆኑን ያህል ማመስገን አልተለመደም፡፡ አንድ ምሥጋና እነሆ፡፡ ከላይ የተዘረዘረው ሐሳብ ወደፊት ይዘታቸውን ለሚለቁ የሚያገለግል ነው፡፡ የዚህ ሐሳብ ምክንያት በቀድሞ ተፈናቃዮች ላይ የደረሰውን ችግር መነሻ በማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ መንግሥት ያለፈው ስህተቱ ስለፀፀተው ቀደም ሲል ባክነው የቀሩ የቀድሞ ተፈናቃዮችን በማፈላለግ ለዘለቄታው ሊያቋቁማቸው የጀመረው ጥረት የሚያስመሰግን ነው፡፡ መሳሳት አንድ ነገር ሆኖ መታረም ደግሞ የትልቅነት ማሳያ ነው፡፡ ለወደፊት ሕዝቡ እንዳያዝን መሬቱ እንዳይባክን የከፍተኛ ምሁራን ስብስብ የሆኑት የክልልና የፌዴራል መንግሥት ካቤኔዎች የሚሉትን እንጠብቅ፡፡ ሁሉንም የሚያቻችል መሪ ሳይጠፋ ቂም የሚያያይዙ ፆመኛና ፆም አዳሪ አንፍጠር፡፡

ከአዘጋጁ፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...