Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየፕራንክ ሀ ሁ

የፕራንክ ሀ ሁ

ቀን:

ቀን ላይ ሰው የዕለት ተግባሩን ለማከናወን ላይ ታች በሚልበት ወቅት ነው፡፡ ግርግር ለሌባ ይመቻል እንዲሉ ግርግሩን ተጠቅሞ አንዱ ከአንዲት መንገደኛ ያላትን መስረቅ ይዟል፡፡ አሰራረቁ ግን ለየት ያለ ነበር፡፡

ልጅቷ የያዘችውን ቦርሳና ሌሎችም ዕቃዎች ለመቀበል ብዙ አልተቸገረም፡፡ ሁሉ ነገር ቀላል ነበር፡፡ ዱቄት መሳይ ነገር ፊቷ ላይ በተነ፡፡ የልጅቷ ሁኔታም ወዲያው ተቀየረ፡፡ እንደ መፍዘዝ አደረጋት፡፡ በዚህን ጊዜ ቦርሳዋንና ሌሎች የያዘቻቸውን መቀበል ጀመረ፡፡ አንዳንዶች ሁኔታውን ዓይተው እንዳላዩ ቢያልፉም ብዙዎቹ ግን በሁኔታው ተደናግጠው ነበር፡፡

ሲያደርግ የነበረውን በቅርብ ርቀት ስትመለከት የነበረች አንዲት ሴት ጭንቅላቷን በሁለት እጆቿ ይዛ ኡኡ ብላ ጮኸች፡፡ ፌዴራል ፖሊስና በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ተሰብስበው ያዋክቡት ጀመረ፡፡ በድንጋይ ሊደበድቡት ያሯሯጡትም ነበሩ፡፡ ነገሮች የተረጋጉት ፕራንክ መሆኑን ሲናገርና ትዕይንቱን ይቀርፅ ወደነበረው ካሜራ ሲጠቁማቸው እንደነበር የሌባውን ገፀ ባህሪ ተላብሶ ሲጫወት የነበረው ልዑልሰገድ ነጋሽ ይናገራል፡፡

ፕራንክ መሥራት የጀመረው ለትወና ሙያ ልዩ ፍቅር ስላለው እንደሆነ ይናገራል፡፡ ሌባ ሆኖ የሠራበት የፕራንክ ቪዲዮ የመጀመሪያ ሥራውና የማይረሳው ነው፡፡ ተዋናይ ሸዊት ከበደን ፕራንክ ያደረገበት አጋጣሚም እንደሚታወሰው ይናገራል፡፡ ከ20 ዓመታት በላይ አይታው የማታውቀው ወንድሟ እንደሆነና በአጋጣሚ እንዳገኛት ሆኖ እያለቀሰ ይነግራታል፡፡ የሆነውን ባለማመን እምባ እየተናነቃት ስሜታዊ ሆና እያነጋገረቸው ሳለ፣ ድንገት ለቅሶውን አቁሞ ወደ ሥውር ካሜራው እጁን ቀስሮ ፕራንክ ተደርገሻል ብሎ ፈገግ አለ፡፡ እሷ ግን በቀላሉ አላለፈችውም፡፡ በንዴት ጦፈች፡፡ ‹‹ልትመታኝ ሁሉ ነበር፡፡ ሰው ነው የገላገለኝ፤›› ሲል አጋጣሚውን ያስታውሳል፡፡

በውጭው ዓለም በስፋት የተለመደው ፕራንክ በአገራችን እጅግም አልተለመደም፡፡ አልፎ አልፎ አፕሪል ዘፉል እያሉ በጓደኞች መካከል የመፎጋገር ነገር ቢኖርም፣ አሁንም ድረስ በማኅበረሰቡ ዘንድ በስፋት የሚታወቅ አይደለም፡፡ ማኅበረሰቡ ለተመሳሳይ አጋጣሚዎች የሚኖረው ምላሽም እጅግ የተለያየ ይሆናል፡፡ ፕራንክ ተደርገሃል፣ ተደርገሻል ሲባሉ የሚስቁ የመኖራቸውን ያህል ዱላ የሚቃጣቸው፣ የሚቆጡና ሌላም የሚያደርጉ ያጋጥማሉ፡፡

‹‹ለታሰበው ጨዋታ ይመጥናል ብለን ወደ አንዱ መንገደኛ ስንሄድ በድፍረት ነው፡፡ የተለያዩ ያልተጠበቁ ነገሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ፡፡ ያንንን በራሳችን ለመወጣት እንሞክራለን፡፡ ከኛ ሲያልፍ ደግሞ ፕሮዳክሽን ማኔጀሩ አሊያም ረዳቱ ደርሶ ለማስተካከል ጥረት ያደርጋል›› ሲል ሊያጋጥሙ የሚችሉ ማንኛውንም ነገሮች በማግባባት እንደሚያልፉ ይናገራል፡፡

አንድ የፕራንክ ቀረፃ ሲሠሩ የሚከፍላቸው የለም፡፡ አጋጣሚው ግን እንዲታወቁና ወደ ትወናው ዓለም እንዲገቡ መንገድ እንደሚከፍትላቸው ልዑልሰገድ ይናገራል፡፡ ‹‹መውጫ ቀዳዳ እንጂ ገንዘብ አይከፈለንም፡፡ ለሻይ ከ25 እስከ 100 ብር ሊሰጠን ይችላል›› ሲል ለሙያው ፍቅር እንደሚሠሩ ይናገራል፡፡

ሰዎችን ፕራንክ ለማድረግ ያልተለመዱ አዳዲስ ፊቶችን መጠቀም ግድ ይላል፡፡ ካልሆነ ግን ማንም አይሸወድም፡፡ ስለዚህም በአንዱ ቪዲዮ ላይ የተጠቀሙትን አለመድገም፣ የግድ የሚደገምበት አጋጣሚ ከተፈጠረም ቆየት እያደረጉ ተዋናዮችን መጠቀም አሊያም በሜካፕ ገጽታቸውን መቀየር ያስፈልጋል፡፡

‹‹ራሳችንን እንቀይራለን፡፡ እንደዚያም ሆኖ አውቅሃለው የሚል ያጋጥማል፣ ሰዎችን ፕራንክ እያደረግን በመካከል ገብተው ፕራንክ ለሚደረገው ሰው እንዳትሸወድ፣ ፕራንክ እያደረጉህ ነው! ብለው የሚናገሩም ያጋጥሙናል›› በማለት ተዋናዮቹን በተደጋጋሚ መጠቀም በሥራቸው ላይ የሚፈጥረው ችግር መኖሩን ይናገራል፡፡ መንገድ ላይ ሲንቀሳቀስ አይተው ካሜራው የት ነው የተሰቀለው ብለው የሚጠይቁትም ያጋጥሙታል፡፡

ያልተጠበቁ ነገሮች የሚፈጠሩበትና የተዋናዮቹን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ አጋጣሚዎችም አሉ፡፡ የአድዋ ድልድይ ብረትን የሚቆርጥ መስሎ አጎንብሶ በመጋዝ እየገዘገዘ ነበር፡፡ የሚሆነውን ነገር የተመለከተ አንድ ሰውዬ እንጨት ወርውሮ ለጥቂት ሳተው፡፡

የተወረወረው እንጨት አግኝቶት ቢሆን ለከፋ አደጋ ያጋልጠው እንደነበር የ25 ዓመቱ አቤል ብርሃኑ ይናገራል፡፡ አቤል የወይኗ ልጅ በሚል የቅጽል ስሙ ይታወቃል፡፡ ፕራንክ መሥራት የጀመረው ኢትዮጵያና ናይጄሪያ እግር ኳስ በሚጫወቱበት ወቅት ነበር፡፡ ‹‹በወቅቱ ጥሩ ጥሩ ፕራንኮችን ሠርተናል›› ይላል፡፡ ሥራው ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሚያገናኘው ሲሆን በገጠመኞች የተሞላ እንደሆነ ይናገራል፡፡ 

ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ሲወጡ አግኝተዋቸው ፕራንክ ያደርጓቸዋል፡፡ ልጆቹ ፕራንክ መደረጋቸውን ሲያውቁ ስቀው ነበር፡፡ ነገር ግን አፍታም ሳይቆይ እንዳይተላለፍ መለመን ጀመሩ፡፡ ከትምህርት ሰዓታቸው ፎርፈው በወጡበት ወቅት ስለነበር ቤተሰብ እንዳያውቅ ነበር ተማጽኗቸው፡፡

ሐበሻ ፕራንክ ያዘጋጅ የነበረው የፕራንክ ቪዲዮዎች በኢቢኤስ ፕሮግራም ላይ ሲተላለፍ፣ የወይኗ ልጅ ዕውቅናን አተረፈ፡፡ ‹‹የሚያዝናኑና የማኅበረሰቡን አመለካከት የሚያሳዩ ሥራዎች ሠርተናል፤›› የሚለው ወጣቱ፣ በአሁኑ ወቅት በሌላ ሥራ ተሰማርቶ እንደሚገኝ ይናገራል፡፡

ፕራንክ በሚሠራባቸው ጊዜያት የተለያዩ ገጠመኞችን ያስተናግድ እንደነበር በፈገግታ ያስታውሳል፡፡ ‹የምትሠሩት የጅል ሥራ ነው› የሚሏቸው ነገር ግን እያንዳንዱን ቪዲዮ ተከታትለው የሚያዩ ሰዎች ያጋጥሙታል፡፡ ታክሲ ላይ ወይም መንገድ ላይም ፕራንክ እያደረጋቸው ያለ የሚመስላቸው አሉ፡፡ ‹‹መንገድ ላይ እየሄድኩኝ ድንገት ቀብ አድርገው ይዘውኝ ‹የቱ ጋር ነው ያስቀረፅከኝ? ካሜራው የት ጋ ነው የተደበቀው?› ብለው የሚይዙኝ አሉ፤›› ይላል፡፡ በአንድ ወቅትም ገርጂ አካባቢ የሚኖሩ አክስቱ ጋር ለመሄድ መንገድ ጠፍቶት ሰዎች እንዲረዱት ጠይቆ ‹‹ፕራንክ እንደምታደርግ እናውቃለን ዞር በል፤›› ብለው አባረውት እንደነበር ያስታውሳል፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሐበሻ ዊክሊ አዘጋጅነት ተቀርጾ የወጣ የፕራንክ ቪዲዮ ብዙዎችን ፈገግ አሰኝቷል፡፡ በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ አንድ ወጣት ሙዚቃ በሄድፎን እያዳመጠ ከአላፊ አግዳሚው ጋር ለመጨፈር ጥረት ያደርጋል፡፡ የሚጨፍረውም እስኪ አስጨፍሩኝ በሚል ዓይነት ሳይሆን ግዴታ በሚመስል መልኩ ሰዎችን እየተከተለ እልህ አስጨራሽ በሆነ መልኩ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ መንገድ ቀይረው ለመሄድ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ እንደመገፋተር ብለው ይሄዳሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ አብረውት የሚጨፍሩም ነበሩ፡፡ አንደኛው መንገደኛ ይዞ የነበረውን ቦርሳ አስቀምጦ ዳንስ ገጥሞታል፡፡

ልጁን ካስጨፈሩ መካከል ያሬድ በለጠ አንዱ ነው፡፡ ሥራ ቆይቶ ከጓደኞቹ ጋር ምሳ ለመብላት ወደተቀጣጠሩበት ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ እየሄደ ሳለ ነበር አስጨፍሩኝ ከሚለው ወጣት ጋር የተገናኘው፡፡ ከፊት ለፊቱ እየቀደመው ሲጨፍር ግራ ገብቶት ነበር፡፡ መንገድ ቀይሮ ለማለፍ ሞክሮም አልተሳካለትም፡፡ ዳንሰኛው በጄ ብሎ አልተወውም፡፡ ‹‹እንደመናደድ አድርጎኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ፕራንክ ሊሆን እንደሚችል ጠርጥሬ አብሬው መጨፈር ጀመርኩኝ፤›› ሲል አዝናኝ እንደሆነ ይናገራል፡፡

በአንፃሩ ደግሞ እንዴት ተቀረፅኩኝ? ብለው አምባጓሮ የሚፈጥሩ ያጋጥማሉ፡፡ የሐበሻ ፕራንክ አዘጋጁ አቶ ያረጋል የኋሌ ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ የተለያዩ የፕራንክ ቪዲዮዎችን በማዘጋጀት ለሕዝብ ዕይታ ያበቃሉ፡፡ በዘርፉ ፈር ቀዳጅም ናቸው፡፡ ‹‹የውጭ አገር የፕራንክ ቪዲዮዎችን በጣም እመለከት ነበር፡፡ ይህንን በኛም አገር የማስለመድ ሐሳብ መጣልኝ፡፡ ከዚያም ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ወደ ሥራው ገባሁ፤›› የሚሉት አቶ ያረጋል፣ እኛ አገር የመዝናናት ባህላችን የተለየ ነው፡ ፕራንክ ማዘጋጀትም ከበድ ይላል ብለዋል፡፡

በተለይም በመጀመሪያዎቹ አካባቢዎች ሰዎችን ፕራንክ ማድረግም ሆነ ካሜራ መቅረጽ ይቸገሩ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ አንዳንዶቹ ፕራንክ መደረጋቸው ሲነገራቸው ይስቃሉ፡፡ ለምን ተቀረፅኩኝ ብለው የሚበሳጩና ድብድብ የሚቃጣቸውም ያጋጥሟቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ‹‹የተሰራጨው ቪዲዮ እንዲተላለፍ አንፈልግም የሚሉና እንዲሰረዝ የሚያደርጉ ብዙ ናቸው፡፡ ታዋቂ ሰዎችም እንደዚህ ያደርጉናል፡፡  ከመጀመሪያው ምን ስሆን ቀረፅከኝ? ብሎ ጣቢያ ድረስ ይዞን የሄደ ሰው አለ፤›› ሲሉ፣ ቪዲዮዎቹን ለማዘጋጀት ያለው ውጣ ውረድ ቀላል አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

በቀረፃ ላይ ሳሉ የፖሊስ አባላት ደርሰው እንዲያቆሙ የሚያስገድዱበት፣ የመቅረፅ ፈቃድ ቢያሳዩም፣ አይሆንም የሚባሉበት አጋሚ መኖሩ፣ ለመሥራት እንዲቸገሩ ያደርጋቸው እንደነበር፣ በአሁኑ ወቅት ግን እየተለመደ በመምጣቱ መጠነኛ መሻሻሎች መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡

እንዲህ ተቸግረው ቪዲዮዎችን ከቀረፁ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይተላለፉ የሚቀሩ ቪዲዮዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ በተለይም ቪዲዮው በሰዎች ዘንድ ያስገምተናል ብለው የሚጨነቁ ሰዎች እንዳይተላለፍ ይጠይቃሉ፡፡

‹‹ማንም መዋረድን አይፈልግም፡፡ በተለይም በሶሻል ኤክስፐርመንት የተለያዩ የተደበቁ የሰዎች ባህሪያት ይወጣሉ፡፡ ስለዚህም ፕሮግራሙ እንዳይተላለፍ የሚጠይቁ ብዙ ናቸው፤›› የሚለው በሐበሻ ዊክሊ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ አቶ ሰለሞን ፀጋዬ ነው፡፡

በቅርብ ሠርተውት በነበረው የፕራንክ ቪዲዮ ላይ የገጠማቸውንም ያስታውሳል፡፡ ከአንድ ሰውዬ ኪስ አሥር ብር ይወድቃል፡፡ ከኋላው የነበሩ ሰዎች ብር ጥለሃል ብለው ይሰጡታል፡፡ ሰውየው ግን ስሜታዊ ሆኖና እምባ እየተናነቀው ኑሮ መሮኛል፡፡ ራሴን ለማጥፋት መርዝ ልገዛ እየሄድኩ ነው፡፡ ሁለት ብር ስለጎደለኝ ጨምሩልኝ፡፡ ብሎ ይጠይቃል፡፡ አንዳንዶቹ ሊያረጋጉት ይሞክራሉ፡፡  የተወሰኑት ሰዎች ግን ምን ቸገረኝ በሚል ስሜት የጠየቃቸውን ሁለት ብር ይሞሉለታል፡፡ ራስን ማጥፋት ወንጀልና ተግባራቸውም የሚያስቀጣ ቢሆንም ሰዎቹ ፕራንክ መሆኑ እስኪነገራቸው ድረስ አላሳሰባቸውም ነበር፡፡ መሸወዳቸው ሲገባቸውና ያደረጉትም በሰዎች ዘንድ ያላቸውን ቦታ የሚያሳጣቸው በመሆኑ ቪዲዮው እንዲጠፋ አድርገዋል፡፡ ቢሯቸውም ተመላልሰው እንደነበር ሰለሞን ይናገራል፡፡ በአንድ ፊልም ላይ ለመሥራት የተወዳደረች አንዲት ልጅ፣ ፕራንክ መሆኑ ሲነገራት ቤተሰቦቿ ተደብቃ መወዳደሯን ቢያውቁ፣ ከባድ ችግር እንደሚገጥማት በመግለጽ የሷ ቪዲዮ ተለይቶ እንዲቀር አድርጋለች፡፡

ፕራንክ የኛ ባህል አይደለም ብለው ቀረፃው እንዲቋረጥ የሚያደርጉ አንዳንድ ሰዎች እንደሚያጋጥሙም ሰለሞን ገልጿል፡፡ በቅርቡ ያጋጠመውንም እንዲህ ያስታውሳል፡፡ የዳንሱን ፕራንክ በሚቀርፁበት ወቅት ነው፡፡ የሚደንሰው ልጅ መንገዱን ታቋርጥ ወደነበረች አንዲት ነጭ ተጠግቶ መደነስ ይጀምራል፡፡ በሁኔታው የተደናገጠችው ነጭም ቆማ ቀረች፡፡ ይኼኔ አንድ ሰውዬ ልጁን እየገፈታተሩና አሰዳቢ እያሉ ከፊቷ ዞር አደረጉት፡፡ ፕራንክ መሆኑ ተነገራቸው፡፡ ረገብ ይላሉ ብለው የገመቱ ቢሆንም ‹‹ይኼ የኛ ባህል አይደለም›› ብለው መቆጣት ጀመሩ፡፡

እንዲህ ያሉ በሥራቸው ላይ ከሚያጋጥሙ ችግሮች በስተቀር በመጠኑም ቢሆን የተለመደ ይመስላል፡፡ ሌላው ቢቀር ሰዎች ለቃሉ እንግዳ አይደሉም፡፡ ጓደኞቻቸውን ፕራንክ እንዲያደርጉላቸው ፕራንክ ወደሚያደርጉ ድርጅቶች ጋር የሚሄዱ ሰዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ ‹‹አሁን ላይ ቢሯችን መጨናነቅ ጀምሯል፡፡ ባል ሚስቱን፣ እናት ልጇን፣ ጓደኛ ጓደኛውን ፕራንክ እንድናደርግላቸው ይጠይቁናል፤›› የሚሉት አቶ ያረጋል፣ ከሰዎቹ ጋር የተገናኘ አንድ ጉዳይ በመምዘዝ የፕራንኩን ሐሳብ እንደሚያዘጋጁ ይናገራሉ፡፡ አንድ ሰው ጓደኛውን ወይም ሌላው የቅርብ ዘመዱን ፕራንክ እንዲያደርጉለት ሲጠየቃቸው የራሱ ሐሳብ እንዳለው ይጠይቁታል፡፡ ካልሆነ ግን ስለ ሰውየው ማንነት፣ እንዲሁም የጤና ሁኔታ እንደ ልብ ድካም፣ ግፊትና ስኳር ያለበት መሆን አለመሆኑን ከነባህሪው በማጥናት ፕራንክ እንደሚያደርጉት ገልጸዋል፡፡

ፕራንክ ማድረግም ሆነ መደረግ በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ልምድ ቢሆንም፣ በውጭው ዓለም የተለመደ ነው፡፡ ፕራንክ መሠረቱ ደስታንና መዝናናት መፍጠር፣ እንዲሁም በጓደኝነት መሀል ያለን ግንኙነት ለማጠናከር ተብሎ የሚደረግ ቢሆንም፣  አሸባሪ መስሎ በማስደንገጥ ሰዎችን አቅል ማሳጣት፣ ቤት ውስጥ ተደብቆ በመቆየት ሰዎች ቤታቸው ሲገቡ ማስደንገጥ፣ መንገድ ላይ ዘራፊ መስለው በመቅረብ ለሞትና ለከባድ የአካል ጉዳት መዳረግ በውጭው የተለመዱ ናቸው፡፡ ፕራንክ እናደርጋለን ብለው የሰው ሚስት በመጎንተላቸው የከፋ ጉዳት ያስተናገዱም አሉ፡፡ በተፈጸመባቸው ፕራንክ በመደናገጥ ከነልብሳቸው ውኃ ውስጥ የገቡ፣ ሮጠው ለማምለጥ ሲሞክሩ በመኪና ተገጭተው የሞቱም አሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ገጠመኞች እዚህ ባይሰሙም፣ ሥራው አድጎ የበለጠ አስደንጋጭ የሆኑ ትዕይንቶችን ማካተት ሲጀምር፣ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ፕራንክ የሚደረጉ ሰዎች ድርጊቱ በተፈጸመበት ጊዜ ባሳዩት ባህሪ ደስተኛ ላይሆኑ ስለሚችሉ ይህም ከግምት መግባት አለበት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...