Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየእህል በረንዳው ትንቅንቅ

የእህል በረንዳው ትንቅንቅ

ቀን:

ሳምንቱን ሙሉ ከፍተኛ የእህል ግብይት የሚካሄድበት ሥፍራ ነው፡፡ የተለያየ እህል ጭነው በሚገቡና አራግፈው በሚወጡ የጭነት መኪኖች የሚጠናቀቀው እህል በረንዳ፣ ወጪና ወራጁ፣ ሸማቹ እንዲሁም ወዛደሩ ሥፍር ቁጥር የለውም፡፡ የከተማዋ ጉሮሮ እንደሆነ በሚነገርለት እህል በረንዳ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ነጋዴዎች፣ ጫኝና አውራጆች እንደሚተዳደሩ ይነገራል፡፡

ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ ባለበት በዚህ አካባቢ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብም ይዘዋወራል፡፡ የተቸገረ ሰው እህል በረንዳ ከገባ ጦሙን እንደማያድር ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡ ከአንዱ የእህል ነጋዴ ጋር ተጠግቶ አንዳንድ ሥራዎችን በመሥራት ቢያንስ የዕለት ጉርስን ያስገኛል፡፡ አንዴ እህል በረንዳን የረገጠ ሰውም ለዓመታት እዛው ይከርማል፡፡ በአካባቢው 250 ሕጋዊ ነጋዴዎችና 15 ሺሕ ጫኝና አውራጆች እንደሚሠሩም ይነገራል፡፡

ከየአቅጣጫው ተጭነው የሚገቡ የእህል ዓይነቶች እህል በረንዳ ይራገፋሉ፡፡ የየነጋዴዎቹ ተወካይ የሆኑ ወዛደሮችም እህሉን ማስወረድ ይጀምራሉ፡፡ እህሎቹን ከጭነት መኪኖቹ ላይ የሚያወርዱት በኩንታል የሚከፈላቸው እንዳወረዱት የእህል ዓይነት ይለያያል፡፡ የጤፍ በኩንታል 10 ብር ሲሆን፣ የበቆሎ ስድስት ብር ነው፡፡ ለዚህም የተለየ ምክንያት አለው፡፡ እነዚህ ላባቸውን ጠብ አድርገው የሚሠሩት ጫኝና አውራጆች ገንዘቡን በቀጥታ አያገኙም፡፡ የሚከፍላቸው የነጋዴው ተወካይ ሲሆን፣ በኩንታል ከሚታሰብላቸው ገንዘብ ላይ ጠቀም ያለ ኮሚሽን ይይዝባቸዋል፡፡ አንድ ጫኝና አውራጅ በኩንታል አሥር ብር የሚከፈለው እንደሆነ ስምንት ብሩን የሚወስደው ተወካዩ ነው፡፡

አቶ ባያብል ብርሃኑ ይባላሉ፡፡ በእህል በረንዳ መሥራት የጀመሩት በ14 ዓመታቸው ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ከቤተሰብ አፈንግጬ ነበር የወጣሁት፡፡ ለመሸከምና የቀን ሥራ ለመሥራት አቅሜ አልደረሰም ነበር፡፡ አዲስ አበባ መጥቼ የምሠራው አልነበረኝም፡፡ ይርበኝም ነበር፡፡ እየቆየሁ ስመጣ የእለት ጉርስ ፍለጋ ወደዚህ ሥራ ገባሁ፤›› ሲሉ ከተወለዱበት ጎጃም በልጅነታቸው ጠፍተው በመምጣት ወደ ሸክም ሥራ የገቡበትን ሁኔታ ያስታውሳሉ፡፡

ሥራ በየቀኑ ላይኖር ይችላል፡፡ በሳምንት የሚሠራባቸው ቀናትም የተወሰኑ ናቸው፡፡ ሰኞ፣ ረቡዕና ዓርብ እህል የሚገባባቸው ቀናት ስለሆኑ በቀን እስከ 150 ብር እንደሚሠሩ አቶ ባያብል ይናገራሉ፡፡ 

አቶ ባያብል ለአንድ ነጋዴ ተወካይ ሆነው እህል በሚገቡባቸው ቀናት ሌሎች ጫኝና አውራጆችን ቀጥረው ያሠራሉ፡፡ የተለያዩ ዓይነት ደረጃ ያላቸውን እንደ ጤፍ ያሉ እህሎች ደንበኛው የሚፈልገውን ዓይነት እስኪያገኝ ድረስ ማመላለስ ሊኖር ስለሚችል፣ ለአውራጁ በኩንታል አሥር ብር ይከፈላል፡፡ እንደ ሥንዴና ገብስ ላሉት በኩንታል ስምንት ብር፣ ለበቆሎ ደግሞ ስድስት ብር እንደሚከፈል ይገልጻሉ፡፡

እንደ አቶ ባያብል፣ ከወዛደርነት ተነስቶ የነጋዴ ተወካይ ሆኖ ለመሥራት በአካባቢው ለዓመታት መቆየትና እምነት ማትረፍ ግድ ይላል፡፡ በሥራቸው ታማኝነት ላተረፉ የሚሰጣቸው ኃላፊነትና የሚከፈላቸው ገንዘብ ከሌሎቹ በተለየ ከፍ ያለ ነው፡፡ ከእህል በረንዳ ብሩን ይዞ ይጠፋል የሚል ሥጋት ሳይኖር፣ ለዓመታት የሠራ አንድ ወዛደር 20 ብር ተከፍሎት የአንድን ነጋዴ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲያስገባ ሲላክ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ‹‹በእህል በረንዳ ለዓመታት በሥራ ላይ ለቆየን ወዛደሮች የሚከፈለን ለሥራችን ሳይሆን ለልምዳችንና በሰዎች ላይ ላሳደርነው እምነት ነው፤›› ይላሉ፡፡

አንድ የማይታወቅ ሰው እህል በረንዳ ገብቶ በጫኝና አውራጅነት ለመሥራት መታወቅና ታማኝ መሆን ግድ ይለዋል፡፡ አለዚያ ግን የሚያሠራው አይኖርም፡፡  እንደ አቶ ባያብል ካሉ ተወካዮች ሥር በመሆን በኮሚሽን ለመሥራትም ቢሆን በመጠኑም መታወቅ ያስፈልጋል፡፡ ተሸካሚው እህሉን ይዞ ቢጠፋ ከፋይ የሚሆኑት እንደ አቶ ባያብል ያሉ ቋሚ ወዛደሮች (ተወካዮች) ናቸው፡፡ በመሆኑም ለጫኝና አውራጆች ከሚታሰብላቸው ገንዘብ ላይ ጠቀም ያለ ኮሚሽን ይይዛሉ፡፡ ‹‹በሦስት ብር የሚሸከመው ሰው የሚከፈለው ለትከሻው ብቻ ነው፡፡ እህሉን ይዞ ቢጠፋ ተጠያቂ የምንሆነው እኛ ነን፡፡ ከዚህም በፊት ይዘው ጠፍተው ከፋይ ሆነን እናውቃለን፡፡ በአሁኑ ወቅትም እንደዚህ ያለ ነገር ቢያጋጥመን የምንከፍለው ገንዘብ ካለው የእህል ዋጋ ውድነት አንፃር ከፍተኛ ነው፤›› በማለት የሚይዙትን የኮሚሽን መጠን ምክንያታዊ ለማድረግ ይሞክራሉ፡፡

ባለትዳርና የልጆች አባት የሆኑት አቶ ባያብል፣ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት በዚህ መልኩ ሠርተው በሚያገኙት ገንዘብ ነው፡፡ ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ የእህል በረንዳ ቋሚ ተወካዮችና ተሸካሚዎች የቤተሰብ ኃላፊ ናቸው፡፡ ከፊሎቹ ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ልከው ለማስተማር የሚጣጣሩ ሲሆን፣ አቅሙ የሌላቸው ደግሞ ልጆቻቸውን አስከትለው አብረው የሚሠሩ ናቸው፡፡ የቅርብ ዘመዶቻቸውን ከገጠር በማስመጣት የሚያሠሩም አሉ፡፡ እህል በረንዳ ለእነዚህ ሁሉ የእንጀራ ገመድ፣ መዋያና ማደሪያም ነው፡፡ በመሆኑም በአካባቢው ላይ ግጭት ሊስተዋል ይችላል፡፡

ሰሞኑን በማኅበር ተደራጅተው ወደ ሥራው እንዲገቡ ከተደረጉ ወጣቶች ጋር የጥቅም ግጭት ተፈጥሮም ነበር፡፡ ‹‹በሥራ ላይ እያለን ድንገት መጥተው ‹የኛ ሥራ ነው፣ ከመኪናዎቹ ላይ ውረዱ፤› ብለው ይገፈትሩን ጀመሩ፡፡ እኛም መሥራት አልቻልንም፡፡ በመካከላችን ስምምነት ባለመፈጠሩም እህል እየገባ አይደለም፣ ሥራ ቀዝቅዟል፤›› ይላሉ አቶ ባያብል፡፡

ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት በማኅበር ለመደራጀት የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ መቅረቱን፣ አሁን በድንገት ሌሎችን አደራጅቶ እነሱ ከሥራ እንዲወጡ የተደረገበት ሁኔታ አግባብ አለመሆኑን በመግለጽ ከ5000 የሚበልጡ ጫኝና አውራጆች ቁጣቸውን ገልጸዋል፡፡

ተደራጅቶ ወደ ጫኝና አውራጅነቱ ሥራ እንዲገባ የተደረገው፣ ሔኖክ ጌትነትና ጓደኞቹ ጫኝና አውራጅ የተባለው ማኅበር ነው፡፡ ማኅበሩ ከተደራጀ አንድ ዓመት ከሁለት ወር ቢያስቆጥርም፣ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሥራ ሳይገባ ቆይቶ ነበር፡፡ የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ጌትነት ተስፋዬ በማኅበር ሲደራጁ በአካባቢው ያለውን የጽዳት ችግር፣ የጥበቃ ሥራ፣ ሕገወጥ ነጋዴዎችን ወደ ሕጋዊነት እንዲገቡ የማድረግ ምክረ ሐሳብ ማውጣታቸውን፣ በዚህ መሠረትም የመሥራት ፍላጎት እንዳላቸውና የጫኝና አውራጅነቱ ሥራ የሌሎቹን ወዛደሮች (የነጋዴ ተወካይ) እንደማይሻማ ይገልጻል፡፡ ይሁንና የጥቅም ግጭት ሊነሳ እንደሚችል ሳይታሰብበት ቀርቶ፣ በጫኝና አውራጅነቱ ለመሥራት ሙከራ አድርገው እርስ በርስ ሳይስማሙ ቀርተዋል፡፡ ‹‹የጫኝና አውራጅነት ፈቃድ ከተሰጠን በኋላ አካሄዳችን መቀየር አለበት ብለን ሌሎች ሥራዎችን መሥራት የምንችልባቸውን አቅጣጫዎች አስቀምጠን ነበር፡፡ አሁንም መሥራት የምንፈልገው በሌሎቹ ነው፤›› ብሏል፡፡

በሁለቱ ወገን የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ጉዳዩ የሚመለከተው የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ጽሕፈት ቤት፣ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ሁለቱንም አካላት ለማነጋገር ሞክሯል፡፡

አቶ ሳሙኤል አባዲ የወረዳ አራት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚና የሕዝብ አገልግሎትና የሰው ሀብት ልማት ጽሕፈት ቤት የዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ ናቸው፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ እህል በረንዳ የአዲስ አበባ የገበያ ማዕከል ቦታ ሲሆን፣ ሰፊ የሆነ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ይታይበታል፡፡ ወጣቶቹን በሕጋዊ መንገድ በማኅበር አደራጅቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ የተደረገበትም ምክንያት ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት ነው፡፡ በዚህ ወር ውስጥም 207 በጥበቃ የሚሠሩ ወጣቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡ ችግር የተፈጠረው በጫኝና አውራጅ የሚሠሩት ሥራ እንዲጀምሩ በመደረጉ ነው፡፡ እነዚህ የተደራጁት ወጣቶች በማረሚያ ቤቶች የነበሩ፣ በስደት የቆዩ ሲሆኑ አደራጅቶ ሥራ እንዲሠሩ ማድረጉ ተገቢ ነው፡፡ ወደ ሥራው ይገባሉ ማለት ግን የነበሩት ይወጣሉ ማለት አይደለም፡፡ እነሱም በሕጋዊ መንገድ እንዲደራጁና አብረው እንዲሠሩ ይደረጋል፡፡

የማኅበሩ አባል እንዳለ ሙሌ በበኩሉ ‹‹የእህል በረንዳ ሥራ ከ80 ወጣት አልፎ ለ20 ሺሕ ሰዎች ይተርፋል፡፡ አብረን እንሥራ፤›› ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...