Monday, April 15, 2024

በመንታ መንገድ ላይ የሚገኘው የእርሻ ኢንቨስትመንት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያ ለእርሻ ሥራ አመቺ የሆነ በሚሊዮን ሔክታር የሚቆጠር መሬት ባለቤት ናት፡፡ አብዛኛው ጠፍ መሬት የሚገኘው ግን በዝቅተኛው የኢትዮጵያ አካባቢ በመሆኑ ሳይደፈር ቆይቷል፡፡

ነገር ግን በተለይ ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም ወዲህ ለሰውና ለእንስሳት ሕይወት አደገኛ የሆኑ በሽታዎች ባሉባቸው በእነዚህ በረሃማ አካባቢዎች፣ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ኢንቨስተሮች በመግባታቸው ታሪክ በመቀየር ላይ ይገኛል፡፡

ከአሥር ዓመታት በፊት በእርሻ መስክ ብዙም ስማቸው የማይጠራው ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብ ኦሞ፣ አፋርና ሶማሌ የበርካታ ባለሀብቶችን ትኩረት ስበዋል፡፡

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከኢትዮጵያ ሚሊኒየም ወዲህ 134 የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በፌዴራል ደረጃ ተመዝግበው ከ500 ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት ወስደዋል፡፡

በክልል ደረጃ ደግሞ የኢንቨስትመንት ፈቃድ በማውጣት 5,240 ባለሀብቶች ከ1.95 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ወስደዋል፡፡ ነገር ግን እነዚህ ባለሀብቶች የተመቻቸ ሁኔታ ገጥሟቸዋል ማለት አይቻልም፡፡ ከመጀመሪያው አንስቶ አዲሱ የኢትዮጵያ የሜካናይዝድ እርሻ ስሙ ያማረ አልነበረም፡፡

በተለይ በርካታ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች መሬት መውሰድ በጀመሩበት ወቅት፣ ‹‹የመሬት ቅርምት›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶ ብዙ ተብሎበታል፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የመንግሥት ተቋማት በቂ ድጋፍ፣ ክትትል የመሬት ቅርምት ተብሎ ለተከፈተው ዘመቻም በበቂ ሁኔታ አፀፋዊ ምላሽ ባለመሰጠቱ፣ ዘርፉ መድረስ ባለበት ደረጃ እንዳልተጓዘ የሚናገሩ አሉ፡፡

በተለይ በቅርቡ የእርሻ ኢንቨስትመንት በበርካታ ችግሮች በመተብተቡ፣ ችግሮቹን ለይቶ ምላሽ ለመስጠት ያስችላል የተባለ ጥናት ተዘጋጅቷል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት የካቢኔ ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ዓለማየሁ ተገኑ የሚመራ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች የተካተቱበት ቡድን ተቋቁሞ ጥናት አካሂዷል፡፡

ይህ ጥናት ከየካቲት 14 ቀን እስከ ግንቦት 19 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ የተካሄደ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 63 ገጾች አሉት፡፡

ጥናቱ ሰባት ጉዳዮች ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ከእነዚህ ነጥቦች መካከል የባለሀብቶች የቀረጥ ነፃ ታክስ ተጠቃሚነት፣ የባንክ ብድር አሰጣጥ፣ መሬት ማዘጋጀትና ማስተላለፍ፣ መልካም አስተዳደርና ኪራይ ሰብሳቢነት የሚሉት ይገኙበታል፡፡

ጥናቱ በፌዴራል ደረጃ እንዲሁም ለብቻው በጋምቤላ ክልል ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በተለይ የችግሮች ሁሉ ማጠንጠኛ የሆነው የጋምቤላ ክልል ሲሆን፣ በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎችም በዚሁ ክልል የሚገኙ ናቸው፡፡ ችግሮቹም ውስብስብና ለመፍታትም ጊዜና  ጥናት የሚፈልጉ ናቸው ተብሎ ለዘርፉ የሚቀርበው ብድር እንዲቆም መደረጉም ይታወሳል፡፡

ጥናቱ ቅዳሜ ታኅሳስ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል ለውይይት ቀርቦ ነበር፡፡ በዚህ ጥናት በርካታ የእርሻ ዘርፍ ኢንቨስተሮች ደስተኞች አልነበሩም፡፡ ለውይይት በቀረበው በዚህ ጥናት ከተበሳጩ ባለሀብቶች መካከል አቶ ኪሮስ በርሄ፣ አቶ ሙላይ አዲሱና አቶ አብረሃሌ ይህደግ ይገኙበታል፡፡

እነዚህ ሦስት ባለሀብቶች በጋምቤላ ክልል በእርሻ ሥራና በተለያዩ ኢንቨስትመንት መስክ የተሰማሩ ናቸው፡፡ ሁለቱ ባለሀብቶች በጥናቱ ውስጥ ባልተገባ ሁኔታ ስማችን ተነስቷል በሚል ተቃውመዋል፡፡ ባለሀብቶቹ የጥናቱን ውጤትም እንደማይቀበሉት ገልጸዋል፡፡ አቶ አብረሃሌ በበኩላቸው ለሠሩት ሥራ ሽልማት ሲጠብቁ የጅምላ ወቀሳ መቅረብ አግባብ አለመሆኑን ይተቻሉ፡፡      

አቶ ኪሮስ በ2001 ዓ.ም. በጋምቤላ ክልል ፒኝዶ ወረዳ ጎግ ቀበሌ 1,000 ሔክታር መሬት ተረክበው ወደ ሥራ እንዲገቡ፣ ለዚህ እርሻ ሥራ 12.5 ሚሊዮን ብር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በትግራይ ክልል የሚገኙ ንብረቶቻቸውን በማስያዝ መበደራቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ ኪሮስ በጥናቱ ስማቸው የተነሳው ከብድር ጋር አይደለም፡፡ ገንዘቡን የራሳቸውን ንብረት አስይዘው የተበደሩት በመሆኑና እስካሁንም ዕዳቸውን እየከፈሉ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

አቶ ኪሮስ በጥናቱ ስማቸው የተነሳው ከቀረጥ ነፃ መብት ተጠቅመው መጠኑ ያልተገለጸ (ሪፖርተር ባለው መረጃ 498.7 ሜትሪክ ቶን) የአርማታ ብረት አስገብተዋል፡፡ ነገር ግን ጥናቱ በሚካሄድበት ወቅት በእርሻ ቦታው ብረቱ የለም የሚል ነው፡፡

አቶ ኪሮስ ለሪፖርተር እንደሚገልጹት፣ እሳቸው በአድዋ ከተማ ባለአራት ኮከብ ሆቴል እየገነቡ ይገኛሉ፡፡ ብረቱን ያስገቡት በሆቴል ዘርፍ የሚሰማሩ ድርጅቶች የቀረጥ ነፃ መብት የሚሰጣቸው በመሆኑ፣ ይህንን መብታቸውን ተጠቅመው ብረት ማስገባታቸውን ገልጸዋል፡፡

‹‹ለእርሻ ሥራ ብረት አላስገባሁም፡፡ መንግሥትስ ለእርሻ ሥራ ብረት ከቀረጥ ነፃ ይፈቅዳል ወይ?›› ሲሉ አቶ ኪሮስ ጥናቱ ሆን ተብሎ መንግሥትን ከግለሰብ ጋር ለማጋጨት ያለመ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሥራዬን የማከናውነው በአንድ የግብር ከፋይ ቁጥር ነው፡፡ ጉዳዩን ለያይተው ማየት አለባቸው፤›› ሲሉ አቶ ኪሮስ ይናገራሉ፡፡

‹‹ብረቱ በእርሻ ስም የገባ ነው የተባለው ሐሰት ነው፡፡ ብረቱ ለሆቴል ሥራ ያስገባሁት መሆኑ መታወቅ አለበት፤›› ሲሉ አቶ ኪሮስ ተከራክረዋል፡፡

አቶ ሙላይም በተመሳሳይ ስማቸው በጥናቱ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ በጥናቱ ውስጥ አቶ ሙላይ አዲሱ በኢታንግ ልዩ ወረዳ 54 ፒክአፕ ተሽከርካሪዎች፣ አራት ሎደሮችና ስድስት ሲኖትራኮች ከቀረጥ ነፃ ማስገባታቸውን ጥናቱ ገልጾ፣ በመስክ ላይ የተገኘው ግን አንድ ፒክአፕ ብቻ መሆኑን አክሏል፡፡

ነገር ግን አቶ ሙላይ ይህን አይቀበሉትም፡፡ አቶ ሙላይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሙላይ አዲሱ አስመጪና ላኪ በሚል የንግድ ስያሜ ሥር በአራት ዘርፎች ሥራዎችን ይሠራሉ፡፡ እነዚህም እርሻ፣ የተለያዩ ተሽከርካሪዎችንና የኮንስትራክሽን መሣሪያዎችን ከውጭ ማስገባት፣ የተለያዩ የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬዎችና ቅመማ ቅመሞችን ወደ ውጭ መላክና የኮንስትራክሽን ዘርፎች ናቸው፡፡

አቶ ሙላይ ጨምረው እንደገለጹት፣ በርካታ ፒክአፖችን ወደ አገር ያስመጡት ʻቦንድድ ዌርሃውስʼ በመጠቀም ነው፡፡ የቀረጥ ነፃ መብት ያላቸው ባለሀብቶች ሙሉ መረጃ ሲያቀርቡ ይህን ግብይት ይፈጽማሉ ይላሉ፡፡

‹‹ነገር ግን አጥኚው ቡድን በቂ መረጃ ሳይዝ ስማችንን በአደባባይ ማንሳቱ አግባብ አይደለም፡፡ መልካም ስምን የሚያጎድፍ ነው፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ሙላይ፣ ‹‹ጥናቱም ጥያቄ ውስጥ ይጥላል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

‹‹የእርሻ ሥራውንም አስመጪነቱንም በአንድ የግብር ከፋይ ነው የምንሠራው፡፡ ተለያይቶ መቅረብ ነበረበት፤›› ሲሉ አቶ ሙላይ ተናግረዋል፡፡

በጋምቤላ ክልል ያሉ ወረዳዎች ለግብርና ኢንቨስትመንት ሜካናይዜሽን በእጅጉ ምቹ መሆናቸውን ጥናቱ ይገልጻል፡፡ ነገር ግን ወረዳዎች ምቹ የመሆናቸውን ያህል ከጥቂቶች በስተቀር ባለሀብቶቹ ከወሰዱት መሬት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የእርሻ መሣሪያዎች እንደሌለው ጥናቱ ጨምሮ ይገልጻል፡፡

ከዚህ በመነሳት መንግሥት ባለሀብቶቹን ለማበረታታት የተለያዩ የማበረታች ፖሊሲዎች ያዘጋጀ ሲሆን፣ በተለይ የቀረጥ ነፃ መብት በመፍቀዱ የተለያዩ የእርሻ መሣሪያዎችንና ተሽከርካሪዎችን እንዲያስገቡ ፈቅዷል፡፡

‹‹የታክስ ቀረጥ ማበረታቻ ደንብ ላይ በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለሚሰማሩ አልሚዎች ምን ምን እንደሚያስገቡ የሚያመላክት ሲሆን፣ ከተሽከርካሪ በስተቀር አፈጻጸም የተዘጋጀለት ባለመሆኑ ለኪራይ ሰብሳቢነት የተመቻቸ ሁኔታ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፤›› ሲል ጥናቱ የቀረጥ ነፃ መብት ላልተገባ ድርጊት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረጉን አመልክቷል፡፡

በጋምቤላ ክልል ከሚገኙ 623 ባለሀብቶች ውስጥ 200 ለሚሆኑት የባንክ ብድር ተፈቅዷል፡፡ ለመሬት ልማት፣ ለካምፕ ግንባታ፣ ለተሽከርካሪ፣ ለማሽነሪ፣ ለሥራ ማስኬጃና ለሌሎች ወጪዎች በድምሩ 4.96 ቢሊዮን ብር ብድር ተፈቅዷል፡፡

ከዚህ ውስጥ ለተሽከርካሪና ለማሽነሪ 784,147 ሚሊዮን ብር መለቀቁን ጥናቱ አመልክቷል፡፡ ‹‹ነገር ግን የተለቀቀው ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ለታለመለት ዓላማ አልዋለም፤›› ሲል ይገልጻል፡፡  

‹‹በጋምቤላ ክልል 623 ባለሀብቶች 630,518 ሔክታር መሬት ተረክበዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ እስካሁን ማልማት የሚጠበቅባቸው 405,572.84 ሔክታር ነበር፡፡ ʻነገር ግን የለማው መሬት መጠን 64,010,62 ሔክታር ብቻ (15.78 በመቶ) ነው፤›› ሲል ጥናቱ ገልጿል፡፡

369 ባሀብቶች ማልማት ያልጀመሩ መሆናቸውን፣ ከእነዚህ ውስጥ 140 ምንጣሮ መጀመራቸውን ይገልጻል፡፡ ወደ ልማት ከገቡት 254 ባለሀብቶች ውስጥ 216 በውላቸው፣ 38 ከውል ውጪ ያለሙ እንደሆኑ በመግለጽ ጥናቱ በዘርፉ የሥራ አፈጻጸም ደካማነት እንደሚታይ አስረድቷል፡፡

ነገር ግን አቶ አብረሃሌ ይህን አይቀበሉትም፡፡ አቶ አብረሃሌና ወንድሞቹ እርሻ ልማት ኩባንያ በጋምቤላ ክልል ኢታንግ ልዩ ወረዳ 2,000 ሔክታር መሬት በ2001 ዓ.ም. እንደተረከበ ይገልጻሉ፡፡

አቶ አብረሃሌ በስማቸው በ2002 ዓ.ም. 1,000 ሔክታር መሬትም ተረክበዋል፡፡ ‹‹በተረከብነው መሬት ላይ ጥጥ፣ ሰሊጥ፣ ማሾ፣ ማሽላ፣ በርበሬና በቆሎ አልምተናል፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የተረከብነውን መሬት ብናለማም አጥኚ ቡድኑ በእርሻችን ተገኝቶ የሰጠን ደረጃ ቢ ነው፡፡ ይህ እንዴት ይሆናል? ደረጃ ከመስጠቱ በፊት እኔ የእርሻዎቹ ባለቤት ልጠየቅ አይገባም ወይ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ 

አቶ አብረሃሌ ጨምረው እንደገለጹት፣ 13 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መስክ በማልማታቸው የጋምቤላ ክልልና ሕዝብ ተባባሪዎች ነበሩ፡፡ የጋምቤላ ክልል አመራሮችም ደስተኞች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል የእርሻ ኢንቨስተሮች ኅብረት ሥራ ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ የማነ ሴፉ ጥናቱ ችግር ያለበት እንደሆነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹ከጅምሩ የጥናቱ ቡድን ሲዋቀር የባለሀብቶች ወኪል ባለመካተቱና የአንድ ወገን ጥናት በመሆኑ የተሟላ ጥናት ነው ብሎ ለመውሰድ እንደማይቻል ሊታወቅ ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹በጥናት ቡድኑ መካተት አለብን ብለን ተደጋጋሚ ጥያቄ ለሚመለከተው አካል በተለይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ ብናስገባም ሰሚ አላገኘንም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

‹‹ጥናቱ ማተኮር የነበረበት የውጭና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የወሰዱትን የመሬት መጠን፣ የብድር መጠን፣ ያለሙትን መጠን፣ ብድር የወሰዱና ያልወሰዱትን ለይቶ ማቅረብ ላይ ነበር፤›› ሲሉ የገለጹት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ የማነ፣ ‹‹ገና ወደ ሥራ ያልገቡ አንድ ዓመት ካልሞላቸው አዳዲስ አልሚዎች ጋር ቀላቅሎ ማቅረብ ተገቢ አይደለም፡፡ ካሉት 623 ባለሀብቶች 194 የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ብቻ ብድር መውሰዳቸው ተለይቶ መቅረብ ይገባው ነበር፤›› ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ልማት ባንክ ከሰጠው 4.9 ቢሊዮን ብር ብድር ውስጥ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የወሰዱት 1.9 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ ከዚህ ውስጥ 30 በመቶ የባለሀብቱ የግል መዋጮ እንደሆነ ጥናቱ ሊያሳይ ይገባ እንደነበር አቶ የማነ ይናገራሉ፡፡ የተቀረው ሦስት ቢሊዮን ብር በጋምቤላ ያሉ ስድስት የውጭ ባለሀብቶች ድርሻ መሆኑን ጥናቱ ሊያረጋግጥ ይገባ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡

የልማት ባንክ ተበዳሪ የሆኑ 194 የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ማልማት የሚጠበቅባቸው 54,179 ሔክታር ሆኖ እያለ፣ ብድር ያልወሰዱትንና በረዥም ጊዜ ሊያለሙ የተረከቡትን መሬት በጅምላ በማስላት አላለሙም ብሎ ማቅረብ አደናጋሪ ጥናት ሊያስብል እንደሚችልም አቶ የማነ ገልጸዋል፡፡

ብድር ከወሰዱት መልማት ያለበት 54,179 ሔክታር መሬት ከ51,000 ሔክታር በላይ መልማቱን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ መረጃ ጠቅሰው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይህም ከ94 በመቶ በላይ መልማቱን ያሳያል፡፡ ይህን ሀቅ መደበቅም አይገባም ነበር፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ የማነ፣ የጋምቤላ የእርሻ ኢንቨስተሮች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነውም ጥሩ የሥራ አፈጻጸም ማስመዝገብ መቻላቸውን ተከራክረዋል፡፡

ስድስት የውጭ ባለሀብቶች የያዙት ከ240,000 ሔክታር መሬት በላይ መሆኑን፣ የወሰዱትም ብድር ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ከስድስቱ ሁለቱ ካሩቱሪና ቢኤችኤ ፈቃዳቸው መሰረዙን፣ የአብዛኛዎቹም የሥራ አፈጻጸም ደካማ እንደሆነ፣ እነዚህን የውጭ ድርጅቶች ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር ቀላቅሎ ማቅረብ እንደማይገባ የጋምቤላ ኢንቨስተሮች ተናግረዋል፡፡

አቶ የማነ ከቀረጥ ነፃ የገቡ ተሽከርካሪዎችን በሚመለከት እንደገለጹት በብድርና ከቀረጥ ነፃ የገቡ ተሽከርካሪዎች ሰነድ (ሊብሬ) በባንክ ኮላተራል የሚያዝ መሆኑ እየታወቀ ለሦስተኛ ወገን ተላልፏል መባሉ ስህተት ነው ይላሉ፡፡

በአገሪቱ በተለይም በጋምቤላ ክልል እርሻ ኢንቨስትመንት ላይ በርካታ ችግሮች እንዳሉ በጥናቱም ታምኖበታል፡፡ ወጥ የሆነ አሠራር አለመኖር፣ አገልግሎቶች በግለሰቦች መልካም ፈቃድ ላይ የተሠረቱ መሆናቸው፣ የአንድን ባለሀብት ይዞታ ለሌላ ባለሀብት መስጠት (መሬት መደራረብ)፣ የፀጥታ ችግር፣ የፍትሕ ተቋማት አድሏዊ አሠራር፣ የአመራሮች ድጋፍ አነስተኛ መሆን፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦት፣ የገበያ ትስስር ችግር፣ ተጠያቂነት አለመኖርና የመሳሰሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡  

ታኅሳስ 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደው ውይይት የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጋትሉዋክ ቱት እንደገለጹት፣ በአመራሩና በባለሀብቱ መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት ጥናት ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡

‹‹ችግሮቻችንን ሲነገረን ካልተቀበልን ችግርን መፍታት አንችልም፡፡ የጥናት ሰነዱን እንቀበላለን፤›› ሲሉ አቶ ጋትሉዋክ ገልጸዋል፡፡

‹‹የጋምቤላ የእርሻ ኢንቨስትመንት አስጨንቆናል፡፡ ትልቁ የዘርፉ ችግር የአመራሩ ነው፡፡ አመራሩ ሥራውን በአግባቡ አልሠራም፡፡ በአግባቡ ቢሠራ የመሬት መደራረብ ችግር አይፈጠርም ነበር፤›› ሲሉ አቶ ጋትሉዋክ ተናግረዋል፡፡

‹‹ጥናቱንና በጥናቱ ውስጥ የተጠቀሱትን ችግሮች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፊት ተቀብለናል፡፡ የመሬት ካርታ በቢሮ አይሠራም፡፡ የሚሠራው በኔትወርክ ከቢሮ ውጪ ነው፡፡ የአቅም ችግር አለ፡፡ የሙስና አመለካከት አለ፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ጋትሉዋክ፣ ‹‹በዘርፉ ችግር እየፈጠሩ ያሉ አካላትን እየለየን ዕርምጃ መውሰድ ጀምረናል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ጋትሉዋክ ክልሉ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ራሱን የሚያስተዳድር መሆኑን በመግለጽ፣ የእርሻ ባለሀብቶች ለክልሉ በርካታ ቁም ነገሮችን መፈጸማቸውን ዘርዝረዋል፡፡ ‹‹በፀጥታ ማስከበር፣ በመሠረተ ልማት ግንባታና በሥራ ፈጠራ ባለሀብቶች ብዙ ድጋፍ አድርገዋል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በተካሄደው ጥናትም ቀደም ሲል መሬት በውክልና በመግባቢያ ሰነድ ከክልሎች ተወስዶ በፌዴራል ደረጃ ለባለሀብቶች የሚሰጥበትና የሚተዳደርበት አካሄድ እንዲቀር መደረጉም ተገልጿል፡፡

በሕገ መንግሥት ከተደነገጉ መሠረታዊ ጉዳዮችና አሁን በክልሉ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተያይዞ፣ የፌዴራል መንግሥት መሬት በውክልና ማስተዳደሩ በኅብረተሰቡ ዘንድ ብዥታ እየፈጠረ በመሆኑ መሬት የማስተዳደርና ለባለሀብቶች የማስተላለፍ ተግባር በክልሎች ባለቤትነት እንዲፈጸም ተወስኗል፡፡ በዚህ መነሻነት የፌዴራል መንግሥት በዚህ ረገድ የክልሎችን አቅም የመገንባት ተቀናጅቶና ተባብሮ ኢንቨስትመንቱ የተሳለጠ የማድረግ ሥራ እንዲሠራ፣ የክልሉ መንግሥት በክልሉ ውስጥ ያለው የተዘበራረቀ፣ ግልጽነት የጎደለውና ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ የሚፈጸመውን የመሬት ማስተላለፍና የይዞታ ካርታ አሰጣጥ ሁኔታ ከሚመለከታቸው የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ጋር በመቀናጀት ጠንካራ የአሠራር ሥርዓት እንዲዘረጋ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ባሉበት በተካሄደ ስብሰባ ላይ መወሰኑ ታውቋል፡፡

መሬት የማስተዳደር ሥራ ከፌዴራል መንግሥት ወደ ክልሎች እንዲሸጋገር መደረጉ ባለሀብቶችን ያስደሰተ ሲሆን፣ የተዘጋጀው ጥናት የአንድ ወገን በመሆኑ ማሻሻያ እንዲደረግበት ባለሀብቶቹ ጠይቀዋል፡፡

የጥናት ሰነዱ በቋሚነት የሚያገለግል በመሆኑ፣ ባለሀብቶች የሚያነሷቸው ጠቃሚ ሐሳቦች ቢካተቱ ችግሮችን ፈትቶ የሚፈለገውን ልማት ለማምጣት አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር አቶ የማነ ገልጸዋል፡፡

በእርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ያሉ ችግሮች አገሪቱን ዋጋ እያስከፈሉ እንደመሆናቸው፣ ችግሮቹን በመፍታት የግብርና ዘርፍን ማሳደግ የፌዴራል መንግሥትን ቁርጠኝነት እንደሚፈልግ እየተገለጸ ነው፡፡                  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -