Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየመድረክ ስም

የመድረክ ስም

ቀን:

ፍልፍሉ፣ ዋኖሶች፣ ጭራ ቀረሽ፣ ቤቲ ጂ፣ ልጅ ያሬድና ጃኪ ጎሲን የመሰሉት የኪነ ጥበቡ ባለሙያዎች የመድረክ ስሞች በብዙዎች ዘንድ ይታወቃሉ፡፡ አንዳንዶቹ ስሞች የባለሙያዎቹ መጠሪያ ስም እስከሚመስሉ ድረስ ጥቅም ላይ ስለሚውሉ የአርቲስቶቹ ትክክለኛ ስም ማን ነው? ቢባሉ ግራ የሚጋቡም አሉ፡፡

ራስ ዮሐንስ (ራስ ጃኒ) የድምፃዊ ዮሐንስ ውብሸት የመድረክ ስም ነው፡፡ ‹‹ሰላምታ›› በተሰኘው አልበሙ ተወዳጅነትን  ያተረፈው ራስ ጃኒ፣ አልበም ከማውጣቱ በፊት ክለብ ውስጥ ይሠራ በነበረበት ወቅትም የመድረክ ስሙን ይጠቀም ነበር፡፡ የመድረክ ስሙን የመረጠው የሚያምንባቸው ጽንሰ ሐሳቦችን ከግምት በማስገባት እንደነሆነ ይናገራል፡፡ ‹‹ራስ የሁሉም መሠረት የሆነውን አካል ያመለክታል፡፡ ራስ ከሌለ ሕይወት የለም፡፡ ከራስተፈሪያኒዝም አንፃር ጃኒ ሲተረጎም ‹‹ጃ›› ፈጣሪ ‹‹ኒ›› ደግሞ ጉልበት ማለት ነው፡፡ ጃኒ የአምላክ ጉልበት የሚል ትርጉም አለው፤›› ሲል ስለ ስሙ ይገልጻል፡፡

ብዙዎች ዮሐንስ የሚለውን ስም የእንግሊዝኛ ትርጓሜ ‹‹ጆን›› በመውሰድ ዮሐንስ የሚባሉ ሰዎችን ጆኒ ብለው ይጠራሉ፡፡ ራስ ጃኒ እንደሚለው፣  ጆኒ የሚለውን አውሮፓዊ መጠሪያ ስለማይቀበል በመድረክ ስሙ ራስ ጃኒ መጠራት ይመርጣል፡፡ ራስ ዮሐንስ ተብሎ ሲጠራም ደስተኛ ነው፡፡ የመድረክ ስሙ ከመጠሪያ ስምነት በላይ አመለካከቱን የሚያንፀባርቅበት እንደሆነ ይናገራል፡፡ ‹‹የመድረክ ስሜ በመጠሪያነትና  ለኅብረተሰቡ መልዕክት በማስተላለፍ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደማለት ነው፤›› ይላል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ራስ ጃኒ የሚታወቅበት የሬጌ ሥልትና የመድረክ ስሙም ይጣጣማሉ፡፡ በሙዚቃዎቹ የሚሰብካቸው እንደ ፍቅርና አንድነት ያሉ ሐሳቦችን ከመድረክ ስሙ በተጓዳኝ በዘፈኖቹ ግጥሞች እንደሚንፀባረቁ ይገልጻል፡፡ በእሱ እምነት በአልበሙ ያካተታቸው ዘፈኖች ኅብረተሰቡ እንዲያውቅለት የሚፈልጋቸውን ሐሳቦች  ይዘዋል፡፡ በተጨማሪም ስለ መድረክ ስሙ ትርጓሜ መናገር አመለካከቱን በተወሰነ ደረጃ ለማንፀባረቅ ይረዳዋል፡፡ ‹‹ራስ ጃኒ የሚለው ስም እኔን የበለጠ ይገልጸኛል፤›› ይላል፡፡

ድምፃዊው እንደሚለው፣ ዮሐንስ የሚለውን ስም በኢትዮጵያ ታሪክ ዮሐንስ ከተባሉ ነገሥታት ታሪክ አንፃርም ያየዋል፡፡ በጓደኞቹና አድማጮች ራስ ዮሐንስ ተብሎ መጠራትን ትልቅ ቦታ የሚሰጠውም ለዚሁ ነው፡፡ ‹‹ዮሐንስ ብላ ስም ያወጣችልኝ እናቴ ናት፡፡ እናቴ አሁንም የምትጠራኝ ዮሐንስ ብላ ነው፤›› ይላል፡፡ ስሙ ለቤተሰቡ ያለውን ትርጓሜም ሲያስረዳ፡፡

እንደ ራስ ጃኒ የመድረክ ስም መጠቀምን የሚመርጡ ሌሎችም ድምፃውያን አሉ፡፡ በመድረክ ስማቸው አመለካታቸውን ከማንፀባረቅ ጀምሮ በቀላሉ የሚያዝ መጠሪያ መጠቀምና ሌሎችም ምክንያቶች አሏቸው፡፡ በተለይም በሙዚቃ የመድረክ ስም ድምፃዊን ከማስተዋወቅና ከቢዝነስ ጋር ሊያያዝም ይችላል፡፡ ራስ ጃኒ የመድረክ ስሙን ራሱን እንደ ድምፃዊ በቀላሉ ከማስተዋወቅ አንፃርም ያየዋል፡፡ ‹‹የድምፃዊ የመድረክ ስም ቀላል፣ ትኩረት ሳቢና ሰዎች ልብ የሚቀር ሲሆን፣ ለማስታወቂያም ይመቻል፤›› ይላል፡፡

ድምፃውያን የመድረክ ስም በመጠቀም ቢታወቁም በሌሎች የኪነ ጥበብ ዘርፎችም በሌሎችም ከመጠሪያ ስማቸው በተለየ የመድረክ ስም የሚገለገሉ ባለሙያዎች አሉ፡፡ አንዳንዴ ከባለሙያዎቹ ባህሪና ከኪነ ጥበብ ሥራዎቻቸው በመነሳት ቅጽል ስም ይወጣላቸዋል፡፡ ስሙን የሙያ አጋሮቻቸው ወይም ሕዝብ ቢሰጣቸውም ከስማቸው ጎን ለጎን እንደ አማራጭ መጠሪያ ይጠቁመበታል፡፡ መጠሪያ ስማቸውን በማሳጠር የመድረክ ስም የሚያወጡ እንዲሁም በቤተሰብና ጓደኞቻቸው የሚጠሩበትን የቤት ስም የሚጠቀሙም አሉ፡፡ አንዳንዶች የመረጡት የመድረክ ስም ሲጠራ ማራኪ ከመሆኑና በሕዝብ ሊወደድ ከመቻሉ ባለፈ ለስሙ ትኩረት አይሰጡም፡፡ በተቃራኒው የመድረክ ስምን ከመጠሪያነት ባለፈ አመለካከታቸውን ለመግለጽ የሚያውሉም ይጠቀሳሉ፡፡

ልጅ ሚካኤል መጠሪያ ስሙ ሚካኤል ታዬ ሲሆን፣ ቀድሞ ክሬዚ አሁን ደግሞ ልጅ ሚካኤል ወይም ፋፍ በሚለው ስም ይታወቃል፡፡ ድምፃዊው በካርኒቫልና ዴይ ፓርቲ በሚዘፍንበት ‹‹ክሬዚ›› የተባለው፣ ‹‹ደስ የሚል የጨዋታ እብደት ስለነበረኝ ነው፤›› ይላል፡፡ ጓደኞቹ የሰጡት መጠሪያ በሩቅ የሚያውቁት ሰዎች ዘንድ ደርሶ የነበረ ቢሆንም ቢደርስም አሁን በዚያ ስሙ የሚጠራው የለም፡፡

ድምፃዊው ከእናቱ በተሰጠው የቤት ስም ፋፍም ይጠራል፡፡ በሕዝብ በበለጠ የሚታወቅበት ልጅ ሚካኤል የሚለውን ስም ከመጠሪያነትም ባለፈ ያየዋል፡፡ አያቱ ልጅ ጽጌ ገዝሞ የሚባሉ ሲሆን፣ ማዕረጋቸው ከፍ ብሎ ሜጀር ጄኔራል ተብለዋል፡፡ ታዳጊ ሳለ የአያቱ ወዳጆች ልጅ ሚካኤል እያሉ ይጠሩት ነበር፡፡ ሌሎችም ከነሱ ተቀባብለው ስሙ ፀና፡፡ ስሙ ከአያቱ ጋር ስለሚያስተሳስረው ይወደዋል፡፡

‹‹ዛሬ ይሁን ነገ›› የተሰኘውን አልበሙን ከማውጣቱ በፊት የነበረውን ስሙን ለመድረክ ስምነት ከመረጠበት ምክንያት አንዱ ስሙ ቤተሰባዊ በመሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የቀድሞ የማዕረግ መጠሪያ የነበረውን ‹‹ልጅ›› መጠቀም ኢትዮጵያዊ ገጽታውን እንደሚያጎላ ያምናል፡፡ ‹‹ልጅ የሚለው ማዕረግ ይሰጥ የነበረው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ የአያቴም መጠሪያ ነው፡፡ ሌላ ከኔ ጋር የማይገናኝ የመድረክ ስም ከማውጣት ልጅ ሚካኤልን መርጫለሁ፤›› ሲል ይገልጻል፡፡

ልጅ የማዕረግ ስም በመሆኑ ልትጠቀምበት አይገባም የሚሉት እንዳሉ ይናገራል፡፡ የማዕረግ ስምነቱን ባለመገንዘብ ከዕድሜ ጋር አያይዘው እንዴት ልጅ ትባላለህ? የሚል አስተያየት የሚሰጡትም አልጠፉም፡፡ ድምፃዊው እንደሚለው፣ በስሙ ጥያቄ ሲነሳ ከጀርባው ያለውን ሐሳብ ለማብራራት ዕድል ይሰጠዋል፡፡ ‹‹ልጅ፣ ራስና ቢትወደድን የመሰሉ የማዕረግ ስሞችን አሁን ማግኘት አይቻልም፡፡ ትርጉማቸውን እየገለጽን ብንጠቀምባቸው ጥሩ ነው፤›› ይላል፡፡

ቤተሰቦቹ፣ ጓደኞቹና አድማጮች ልጅ ሚካኤል፣ ልጅ ማይክና ፋፍን እያለዋወጡ የሚጠሩት ድምፃዊው፣ የሂፕ ሃፕ አርቲስት የመድረክ ስም ከምዕራባውያን ጋር መመሳሰል አለበት የሚል አመለካከት ያላቸው እንዳሉም ይናገራል፡፡ ስም ከመጠሪያነት ባለፈ ስለ ሙዚቀኛው ማንነት መግለጽ ጉልበት እንዳለበት የሚያምነው ልጅ ሚካኤል ግን ሂፕ ሃፕን አገርኛ ገጽታ ማላበስ በመድረክ ስምም እንደሚገለጽ ያስረዳል፡፡

ሳሙኤል ብርሃኑ መጠሪያ ስሙ ሲሆን፣ ለመድረክ ስምነት የመረጠው ሳሚ ዳን በተለይም ‹‹ከራስ ጋር ንግግር›› የተሰኘ አልበሙን ከለቀቀ በኋላ ዕውቅና አግኝቷል፡፡ ስሙን በማቆላመጥ ሳሚ ሲለው፣ ዳን የሚለውን ስም የወሰደው ከአሥራ ሁለቱን ነገድ (የያዕቆብ ልጆች) ሰባተኛ የሆነውን ዳን ተምሳሌት በማድረግ ነው፡፡ ሳሚ ዳን የተወለደው በጥቅምት ወር ሲሆን፣ አሥራ ሁለቱን ነገድ መሠረት በማድረግ ከሚያዝያ አንስቶ ያሉት ወራት ተቆጥረው ሰባተኛው ወር ጥቅምት (የዳን) ይሆናል፡፡ የያዕቆብ ልጅ ዳንን ከሚገልጹት አንዱ ሰማያዊ ቀለም ሲሆን፣ ከሰውነት ክፍል ደግሞ የጀርባ አጥንትን ይወክላል፡፡ ይህ የሱንም ማንነት እንደሚያሳይ ድምፃዊው ይናገራል፡፡ ‹‹ስሙ ማንነቴን ይገልጽልኛል፤ ባህሪዬንም ይወክላል፤›› ይላል፡፡

አልበሙን ከመልቀቁ አስቀድሞ የማስታወቂያ ሲዲ ለመልቀቅ በሚዘጋጅበት ወቅት ነበር የመድረክ ስሙን አያይዞ ለማሳወቅ የወሰነው፡፡ ‹‹ብዙ ድምፃውያን መጀመሪያ በለቀቁት ነጠላ ዜማ ወይም በዘፈናቸው ሥልት ሰው መጠሪያ ይሰጣቸው፡፡ እኔ ግን የሚገልጸኝና የሚወክለኝ የመድረክ ስም ለራሴ መስጠት እፈልግ ነበር፤›› ይላል፡፡

በአገሪቱ የመድረክ ስም ብዙ ትኩረት እንደማይሰጠው ሳሚ ዳን ይናገራል፡፡ ብዙዎች ሙሉ ስማቸውን ሲጠቀሙ ሌሎች ሰዎች ከዘፈናቸው ተነስተው የሚሰጧቸው ቅጽል ስም ሲጸና ይስተዋላል፡፡ በእሱ እምነት፣ በአንድ ዘፈን ብቻ በመመርኮዝ ሰዎች ለድምፃውያን የሚሰጧቸው ስሞች የዘፋኞቹን አጠቃላይ ሥራ ሊወክሉ አይችሉም፡፡ ድምፃውያንን ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የማይገልጿቸው የመድረክ ስሞችን ሰዎች ከሚሰጧቸው፣ ማንነታቸውን የሚገልጹና መልዕክት አዘል የመድረክ ስሞች ለራሳቸው ቢያወጡ ይመረጣል ይላል፡፡

የመድረክ ስም ድምፃዊ ገበያ ውስጥ ሲገባ ከሚሰጠው ቦታ ጋር እንደሚያያዝም ድምፃዊው ያምናል፡፡ ‹‹የመድረክ ስም ሰውን የሚማርክ መሆን አለበት፡፡ የድምፃዊው ስም ሲሰማ በአድማጭ ጭንቅላት ውስጥ የሚፈጥረው ምስልም መታሰብ አለበት፤›› ሲል ይገልጻል፡፡ እሱም ሳሚ ዳን የሚለውን ስም ከመምረጡ በፊት በሰዎች የሚያዝ መሆኑን ሞክሯል፡፡ ዛሬ ላይ ስሙ በጓደኞቹና በቤተሰቦቹም ተለምዶ ሳሙኤል የሚለው ስሙ እስከመዘንጋት ደርሷል፡፡

የአንድ ሰው መጠሪያ ስም  ለመድረክ ሥራ ሳቢ አይደለም ተብሎ ሲታሰብ ማራኪ የመድረክ ስም የሚመረጥባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ በአንዳንድ አገሮች ለመጥራትና ለመጻፍም ከባድ የሆነ ስም ያላቸው ድምፃውያን እንዲሁም ተዋንያን በሚመርጡት ስም ይጠራሉ፡፡ ከሌላ ባለሙያ ጋር ተመሳሳይ ስም ሲኖር ወይም በአንድ ሰው በቤተሰብ ውስጥ ታዋቂ ግለሰብ ካለ በተመሳሳይ ስም ምክንያት በዚያ ሰው ዕውቅና ጥላ ሥር ላለመውደቅ የመድረክ ስም ይወጣል፡፡ የእከሌ ልጅ ወይም የእከሌ ዘመድ ከመባል የራስን ዕውቅና ለመፍጠር የሚደርግ ጥረትም ይሆናል፡፡

ከመድረክ ስም ጋር በቀጥታ ባይገናኝም የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቻቸውን ለንባብ ሲያበቁ ማንነታቸውን ለመደበቅ የብዕር ስም የሚጠቀሙ ደራስያን አሉ፡፡ በጋዜጣ፣ በመጽሔት ወይም በማኅበረሰብ ድረ ገጽ በሚያሰፍሯቸው ሐሳቦች ምክንያት ጥያቄ እንዳይነሳባቸው ወይም ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ በብዕር ስም ይገለገላሉ፡፡

በሙዚቃው ዘርፍ ከሚሠሩበት ባንድ በመነሳት፣ ሥራዎቻቸውን በመመርኮዝ፣ በሚመርጡት የሙዚቃ ዘዬ፣ በቁልምጫ ወይም ከሕዝብ የተሰጣቸውን ቅጽል ስም እንደ መድረክ ስም የሚገለገሉ ድምፃውያን አሉ፡፡ አሊ መሐመድ (አሊ ቢራ)፣ ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ)፣ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፣ እጅጋሁ ሽባባው (ጂጂ)፣ ሔለን በርሔ (ሔሊ ቤሪ)፣ ኃይለሚካኤል ጌትነት (ኃይሌ ሩትስ) ፀሐይ ዮሐንስ (ፀሐዬ ዮሐንስ)፣ ዮሐንስ በቀለ (ጆኒ ራጋ) እና ጎሳዬ ቀለሙ (ጃኪ ጎሲ) መጥቀስ ይቻላል፡፡

‹‹ሎሚ ብወረውር ደረቱን መታሁ፤ አወይ ኩላሊቱን ልቡን ባገኘው፤›› የሚለው የዘነበች ታደሰ (ጭራ ቀረሽ) ዘፈን ከብዙዎች ህሊና አይጠፋም፡፡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው ድምፃዊቷ ወገቧን ወደ ግራና ቀኝ እየወዘወዘች፣ በምትዘፍንበት መድረክ ከጥግ እስከ ጥግ መውረግረግ ልማዷ ነው፡፡ ከዘፈኖቿ አንዱን እያቀነቀነች ስትውረገረግ የተመለከቱት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ‹‹አሁንስ ጭራ ቀረሽ›› ብለው ከዚያ በኋላ ቅጽል ስሟ ሆኖ እንደቀረም ይነገራል፡፡

የሳክስፎኑ ንጉሥ ጌታቸው መኩሪያ፣ ጌታቸው ማንቆርቆሪያ በሚል ቅጽል ስም ይጠራል፡፡ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ጌታቸው፣ ሳክስፎኑን ወደ ላይ ከፍ አድርጎ ሙዚቃውን ሲያንቆረቁር ከሚያወጣው ድምፅ፣ ማንቆርቆያ ከሚመስለው ሳክስፎኑና አጠቃላይ ክንውኑን በመመርኮዝ የተሰጠው ስም ነው፡፡ ዓለማየሁ እሽቴ በአለባበሱ፣ አዘፋፈኑና አኳኋኑ ኤልቪስ ፕሪስሊ ሲባል ብዙነሽ በቀለ ደግሞ አሪታ ፍራክሊን ተብላለች፡፡

 በርካታ የምዕራቡ ዓለም አርቲስቶችም በመድረክ ስማቸው ይታወቃሉ፣ ጄይዚ፣ ፒንክ፣ ኤምነም፣ ሌዲ ጋጋ፣ ፕሪንስ፣ ክዊን ላቲቫና ሌሎችም የመድረክ ስሞች የአርቲስቶቹ መጠሪያ እስኪመስሉ ድረስ በስፋት ይታወቃሉ፡፡

 

                         

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...