የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(1)ን በመተላለፍ ለሽብር ቡድን መረጃ ሲያስተላልፍ እንደ ነበር ተጠቅሶ የሽብር ተግባር ወንጀል ክስ ተመሥርቶበት የነበረው የሰማያዊ ፓርቲ ልሳን የነበረው ‹ነገረ ኢትዮጵያ› ዋና አዘጋጅ፣ የተከሰሰበት አንቀጽ ተቀይሮ እንዲከላከል ብይን ተሰጠ፡፡
አቶ ጌታቸው ሽፈራው ከተመሠረተበት የሽብር ተግባር ወንጀል ክስ ‹‹በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ ስለመሳተፉ›› የሚለው ውድቅ ተደርጎ፣ በወንጀል ሕግ ቁጥር 257(ሀ) ‹‹በንግግር፣ በሥዕል ወይም በጽሑፍ አማካይነት በግልጽ የቀሰቀሰ›› ወደሚል የተቀየረው፣ ዓቃቤ ሕግ ቀድሞ የመሠረተውን የሽብርተኝነት ወንጀል የሚያቋቁም መረጃ ባለማቅረቡ ነው፡፡
በመሆኑም ተከሳሹ በወቅቱ ፈጽሟል የተባለው የወንጀል ድርጊት ወንጀል አለመሆኑንና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 መሠረት የተፈቀደና መብት ጭምር መሆኑን የሚያስረዱለት አምስት መከላከያ ምስክሮች እንዳሉት፣ ክሱን እየመረመረው ለሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ ወንጀል ችሎት አስመዝግቧል፡፡
እንዲከላከል ብይን ሲሰጥ የተቀየረው የወንጀል ሕግ ቁጥር 257(ሀ) ዋስትና ስለማይከለክል፣ ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብቱ እንዲፈቀድለትም ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ ባቀረበው ዋስትና መብት ጥያቄ ላይ ብይን ለመስጠት ለታኅሳስ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
አቶ ጌታቸው ባለፈው ዓመት በተጠረጠረበት የሽብር ተግባር ወንጀል ማለትም በድረ ገጽ፣ በፌስቡክና በተንቀሳቃሽ ስልኩ መረጃዎችን በመልቀቅና በመሰብሰብ፣ በተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ለተፈረጀው ግንቦት ሰባት አመራሮች መረጃ እንደሚያቀብልና በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው የነበሩ ረብሻዎች እንዲፋፋሙ የሚያደርጉ መረጃዎችን ሲያስተላልፍ እንደነበር በመግለጽ፣ ዓቃቤ ሕግ ክስ መመሥረቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡