Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየረዥም ርቀት ሩጫ ጀግናው ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ሥርዓተ ቀብር በወታደራዊ ሥርዓት ተፈፀመ

የረዥም ርቀት ሩጫ ጀግናው ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ሥርዓተ ቀብር በወታደራዊ ሥርዓት ተፈፀመ

ቀን:

  • ለክብሩ ዘጠኝ ጊዜ ተተኮሰ

በኦሊምፒክ፣ በሉላዊና በአህጉራዊ የአትሌቲክስ መድረኮች በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ ተደራራቢ ድሎቹ ነግሦ የነበረው ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ሥርዓተ ቀብር፣ እሑድ ታኅሣሥ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ፡፡

በ5,000 ሜትርና በ10,000 ሜትር ሩጫ ከአሯሯጥ ስልቱና ከአጨራረስ ስኬቱ በመነሣት ‹‹ይፍተር ዘሺፍተር››- ማርሽ ቀያሪው ይፍጠር፣‹‹ይፍተር ዘማስተር››- የሩጫው ጌታ ይፍጠር- የሚሉ ቅፅል ስሞችን በዓለም ዙርያ የተጎናፀፈው የአየር ኃይል ሻምበል ምሩፅ፣ እሑድ በስምንት ሰዓት በወታደራዊ መኰንን ሥርዓት በክብር ዘብና በማርሽ ባንድ ሐዘናዊ ቃና ታጅቦ ከመፈጸሙም ባሻገር፣ ግብዓተ መሬቱ ሲፈጸም ለክብሩ ዘጠኝ ጊዜ የተኩስ ድምፅ ተሰምቷል፡፡

በሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ ከአገር ቤትና ከካናዳ የመጡ ቤተሰቦችና ዘመዶች፣ ወዳጆችና የአሁንና የቀድሞ ሚኒስትሮች፣ የአሁንና የቀድሞ ጄኔራል መኰንኖች፣ ዲፕሎማቶች፣ ልዑላን ቤተሰቦችና አድናቂዎች በተገኙበት ሥርዓተ ቀብር ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የምሩፅን ሀገራዊ ውለታ ያስታወሰ የሐዘን መግለጫ መልእክት በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ርስቱ ይርዳው አማካይነት ተነቧል፡፡ ብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴም ባደረገው ንግግር ምሩፅ የብዙዎች አርአያ እንደነበረ አስታውሷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በካናዳ ቶሮንቶ ሐሙስ ታኅሣሥ 13 ቀን ያረፈው ሻምበል ምሩፅ አስክሬን አዲስ አበባ የደረሰው እሑድ ማለዳ ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ከከፍተኛ ሹማምንት፣ ከስፖርት ማኅበረሰቡና ከቤተሰቡ ጋር በመሆን ተቀብለውታል፡፡ አስክሬኑ ከአውሮፕላን እንደወረደ የክብር ዘብ አጅቦታል፡፡

 እስከ ረፋዱ አምስት ሰዓት በቦሌ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በሚገኝ መኖሪያ ቤት ቆይታ ካደረገ በኋላ በዳግማዊ ምኒልክ ጎዳና በመስቀል አደባባይ በኩል ወደ መንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በማርሽ ባንድና በክብር ዘብ ዝግታ ጉዞ ሲያደርግ በየመንገዱ የነበሩ እግረኞችና ባለተሸከርካሪዎች ሐዘናቸውን ሲገልፁ ታይተዋል፡፡

በቤተ ክርስቲያኒቱ እንደደረሰም ጸሎተ ፍትሐቱ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ መሪነት የተከናወነ ሲሆን በካናዳ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማትያስ ዳግማዊ ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ንብ ስፖርት ክለብ አባል በመሆን በ1961 ዓ.ም. ውድድር የጀመረው ምሩፅ፣ በአትሌትነት ሕይወቱ በዋናነት በኦሊምፒክ በሞስኮ (1972 ዓ.ም.) እና በሙኒክ (1964 ዓ.ም.) 22ኛና 20ኛ ኦሊምፒያዶች፣ ሁለት ወርቅ (በ5ሺና 10ሺ) እና አንድ ነሐስ (በ10ሺ) ሜዳሊያዎችን፤ በሁለት የዓለም ዋንጫዎች በዱዞርዶልፍ (1969 ዓ.ም.) እና ሞንትሪያል (1971 ዓ.ም.) በሁለቱ ርቀቶች ለአፍሪካ አራት ወርቅ ሜዳሊያዎችን አስገኝቷል፡፡

የሞስኮ ኦሊምፒክ ድሉ ምሩፅን አስደናቂና ትንግርተኛ አትሌት ያደረገው፣ በዘመኑ ኦሊምፒክ እንዳሁኑ በቀጥታ የ10 ሺሕ ፍፃሜ ብቻ ሳይሆን ማጣሪያውን አልፎ በጥቅሉ 20 ሺሕ ሜትር መሮጡ፣ እንዲሁም በ5ሺ ለፍፃሜ ድሉ የበቃው ሁለት ማጣሪያዎቹን በድል በመወጣትና በጥቅሉ 15ሺ ሜትር በመሮጥ ነበር፡፡ 

ምሩፅ የኦሊምፒክ አምሳያ በሆነው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎችም በሌጎስ (1963 ዓ.ም.) በሁለቱ ርቀቶች ወርቅና ነሐስ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ስፖርት ኮከብ፣ የዓለም የኮከቦች ኮከብ ተብሎ ወርቅ ጫማ ለመሸለም የበቃው ሻምበል ምሩፅ በ1971 ዓ.ም. ለብሔራዊ ጀግንነቱ ማስመስከርያ ከኢትዮጵያ መንግሥት የጥቁር ዓባይ ኒሻን መሸለሙ አይዘነጋም፡፡

ከ300 በላይ ውድድሮች አድርጎ 271 ጊዜ ድል ማድረጉ የሚነገርለትና በ72 ዓመቱ ያረፈው ምሩፅ ባለትዳርና የስምንት ልጆች አባት ነበር፡፡ በትግራይ ዓጋመ አውራጃ ዛላምበሳ አካባቢ ከአባቱ አቶ ይፍጠር ተክለሃይማኖትና ከእናቱ ወ/ሮ ለተገብርኤል ገብረአረጋዊ በ1936 ዓ.ም. መወለዱ ታውቋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...