የአገሪቱን የክፍያ ሥርዓት ለማዘመን ያስችላሉ ተብለው ወደ ሥራ ከተገባባቸው አገልግሎቶች መካከል አንዱ በባንኮች ትብብር በተቋቋመ ኢትስዊች አክሲዮን ኩባንያ በኩል የተጀመረው ሥራ ይጠቀሳል፡፡ ኩባንያው ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ሁሉም ባንኮች በማሳተፍና የአክሲዮን ድርሻ ኖሯቸው የተቋቋመ ነው፡፡ ኩባንያው በባንኮች መካከል በኤሌክትሮኒክ ዘዴዎች የሚተላለፉ አነስተኛ ክፍያዎችን የሚያስተላልፍ ብሔራዊ ስዊች፣ የሒሳብ ማጣሪያና ማወራረጃ መሠረተ ልማትን በመገንባት ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ ይህም በሁሉም ባንኮች የክፍያ ሥርዓቶች መካከል ተነባቢነት እንዲኖር ያስቻለ ነው፡፡ አክሲዮን ኩባንያው የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ቢሆንም አገልግሎቱን ለመጀመር የሚያስችለውን መሠረተ ልማት ግንባታ አጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ባለፈው ግንቦት 2008 ዓ.ም. ነው፡፡
ቀዳሚ ሥራው አድርጎ ወደ አገልግሎት የገባው ደግሞ የሁሉንም ባንኮች የኤቲኤም ካርዶች በሁሉም ባንኮች ይዞታ ሥር ባሉ ኤቲኤሞች እንዲጠቀሙ በማድረግ እንደሆነም ይታወሳል፡፡
ባንኮች ተወዳዳሪዎች ቢሆኑም በኢትስዊች ኩባንያው ውስጥ የሚያደርጉት ትብብር ለባንኮቹም ሆነ ለአገሪቱ የክፍያ ሥርዓት ማደግ የተፈለገውን ውጤት እንደሚያመጣ የማድረግ ዓላማ ጭምር የያዘ ስለመሆኑም የኩባንያው ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡ የየትኛውንም ባንክ ኤቲኤም ካርድ የያዘ የባንክ ደንበኛ በየትኛውም ባንክ ኤቲኤሞች ላይ በመጠቀም ገንዘብ ማንቀሳቀስ ከመቻሉም በላይ፣ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ዘመናዊ የክፍያ አገልግሎቶችን መጠቀም ይችላል፡፡
የኢትስዊች ባለአክሲዮኖች ባለፈው ሐሙስ ባደረጉት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የኩባንያው የ2008 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን የተመለከተ ሪፖርቱም ይፋ ሆኗል፡፡
ኢትስዊችና 2008
ኢትስዊች ባለፈው ሐሙስ ባከናወነው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በኩባንያው ዳይሬክተሮች ቦርድ የቀረበው ሪፖርት የ2008 ዋነኛ ስኬቱ ኩባንያው ወደ አገልግሎት መግባቱ ነው፡፡
የመሠረተ ልማት፣ የሲስተም፣ የደንብና የአሠራር ሥርዓት ዝርጋታ ሥራዎችን አከናውኖ የብሔራዊ የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ስዊች መሠረተ ልማቱ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር ማድረጉ ዋና ክዋኔው መሆኑን ጠቅሷል፡፡ በብሔራዊ ስዊቹ አማካይነት በባንኮች መካከል የሚተላለፉ የገንዘብ ዝውውሮችን በተገቢው መንገድ ለመምራት የሚያስችል ደረጃ፣ ደንብ፣ የችግር አፈታት መመርያና የዋጋ ተመን በማውጣት ወደ ሥራ መገባቱ፣ በበጀት ዓመቱ ከተከናወኑ ዋና ዋና ሥራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ተብሏል፡፡ ከዚህም ሌላ ኢትዮ ፔይ በሚል የንግድ ስምና ምልክት የሚታወቀውን የብሔራዊ ስዊች መሠረተ ልማት ዓለም አቀፍ ደረጃ በጠበቀ መልኩ ማዘጋጀቱንና አገራዊ የክፍያ ካርድን መተግበር መጀመሩም በበጀት ዓመቱ ዋና ዋና ክንዋኔዎች ውስጥ አንዱ ሆኖ ተጠቅሷል፡፡ ከኢትዮ ፔይ ካርድ አገልግሎት መጀመር ጋር ተያይዞ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ብዙነህ በቀለ በሪፖርቱ እንደገለጹት፣ ኢትዮ ፔይ የተባለውን ብሔራዊ ካርድ አምስት ባንኮች ወስደው ጥቅም ላይ እያዋሉትና ለማዋል እየተዘጋጁ መሆኑን ነው፡፡ ይህ ካርድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ካርድ ጭምር በመሆን የሚያገለግል ሲሆን፣ ባንኮች አሁን በየግል ከሚጠቀሙበት ካርድ ጎን ለጎን ሥራ ላይ የሚውልና ወደፊት ግን ለአገልግሎት አመቺነት ሲባል በተነጣጠለ መንገድ ያሉትን ካርዶች እንደ አንድ ብሔራዊ ካርድ አገልግሎት ውስጥ እንዲገባ የሚፈለግ ነው ተብሏል፡፡
የኢትስዊች ተገልጋዮችና ያለፉት አምስት ወራት
በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ ከ2,000 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ኤቲኤሞች በባንኮች ተተክለው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ ከፕሪምየም ስዊች ሶሉሽን ተጨማሪ ባንኮች ውጭ ያሉት ኤቲኤሞች ለየባንኮቹ ደንበኞች ብቻ አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ናቸው፡፡ ካለፈው ግንቦት 2008 ወዲህ ግን ከማንኛውም የኤቲኤም ካርድ ከየትኛውም ባንክ ኤቲኤም ገንዘብ ማውጣት ተችሏል፡፡ እንደ ኢትስዊች ዓመታዊ ሪፖርት የ2008 በጀት ዓመት የመጨረሻዎቹ ሁለት ወራት (ግንቦትና ሰኔ 2008 ዓ.ም.) ድረስ ብቻ 71,235 በሆኑ የክፍያ ካርድ ተጠቃሚ የባንክ ደንበኞች፣ ደንበኛ ከሆኑበት ባንክ ውጭ ካሉ ኤቲኤሞች አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ በዚሁ ወቅት 173,228 የሆኑ ክፍያዎችን በኢትስዊች በኩል እንዲፈጸም ማስቻሉንም ሪፖርቱ ያሳያል፡፡ እነዚህ ደንበኞች በሁለት ወራት 101,054 ሚሊዮን ብር ካልተመዘገቡበት ባንክ ኤቲኤሞች በማውጣት አገልግሎት እንዲያገኙ አስችሏል፡፡ ከሐምሌ እስከ ኅዳር 2009 ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ ስለመምጣቱ የሚጠቅሱት አቶ ብዙነህ፣ ባለፉት ጥቂት ወራት የታየው እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን ያመለክታል የሚል እምነት አላቸው፡፡
ሪፖርቱ 427,732 የሚሆኑ የካርድ ተጠቃሚዎች አገልግሎቱን ለማግኘት ሙከራ ማድረጋቸውን ይገልጻል፡፡ ከነዚህ አገልግሎት ፈላጊዎች ውስጥ 352,920 የሚሆኑት ወይም 82.5 በመቶዎቹ 1.17 ቢሊዮን ብር ከተለያዩ ኤቲኤሞች ማውጣት ችለዋል፡፡
በእስካሁኑ የኢትስዊች አክሲዮን ማኅበር ጉዞ የብሔራዊ ስዊቹ ሥራን ለማስጀመር ወሳኝ የነበረውን የፕሮጀክቱ ምዕራፍ አንድን ሥራ በስኬት ስለመጠናቀቁ አመላካች ስለመሆኑም የኩባንያው ሪፖርት ያሳያል፡፡ ሆኖም በየትኛውም ቦታ በማንኛውም ጊዜ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አንድ ወጥ የሆነ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት የኤሌክትሮኒክ ክፍያ መሠረተ ልማት መደላደል የሚለውን የኩባንያውን ራዕይ ለማሳካት ረዥም ጉዞ ይጠብቀዋል ይላል፡፡
የወደፊቱ ጉዞ
እንደ ሪፖርቱ ከሆነ የክፍያ ሥርዓቱን ከማዘመን አንፃር ይሠራሉ ተብለው ከተያዙት ውስጥ አዳዲስ አገልግሎቶችን ማስጀመር ነው፡፡ ብሔራዊ ስዊች ፕሮጀክቱ ውስጥ የተካተቱ አገልግሎቶችን ዓይነት፣ ብዛትና ውስብስብነትን ከግምት ባስገባ መንገድ ቀሪ የፕሮጀክቱን ሥራዎች በምዕራፍ ከፋፍሎ ለማከናወን መታቀዱን ያመለክታል፡፡ ለዚህም ከብሔራዊ ስዊች አቅራቢው ጋር በተደረገው የኮንትራት ማሻሻያ መሠረት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተሰጠው መመርያ በግዴታ ሊተገበሩ የሚገቡ አገልግሎቶች ጥናትና በፍላጎት ሊተገበሩ የሚችሉ አገልግሎቶችን ለይቶ የፕሮጀክቱን ማከናወን የሚለው ሥራ ቀዳሚ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ ይህ ማለት ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓቱን ለማስፋት በብሔራዊ ስዊቹ በኩል የሚሰጡ አገልግሎቶች ግዴታ የሚሆኑበትን አሠራር የሚጠቀም ነው፡፡
ከዚህ ሌላ ኩባንያው በቀጣይ እተገብራቸዋለሁ ብሎ ከያዛቸው ዕቅዶች መካከል በብሔራዊ ስዊቹና በአባል ባንኮቹ መሠረተ ልማት ላይ ዓለም አቀፍ ደረጃዎች እንዲተገበሩ ማድረግ የሚለው ይገኝበታል፡፡ ይህም ሁሉም ባንኮች አንድ ወጥ የሆነ ደረጃውን የጠበቀ ካርድ እንዲኖራቸው ከማድረግ ጀምሮ፣ ተመሳሳይ በሆነ ቴክኖሎጂና ሲስተም እንዲጠቀሙ ወደማድረግ የሚገባበት ነው፡፡
በአገሪቱ ያሉ የባንክ ደንበኞች ፍላጎትንና አቅምን መሠረት ያደረጉ፣ የአገሪቱን የንግድ አሠራር ለማቀላጠፍ ምቹ የሆኑ፣ እንዲሁም ወጪ ቆጣቢ የሆኑ የኤሌክትሮኒክ ዘዴ የክፍያ አገልግሎቶችን በኢትዮ ፔይ የንግድ ስምና ምልክት እንዲስፋፋ ማድረግም የኩባንያው ቀጣይ ዕቅድ ነው ተብሏል፡፡
በኢትዮ ፔይ የንግድ ስምና ምልክት የሚታተሙ የክፍያ ካርዶችን፣ ከዓለም አቀፍ የካርድ ኩባንያዎች ጋር በጥምር የንግድ ምልክት በማቀናጀት በዓለም አቀፍ ሐዋላ አማካይነት ወደ አገር ውስጥ በሚገባ የውጭ ምንዛሪ ማሳደግ የሚልም ዕቅድ አለኝ ብሏል፡፡
ባንኮች በኤሌክትሮኒክ ክፍያ ዘዴ የታገዙ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ለደንበኞቻቸው በስፋትና በዓይነት እንዲያቀርቡ በማገዝ፣ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማት፣ የንግድ ድርጅቶችና ግለሰቦች በኤሌክትሮኒክ የክፍያ ሥርዓት ታግዘው ገቢዎቻቸውን እንዲሰበስቡና ክፍያዎቻቸውን እንዲፈጽሙ ለማድረግም እንደሚሠራ ተገልጿል፡፡
የፋይናንስ ተቋማትን ማስገባት
ኢትስዊች ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ በሁሉም የአገሪቱ ባንኮች የአክሲዮን ባለቤትነት የተቋቋመ ቢሆንም፣ ከባንኮች ውጭ ያሉ የገንዘብ ተቋማትን ወደ አክሲዮን ኩባንያው የማስገባት ውጥን አለው፡፡ ይህንን ውጥኑን ለማሳካት አነስተኛ የቁጠባና የብድር ተቋማት ሲስተሞቻቸውን ከብሔራዊ ስዊቹ ጋር እንዲያቀናጁና የፋይናንስ አገልግሎትን ለማዘመንና ተደራሽነቱን ለማስፋት ይፈለጋል፡፡ በክፍያ ሥርዓቱ ውስጥ በሦስተኛ አካል የፋይናንስ ቴክኖሎጂ አገልግሎት ሰጪነት የተሰማሩ ኩባንያዎችም ሲስተሞቻቸውን ከብሔራዊ ስዊቹ ጋር በማቀናጀት አገልግሎቶቻቸውን በባንኮች በኩል ተደራሽ እንደሚያደርጉ የሚጠበቅ ስለመሆኑ የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ ለዚህም ተፈጻሚነት የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልጿል፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ ኮርፖሬሽኖችና ሌሎች ተቋማት የሚሰበስቧቸውን ገቢዎችም ሆነ ክፍያዎቻቸውን ወደ ኤሌክትሮኒክ ዘዴ በመለወጥና ከባንኮችና ከብሔራዊ ስዊቹ ጋር በማስተሳሰር የገቢ አሰባሰባቸውንና ክፍያ አፈጻጸማቸውን እንዲተገብሩ ለማድረግም የተጀመሩ ሥራዎች አሉ ተብሏል፡፡ አቶ ብዙነህ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የክፍያ ሥርዓታቸውን በኤሌክትሮኒክ የክፍያ ሥርዓት ከኩባንያቸው ጋር ለማስተሳሰር ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ከሚጠበቁት ተቋማት ውስጥ አንዱ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ነው፡፡
ግብር ከፋዮች በቀጥታ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ክፍያ እንዲፈጽሙ ለማድረግ የመሠረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች እየተሠሩ ሲሆን፣ ይህ ሲጠናቀቅ በተለይ ከፍተኛ የግብር ከፋዮች ያሉበት ቦታ ሆነው ክፍያ እንዲፈጽሙ ያስችላል ብለዋል፡፡ እንደ ኤሌክትሪክ፣ ውኃና የመሳሰሉ ክፍያዎችም በዚህ ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በኤሌክትሮኒክ ዘዴ የሚደረገው የክፍያ ሥርዓት መስፋፋት የፋይናንስ አገልግሎቱ እንዲስፋፋና ለኢኮኖሚ ዕድገቱም ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ያግዛል፡፡ ከዚህም ሌላ በገበያው ውስጥ የሚዘዋወረው የጥሬ ገንዘብ መጠንን በመቀነስ በገንዘብ ማሳተም፣ ማጓጓዝ፣ መቁጠር፣ መጠበቅና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ በመቀነስ ተጨባጭ የሆነ አገራዊ ጥቅም የሚያስገኝ ይሆናል የሚል እምነት ተይዟል፡፡
አገልግሎቱና የደንበኞች ቅሬታ
የኢትስዊች ወደ ሥራ መግባት ማንኛውም የኤቲኤም ተጠቃሚ በፈለገበት ቦታ በቀረበው የየትኛውም ባንክ ኤቲኤም እንዲጠቀም ማስቻል ነው፡፡ ባለፈው ስድስት ወራት የባንክ ደንበኞች በዚህ አገልግሎት እየተጠቀሙ ነው፡፡
ኢትስዊችም ቢሆን ከዚህ አገልግሎት በተጨማሪ ሌሎች በርካታ አገልግሎቶችን እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡ ይሁንና ከዚህ አገልግሎት ጋር በተያያዘ እየቀረቡ ያሉ ቅሬታዎች ግን በየዕለቱ ይሰማሉ፡፡ ወደ አንድ የባንክ ኤቲኤም ማሽን ሄደው ገንዘብ ለማውጣት ሲሞክሩ የማያገኙበት አጋጠሚ አለ፡፡ የጠየቁት ገንዘብ እንደተከፈላቸው ሪፖርት ቢደረግላቸውም፣ ገንዘቡን ሳይወስዱ የሚቀሩበት አጋጣሚ ስለሚፈጠር ወደ ተለያዩ ኤቲኤሞች በመሄድ መሞከር ግድ ሲላቸውም ይታያል፡፡
በአንዴ የሚፈልጉትን ክፍያ አላገኘንም የሚል ቅሬታ ይቀርባሉ፡፡ ገንዘብ ለማስመለስ፣ ቀናት የሚወስድ መሆኑም ከአገልግሎት አሰጣጡ ጋር በተገናኘ የሚቀርብ ቅሬታ ነው፡፡
አቶ ብዙነህም እንዲህ ያለው ቅሬታ ስለመኖሩ አልሸሸጉም፡፡ ነገር ግን ከጠቅላላ ተገልጋዮች የተወሰኑት የገጠማቸው ችግር ብዙ ምክንያት ያለው ነው ይላሉ፡፡ ከተጠቃሚው፣ ከባንኩ ሲስተም ወይም ከራሱ ከኢትስዊች ጋር የተያዘ ክፍተት ይሆናል ያሉት አቶ ብዙነህ፣ በኢትስዊች በኩል ያለውን ወዲያው እንዲታረም ይደረጋል ብለዋል፡፡ የአገልግሎቱ መስተጓጎል ከባንኮች ሲስተም ጋር በተገናኘ በሚሆንበት ጊዜ ችግሩን በመግለጽ እንዲያስተካክሉ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ሌሎች ምክንያቶች ቢኖሩም እነዚህን ክፍተቶች እየደፈኑ እንዲሄዱ በማድረግ ቅሬታው መፍትሔ እንዲያገኝ ከባንኮች ጋር እየሠሩ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡
ነገር ግን በአንድ አጋጣሚ በአንድ ኤቲኤም ገንዘብ ማግኘት ያልቻለ ደንበኛ ወደ ሌላ ኤቲኤም ቢሄድ ያገኛል፡፡ ያላግባብ ከተቆረጠበትም ገንዘቡ የትም ሳይሄድ እንዲከፈለው ይደረጋል ብለዋል፡፡
ያላግባብ እንደተቆረጠ የሚደረገውን ገንዘብ ለማስመለስ የስምንት ቀናት ጊዜ ስለመሰጠቱ የጠቀሱት አቶ ብዙነህ፣ ገንዘቤ ከአካውንቴ ተቆርጧል ያለ ደንበኛ ለባንኩ ባመለከተ በሳምንት ቀን ውስጥ ገንዘቡን ማግኘት አለበት ብለዋል፡፡ ‹‹ገንዘቡን ወስዶም ከሆነ መረጃ ስለሚቀርብ ይህንን ገንዘብ አውጥተሃል ተብሎ ይገለጽለታል እንጂ የሚቀር ገንዘብ አይደለም፡፡ አጠቃላይ ሲስተሙም ቢሆን በአግባቡ ይሠራል፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ኢትስዊች ምን አገኘ?
በኤቲኤም የሚፈጸሙ ክፍያዎችን በማዕከል በመሆን ለሚሰጠው አገልግሎት የራሱ የሆነ ክፍያ አለው፡፡ በ100 ብር 25 ሳንቲም ያገኛል፡፡ እስካለፈው ወር መጨረሻ ድረስም 207 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ስለመቻሉ ተጠቅሷል፡፡
በአሁኑ ወቅት ባንኮች የኤቲኤሞቻቸውን ቁጥር እያሳደጉ በመመጣታቸውና የተገልጋዩ ቁጥርም እየጨመረ ስለመጣ፣ ገቢውም የዚያኑ ያህል ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ገቢውም ለአገልግሎቱ ማስፋፊያ በማዋል ዘመናዊ የክፍያ ሥርዓቱ እንዲያድግ ያደርጋል ተብሏል፡፡